ዛሬ ባለበት ነገ የሚገኝ ነገር ካለ እሱ ምን እንደ ሆነ ማወቅ ይከብዳል። እንደ ድሮው ጊዜ “ድንጋይ” እንዳንል እንኳን ድሮ የምናውቃቸው ድንጋዮች ዛሬ የሉም። ዛፎች እንዳንል አሁን የሚተከሉት እንጂ እድሜ ያስቆጠሩት ተመንጥረዋል፤ በአዲሱ አገላለፅ ተጨፍጭፈዋል። ወንዞች እንዳንል የደረቁትን ሳንጨምር ያሉትም ቀጥነዋል። ሀይቆች እንዳንል አብያታ እንኳን ባለፉት 30 እና 40 ዓመታት ውስጥ ስንት ኪሎ ሜትር ነው ወደ ውስጥ ተሰብስቧል የሚባለው?። ስለዚህ ከሞባይል ካርዶች በስተቀር ባሉበት ሁኔታ ላይ ያሉ ነገሮች (ሸቀጦች፣ ምግቦች፣ ወንዝና ፏፏቴዎች፣ ጋራና ሸንተረሮች . . .) የሉም ማለት ይሆናልና አበስኩ ገበርኩ ያሰኛል። ኧረ እንደውም ያስፈራል (ፈሪሀ እግዚአብሔር ላለው)።
ነፍሱን ይማረውና የተረት ሰፈሩ (አይ ተረት ሰፈር፣ እንዴት ነሽ? ጋሽ ስብሀትና ሌሎችም ሰላም ብለውሻል፤ አልተገናኛችሁ ይሆን እንዴ?) ኮመዲያን ተስፋዬ ካሳ ለዓመት በአል ወደ አንድ በአካባቢው ወደ’ሚገኝ በግ ተራ ሄዶ “ይሄ ስንት ነው?” በማለቱ ምክንያት “347 ብር“ የሚል መልስን በማግኘቱ ተደናግጦ “ምነው ዲፕሎም አለው እንዴ?” የሚል መልስ መልሶ መስጠቱን በዛው በተከበረ ሙያው አጫውቶን፣ አዝናንቶን፣ አስተምሮንና ተምብዮም ነበር። አይ ተስፍሽ ዛሬ ቢኖር ኖሮ ምን ይል ይሆን፣ ምንስ ብሎ ያጫውተን፣ ያዝናናን፣ ያስተምረንና ይተነብይ ይሆን ነበር።? ነው ወይስ ምንም ሳይል ደንግጦ በርሮ ይጠፋ ይሆን።?
ገዥ – ይሄ በግ ስንት ነው?
ሻጭ – 16ሺህ ብር።
ገዥ – መጨረሻው፤
ሻጭ – ይሄው ነው፤ አይቀንስም።
መግቢያ ቢበዛ ባህያ አይጫንም እንዲሉ (ባይሉም) መግቢያችንን ገታ አድርገን ወደ ጉዳያችን፣ ወደ ምስጋናችንና እጅ መንሳት ተግባራችን እንመለስ።
በእርግጥ ባለበት መቆየትን በተመለከተ ብዙ አይነት አተያዮች አሉ። ባለበት የቆየ ውሃ እንደሚበላው ሁሉ ባለበት የቆየ ጭንቅላትም ያው እንደሚታወቀው ነው። በመሆኑም ባሉበት መቆየት ወደ እነዚህ አካባቢ አይመከርም ማለት ነው።
ወደ ገበያና ግብይት፣ ገዥና ሻጭ ስንመጣ ግን ጉዳዩ ከእነዚህ የተለየ ሆኖ ነው የምናገኘው። ምክንያቱ ደግሞ በእነዚህ አካባቢ ባሉበት መቆየት ማለት ትርጉሙ የፖለቲካ መረጋጋት፣ የገንዘብ የመግዛት አቅም መጠናከር፣ የሸማቾች የመሸመት አቅም መኖር፣ የግሽበት መጠን መውረድ፣ ወዘተርፈ ሲሆን፤ ሲጠቃለል የሰው ልጅ በልቶ መኖር ማለት ስለሚሆን ነው።
እንደዚህ ጸሐፊ ግንዛቤና ተከታታይ እይታ እነዚህን ሁሉ በትክክል የተገነዘቡ ወገኖች ቢኖሩ አምስቱ የሞባይል ካርዶች (ከባለ 5 እስከ ባለ 100 ብር ያሉት) ብቻ ናቸው። በመሆኑም እነዚህን ወገኖች ጎንበስ ብለን እጅ ልንነሳቸው ይገባል። እነሱም እንደ ሌሎች ሸቀጦች ከማበዳቸው በፊት ልንከባከባቸው፣ በሰላምታም ቢሆን ውለታቸውን ልንመልስላቸው ይገባል።
