ቀደም ሲል በአገራችን ለፋሽን ኢንዱስትሪው የሚሰጠው ትኩረት አነስተኛ ሆኖ ቆይቷል:: አሁን ላይ በኅብረተሰቡ ዘንድ ለፋሽን የሚሰጠው አመለካከት እየተለወጠ መጥቷል፤ በዚያው ልክ ተደራሽነቱም እየሰፋ መነቃቃት እያሳየ መምጣቱን በዘርፉ የተሰማሩ ባለሙያዎች ይገልጻሉ::
የፋሽን ተደራሽነትን የማስፋት ሥራ የተለያዩ ዘዴዎች በመጠቀም ማስተዋወቅን ይጠይቃል:: አሁን ፋሽንን በመድረክ ትርዒት ከማስተዋወቅ ባሻገር የተለያዩ አማራጮች በመጠቀም የማስተዋወቅ ሥራዎች ሲሠሩ እንመለከታለን:: ባለሙያዎቹ የፋሽን ተደራሽነትን ለማስፋት የሚያስችሉ ሁኔታዎች እየጨመሩ መምጣታቸውንና ወቅቱ ለፋሽን መልካም የሚባል እንደሆነም ይገልጻሉ::
የፋሽን ዲዛይነሯ ሰርካለም ኮራ እንደምትለው፤ ፋሽን በአይን የሚታይ ጥበብ (አርት) ነው:: ግለሰብም ሆነ ማህበረሰብ የራሱን ሀሳብ፣ አመለካከትና ውበት የሚገልጽበት መንገድ ነው:: ለሚያየው ሰው ደግሞ የእይታ ጉዳይ መሆኑን ትገልጻለች::
ያለንበት ዘመን የግሎባላይዜሽን እንደመሆኑ መጠን ፋሽንን ለማስተዋወቅ አሁን ያለው ሁኔታ ቀደም ሲል ከነበረው ይሻላል የምትለው ዲዛይነር ሰርካለም፤ እንደፌስ ቡክ፣ ኢንስታግራም፣ ቲክቶክ ዓይነት የማህበራዊ ሚዲያዎችንና የኔትወርክ አማራጮች በመጠቀም የፋሽን ተደራሽነትን ማስፋት እንደሚቻል ትጠቁማለች:: የተለያዩ ፋሽን ትርዒት መድረኮች በመጠቀም እይታ ማግኘት ለፋሽን ተደራሽነቱ አስተዋፅኦ እንዳለው ትናገራለች::
በሌላ በኩል ታዋቂና ተፅእኖ ፈጣሪ ሰዎች በመጠቀም በማስተዋወቅ ይቻላል:: በተለይ ወጣቶች ታዋቂና ተፅእኖ ፈጣሪ ሰዎች የሚለብሱትን ፋሽን ስለሚከተሉ ያንን አማራጭ መጠቀም የፋሽን ተደራሽነት የሚሰፋበትን መንገድ ማስፋት የሚቻል መሆኑን ነው የምትገልጸው::
የፋሽን ኢንዱስትሪውን ለማስተዋወቅ በብሪትሽ ካውንስል፣ በኢንኩቤሽን ማዕከላት፣ በአፍሪካ ዊክ ፋሽንና በግለሰቦችም እየተደገፉ የሚዘጋጁ መድረኮችም መኖራቸውን የምትገልጸው ዲዛይነሯ፤ እሷ ከእነዚህ መድረኮች በተጨማሪ ቲክቶክ፣ ኢንስታግራም፣ ፌስ ቡክ፣ የመሳሰሉትን የማህበራዊ ሚዲያ ፕላትፎርሞችን በመጠቀም የፋሽን ሥራዎቿን ተደራሽ ለማድረግ እየሞከረች ነው::
