የዛሬው ፍረዱኝ አምድ ዝግጅታችን በኢትዮጵያ የመንግሥት ሠራተኞች ማኅበራዊ ዋስትና አስተዳደር በአዲስ ባካሄደው የሠራተኞች የሥራ ምደባ ጋር ተያይዞ የተፈጠረ ውዝግብን የሚያስቃኝ ነው፡፡
«በኢትዮጵያ የመንግሥት ሠራተኞች ማህበራዊ ዋስትና አስተዳደር እንደ አዲሰ ያደረገው የሥራ ምደባ መመሪያን ያልተከተለ ከመሆኑም ባሻገር መድልዎ የታየበት እና ግልጽኝነት የጎደለው በመሆኑ 300 የሚደርሱ የተቋሙ ሠራተኞች ከሥራ ውጪ እንድንሆን ተደርጓል፡፡ ይህም ራሳችንንም ሆነ ልጆቻችንን ማስተዳደር እንዳንችል አድርጓል፡፡ በዚህም አሁን ያለውን የኑሮ ውድነት መቋቋም ባለመቻላችን ከነቤተሰቦቻችን ወደ ጎዳና ልንወጣ ነው፡፡ እየተፈጸመብን ያለውን በደል የኢትዮጵያ ሕዝብ ይፍረድ» ሲሉ ከሥራ ውጪ የተደረጉ የመንግሥት ሠራተኞች ማኅበራዊ ዋስትና አስተዳደር ሠራተኞች ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት የአዲስ ዘመን ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል አቤት ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ሕዝብ ግራ ቀኙን አይቶ መፍረድ ይችል ዘንድ የአዲስ ዘመን ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል ከሰዎች እና ከሰነድ ያገኛቸውን ማስረጃዎች በጥልቀት በመመርመር ለክፍል አንድ የሚከተለውን ዘገባ ሠርቷል፡፡ መልካም ንባብ፡፡
አቤቱታ አቅራቢዎች
አቤቱታ አቅራቢዎች በርካታ ስለሆኑ ከሁሉም ጋር ቃለምልልስ ማድረግ አይቻልም፡፡ በመሆኑም ከአቤቱታ አቅራቢዎች መካከል የተወሰኑትን መርጠን ስለጉዳዩ ቃለመጠየቅ አድርገናል፡፡ ከእነኝህ መካከል አቶ ሰብስቤ ኃይለማርያም አንዱ ናቸው፡፡
አቶ ሰብስቤ እንደሚናገሩት፤ በተቋሙ በተለያዩ የሥራ መደቦች ለ24 ዓመታት ሠርተዋል፡፡ አሁን በአዲሱ መዋቅር ከሥራ እስኪነሱ ድረስ በአዲስ አበባ ሪጅን ጽሕፈት ቤት የከፍተኛ ሂሳብ ባለሙያ ነበሩ፡፡ አሁን በመስሪያ ቤቱ በተሠራው አዲስ የሥራ ድልድል በዲስፕሊን ምክንያት ያልተመደቡ መሆናቸውን ለማወቅ ችለዋል፡፡
አዲሱ የሥራ ድልድል የተደረገው ከጥር 1 ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮ ነው ያሉት አቶ ሰብስቤ፣ በዚህ ድልድል መመሪያ መሠረት ማንኛውም ሠራተኛ በመረጣቸው ሁለት መደቦች መወዳደር እንደሚቻል ተገልጾ እንደነበር ይናገራሉ፡፡ ይህን ተከትሎ ሁሉም የተቋሙ ሠራተኞች ሁለት መደቦችን መርጠው ተወዳደሩ፡፡ ይሁንና መስሪያ ቤቱ ባወጣው መመሪያ እንደተመላከተው የድልድል መመሪያው ከመውጣቱ በፊት የዲስፕሊን ኬዝ ያለባቸው የመሥሪያ ቤቱ ሠራተኞች በየትኛውም መደብ መወዳደር እንደማይችሉ ተነገራቸው፡፡ ይህም ከአዲሱ የሥራ ድልድል ውጪ እና አጠቃላይ ከመሥሪያ ቤቱ እንዲሰናበቱ ምክንያት መሆኑን ይናገራሉ፡፡
