አዲስ ዘመን ጋዜጣ የዘመን መስታወት ነው:: ዛሬ 21ኛው ክፍለ ዘመን ላይ ሆኖ የ20ኛውን ክፍለ ዘመን ሁነቶች የሚናገር ነው:: የዓመታት ብቻ ሳይሆን የክፍለ ዘመንም መስታወት ነው:: ሰዎች ያልኖሩበትን ዕድሜ እንዲኖሩ ያደርጋል::
አዲስ ዘመን ጋዜጣ ‹‹አዲስ ዘመን ድሮ›› የሚል ዓምድ አለው:: በዚህ ዓመት ከዘመናት በፊት የተከሰቱ አስገራሚ ሁነቶች፣ ማስታዎቂያዎች፣ ፎቶዎች.. በአጠቃላይ ለዛሬው ትውልድ ግርምትን የሚፈጥሩ ነገሮች ለትውስታ የሚቀርቡበት ነው::
በዚህ ዓመት የሚወጡ አስገራሚ ዜናዎች በማህበራዊ የትስስር ገጾች በስፋት ይዘዋወራሉ:: አንዳንዶችም በብሮድካስት ሚዲያዎች ይቀርባሉ:: ፎቶዎችና የድሮ ማስታወቂያዎች ‹‹አዲስ ዘመን ጋዜጣ›› እየተባሉ ይዘዋወራሉ:: ለምሳሌ፤ ያለ ሰፈሯ ስትዘዋወር የተያዘችው ሴት፣ አጭር ቀሚስ መልበስ ተከልክሎ የነበረበት፣ ሴት መስሎ ሲሰራ የነበረው ወንድ፣ የዶሮዎችን ዝቅዝቆ መያዝ የሚከለክለው ትዕዛዝ… የመሳሰሉት ፌስቡክ ላይ ሲዘዋወሩ ነበር::
በብዙ የሬዲዮና ቴሌቪዥን ፕሮግራሞች ላይ (ትዝታችን፣ ትዝ አለኝ የጥንቱ፣ ትዝታን በዜማ) አዲስ ዘመን ጋዜጣ በተደጋጋሚ ይጠቀሳል:: ከእነዚህ ቋሚ ፕሮግራሞች በተጨማሪ በአንዳንድ ወቅታዊና ታሪካዊ ፕሮግራሞች እንደ ምንጭ ይጠቀሳል::
አዲስ ዘመን ጋዜጣ ከታሪክ መጻሕፍት ጀርባ ማጣቀሻ ሆኖ እናገኘዋለን:: የታላላቅ ሰዎች ግለ ታሪክ ሲጻፍ ምንጭ ሆኖ ይገኛል:: የታላላቅ ደራሲዎችና ፖለቲከኞች ሥራዎች ይገኙበታል:: ለአንድ ምዕተ ዓመት የተጠጉ (የ82 ዓመታት) ሁነቶች ተሰንደው ይገኙበታል::
ከ82 ዓመታት በፊት የኢትዮጵያ ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ጥበባዊ ሁኔታዎች ይገኙበታል:: በሦስት ሥርዓተ መንግሥታት ውስጥ(ንጉሣዊ፣ ወታደራዊ፣ አብዮታዊ ዴሞክራሲ) ኢትዮጵያ ምን ትመስል እንደነበር የኢትዮጵያ ታሪክ በዚህ ጋዜጣ ውስጥ ይገኛል::
አዲስ ዘመን የዘመን መስታወት ነው የምንለው ለዚህ ነው:: የተለያዩ ዘርፎች በየዘመኑ ምን ይመስሉ እንደነበር ስለሚያሳየን ነው:: አጭር ቀሚስ መልበስ ሲከለከል ጋዜጣው የወጣበት ዘመን ምን አይነት ባህላዊና ማህበራዊ ይዘት እንደነበር ይጠቁማል:: ዶሮዎችን ዘቅዝቆ መያዝ የሚከለክል ትዕዛዝ ሲወጣ ምን አይነት ማህበረሰባዊ ሞራል እንደነበር ይጠቁማል:: በባህልና ኪነ ጥበብ ዓምዶች የዘመኑን ጥበባዊ ሂደት ያሳየናል::
