ይቺን ቀልድ ታውቋት ይሆን? ከቀልዷ በፊት ግን አንድ ሁላችንም የምናውቀው ነገር ቢኖር ‹‹ምን መሆን ትፈልጋለህ›› ሲባል ‹‹ዶክተር›› የሚለው እንደሚበዛ ነው። አንድ ቀን መምህሩ ተማሪዎችን እየዞረ ሲያድጉ ምን መሆን እንደሚፈልጉ እየጠየቀ ነው። ተማሪዎቹ ‹‹ዶክተር›› ይላሉ፤ የሁሉም ተማሪዎች ምኞት ዶክተር መሆኑ የገረመው አንደኛው ተማሪ ‹‹ምን መሆን ትፈልጋለህ›› ተብሎ ሲጠየቅ ‹‹ታማሚ›› አለ። ተማሪዎችም ስቀውበት መምህሩም ተገርሞ ‹‹ምነው›› ሲባል ‹‹አይ ሁሉም ዶክተር ሆነ፤ ታዲያ ህመምተኛ ከየት ይገኛል?›› አለ ይባላል።
ገና ከአንደኛ ክፍል ጀምሮ ‹‹ምን መሆን ትፈልጋለህ›› ሲባል ‹‹ዶክተር›› ማለት የብዙ ተማሪዎች መልስ ነበር። የተማሪዎች ብቻ ሳይሆን የወላጆችም ምኞት ነበር። በነገራችን ላይ የአሁን ተማሪ ግን እንደዚያ ይል ይሆን? እኔ ግን ስገምት ‹‹አክቲቪስት›› የሚሉ ይመስለኛል።
ዶክተርነት የተማሪዎች ምኞት የሆነው ከሙያው ትልቅነት የተነሳ ነው። ሙያ ከሙያ አይበልጥም ቢባልም የሰውን ሕይወት ማዳን ግን ትልቅ ነው። እንዲያውም እኮ ከሁሉም ነገር ጤና እንደሚቀድም ተደጋግሞ ይነገራል። በማህበራዊ ሕይወታችን ውስጥ ‹‹ዋናው ነገር ጤና ነው›› የሚለው ሀሳብ ተደጋግሞ ይነገራል። ከጤና ጋር የተያያዙ አባባሎችም አሉን።
‹‹ታሞ ከመማቀቅ አስቀድሞ መጠንቀቅ፣ ህመሙን የሸሸገ መድሃኒት አይገኝለትም፣ ታሞ የተነሳ ፈጣሪን አይረሳ….›› የሚሉት አባባሎች ቀዳሚው ጤንነት መሆኑን የሚናገሩ ናቸው። ለዚህ ነው የልጆች ምኞት ሁሉ ዶክተርነት የሆነው።
ስለዶክተር ያነሳሁት ሰሞኑን ዶክተሮች የሆነ ነገር ስላነሱ ነው። ነገሩ ቅሬታን የመግለጽ እንቅስቃሴ ነው። ይሄ እንቅስቃሴያቸው ከማህበራዊ ሚዲያ አልፎ በዋናው ሚዲያም ሽፋን አግኝቷል፤ ምን ይሄ ብቻ! ከዚያም አልፎ ዛሬ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር ይወያያሉ (ይሄን ከውይይታቸው በኋላ እናወራዋለን)።
ጎበዝ የእነዚህን ዶክተሮች ችግር ለመረዳት ዶክተር መሆን አያስፈልግም፤ ታማሚ መሆን በቂ ነው። መቼም ወደ ሆስፒታል ሄዶ የማያውቅ አይኖርም። ምንም ባይታመም እንኳን ሰው ይዞ ወይም ሰው ለመጠየቅ ያልሄደ የለም። ቢያንስ ቢያንስ ሥራ ለመቀጠር ለጤና ምርመራ የግድ የሄደ አይጠፋም። እና ምን ለማለት ነው፤ በሆስፒታል ውስጥ ያለ ችግር ለሁላችንም ግልጽ ነው። ግልጽ ያልሆነው ነገር ችግሩ የማነው የሚለው ነው?