ሌሎች ጓደኞቻቸውም ወይም የሥራ ባልደረቦቻቸው ለአዲሱ የሥራ ድልድል ፈተና በመውሰድ ተወዳድረው የነበረ ቢሆንም የሰው ኃይል እና ሠራተኛው ባላወቀበት ሁኔታ የዲስፕሊን ግድፈት እንዳለባቸው ተነገራቸው። በዚህም ፈተና ወስደው የነበሩ በርካታ ሠራተኞች እንደ አቶ ሰብስቤ ሁሉ በየትኛውም የሥራ መደብ እንዳይመደቡ ተደረገ፡፡
ይህ በደል የተፈጸመባቸው ሠራተኞችም ‹‹የሰው ሀብት በማያውቀው እና ለሠራተኛውም የዲስፕሊን ግድፈት እንዳለብን የሚገልጽ ደብዳቤ ሳይሰጠን እንዴት የዲስፕሊን ግድፈት አለባችሁ እንባላለን?» ብለው ይጠይቃሉ፡፡ ይሁን እንጂ አቤቱታቸውን ሊሰማ የሚችል ሰው ማጣታቸውን አቶ ሰብስቤ ይናገራሉ፡፡
አዲስ አበባ ሪጂን ብቻ በዲስፕሊን ግድፈት እና መሰል ተልካሻ ምክንያቶች 46 ሠራተኞች ከሥራ ውጪ መደረጋቸውን ይገልጻሉ፡፡
ለዲስፕሊን ቅጣት የዳረጋቸውን ምክንያት ያብራሩት አቶ ሰብስቤ፣ ከአንድ ዓመት በፊት የሂሳብ ሠራተኛ ሆነው በተቋሙ ይሠሩ ነበር፡፡ በሥራ ላይ እያሉ በአጋጣሚ ክፍለ አገር የሚኖሩት ባለቤታቸው መታመማቸውን ይሰማሉ። ይህን ተከትሎ ክፍለ አገር ያሉትን ባለቤታቸውን ወደ አዲስ አባበ አምጥቶ ለማሳከም ፈቃድ ይጠይቃሉ፡፡ መሥሪያ ቤታቸውም ለጥር 5 ቀን 2015 ዓ.ም የአንድ ቀን ፈቃድ ይሰጣቸዋል፡፡ ባለቤታቸውንም ከክፍለ አገር ወደ አዲስ አበባ ለማምጣት ባለቤታቸው ወደሚገኙበት አዳማ ይሄዳሉ፡፡
ይሁንና የተሰጣቸው አንድ ቀን ብቻ ስለነበር በአንድ ቀን መመለስ ሳይችሉ ቀሩ፡፡ በዚህም አንድ ቀን አሳልፈው ወደ ሥራ ገበታቸው ይመለሳሉ፡፡ በዚህም መሥሪያ ቤታቸው ‹‹ከተሰጠህ ፈቃድ ውጪ አንድ ቀን አሳልፈሃል›› በሚል ምክንያት የአንደኛ ደረጃ የፅሑፍ ማስጠንቀቂያ እንደሰጣቸው ያስረዳሉ፡፡
ይህን ተከትሎ አንድ ቀን በሥራ ገበታቸው ያልተገኙበት ምክንያት በተፈጠረ የትራንስፖርት ችግር መሆኑን እና ከዚህ በፊት ሳያስፈቅዱ አንድም ቀን ቀርተው እንደማያውቁ፤ የቃል ማስጠንቀቂያ እንኳን ተሰጥቷቸው እንደማያውቁ በማመላከት የተወሰደባቸው የፅሑፍ ማስጠንቀቂያ ተገቢ አለመሆኑን ለቅርብ አለቃቸው ያመለክታሉ፡፡ ይህን ተከትሎ የፅሑፍ ማስጠንቀቂያውን ‹‹አልቀብልም አሉ›› ተብሎ የፅሑፍ ማስጠንቀቂያው ማስታወቂያ ቦርድ ላይ እንዲለጠፍ ተደረገ፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ የዓመት ፈቃድ እንዲሰጣቸው ጠይቀው የዓመት ፈቃድ ወሰዱ፡፡ ከዓመት ፈቃድ ሲመለሱ ግን ያልጠበቁት ነገር ገጠማቸው፡፡ የመጀመሪያ ደረጃ ማስጠንቀቂያው በዲስፕሊን እየታየ አገኙት፡፡ ለዚህም ያበቃቸው የፅሑፍ ማስጠንቀቂያ በተሰጡ ጊዜ ቢሮ ውስጥ ‹‹ጮህ ብለህ ተናግረሃል›› የሚል ነበር፡፡ በዚህም የዲስፕሊን ውሳኔ የአንድ ወር ደመወዛቸውን መቀጣታቸውን ይናገራሉ፡፡
