በብዙ የሬዲዮና ቴሌቪዥን ፕሮግራሞች ላይ ‹‹ጥናቶች እንደሚጠቁሙት›› የሚል መረጃ መስማት የተለመደ ነው:: ጋዜጦችና መጽሔቶች ላይ የሚጻፉ የግለሰብ አስተያየቶች ሀሳባቸውን ለማጠናከር ‹‹ጥናቶች እንደሚጠቁሙት›› ይላሉ:: ሀሳባቸውን ታማኝነት ያለው ለማድረግ ነው::
‹‹ጥናቶች…›› ተብለው የሚጠቀሱት ደግሞ በአውሮፓ፣ አሜሪካና እስያ ውስጥ በሚገኙ አገራት የተሠሩ ናቸው:: አንዲት አውሮፓ ወይም እስያ ውስጥ የምትገኝ አገር ጠቅሶ ‹‹..ይህን ያህል ሰዎች እንዲህ እንደሚያደርጉ፣ እንዲህ እንደሚወዱ፣ ይህን እንደሚጠሉ….›› እየተባለ ለኢትዮጵያ ማኅበረሰብ ይነገራል::
በማኅበረሰብ ላይ የሚደረግ ጥናት የዚያን ማኅበረሰብ ማኅበራዊ፣ ባሕላዊና ተፈጥሯዊ ሁኔታ መሠረት ያደረገ ነው:: የአሜሪካ ወይም ፈረንሳይ አገር ሕዝብ የሚወደውም ሆነ የሚጠላው ነገር ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር ሰፊ ልዩነት ይኖረዋል:: እንኳን ሰዋዊ ስሪት የሆነው ማኅበራዊና ባሕላዊ ነገር ይቅርና ተፈጥሯዊ የሆነው አካላዊ ሁኔታ እንኳን ከአገር አገር ይለያያል:: የአየር ንብረት ሁኔታ ይወስነዋል:: የኑሮና የሥልጣኔ ደረጃ ይወስነዋል::
በተለይም በማኅበረሰባዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ የሚሠሩ ጥናቶች የዚያን አገር(ቢያንስ አህጉር) ነባራዊ ሁኔታ ሊገልጹ ይችላሉ እንጂ ሌላ አገር ማሳያ ሊሆኑ አይችሉም:: መረጃው መነገር ካለበትም የዚያ አገር ሕዝቦችን ባሕሪ መንገር እንጂ፤ እዚያ አገር እንደዚህ ስለሚወዱ እኛም መውደድ አለብን፣ ይህን ስለሚጠሉ እኛም መጥላት አለብን ሊባል አይገባም:: እርግጥ ነው ተሞክሮ ይወሰዳል፤ ዳሩ ግን ሌላ አገር የተሠራ ጥናት የሌላን አገር ሕዝብ ባሕሪ ይገልጻል ብሎ ማጣቀስ ልክ አይሆንም:: እዚህ አገር በተሠራ ጥናት ሰዎች እንዲህ ማድረግ ይወዳሉ ብሎ መደምደም አይቻልም::
በማኅበረሰባዊ ጉዳይ ላይ የሚሠሩ ጥናቶች፣ እንኳን ለሌላ አገር ከአንድ አገር ውስጥ ራሱ ሁሉንም አይወክሉም:: ኢትዮጵያን እንደ ምሳሌ ብንወስድ፤ የሰሜኑ ከደቡብ፣ ከምሥራቁ ከምዕራብ ልዩነት አላቸው:: ማኅበራዊ ስሪታቸው በሚከተሉት እምነት፣ ባሕልና አካባቢያዊ ፍልስፍና ነው የሚገነባው:: ለምሳሌ ሐረር አካባቢ የምናውቀው ሥነ ልቦናዊ አስተሳሰብ ጎንደር አካባቢ ካለው ማኅበረሰብ ጋር ይለያያል:: አንዱ ወግ አጥባቂ ሲሆን ሌላው ደግሞ ለቀቅ ያለ ሊሆን ይችላል:: ስለዚህ ኢትዮጵያ ውስጥ እንኳን ሰዎች ይህን ይወዳሉ፣ ይህን ይጠላሉ ልንል አንችልም ማለት ነው::