እስቲ ቆይ ትንሿ የፖስታ ሳጥን ቁጥር ከ85 ብር ተነስታ 600 ብር (ዓመታዊ የሳጥን ኪራይ) ስትገባ ባለ 5 ብሯ ካርድ 0.5 ሳ. እንኳን መጨመርን ማን ከለከላት፤ ህሊናዋ እንጂ ማንም።
እነ ምስር፣ ነጭ ሽንኩርት፣ እንቁላል . . . “አትንኩን”፣ “አትድረሱብን” እያሉ ደሀን ሲፀየፉ እነ ባለ 10 ብር ካርድ ከማን ያንሱና ነው ባሉበት ሁኔታ ላይ ሊገኙ የቻሉት፤ ሰብአዊነት ይዟቸው፣ ህሊናቸው ገዝቷቸው፤ ፈሪሀ እግዚአብሄር አድሮባቸው ነው እንጂ እነሱም ከማንም አያንሱም እኮ፤ ከማንም።
በስንዴ አገር ሞኮሮኒ ባለ 80 እና ባለ 90 (በኪሎ) ነኝ ሲል፣ ባለ 25 ብር ካርድ ብድግ ብሎ ከዛሬ ጀምሮ እኔም ባለ 100 ሆኛለሁ ቢል ማን ይከለክለዋል። የህሊና ጉዳይ፣ የሰብአዊነት ጉዳይ፣ የስነምግባር ጉዳይ . . . ነው እንጂ ዛሬ እኮ እሱም ከእህል እና ውሀ እኩል አስፈላጊ ሆኗል።
ዛሬ ቁርስ ለመብላት በክበባት ሳይቀር 100 ብር ዋጋ ሲያጣ፤ ዛሬ 100 ብር ሶስት ሲንግል እንኳን ለማስጎንጨት አይናፋር ሲሆን . . . እራሱ 100 ብር ለ200 ብር መልስ ሲሆን ባለ 100 ብሩ ካርድ እንጣጥ ብሎ ከዛሬ ጀምሮ እኔም ባለ 100 መሆኔ ቀርቶ ባለ1000 ሆኛለሁ ቢል አዳሜ ምን ታመጫለሽ፤ ምንም። እሱ ግን ጉዳዩ የህሊና ጉዳይ ነውና፣ ጉዳዩ የስነምግባር ጉዳይ ነውና፤ ጉዳዩ የአገርና የህዝብ ጉዳይ ነውና አላደረገውም። እሱ ብቻ አይደለም፤ በድምሩ “ካርድ” ወይም “የሞባይል ካርድ” ብለን በጥቅል የምንጠራቸው አምስቱም ካርዶች የነፃ ገበያ ጽንሰ-ሀሳብ እጅጉን የገባቸው፤ በተወዳድሮ ማሸነፍ እንጂ በአቋርጦ መክበር የማያምኑ በመሆናቸው እንደዚህ አይነት የስነምግባር ጥሰት ውስጥ አልገቡም። እንደ እነ ዘይት፣ ስኳር፣ ማኪያቶ ምናምንቴዎች ኢሰብአዊ ተግባራት ውስጥ አልተዘፈቁም። ብታምኑም ባታምኑም አምስቱም ጨዋዎች ናቸው። እነ ስነምግባር ለምኔ “አሳጣችሁን”፣ “አዋረዳችሁን”፣ “አሳቀላችሁን” . . . ቢሏቸውም፤ እነሱ ግን ማተባቸውን ለመበጠስ፣ ወገናቸውን ለማስለቀስ አልተዘጋጁም እና “ንክች ያባ ቢላዎ ልጅ” እንዳሉ ናቸው። እኛም ይህንን አቋማቸውን በመደገፍ ከጎናቸው ልንቆም ይገባን ነበር፤ አልነበረም?
ካርዶች፣ እውነት እውነት እላችኋለሁ “. . . ነብር ዥንጉርጉርነቱን ይቀይራልን?” የሚለውን በእናንተ፣ በሁላችሁም፤ ባምስታችሁም አየሁት። ስለ እውነት በእናንተ አየሁት፤ ኮራሁም። ወገን አለኝም አልኩ። የሌላውንማ . . . የለማ እውነት እሱ የለማ . . . (ገጣሚት ሜሮን ጌትነት ስፖርት ስታሰራ ነው ወይስ . . . – ”ወደ ላይ” ስትል ነበር የተባለው?)።
በመጨረሻም፣ ርእሳችንን እንደግመዋለን። “ባላችሁበት ሁኔታ ላይ ያላችሁት የሞባይል ካርዶች፣ ቃላችሁን ያላዛነፋችሁት፣ ከነፈሰው ጋር ያልነፈሳችሁት፣ ከተስገበገበው ጋር ያልተስገበገባችሁት፣ “ሰው ተኮር” የሆናችሁት . . . አምስታችሁንም በድጋሚ እጅ እንነሳለን!!!”
ግርማ መንግሥቴ
አዲስ ዘመን ሰኔ 5/2015