በሲቪል ሰርቪስ መመሪያ 1064/2010 የዲስፕሊን ግድፈት ያለባቸው ሰዎች ከሥራ ድልድል ይወጣሉ የሚል መመሪያ የለም፡፡ ነገር ግን ከ40 በላይ የሚሆኑ ሰዎችን እንደ ተቋም በአገር አቀፍ ደረጃ ከውድድር ውጪ ተደርገዋል የሚሉት አቶ ሰብስቤ፣ ይህ አሠራር መመሪያን ያልተከተለ መሆኑን ይናገራሉ፡፡
መመሪያን ባልተከተለ አኳኋን በደል ድርሶብናል የሚሉት አቶ ሰብስቤ፣ የሥራ ድልድሉን ተከትሎ በተቋሙ ብድር እና ቁጠባ የነበረንን ገንዘብ እንኳን ለመጠየቅ ወደ ተቋሙ በሄዱ ወቅት ወደ ተቋሙ ቅጥር ግቢ እንዳይገቡ መከልከላቸውን ይናገራሉ፡፡
ድልድሉን ተከትሎ ከሥራ ውጪ መሆናቸውን የተናገሩት አቶ ሰብስቤ፣ እስከ ግንቦት 14 ቀን 2015 ዓ.ም ድረስ በእጃቸው ያለውን ማንኛውንም የተቋሙ ንብረት እንዲያስረክቡ መታዘዛቸውን ጠቁመው፤ እስከ ሐምሌ ወር ድረስ ደመወዝ እንደሚከፈላቸውና ከሐምሌ ወር በኋላ ግን ደመወዝ እንደሚቋረጥ በቪዲዮ ኮንፈረንስ መናገራቸውን ያስረዳሉ፡፡
በአዲሱ የሥራ ድልድል እንደ አገር ከ300 በላይ ሠራተኞች ከሥራ ምድብ ውጪ ሆነዋል የሚሉት አቤቱታ አቅራቢው፣ በአዲስ አበባ ከ40 በላይ የሚሆኑ ሠራተኞች ከሥራ ውጪ መደረጋቸውን ተናግረዋል፡፡
ሠራተኞች ከሥራ ውጪ የተደረጉባቸው ምክንያቶች የተለያዩ ቢሆንም ዐብይ ምክንያቱ ግን ተቋሙ በፍትሕ ሚኒስቴር ባላስመዘገበው የድልድል መመሪያ በተፈጠረ ችግር መሆኑን ይናገራሉ፡፡
በውድድሩ ከሥራ ውጪ የሆኑ ሰዎች ከድልድሉ በፊት ከነበሩበት ደረጃ ዝቅ ብለው ለመሥራት መሥሪያ ቤታቸውን በማመልከቻ የጠየቁ ቢሆንም፤ ማመልከቻቸው ተቀባይነት ሊያገኝ አለመቻሉን ያስረዳሉ፡፡
በአዲሱ የሥራ ድልድል 2ሺህ 800 የሚደርሱ የሥራ መደቦች የነበሩ ቢሆንም፤ አሁን ላይ ከ 1ሺህ 700 በላይ የሚደርሱ ሠራተኞችን በአዲሱ የሥራ መደብ ተመድበዋል፡፡ ይህ ማለት 800 የሚደርሱ ክፍት የሥራ መደቦች አሉ፡፡ ይሁንና ባሉት ክፍት የሥራ መደቦች እንኳን ሊመደቡ አለመቻላቸውን ይገልጻሉ፡፡
በአዲሱ መዋቅር የጠየቁትን የሥራ መደብ ለማግኘት በትምህርት ዝግጅትም በአገልግሎትም ቅድመ ሁኔዎችን ቢያሟሉም በአንድ ቀን ቀሪ ተፈጠረ በተባለ ዲስፕሊን ቅጣት በምደባ እንዳይወዳደሩ መታገዳቸውን ያስረዳሉ፡፡