ወዲህ ደግሞ ወደ ፖለቲካው ስንመጣ፤ የኢትዮጵያን መንግሥታት ባህሪ መስታወት ሆኖ ያሳየናል:: በንጉሡ ጊዜ ምን አይነት ሁነቶች በምን መንገድ ሽፋን ይሰጣቸዋል፣ በወታደራዊው የደርግ መንግሥት ጊዜ ምን አይነት ጉዳዮች በምን መንገድ ሽፋን ይሰጣቸዋል፣ አብዮታዊ ዴሞክራዊ በሆነው የኢህአዴግ ዘመን ምን አይነት ጉዳዮች በምን አይነት ሁኔታ ሽፋን ያገኛሉ… እነዚህንና የመሳሰሉትን መስታወት ሆኖ ያሳየናል:: ስለዚህ አዲስ ዘመን ጋዜጣ የዘመን መስታወት ነው:: ዘመን በአዲስ ዘመን ጋዜጣ ይታያል::
አዲስ ዘመን ጋዜጣ በአገሪቱ እነሆ ዛሬ ድረስ ብቸኛ ዕለታዊ ጋዜጣ ነው:: በዚሁ እግረ መንገድ ወደ ትዝብት ነው የምሄደው::
ኢትዮጵያ ውስጥ ከፍተኛ የትምህርት ማዕረግ ካላቸው ሰዎች እስከ ተራው ዜጋ ድረስ የሚዲያ ግንዛቤ (Media literacy) ዝቅተኛ ነው:: የሚያስገርመው ይህ የሆነው እስከ ሚዲያ ባለሙያዎችና አመራሮች ድረስ ነው:: በብዙ የውይይትና ሥልጠና አጋጣሚዎች
የሰማሁት ‹‹የህትመት ሚዲያ ዘመኑ አልፎበታል›› የሚል የሰነፍ አስተያየት ነው:: በዚህ ነገር ከመገረሜ የተነሳ የሥልጣኔ ማማ ላይ ያሉ አገራትን የህትመት ሚዲያዎች ሁኔታ ነው የምዳስሰው:: አውሮፓና አሜሪካ አገራትን የማየት ዕድል ያላቸው ሰዎች በአካልም ሆነ በበይነ መረብ ሳገኝ የምጠይቃቸው ይህንኑ ነው::
እንደ ኢትዮጵያ ባለ አንድ ዕለታዊ ጋዜጣ ብቻ ባላት አገር የህትመት ሚዲያ አልፎበታል ይባል እንጂ ብዙ ዕለታዊ ጋዜጣ ባላቸው አገሮች ግን ትልቁ ተፅዕኖ ፈጣሪ የህትመት ሚዲያ ነው:: እነዚህ አገራት በዓይነትም ሆነ በጥራት ከኢትዮጵያ በብዙ እጥፍ የተሻለ የኢንተርኔትም ሆነ ሌላ ቴክኖሎጂ ተጠቃሚዎች ናቸው:: ዳሩ ግን የወረቀት ጋዜጣ ዛሬም አላቸው:: ትንታኔዎችና የምርመራ ዘገባዎች የሚሰሩት በጋዜጦች ነው:: ዓለም አቀፉ ‹‹ፑልቲዘር ፕራይዝ›› የሚሸልማቸው ጋዜጠኞች በብዛት በህትመት ጋዜጣ የምርመራ ዘገባ የሰሩ ናቸው:: ይህንን በቀላሉ ወደ በይነ መረብ በመግባት ማረጋገጥ የሚቻል ነው::
እንዲያውም አሁን አሁን ጋዜጣና መጽሔትን ብቻ ሳይሆን ሬዲዮና ቴሌቪዥንንም ‹‹አልፎበታል›› ማለት እየተጀመረ ነው:: ጀማሪዎቹ አገራት አለፈበት ያላሉትን፣ ገና አዳርሰን እንኳን ሳንጨርስ አለፈበት ልንል አይገባም:: ለመሆኑ ስንት የበይነ መረብ አማራጭ ተጠቃሚ ዜጋ ኖሮን ይሆን?