ማኀበረሰባዊ ጉዳዮች ላይ የሚሠራ ጥናትን ሙሉ በሙሉ እንዳላምን የሚያደርጉኝ አንዳንድ ትዝብቶችም አሉ:: የሰዎች ስሜት ከጊዜ ጊዜ፣ ከሁኔታ ሁኔታ ይለያያል:: አንድ ሰው የሞላውን መጠይቅ ከሳምንት በኋላ በድጋሚ ቢሰጡት ባለፈው ሳምንት ያከበባቸውን መልሶች ላያከብ ይችላል:: ከ20 ጥያቄዎች ውስጥ ቢያንስ ሦስት ወይ አራት ሀሳቡን ሊቀይር ይችላል::
እስኪ ልብ በሉ! መቼም በዚህ ዘመን አልፎ አልፎም ቢሆን ፌስቡክ የማይጠቀም ብዙም አይኖርም:: ፌስቡክ ላይ ከዓመታት በፊት የጻፍናቸውን ጽሑፎች ‹‹ሚሞሪ›› ብሎ ያመጣልናል:: ስናነበው በአንዳንድ ሀሳቦች ‹‹ምን ነክቶኝ ነው እንዲህ ያልኩት?›› እንላለን:: በዚያ ጉዳይ ላይ ሌላ አስተያየት ጻፉ ብንባል ባለፈው ዓመት በጻፍነው ልክ ላይሆን ይችላል:: ምክንያቱም ጊዜና ሁኔታ ስሜቶቻችንን ይቀይሩታል:: ሰዎች የሚሞሏቸው የጥናት መጠይቆች ራሱ የተጠናበትን ማኅበረሰብ እንኳን ሙሉ በሙሉ አይገልጹም ማለት ነው::
ስለዚህ ጥናቶች ይጠኑ ቢባል ሌላ የጥናት ውጤት ይወጣቸዋል:: ለምሳሌ አንድን መጠይቅ ለአሥር ሰዎች ሰጥተን፣ ከወራት ወይም ዓመታት በኋላ ያንኑ መጠይቅ ለእነዚያው ሰዎች ብንሰጣቸው፤ ከወራት ወይም ዓመታት በፊት ከሞሉት ጋር ብናመሳክረው ሙሉ በሙሉ አንድ አይነት ላይሆን ይችላል:: ይሄ ራሱ ቢጠና ጥሩ ነበር::
ሌላው ትልቁ ድክመታችን የምንጠቅሳቸውን ጥናቶች ጊዜ አለመለየት ነው:: ጥናቶች በየጊዜው ይሻሻላሉ:: በአንዳንድ መገናኛ ብዙኃን የምንሰማው ግን ከኢንተርኔት ላይ በቀላሉ ያገኙትን ጥናት ዝም ብሎ ማቅረብ ነው::
እንኳን ማኅበራዊ ጉዳዮች ላይ በመጠይቅ የሚሠሩ ጥናቶች፤ የተፈጥሮ ሳይንስ ላይ በሳይንቲስቶች የሚሠሩ ምርምሮች ራሱ በየጊዜው ይታደሳሉ:: ተጨማሪ ግኝቶች ይገኛሉ:: በሥነ ሕይወት፣ ኬሜስትሪ፣ ሥነ ሕዋ…. ላይ የሚደረጉ ጥናቶች በየዘመኑ ማሻሻያ ይደረግባቸዋል:: የተፈጥሮ ሳይንስ ከማኅበራዊ ሳይንስ የተሻለ ቋሚ ነገር አለው፤ ዳሩ ግን እሱ እንኳን በየጊዜው ተለዋዋጭ ነገር ይታይበታል::
ማኅበራዊ ጉዳይ ደግሞ ከዚህም በላይ ተለዋዋጭ ነው:: ምክንያቱም ማኅበራዊ ጉዳዮች በብዛት ሰው ሠራሽ ናቸው:: በሰዎች እንቅስቃሴዎችና ድርጊቶች የሚከናወኑ ናቸው:: ይህን ደግሞ የተለያዩ ሁኔታዎች ይወስኑታል::