አንድ ቀን በችግር ምክንያት ስለቀረሁ የአመት ፈቃድ እያለኝ ከአመት ፈቃድ መቀነስ እየተቻለ ሆነ ተብሎ የዲስፕሊን ቅጣት የተላለፈው አሁን ላይ በሚደረገው የሥራ ድልድል ተሳታፊ እንዳይሆኑ ለማድረግ ታስቦ መሆኑን ይናገራሉ፡፡
ሌላኛው አቤቱታ አቅራቢ ደግሞ አቶ መሰለ አረጋኢ ናቸው፡፡ እንደ አቶ መሰለ ገለጻ፤ ከድልድሉ በፊት በአዲስ አበባ ሪጂን ሽሮ ሜዳ ቅርንጫፍ በምዝገባ ባለሙያነት ይሠሩ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ በውክልና የጡረታ የአበል ውሳኔ ባለሙያ በመሆን ይሠሩ ነበር፡፡ በተቋሙ ለሦስት ዓመታት ገደማ ሠርተዋል፡፡ በአጠቃላይ 13 ዓመት የሚደርስ የሥራ ልምድ አላቸው፡፡
በተቋሙ ሲመጡ በደረጃ 11 በአበል ውሳኔ ባለሙያነት ተቀጥረው ነበር፡፡ ቀጥሎም ባላቸው የሥራ ልምድ እና የትምህርት ደረጃ በመነሳት ደረጃ 12 አበል ባለሙያነት ተመደቡ፡፡ ይሁን እንጂ አበል ውሳኔ የሚሠራ ባለሙያ እርሳቸው በሚሠሩበት ቅርንጫፍ ስላልነበረ በውክልና በአበል ውሳኔ ሲሠሩ ቆዩ፡፡ አዲሱ የሥራ ድልድል እስኪወጣ ድረስም ሲሠሩ የነበረው በአበል ውሳኔ ባለሙያነት መሆኑን ይናገራሉ፡፡
ለአዲስ ዘመን ዝግጅት ክፍል አቤቱታ ያቀረቡት ሁሉም ሠራተኞች ከሥራ የተነሱበት ምክንያት የተለያየ ቢሆንም የጋራ የሚያደርጋቸው ነገር አለ የሚሉት አቶ መሰለ፣ ይህም ሕግ እና መመሪያን ባልተከተለ መንገድ ጸድቋል ተብሎ የወጣው መመሪያ መሆኑን ይናገራሉ፡፡
በመጀመሪያ ደረጃ የድልድሉ መመሪያ በፍትሕ ሚኒስቴር የጸደቀ እና የሚታወቅ መሆን ነበረበት፡፡ ነገር ግን የውድድሩ መመሪያ የፍትሕ ሚኒስቴር የማያውቀውና በፍትሕ ሚኒስቴር ያልተመዘገበ ነው፡፡
ፍትሕ ሚኒስቴርን ምደባ ስለተደረገበት መመሪያ ሕጋዊነት ጠይቀናል የሚሉት አቶ መሰለ፣ መመሪያው በፍትሕ ሚኒስቴር እንዳልተመዘገበና እውቅናም እንደሌለው ከፍትሕ ሚኒስቴር ከተሰጣቸው ምላሽ ማረጋገጣቸውን ይናገራሉ፡፡
አሁን ላይ የመንግሥት ሠራተኞች ማህበራዊ ዋስትና አስተዳደር ተጠሪነቱ ለብሔራዊ ባንክ ነው የሚሉት አቶ መሰለ፣ የመንግሥት ሠራተኞች ማህበራዊ ዋስትና አስተዳደር ድልድሉ የወጣውም ተጠሪነቱ ለብሔራዊ ባንክ መሆኑን ተከትሎ እንደሆነ ያስረዳሉ፡፡
ለሥራ ድልድል የሚወጡ መመሪያዎች በሕግ የተመዘገቡ መሆን አንደሚገባቸው በተለያዩ የአገሪቱ ሕጎች የተመላከተ ቢሆንም፤ የመንግሥት ሠራተኞች ማህበራዊ ዋስትና አስተዳደር ግን በአገሪቱ መንግሥት እውቅና የሌለው የራሱን መመሪያ እንዲሁ በዘፈቀደ በማውጣትና ተግባራዊ በማድረጉ የተቋሙ አመራሮች የሥራ ድልድሉን ሂደት የራሳቸውን ፍላጎት ማስፈጸሚያ ማድረጋቸውን አቶ መሰለ ይገልጻሉ፡፡
