ወሳኙና ትኩረታችንን ልንጥልበት የሚገባው ነገር የሌላው ሰው ጉዳይና ደካማ ጎን ሳይሆን የራሳችን ጉዳይ ላይ ነው። በየዕለት ከዕለት ኑሯችን ከዋናው ዓላማችን የሚያስወጡንን ተጽእኖዎች ስለማስወገድ ማሰብ እና መተግበር እንዳለብን ሁሉ ስለሌሎች ሰዎች ከማውራት ይልቅ ወደ ተልዕኳችን የሚያደርሱንን ቅንጣት እርምጃዎች መራመድ ግድ ይለናል።
አብዛኛውን ጊዜ ከዋናው ተግባራችን ሃሳባችንን በመስረቅና ትኩረታችንን በመውሰድ ውድ እና ዳግም የማናገኘውን ጊዜያችንን የሚሻሙን ጉዳዮች ብዙ ናቸው። ጉልበታችንንና እውቀታችንን ከሚያባክኑብን ሁኔታዎች አንዱ በማያገባን የሰዎች ጉዳይ ላይ እየገባን መፈትፈት ነው::
በእኛ በኢትዮጵያውያን ዘንድ በአዘቦትም ሆነ የአውዳመት ቀን ጠብቆ ቡና መጠራራት የተለመደ ነው:: አቦሉን፣ ቶናውንና በረካውን በየቅደም ተከተሉ እየተጎነጨን አለማማት ወንጀል ነው የተባልን እስኪመስለን ድረስ የሩቅና የቅርብ ወዳጆቻችንን እያነሳን በሃሜት የምንጠመድ ጥቂት አይደለንም። ትንሽ በእውቀታችንና በአስተሳሰባችን ላቅ ያልን እንደሆነ የቅርብ ወዳጆቻችንን ከማማት ከፍ ብለን ስለመንግሥት እናወራለን፤ በዚሁ ከቀጠልን ፈጣሪንም ማማት እንዳንጀምር ነው ስጋቴ::
ግርም የሚለው ደግሞ ከእኛም ብሶ ‹‹እኛ ኢትዮጵያውያን ሃይማኖተኞች እና ባህላችንን አጥባቂዎች ነን›› እያልን የምናወራው ነገር ነው፤ ሰው ማማት፣ በማያገባን በሰው ጓዳና ጎድጓዳ እየገቡ መፈትፈት ከእኛ ባህልና ወግ ጋር አይጣረስም?
ለምን ስለራሳችን ዞር ብለን አናይም? አምላክ እኮ እኛን በአምሳሉ ፈጥሮ ወደዚች ዓለም ሲያመጣን ስለሰዎች አውርተን እንድናልፍ ሳይሆን የተፈጠርንበትን ዓላማ አሳክተን በምንኖርባት ምድር ላይ የራሳችንን አሻራ እንድናኖር ነው::
አንድ ያስተማረኝ የሀይስኩል መምህር ትዝ አለኝ:: መምህሩ የባይሎጂ መምህር ሲሆን ሲጋራ ሳንባን እንደሚጎዳ ካስተማረን በኋላ ዞር ብሎ ሲጋራ ሲያጨስ እናየው ነበረ፤ ‹‹እኔ የማደርገውን ሳይሆን የምላችሁን ስሙኝ›› ያለን አንተ ማን ሆነህ ነው ይህን የምትለው ለሚሉ መልስ ነው። ያው ቄሱም እንደዚያ አይደል የሚሉት::
ኢትዮጵያዊነት በችግር ጊዜ መጠያየቅ፣ መደጋገፍ፣ መረዳዳት እንዲሁም ወዳጆቻችን ችግር ካለባቸው ፊት ለፊት በመነጋገር ለችግሮቻቸው በጋራ በመሆን መፍትሔ መፈለግ እንጂ የወዳጅን ገመና ይዞ ገበያ መውጣት አይደለም::
ብዙ ሰዎች ስለሌላ ሰው ምንም ዓይነት የፍርድ ሃሳብ ላለማሰብ ሙከራ ቢያደርጉ የሚያስቡትን፣ የሚያወጡ የሚያወርዱትን የሚያጡ ይመስላቸዋል። የአብዛኞቻችን የሃሳብ ባህር የተሞላው ማን ምን እንዳደረገ እንጂ እኔ ምን አደረኩ በሚሉ ጉዳዮች ላይ አይደለም። እኚህ ሃሳቦች በሰዎች ስህተት ላይ ያተኮሩ መሆናቸው ደግሞ የበለጠ አስገራሚ ነው:: ለእምነታችንና ላስቀመጥነው የሕይወት ከፍታ የማይመጥነውን ተራ ሃሳብ ከአእምሯችን በመጣበት ፍጥነት እንዲወጣ መቃወም አስፈላጊ ነው:: ይህንንም ልምምድ የዘወትር ተግባራችን ማድረግ አለብን::