አልፎ አልፎ ደግሞ ‹‹ጥናት›› የሚለውን ነገር እንደ ማጭበርበሪያና ማታለያ የሚጠቀሙትም አይጠፉም:: እነዚህ ሰዎች ያንን ‹‹አለ›› የተባሉትን ጥናት በዚያ በሚናገሩበት ቅጽበት ማንም አይቶ አያረጋግጥም በሚል ነው:: ቢያንስ ተናግረው እስከሚጨርሱ ድረስ ተቀባይነት እናገኝበታለን በሚል ነው:: ተናግረው ከጨረሱ በኋላም ቢሆን ማንም እሱን ለማረጋገጥ ብሎ ‹‹ቼክ›› አያደርገውም በሚል ነው::
በነገራችን ላይ ይህ የሆነው በስንፍናችን ምክንያት ነው:: የተባሉ ነገሮችን ተከታትሎ የማረጋገጥና የማመሳከር ልምድ ቢኖረን ኖሮ የማንም መቀለጃ አንሆንም ነበር:: ሐሰተኛ መረጃዎች ራሱ በማኅበራዊ ገጾች የተበራከቱት የማረጋገጥና የማመሳከር ልምድ እንደሌለን ስለታወቀ ነው:: የተባለውን ሁሉ አሜን ብለን ስለምንቀበል ነው:: አጭበርባሪው አካል የሚጠቀመው ነገር ስላለው ነው::
በጥናቶች ላይ፣ በምርምሮች፣ በዘገባዎች፣ በመጽሐፍት ላይ ምንጭ ይጠቀሳል:: ያ ምንጭ የተቀመጠው የምርምሩን ወይም ዘገባውን ታማኝነት ለማሳየት ነው:: የተጠራጠረ ሰው ሄዶ እንዲያየው ነው:: ስለዚህ ጥናቶች እንዲህ አሉ ስንል የተቀመጡ ማጣቀሻዎችን ሁሉ በማየት ቢሆን የተሻለ ነው:: የባሰው ችግር ግን ጭራሹንም ዋናውንም ሳያዩ ‹‹ጥናት እንዲህ አለ…›› እያሉ የሚዋሹት ናቸው::
ወደ ‹‹ጥናቶች ይጠኑ›› ስንመለስ፤ ጥናቶች የሚሠሩት በሆነ ወቅት፣ በሆነ ማኅበረሰብ ላይ፣ ለሆነ ዓላማ ነው:: ስለዚህ ጥናት ጠቅሰን ስንናገርም ሆነ ስንጽፍ ዐውዳዊ መሆንን ይጠይቃል:: ከ20 ዓመት በፊት በተሠራ ጥናት የዛሬውን ነባራዊ ሁኔታ መናገር አይቻልም:: ጃፓን ውስጥ በተሠራ ጥናት ‹‹ሴቶች ወይም ወጣቶች እንዲህ ናቸው›› ማለት አያስተማምንም:: ቻይና በተሠራ ጥናት መምህራን እንዲህ ናቸው ብሎ ለኢትዮጵያ ማድረግ በትክክል ሊገልጽ አይችልም::
ይህ ሲባል ግን በሳይንቲስቶች በዘመናዊ ቴክኖሎጂ በታገዘ ቤተ ሙከራ የሚሠሩ ጥናቶችን ሁሉ እንጠራጠር ማለቴ አይደለም:: በእርግጥ እሱም ቢሆን ይሻሻላል፣ ይታደሳል:: ቢሆንም ግን በሳይንቲስቶች በረቀቀ ቴክኖሎጂ ቤተ ሙከራ የሚሠሩ ጥናቶች የተሻለ አስተማማኝ ናቸው:: ከዚያ ውጭ ግን በመጠይቅ የሚሞሉ ጥናቶችን ከአንዱ አገር ወስዶ ለሌላ አገር መጠቀም በትክክል ሁኔታውን አይገልጽምና ጥናቶችን እናጥና!
ዋለልኝ አየለ
አዲስ ዘመን ግንቦት 16/2015