አገር ከራት- ቀዳማይ ተምሳሌት
የድንቅነሽ ሉሲ- መገኛ እናት
የመደማመጥ ቀና ዘይቤ
የውብ ባህል መናኸሪያ
የተፈጥሮ ፀጋ -የአብሮነት መታያ
ሉሲ መለያችን
ኩአሶ ጨዋታችን
ሰድአ ሰርጋችን
እንግዳ ተቀባይ- ክቡር ባህላችን
ከበራሕሌ እስከ አፍዴራ
ከያሎ እስከ ሰመራ
ከሰሙሮቢ እስከ ተላላ
ከአዋሽ እስከ ጭፍራ
ገፅታ መላያችን
መገለጫ -ኩራታችን
ለቸገረ የሚሰጥ- እጁ የማይሰስት
በረኸኛው አፋር -ያውቃል መረዳዳት
እጅ ከምን ቢሉት – በቶሎ የሚደርስ
ለጋስ ነው ህዝባችን -አንጀትን የሚያርስ
ልክ እንደልባችን -ታማኙ ወንዛችን
አዋሽ አባመስጠት -አልምቶ አኮራን
ለውጭ እጅ ሳይሰጥ -እዚሁ አንጎራጉሮ
ለስንቱ ስራ ፈት- ለስንቱ ጉሮሮ
መከታና አለኝታ -ወንዛችን ይናገር
ጥጡና ሸንኮራው በይፋ ይመስክር
በጣም-ሚዋደዱ ሁለት ባልንጀሮች
ከዕለታት አንድ ቀን- ሸይጣን መሀል ገብቶ
ፍቅራቸው ጎምዞ- ሆኑ ባለንጋሮች
መንገድን በደረቅ -ነገርን በእርቅ አንዲሉ አባቶች
መዳኘት ያውቃሉ- የአፋር ሽማግሌዎች
ሙዚቃውስ ቢባል -ስልተምት ጠብቆ
እንጠጥ ዝልል ሲል- ስሜትን ሸምቆ
ውዳሴ ሙገሳወ-የቃላት ጨዋታው
በዳጉ ይቃኛል -በዳጉ ይሾራል
በቀደምት አባቶች -በተረት ተዋዝቶ
በወግ ተቀምሮ -ታሪክን አጉልቶ
በእኛነት መስታወት-ዘመናት ሲገለጥ
ቀደምት መሆናችን -ይታወቃል በርግጥ
ሬጌ፤ራስታ- ፍሪዝ ቢንጨባረር
ከባለቤት ወስዶ -ለራስ ለማሳመር
የጣሩት ባዕዶች -ይህ የፀጉር ስሪት
ማን በነገራቸው ማነስ ባስረዳቸው
የአፋሮች መሆኑ -ፍሪዙ ፀጉራቸው
ሰለሞን ብርሀኑ 2005 ዓ/ም
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 28/2011