እነዚህን ሃሳቦች ማብሰልሰል ስናቆም ስለሌሎች ነገሮችና ስለራሳችን ሕይወት፣ የወደፊት ራዕይ ለማሰብና ለማብሰልሰል ብዙ ጊዜ ልናገኝ እንችላለን። ስለሰዎች ውድቀት፣ ስህተትና ሌሎችም የወቀሳና የፍርድ ሃሳቦችን ማሰብ በቀላሉ የሚለመድ ነገር መሆኑ ግራ ያጋባል። ስለሰዎችም ሆነ ስለሁኔታዎች ጤናማውን ማሰብ እንዴት ከባድ እንደሆነም ይገርማል። ይህንን የአስተሳሰብ ሂደት መለወጥ ከባድ ቢሆንም ለማስተካከል ጥረት ማድረግን መላመድ ያስፈልጋል።
በየቀኑ ሊያገኙን የሚፈልጉን ጓደኞቻችን ጋር ስንገናኝ ልክ ስለ ሰዎች የፍርድ፣ የሃሜትና የመሳሰሉትን ዓይነት ንግግሮች ማሰብና መናገር ስንጀምር ስለ ሌሎች ሰዎች የምናመጣቸው ተራ ፍሬ ከርሲኪ ወሬዎች እንደሆኑ ማወቅ መዘመን ነው።
የትኩረትን ኃይል በሚገባ የተገነዘበ ሰው ከማያገባውና እሱን ከማይመለከተው የሰው ጉዳይ ራሱን ያገለለ ሰው ነው:: ስለ ሰዎች ስህተትና ጉድለት ማሰብ የሚገባው ጊዜ እንዳለ ያውቃል:: ሆኖም ያንን የሚያደርገው ሰውን በምን መልክ ሊደግፍ እንደሚችልና የመፍትሄ ምክንያት ከመሆን አንጻር እንጂ ስለሌላ በማሰላሰልና በማውራት ስውር የድል ስሜት ለማግኘት ወይም የእነሱን ተጽእኖ ለማውረድ አይደለም::
ስለ ሰዎችም ሆነ ስለሌሎች አሉታዊ ጉዳዮች ወደ እኛ የሚመጣውን ወይም በውስጣችን የሚፈጠረውን ሃሳብ ማስተናገድ በሕይወታችን ላይ የሚያመጣው ፋይዳ አይኖርም:: ከዚህ ተግባር ለመላቀቅ አስተሳሰባችንን ሳንለውጥ ሕይወታችንንም ሆነ ሁኔታችንን መለወጥ አንችልም:: ይህ የሚሆንበት ምክንያት የሁሉ ነገር መጀመሪያ አስተሳሰብ ስለሆነና አስተሳሰባችን የማንነታችን መለኪያ በመሆኑ ነው::
በመጀመሪያ አንድ ሃሳብ ወደ አእምሮአችን ይገባል:: በመቀጠልም ይህ ሃሳብ በውስጣችን ይብላላና በንግግርና በተግባር መገለጥ ይጀምራል:: ይህም ወደ ልማድ ከተለወጠ በኋላ የሕይወት መንገዳችንን የመለወጥና የመቅረጽ ጉልበት ይኖረዋል:: ስለዚህ የመጣልን ሃሳብ ሁሉ በአእምሮአችን ስፍራ ማግኘት የለበትም:: ከዚህ በፊት በውስጣችን ያስተናገድናቸውን ጤና ቢስ ሃሳቦች መልካምና ስኬታማ በሆኑ ጤናማ ሃሳቦች መለወጥ መጀመር አለብን::
እስኪ በቀላሉ እንሞክረው፤ ለምሳሌ በዚህ ሳምንት ስለማንኛውም ሰው ማንነትና ተግባር ምንም ዓይነት የፍርድም ሆነ የሃሜት ሃሳብ ሳናስተናግድ ለመቆየት እንሞክር። ከሰዎች ጋርም ስንገናኝ ስለሌላ ሰው ምንም ዓይነት አሉታዊ ነገሮችን ላለመወያየት ጥረት እናድርግ።
ቃልኪዳን አሳዬ
አዲስ ዘመን ግንቦት 23/2015