አቶ መለስ፣ ‹‹መመሪያን ሳይከተሉ ሠራተኞችን እንደፈለጉ መመደብ ከባድ ወንጀል ነው›› ሲሉ ተናግረው፤ የመንግሥት ሠራተኞች ማኅበራዊ ዋስትና አስተዳደር ለሥራ ድልድሉ አወጣሁት ያለው መመሪያው ድብቅ፣ ሠራተኞች ያልተወያዩበትና ፈጽሞ የማያውቁት መሆኑን አስረድተዋል፡፡ መመሪያው ሲወጣ ተቋሙ ለሠራተኛው ለማሳወቅ አስገዳጅ ነገሮች ተፈጥረው ከሆነ እንኳን አንድ መመሪያ መመሪያ ሆኖ ዜጎችን ለማስተዳደር እንዲችል መመሪያው ሕጋዊ ሊያደርጉ የሚችሉ ሕጋዊ ሂደቶችን ተከትሎ በሚመለከተው አካል የጸደቀ መሆን ነበረበት ሲሉም አመልክተዋል፡፡
አዲስ የሥራ ምደባ መመሪያ በመንግሥት ሠራተኞች ማኅበራዊ ዋስትና አስተዳደር መውጣቱን የሰሙ በሁሉም ቅርንጫፎች የሚገኙ የተቋሙ ሠራተኞች መመሪያውን ይሰጠን ሲሉ ቢጠይቁም፤ መመሪያው ለሠራተኛ አይሰጥም የሚል ምላሽ እንደተሰጣቸው ይናገራሉ። መመሪያው ለሠራተኛ ምስጢር እንደሆነ እንዲቀጥል ተፈልጎ ነበር ያሉት አቶ መሰለ፣ ይሁን እንጂ ሠራተኞች የተለያዩ ዘዴዎችን ተጠቅመው መመሪያ የተባለውን ‹ሠራተኛ ጠል ሰነድ› በእጃቸው ማስገባታቸውን ይናገራሉ፡፡ ውድ አንባቢያን ሰነዱ ለአዲስ ዘመን ዝግጅት ክፍልም ደርሷል፡፡
እንደ አቶ መሰለ ገለጻ፤ ስለመመሪያው አመራሮች እንዲሁ በቪዲዮ ኮንፈረንስ ከመናገራቸው ውጪ አሁንም አብዛኛው ሠራተኛ በውል የሚያውቀው ነገር የለም፡፡
ስለመመሪያው የተቋሙ አመራሮች በቪዲዮ ኮንፈረንስ በሚናገሩበት ወቅት በርካታ የተቋሙ ሠራተኞች ስለመመሪያው ሕጋዊነት ጥያቄ አንስተው ነበር፡፡ ስለመመሪያው አግባብነት የተጠየቁ ሠራተኞችም ለምን ይጠይቁናል በሚል ጥርስ እንደተነከሰባቸውና ከምደባ ውጪ ሊደረጉ እንደቻሉ ስለመመሪያው ይናገራሉ፡፡
ስለመመሪያው ሕጋዊነት ጥያቄ አንስተው እንደነበር የተናገሩት አቶ መሰለ፣ ከከፍተኛ አመራሮች ‹‹መመሪያው መመሪያ ነው!›› የሚል ‹ትዕቢት› የተሞላበት ምላሽ እንተደተሰጣቸው ይናገራሉ፡፡ የአመራሩን ምላሽ ተከትሎ ይህ የቀረበው መመሪያ ትክክል አይደለም፡፡ ሠራተኞች ሁለት ምርጫ እንዲመርጡ መደረጉ ተንሳፋፊ ሠራተኞችን ይጨምራል፡፡ ስለሆነም ምርጫው ሦስት ቢደረግ ብለው ሃሳብ ሰጥተው እንደነበር የሚናገሩት አቶ መሰለ፣ ‹‹አንተ እዚህ ስለተከራከርክ የሚለወጥ ነገር የለም›› የሚል ምላሽ እንደተሰጣቸው ያስረዳሉ፡፡
ተቋሙ ለሥራ ድልድሉ ያወጣው መመሪያ ትክክል ቢሆን ኖሮ ከፍትህ ሚኒስቴር ከመመዝገብም ባለፈ በተቋሙ ድረ ገጽ ላይ መለቀቅ ነበረበት ሲሉ የሚሞግቱት አቶ መሰለ፣ ለዚህ ዘገባ ቃለመጠየቅ እስካደረጉበት ሰዓት ድረስ መመሪያው በተቋሙ ድረ ገጽ ላይ እንደሌለና እንዳልተመዘገበ ጠቁመዋል፡፡ ባልተመዘገበና ሕጋዊ ባልሆነ መመሪያ እንዲሁም ለሠራተኛው ቀርቦ ባልተወያየበትና ሠራተኛው በማያውቀው መመሪያ ይህን ያህል ቁጥር ያለው ሠራተኛ ከሥራ ውጪ መደረጉ አግባብነት የጎደለው መሆኑን ይነገራሉ፡፡
