አዲስ አበባ፡– በአገሪቱ የመጣውን ለውጥ ተከትሎ በሚዲያው ዘርፍ የተወሰዱ እርምጃዎች በዘርፉ ለተመዘገበው ለውጥ አስተዋጽኦ ማበርከታቸውን የኢፌዲሪ ፕሬዚደንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ገለጹ፡፡
ከትናንት በስቲያ ጀምሮ በኢትዮጵያ መንግስት፣ በአፍሪካ ህብረትና በዩኔስኮ አስተባባሪነት በኢትዮጵያ በመከበር ላይ የሚገኘው 26ኛው አለም አቀፍ የፕሬስ ነፃነት ቀን፥ በትናንትናው ዕለትም በአፍሪካ ህብረት አዳራሽ በተካሄደው ውይይት ቀጥሎ ውሏል። በመርሃ ግብሩ ላይም መገናኛ ብዙሃን በነፃና ፍትሃዊ ምርጫ እንዲሁም በዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ላይ ያላቸውን ሚና አስመልክቶ ትኩረት በማድረግ ውይይት ተካሂዷል።
በመድረኩ ንግግር ያደረጉት የኢፌዲሪ ፕሬዚ ዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ እንደተናገሩት፤ ባለፈው አንድ ዓመት በተለይም የመናገር ነጻነትን ለማረጋገጥ በርካታ ተግባራት ተከናውነዋል፡፡ በእስር የነበሩ ጋዜጠኞች ተለቀዋል፤ በአንዳንድ ሚዲያዎች ላይ ተጥሎ የነበረው እገዳ ተነስቷል፤ አፋኝ ህጎችና መመሪያዎችን የማሻሻል ስራ ተሰርቷል፡፡ እነዚህን ተግባራት ተከትሎ የአገሪቱ የሚዲያ ነጻነት ላይ ለውጥ መጥቷል፡፡
ባለፈው አንድ ዓመት ኢትዮጵያ ያከናወነቻ ቸውን በጎ ተግባራት ተከትሎ አገሪቱ በፕሬስ ነጻነት አበረታች ውጤት አስመዝግባለች ያሉት ፕሬዚዳንቷ፤ ይህን ተግባር እውቅና ለመስጠት የዓለም የፕሬስ ነጻነት ቀን በኢትዮጵያ መከበሩ በአገሪቱ የፕሬስ ነጻነቱ ቀጣይነት ያለው ለማድረግ እንደሚረዳ ጠቁመዋል፡፡
እንደ ፕሬዚዳንቷ ማብራሪያ፤ በአገሪቱ ሀሳብን የመግለጽ ነጻነት ቢረጋገጥም ትኩረት የሚሹ ተግዳሮቶች ተፈጥረዋል፡፡ በማህበራዊ ሚዲያዎች ምክንያት የአገሪቱ የፖለቲካ ትርክቶች ዋልታ ረገጥ እየሆኑ መጥተዋል፡፡ የሀሰት መረጃና የመረጃ ብክለት ኢትዮጵያን ጨምሮ በርካታ አገራትን እየተፈታተነ ነው፡፡
የፖለቲካ ባህሉና ጠንካራ ተቋማት በሌሉባቸው እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አገራት የሀሰት መረጃዎችን ለመለየትና የመረጃ ብክለትን ለመከላከል የሚያስችል ሁኔታ በሌለበት እውነተኛ ዜናን ከልቦለድ ለመለየት አስቸጋሪ እየሆነ ነው፡፡ እነዚህን ችግሮች ለመቅረፍ ውይይት አስፈላጊ መሆኑን በመጠቆም፤ የፕሬስ ቀንን በማስመልከት እየተዳረጉ ያሉ ውይይቶችም የራሳቸውን አስተዋጽኦ ያበረክታሉ ብለዋል፡፡
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) ዳይሬክተር ጄኔራል አውድሬይ አዛውለይ፤ ‹‹ኢትዮጵያ 40 ደረጃዎችን በማሻሻል ያስመዘገበችው ውጤት የሚደነቅ ነው።›› ካሉ በኋላ አገሪቷ የፕሬስ ነጻነትን ለማረጋገጥ የጀመረቻቸውን ተግባራት አጠናክራ መቀጠል አለባት ብለዋል፡፡
ለይፋዊ የስራ ጉብኝት አዲስ አበባ የሚገኙት የብሪታኒያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጀርሚ ሃንት እንደተናገሩት፤ ባለፈው አንድ ዓመት ኢትዮጵያ 40 ደረጃዎችን ማሻሻል መቻሏ ትልቅ ስኬት ነው፡፡ የብሪታኒያ መንግስትም በዓለም ዙሪያ የፕሬስ ነፃነትን ለማረጋገጥ ለሚከናወነው ስራ ድጋፉን አጠናክሮ ይቀጥላል።
በዚህ ረገድም በኢትዮጵያ የብሪታኒያ ኤምባሲ ባለፉት ሁለት ዓመታት ብቻ ለ100 ጋዜጠኞች የተለያዩ ስልጠናዎችን መስጠቱን ለአብነት የጠቀሱት ጀርሚ ሃንት ድጋፉን አጠናክሮ ለማስቀጠል በዛሬው እለትም አዲስ የድጋፍ ማእቀፍ ይፋ አድርገዋል።
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 25/2011
በመላኩ ኤሮሴ