‹‹ባለሙያ የለም፤ ብቃት የላቸውም›› የሚለው ወቀሳ ስንሰማው የቆየነው ነው። ታዲያ ሰሞኑን ከሐኪሞች የተነሳው ቅሬታ የባለሙያ ሳይሆን የመሳሪያ እጥረት እንዳለ ነው የሚናገረው። በህክምና ትምህርት ክፍል ተመርቀው ያልተቀጠሩ ተማሪዎች መኖራቸውን የባለሙያ እጥረት እንዳልሆነ እንደ ማሳያ ጠቅሰዋል። ያልተቀጠሩት ብቻ ሳይሆን የተቀጠሩትም በመሳሪያና በመድኃኒት እጥረት ህሙማን እየሞቱባቸው እንደሆነ ተናግረዋል። ይሄ ሁሉ የሆነውም በመንግሥት የተዝረከረከ አሰራር የህክምና ጉዳይ ትኩረት ስላልተሰጠው ነው ብለዋል።
አሁን እንግዲህ ጥፋቱ የመንግሥት ይሁን የባለሙያ ይሁን እኛ አናውቅ ይሆናል፤ ችግሩ መኖሩን ግን ሁላችንም እናውቃለን። በነገራችን ላይ የባለሙያ እጥረትም ከሆነ እኮ የመንግሥት ችግር ነው አይደል? ምክንያቱም በቂ ባለሙያ የሚኖርበት ሥርዓት መኖር አለበት።
ምንም እንኳን በብዙ የአገልግሎት መስጫ ተቋማት ውስጥ ችግር ቢኖርም ወደ ህክምና ተቋም ሄዶ ያልተማረረ የለም። የህክምና ተቋም እንደሌላው ተቋም አይደለም፤ የሕይወት ጉዳይ ነው። ህመም ተይዞ ነው ያ ሁሉ መጉላላት የሚኖረው። ህመሙ ጊዜ አይሰጥም።
በየሆስፒታሉ እንዲህ ነው። ገና ግቢውን ስትገቡ ሌላ ተጨማሪ ህመም ነው የሚሰማችሁ። በጣም ለተጎዳው ቅድሚያ ይሰጥ እንዳይባል በጣም የተጎዳው ራሱ ቀላል አይደለም፤ ማን ከማን ይቀድማል?
አንድ ህመምተኛ በአልጋ መጥፋት ምክንያት ከዓመት በላይ ቀጠሮ ይጠብቃል። አስቡት! በሽታው አንድ ዓመት ሙሉ ይጠብቃል? ይህን ያህል ጊዜ የሚጠብቅ በሽታ ከሆነማ መጀመሪያውኑም መሄድ አያስፈልግም ነበር፤ ወይም በራሱ ጊዜ ይድናል ማለት ነው።
እዚህ ጋ ገና ህመም እንደተሰማን ወደ ሐኪም ቤት መሄድ እንዳለብን ይመከራል፤ እዚያ ጋ ደግሞ በአንገብጋቢ በሽታ ተይዞ ከአንድ ዓመት በላይ ቀጠሮ ይጠብቃል። ታዲያ ይሄ የአልጋ ችግር የመንግሥት ችግር አይደለም?
ሌላው የመድሃኒት እጥረት ነው። ይሄ በተደጋጋሚ የምንሰማው ሀሜት ነው። እንደምንም ተራ ደርሶት ለምርመራ የበቃ ህመምተኛ የመድሃኒት ዝርዝር ይጻፍለታል፤ ያንን ይዞ ከመድሃኒት ቤት መድሃኒት ቤት መዞር ነው።
የህክምና መሳሪያ እጥረት መኖሩንም ዶክተሮች ሲናገሩ ነበር። የአልጋ እና የመድሃኒቱን ነገር ማንም ታካሚ የሚታዘበው ነው። የህክምና መሳሪያውን ችግር ግን ሐኪሞችና መንግሥት ብቻ ናቸው የሚያውቁት። መንግሥት በቂ መሳሪያ አለ ሲል ዶክተሮች ደግሞ የለም ይላሉ።
የለም ብቻ ሳይሆን ያሉት መሳሪያዎች ዘመናዊ አለመሆናቸውን፣ ተገቢውን አገልግሎት ስለማይሰጡ ዓይናችን እያየ ህመምተኛ ይሞታል ነው ያሉት። ኧረ እንዲያውም እነርሱ ራሳቸውም እየታመሙ ነው። ይሄ ማለት ከህመምተኛ ጋር ሲሆኑ በበቂ ሁኔታ የሚከላከል መሳሪያ የለም ማለት ነው። ይሄ ነው ከባዱ! ከልጅነቱ ጀምሮ ዶክተርነት ተመኝቶ ዶክተር የሆነው ሲታመም?
አሁንም የዶክተሮች ምኞት ዶክተር መሆን ነው። ገና እንዳልሆኑ ነው የቆጠሩት ማለት ነው። ምክንያቱም በቂ መሳሪያ ከሌለ፣ በቂ መድሃኒት ከሌለ፣ ህመምተኛ የሚታመምበት አልጋ ከሌለ ገና ዶክተር አልሆኑም ማለት ነው። ስለዚህ ዶክተር ይሆኑ ዘንድ ድምጻቸው መሰማት አለበት።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሚያዝያ 26/2011
በዋለልኝ አየለ