አቶ መሰለ እንደሚናገሩት፤ ከምደባ ውጪ የሆኑ ሠራተኞችን አንድ የሚያደርጋቸው ነገር አለ፡፡ ይህም ከሥራ ውጪ የተደረጉ ሁሉም ሠራተኞች ከሕግ ውጪ የወጣውን መመሪያ ቢቀበሉም እንኳን አመዳደቡ ፍትሐዊነት የጎደለው በመሆኑ ከሥራ ውጪ መደረጋቸው ነው፡፡ በምደባው ሁሉም ሠራተኞች በእኩል ዓይን ሊታዩ አልቻሉም፡፡ አመራሮች ያወጡትን ሕግ እንኳን በትክክል አልተገበሩትም፡፡ ያወጡት ሕግ ትክክል ነው ቢባል እንኳን ካወጡት ሕግ በተጻራሪ ሠራተኞች ከቤት እየተጠሩ ‹‹ይሄን ቦታ ትፈልጋለህ ወይስ አትፈልግም?›› ብለው በመጠየቅ ሠራተኞችን ሲመድቡ ነበር፡፡ በዚህም በርካታ ሠራተኞች ተረስተው ሳይመደቡ የቀሩ አሉ። ለምሳሌ አቶ መሰለ እና መሰል ሰዎች የዲስፕሊን እና መሰል ችግሮች የሌለባቸው ቢሆንም በተቋሙ አመራሮች ተረስተው ሳይመደቡ ቀርተዋል፡፡
እንደ አቶ መሰለ ገለጻ፤ መጀመሪያ ወደ መስሪያ ቤቱ ሲቀጠሩ በአዲስ ዘመን ጋዜጣ በወጣ ማስታወቂያ የአራት ዓመት ልምድ አቅርበው ነበር፡፡ በወቅቱ ቦታውን ለማግኘት የነበራቸው የሥራ ልምድ እና የትምህርት ዝግጅት ታይቶ ዛሬ ላይ ተወዳድረው ደረጃ 11 ላይ ተቀጠሩ፡፡ ይህ ቦታ በሥራ እድገት ምክንያት አልፈውት የነበረ ቢሆንም ዛሬ ላይ አዲስ በወጣው ድልድል ላይ ግን ለመወዳደር መርጠውት ነበር፡፡ ነገር ግን ምክንያቱ በውል ባልታወቀ ምክንያት የሥራ መደቡን አጡት፡፡
በአዲሱ ድልድል የተወዳደሩት መጀመሪያ ሲቀጠሩ በነበረው እና ለሦስት ዓመት ያህል በሠሩበት የሥራ መደብ ሲሆን፣ በዚህ የሥራ መደብ ላይ ብቸኛ ተወዳዳሪ መሆናቸውን ይናገራሉ፡፡ ለዝግጅት ክፍላችን ያቀረቧቸው ሰነዶችም ይህንኑ ሃቅ ያመላከታሉ፡፡ ይሁን እንጂ አቤቱታ አቅራቢውን ከሥራ ለማባረር ስለፈለጉ ብቻ ለሦስት ዓመታት ሲሠሩበት ከነበረው እና መጀመሪያውኑ ወደ ተቋሙ ሲመጡ ተቀጥረውበት ከነበረው መደብ እንዲነሱ መደረጋቸውን ያብራራሉ፡፡
ይህን ተከትሎ ለምን የሥራ መደቡን ሊያጡት እንደቻሉ? ለተቋሙ ጥያቄ ማንሳታቸውን የሚናገሩት አቶ መሰለ፣ ‹‹ድሮ ስትቀጠር የነበረው መመሪያ እና አዲሱ መመሪያ አንድ አይደለም›› የሚል ምላሽ እንደተሰጣቸው ይናገራሉ፡፡›› ይሁን እንጂ አቤቱታ አቅራቢው ከሦስት ዓመት በፊት ሲቀጠሩ በአዲስ ዘመን ጋዜጣ ወጥቶ የነበረውን ማስታወቂያ ላይ የተገለጸው ትምህርት ዝግጅት እና የሥራ ልምድ አሁን ለሥራ መደቡ የተጠየቀው መስፈርት ጋር ምንም ልዩነት አልነበረውም፡፡ ነገር ግን ‹አውቆ የተኛን ቢቀሰቅሱት አይሰማም› እንደሚባለው በመሆኑ «አቤቱታዬን ሊሰሙኝ አልቻሉም፡፡» ሲሉ ይናገራሉ፡፡
