በመላው ዓለም በተለይም በዚህ ዘመን ስፖርት ከመዝናኛነት ያለፈ ትርጉምና ዘርፈ ብዙ ጥቅም እንዳለው የተረዱ አገራት በትኩረት እየሠሩበት ይገኛሉ:: ስፖርት ዓለም ላይ ከፍተኛ ገንዘብ የሚዘዋወርበት ዘርፍ እንደመሆኑ በሃገር ኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ አስተዋፅዖ ማድረግ ከጀመረ በርካታ ዓመታት ተቆጥረዋል:: ለአብነት ያህል ተወዳጅ የእግር ኳስ ሊግ ያላት እንግሊዝ ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ በስፖርቱ ታፈሳለች:: እአአ በ2019/20 የውድድር ዓመት ከፕሪምየር ሊጉ ብቻ 10ነጥብ4 ቢሊዮን ዶላር ማግኘቷን መረጃዎች ያሳያሉ:: እንደ አጠቃላይ ከስፖርት ዘርፍ ደግሞ ከዚህ የላቀ ኢኮኖሚያዊ አስተዋፅዖ ምንጭ እንደሚያበረክት መገመት ቀላል ነው::
በአንጻሩ ስፖርት ለኢትዮጵያ በርካታ አስተዋፅዖዎችን ያበረከተ ዘርፍ ይሁን እንጂ በኢኮኖሚው ላይ ያለው ሚና ምን ያህል እንደሆነ አይታወቅም:: በዘርፉ የሚልቀውን ገንዘብ የሚያንቀሳቅሰው መንግሥት ነው:: የስፖርት ማኅበራት፣ ክለቦች፣ የማሰልጠኛ ተቋማት፣ ብሔራዊ ቡድኖች፣… የመንግሥትን እጅ የሚጠብቁ እንደመሆኑ ወጪውን ማስላት ይቻል ይሆናል:: ይሁን እንጂ ስፖርት በአገር ኢኮኖሚ ላይ ያለውን ፋይዳ በደፈናው ከመናገር ባለፈ ምን ያህል እንደሆነ በገንዘብ ተምኖ ወይም በመቶኛ ተሰልቶ ከሌሎች ዘርፎች ጋር በማነፃፀር ይህ ነው ተብሎ የሚነገርለት አይደለም::
በመሆኑም መንግሥት ይህንን ለመለየት፤ ታዳጊዎችን ከማሰልጠን ሥራው ጎን ለጎን ሳይንሳዊ የጥናትና ምርምር ሥራዎችን የሚያከናውነው የኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ የኢትዮጵያ ስፖርት በኢኮኖሚው ላይ ምን አበርክቶ አለው የሚለውን እንዲያጠና ተልዕኮ ተሰጥቶታል:: ይህም ሥራ ከሁለት ዓመታት በፊት የተጀመረ ሲሆን፤ በተለያዩ ምክንያቶች እስካሁን መጠናቀቅ አልቻለም:: ከሰሞኑ አካዳሚው ባካሄደው 8ኛው ሃገር አቀፍ የስፖርት ሳይንስ ጥናትና ምርምር ጉባኤ ላይም ትልመ ጥናቱ (Proposal) ቀርቧል::
‹‹ስፖርት በኢትዮጵያ ሃገራዊ ልማት ላይ ያለው ፋይዳ›› በሚል ርዕስ እየተሠራ ያለው ይህ ጥናት፤ ስፖርት በሥራ ዕድል፣ በውጪ ምንዛሪ፣ በኢንቨስትመንት፣… ያለውን ድርሻ ማወቅ የጥናቱ ዓላማው መሆኑ ተጠቁማል:: ከዚህ ቀደም በዘርፉ መሰል ጥናቶች ተከናውነው አለማወቃቸው እና በመንግሥትም ሆነ መንግሥታዊ ባልሆኑ ተቋማት የተደራጀ መረጃ አለመኖሩ የጥናቱ ተግዳሮት ሊሆን እንደሚችል የተጠቆመ ሲሆን፣ ጥናቱ ትኩረቱን በተለይ በአትሌቲክስ፣ እግር ኳስ እና ባሕል ስፖርቶች ላይ እንደሚያደርግ ተገልፃል:: እነዚህ ስፖርቶች የተመረጡበት ምክንያትም ትኩረት ሳቢ እና ተጽዕኖ ፈጣሪ በመሆናቸው ነው:: የስፖርት ክለቦች፣ ፕሮጀክቶች፣ የማሰልጠኛ ማዕከላት፣ የስፖርት ማዘውተሪያዎች፣ በስፖርት ላይ የሚሠሩ ተቋማት፣ … በጥናቱ የሚካተቱ ይሆናል:: በዚህም መሠረት ጥናቱ በመጪው ዓመት (2016ዓም) እንደሚጠናቀቅ ይጠበቃል:: ውጤቱም የስፖርት ፖሊስን ለማሻሻል ግብዓት እንደሚሆን በመድረኩ ተጠቁሟል::
በአካዳሚው የጥናትና ምርምር ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አመንሲሳ ከበደ፤ በኢትዮጵያ ስፖርት በኢኮኖሚው ላይ ያለው ድርሻ ከንድፈ ሃሳብ በዘለለ በሰፊው ያልተሠራበት መሆኑን ይጠቁማሉ:: ለዚህም እንቅፋት ከሆኑ ጉዳዮች መካከል አንዱ አካዳሚው በቂ ተመራማሪዎች ያልነበሩት መሆኑ ነው:: አሁን ግን በተሠራው አዲስ መዋቅር መሠረት አካዳሚው የስፖርት ሳይንስ ተመራማሪዎችን ማግኘት ስለቻለ ትልልቅ ጥናቶችን መሥራት የሚቻልበት ቁመና ላይ ደርሷል:: በመሆኑም ከሃገር አቀፍ የስፖርት ፖሊሲም ጋር ተያይዞ በርካታ ጥናቶችን በመሥራት ላይ ይገኛል:: ስፖርት በሃገር ኢኮኖሚ ላይ ያለውን ድርሻ በተመለከተ የሚሠራው ጥናትም የዚህ አንድ አካል መሆኑ ተጠቁማል::
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ግንቦት 26/2015