አዲስ አበባ ፡-በአገሪቷ ትምህርትን ለሁሉም ለማዳረስ በሚደረገው ጥረት ውስጥ አካል ጉዳተኞችን ታሳቢ ያደረጉ የልማት ተግባራት ተጠናክረው እንደሚተገበሩ ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው አስታወቁ።
ቀዳማይ እመቤቷ አዲስ አበባ ውስጥ ለሚገነባው ዘመናዊው የዐይነ ስውራን አዳሪ ትምህርት ቤት ግንባታ ከትናንት በስቲያ የመሰረት ድንጋይ ባስቀመጡበት ወቅት እንዳሉት፤ ትምህርቱ ቤቱ ለዐይነ ስውራን ተማሪዎች ምቹ ተደርጎ ይገነባል፡፡አይነ ስውራን ደረጃውን የጠበቀ ትምህርት እንዲያገኙም ያስችላቸዋል።
በአገሪቷ ትምህርትን ለሁሉም ለማዳረስ በሚደረገው ጥረት ውስጥ አካል ጉዳተኞችን ታሳቢ ያደረጉ ተግባራት በቀጣይም ተጠናክ ረው እንደሚቀጥሉም ቀዳማዊ እመቤቷ አስታው ቀዋል፡፡
በፕሮግራሙ ላይ የተገኙት ሎሬት የትነበርሽ ንጉሴ በበኩላቸው፤ትምህርት ቤቱ አይነ ስውራን ደረጃውን የጠበቀ ትምህርት እንዲያገኙ ከፍተኛ እግዛ ያበረክታል ብለዋል።ትምህርትን ለሁሉም ለማዳረስ በሚደረገው ጥረት ውስጥ ለዐይነ ስውራን ትኩረት መሰጠቱም በአገሪቱ ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ ላይ የበኩላቸውን አሻራ እንዲ ያሳርፉ መልካም አጋጣሚን እንደሚፈጥር አብራርተዋል።
ትምህርት ቤቱ የሚገነባው ፋቲማ ቢን ሙባረክ በተባሉ የዱባይ ዜጋ ድጋፍ ሲሆን ‘F-B-M’ የሚል ስያሜ ተሰጥቶታል። ግንባታው በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ እንደሚጠናቀቅ ይጠበቃል፡፡ ከመላ አገሪቱ የተወጣጡ 300 አይነስውራን ተማሪዎችን ተቀብሎ እንደሚያስተምርም ታውቋል። ትምህርት ቤቱ ደረጃቸውን የጠበቁ መማሪያ ክፍሎች፤ቤተ መፅሃፍት፤ የስልጠና ማዕከላት ይኖሩታል።
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 29/2011
በጋዜጣው ሪፖርተር