አያይዘውም በብቸኝነት ተወዳድረውበት በነበረው ቦታ ላይ በሌላ ሁለት መደብ ላይ ተወዳድሮ የተሸነፈን ሰው እንዲመደብ መደረጉን ያስረዳሉ፡፡
አቶ መሰለ ውድድሩን ሕገ ወጥ መሆኑን ማሳያ አድርገው ያቀረቡበት ሌላው ጉዳይ ደግሞ ከውድድር ጋር ተያይዞ የነበረውን ፈተና ነው፡፡ ለውድድሩ ሁሉም የተቋሙ ሠራተኞች ፈተና ይፈተኑ እንጂ የፈተናው ውጤት ባለመለጠፉ ሁሉም ሠራተኛ በፅሑፍ የፈተናውን ውጤት ምን ያህል እንዳገኘ የሚያውቅ አንድም ሠራተኛ አለመኖሩን ይናገራሉ፡፡ ለዚህም በምክንያትነት ያነሱት ፈተናውን ከተፈተኑ በኋላ የፈተና ውጤት አለመለጠፉን ነው፡፡
ሌላው አቶ መሰለን ምደባው የተካሄደበት መንገድ ኢፍትሃዊ ነው እንዲሉ ያስቻለው ዐብይ ምክንያት ደግሞ የሠራተኛው የማህደር ጥራት፣ የሥራ አፈጻጸም እና መሰል ነገሮችን የያዘው ውጤት ‹እከሌ ይሄን እከሌ ደግሞ ይሄን አገኘ› ተብሎ በግልጽ ለሠራተኛው መለጠፍ አለመቻሉ ነው፡፡
አቶ መሰለ እንደሚሉት፤ ትክክለኛ የሥራ ምደባ ቢከናወን ኖሮ ሠራተኛው ከማህደር ጥራቱ፣ ከሥራ አፈጻጸሙ እና መሰል ተያያዥነት ካላቸው ጉዳዮች የተገኙ፤ በሰው ኃይል እና በተቋሙ አመራር የሚሞሉ ነጥቦች ለሁሉም ሠራተኞች በግልጽ ይመላከቱ ነበር፡፡ አንድ ሰው በማህደር ጥራቱ፣ በሥራ አፈጻጸም እና መሰል መመዘኛዎች ስንት እንዳገኘ አይታወቅም፡፡ እንዲሁ ሠራተኛው ያለው አጠቃላይ ድምር ውጤት ብቻ ነው የተገለጸው፡፡ ይህም ሥራ ምደባው ‹ደባ› እንዳለበት ሁነኛ አመላካች ነው፡፡
ይህ የተደበላለቀ እና ግልጸኝነት የጎደለው አሠራር አመራሮች የፈለጉትን ሰው መርጠው ያልፈለጉትን ደግሞ ከሥራ ውጪ እንዲያደርጉ በር መክፈቱን አቶ መሰለ ጠቁመዋል፡፡
የአሠራር ሂደቱ ድብብቆሽ ከመሆኑም ባሻገር የምደባ ውጤቱ በአንድ ቀን ተለጥፎ ሠራተኛው እንዲውቀው አልተደረገም፡፡ ለሥራ በመደቦች የተመረጡ ሠራተኞችን ለማሳወቅ በሦስት በተለያዩ ዙሮች ማስታወቂያ ተለጠፈዋል፡፡ ይህ ደግሞ ሆነ ተብሎ ለማጭበርበር እንዲመቻቸው ያደረጉት መሆኑን አቶ መሰለ ይናገራሉ፡፡
በሦስቱም ዙሮች ያልተመረጡ ሠራተኞች በአራተኛ ዙር እንመረጣለን ብለው ቢጠብቁም አራተኛ ዙር ምደባ እንደሌለ በአመራሩ ተነገራቸው፡፡ ይህን ተከትሎ ያልተመረጡ ሠራተኞች ስለምን ከምደባ ውጪ እንደተደረጉ ጥያቄ አነሱ፡፡ ይህን ተከትሎ ምደባ አቁመናል ብሎ የነበረው ተቋሙ ጥያቄ ያነሱ የተወሰኑ ሠራተኞችን ባልተወዳደሩበት ቦታ መደበ፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ ከምደባ ውጪ የሆኑ ሠራተኞች ለድልድል ኮሚቴው የቅሬታ ደብዳቤ አስገቡ፡፡ ይህን ተከትሎ ቅሬታ ያስገቡ ሠራተኞችን በስልክ ደውለው ቢሯቸው ድረስ እንዲመጣ በማድረግ፤ ‹‹እዚህ ቦታ ላይ ልንመድብህ ነው፡፡ ትቀበላለህ ወይስ አትቀበልም? የምትቀበል ከሆነ ያስገባኸውን ወይ ያስገባሽውን ቅሬታ ደብዳቤ አንሳ ወይም አንሺ›› ተብለው ይጠየቁ ገቡ፡፡