ከፍተኛ ባለሥልጣናትን ጨምሮ በታዋቂ ሰዎችና በተራ ግለሰቦች ሁሉ በሥራ አጋጣሚ ብዙ የታዘብኩት ነገር አለ:: ሚዲያ የሚመስላቸው ከፊታቸው ትልቅ ካሜራ ሲደቀን ነው:: ሚዲያ የሚመስላቸው በቴሌቪዥን መስኮት መታየት ነው:: ለቃለ መጠይቅ ሲጠየቁ ጋዜጣ መሆኑን ካወቁ በኋላ ወኔያቸው ይቀንሳል:: እንዲያውም ከቅርብ ዓመታት በፊት በመግለጫዎች ላይ የአንድ ቴሌቪዥን
መቅረት እንጂ የጋዜጣ መቅረት ብዙም አያሳስባቸውም:: ይህ የሆነው የይዘት ልዩነትን በመምረጥ ሳይሆን ሚዲያ ማለት በቴሌቪዥን የሚታይ ነው ተብሎ ስለሚታሰብ ነው::
ይህ ዝቅተኛ የሚዲያ ግንዛቤ ከሙያው ውጭ ባሉ ሰዎች ብቻ አይደለም፤ በራሳቸው በጋዜጠኞችም በስፋት የሚታይ ነው:: ጋዜጠኛ ነኝ ብለው የሚያስቡት ዜና አንባቢ ሲሆኑ ነው:: የዜና ዋናው ጉዳይ ግን ሰሪው ነው:: ወጥቶ ወርዶ፣ የብዙ ሰው ፊት ገርፎት ዜናውን የሰራው ሪፖርተሩ ነው:: ብዙ ህፀፆችን ነቅሶ ለአድማጭ ተመልካች ወይም አንባቢ ያበቃው አርታኢው (ኤዲተር) ነው::
እነሆ ለ82 ዓመታት ያህል የዘለቀው አዲስ ዘመን ጋዜጣ የህትመቱን ተግዳሮቶች ተቋቁሞ እዚህ ደርሷል:: ዘመኑ ያመጣቸውን የቴክኖሎጂ አማራጮች በመጠቀም ሁሉንም የአዲስ ዘመን ጋዜጣ ይዘቶች በበይነ መረቡ ዓለም ማግኘት ቢቻልም ጋዜጣ ግን የራሱ የሆነ ውበት አለው:: ለምሳሌ ትልልቅ ሰዎች በወረቀቱ ጋዜጣ ነው ማንበብ የሚፈልጉት::
ምንም እንኳን ወረቀትም ለአደጋ ተጋላጭ ቢሆንም የበይነ መረቡን ዓለም ብቻውን ማመንም ልክ አይሆንም:: ባለፈው ወር አካባቢ የፌስቡክ (ሜታ) ካምፓኒ እንዳጋጠመው አይነት ችግር ቢያጋጥም የበይነ መረቡ ዓለም ሊበላሽ ይችላል:: የፌስቡክ መጠነኛ ችግር ስለነበር ወዲያውኑ ተስተካከለ:: ሰው ሰራሽ ነውና የበይነ መረቡ ዓለም የሚበላሽበት አጋጣሚ ቢከሰት ያስቀመጥናቸው መረጃዎች ሊጠፉም ይችላሉ:: ስለዚህ ወረቀቱም መኖር አለበት ለማለት ነው::
በአጠቃላይ አዲስ ዘመን ጋዜጣ ለህትመቱ ሚዲያ ተምሳሌት ሆኖ፣ የወረቀት ውድነትን ተቋቁሞ ነባር ማንነቱን በአዲስ አሰራር እያስቀጠለ ነው:: አዲስ ዘመን ጋዜጣ የዘመን መስታወት ነውና ይህ አሰራር ይቀጥል እያልኩ፤ ለጋዜጣውና ሠራተኞቹ እንኳን ለ82ኛ ዓመቱ አደረሰን!
ዋለልኝ አየለ
አዲስ ዘመን ግንቦት 30/2015