ይህን ተከተሎ ተራቸው ደርሷቸው በስልክ የተጠሩት የዛሬ አቤቱታ አቅራቢው አቶ መሰለ ነበሩ፡፡ አቶ መሰለም ‹‹እኛ በምንመድብህ ቦታ ላይ ለመሥራት ፈቃደኛ ነህ?›› ተብለው መጠየቃቸውን ይገልጻሉ፡፡ አቶ መሰለም በሚመደቡበት ቦታ ለመመደብ ይስማማሉ፡፡
ነገር ግን መዳቢዎች አንድ ቅድመ ሁኔታ አስቀመጡ፡፡ ይህም ‹‹በተወዳደርኩበት መደብ በውድድር ስለተሸነፍኩ ተቋሙ በመደበኝ ቦታ ለመሥራት ተስማማቻለሁ፡፡ በዚህም አስገብቸው የነበረውን ቅሬታ አንስቻለሁ›› ብለህ ፈርም የሚል ነበር፡፡ በዚህም ‹‹እኔ በተወዳደርኩበት መደብ ብቸኛ ተወዳደሪ ሆኜ እያለ ስለምን በውድድር ተሸንፌአለሁ የሚል ሰነድ ላይ እፈርማለሁ›› ሲሉ መጠየቃቸውን ይናገራሉ፡፡ በዚህም ‹‹ከግቢ ውጣ!›› ተብለው መባረራቸውን ያስረዳሉ፡፡
ደረጃ አስር መግባት ትፈልጋለህ ተብለው መጠየቃቸውን እና ይህን ተከትሎ የነበርኩበት ደረጃ አስራ ሁለት ነው፡፡ የተወዳደርኩት ደግሞ ደረጃ አሥራአንድ ነው፡፡ በዚህም ጉዳዩን ለቅሬታ ሰሚ ኮሚቴ አስገብቼ እየተጠባበኩ ነው፡፡ ስለዚህ እኔ በብቸኝነት ከተወዳደረኩበት እና ዝቅተኛውን ተፈላጊ ችሎታ አሟልቼ እያለ የተወዳደርኩበት መደብ ላይ መቀጠር ሲገባኝ እንዲሁ በዘፈቀደ ደረጃ 10 መግባት ከፈግህ ግባ እባላለሁ? በሚል በዚህ አካሄድም አልሰማማም ማለታቸውን ይናገራሉ፡፡
በስልክ ተጠርተው አመራሩ በፈለገው የሥራ መደብ እንዲገቡ የተደረጉ ሰዎች አሉ የሚሉት አቶ መሰለ፣ ለቅሬታ ሰሚ አስገብተው የነበሩት የቅሬታ ደብዳቤም አንስተናል የሚለውን ፊርማ ተገደው ማንሳታቸውንም አመላክተዋል፡፡
አመራሩ ሠራተኞችን በስልክ እየጠራ በመደበ ጊዜ ትንሽ ሥራ ልምድ እና ዝቅተኛ የትምህርት ዝግጅት ያለው ሰው ከፍተኛ ቦታ የተሰጠው ሲሆን፣ የማስተር የትምህርት ዝግጅት እና ከፍተኛ የሥራ ልምድ ያላቸው ሠራተኞች ደግሞ ከደረጃ በታች የዲፕሎማ የትምህርት ዝግጅት በሚያስፈልገው የሥራ መደብ ላይ እንዲመደቡ መደረጉን ይገልጻሉ፡፡
ውድ አንባቢያን በሚቀጥለው ዝግጅታችን ከሌሎች አቤቱታ አቅራቢዎች፣ ከሰነዶች እና ከማኅበራዊ ዋስትና ዋና ሥራ አስፈጻሚ ያገኘናቸውን ምላሾች ይዘን የምንቀርብ መሆኑን ከወዲሁ ለመጠቆም እንወዳለን፡፡ እስከዚያው ቸር እንሰንብት፡፡ ሰላም!
ሙሉቀን ታደገ
አዲስ ዘመን ሰኔ 14/2015