‹‹ቀደም ሲል ለፋሽን ኢንዱስትሪ ትኩረት አይሰጠውም ነበር›› የምትለው ዲዛይነሯ፤ አሁን ላይ ትምህርቱ በዩኒቨርሲቲ ደረጃም እየተሰጠ መሆኑንና በዘርፉ በጣም ብዙ ዲዛይነሮች ስላሉ የፋሽን ተደራሽነት ከምንም ጊዜውም በላይ እየሰፋ ነው ትላለች:: በተለይ ወጣቶች ትኩረት ሰጥተው እየሠሩበት እንደሆነም ነው የምትጠቅሰው::
በመንግሥት በኩል ፋሽን ላይ ለተሰማሩ ሰዎች የመስሪያ ቦታዎች በመስጠት እና ማሽነሪዎች ለመግዛት 15 በመቶ ቅድሚያ እንዲከፈል በማድረግ በረጅም ጊዜ ክፍያ እንዲሰጥ በማድረግ የሚደረጉ ድጋፎች ዘርፉ እንዲስፋፋ ትልቅ አስተዋፅኦ ይኖረዋል ብላለች::
በሌላ በኩል የፋሽን ኢንዱስትሪው እንዳይስፋፋ የሚያደርጉ ብዙ ተግዳሮቶች መኖራቸውን ጠቅሳ፤ በተለይ ጨርቃጨርቅ ላይ የሚታዩ ችግሮች ከሥራው አንጻር የታሰበው ዓይነት ሥራ ለመሥራት እንደማያስችሉና አንዳንዴም ለኪሳራ የሚዳርጉ መሆናቸውን ነው የምትጠቁመው:: «እኔ መሥራት የምወደው በሁነት (በኢቨንት) ጊዜ የሚለበሱ ልብሶችን ነበር» የምትለው ዲዛይነሯ፤ ሆኖም ግን የውስጤን እንዳልኖር ያደረገኝ የምፈልገውን ጨርቅ በፈለግኩት መልኩ ለመጠቀም ከፋብሪካ ጀምሮ የአቅርቦትና ሌሎች ተደራራቢ ችግር ያሉበት መሆኑን ትገልጻለች ::
ፋሽን እንዲበረታታ የሚያደርጉ መድረኮች በማዘጋጀት ረገድ ኢንቨስተሮች ስፖንሰር ከማድረግ ጀምሮ መድረኮች በማዘጋጀትና በመደገፍ የፋሽን ዘርፉን ማሳደግ እንደሚጠበቅባቸው የጠቆመችው ዲዛይነሯ፤ ፋሽን ፈጠራዊ የሆነ እይታ የሚፈልግ ስለሆነ ማበረታታትንና ሞራል የሚሰጥን እንደሚፈልግ ጠቁማለች::
ፋሽን ኢንዱስትሪው እንዲያድግ ከሚያደርጉት ነገሮች ዋንኛው ወደ ውስጥ ማየት አለመቻል መሆኑን ጠቅሳ፤ አብዛኞቻችን ከውጭ የመጣን ልብስ መልበስ እንፈልጋለን ትላለች:: ሁሉም ራሱን እንዲያይም ታሳስባለች:: ዲዛይነሯ እንደምትለው፤ አሁን ግን ብዙ ለውጦች እየመጡ ናቸው፤ ይህ ወቅት ኢትዮጵያውያን የአገራቸውን አልባሳት እየወደዱ የመጡበት ጊዜ ነው:: ትላልቅ የሚባሉ ባለስልጣናትና አርቲስቶች ጨምሮ ታዋቂ ሰዎች የፋሽን አልባሳትን በመልበስ ትላልቅ ፕሮግራሞች ላይ በመገኘት ማበረታት ጀምረዋል ስትል ትናገራለች::
አንዳንዴ ከቻይና በጋርመንት ደረጃ በብዛት ተመርቶ የሚመጣን ልብስ መግዛት በዋጋ ቅናሽ ሊያስገኝ ይችል ይሆናል የምትለው ዲዛይነሯ፤ እኛ አገር ደግሞ ባማረ ዲዛይን ጥራት ያለው ልብስ ሠርቶ ለማቅረብ የኅብረተሰቡ ግንዛቤ መስፋትና መክፈል ያለበትን ዋጋ ለመክፈል ዝግጁ መሆን አለበት ትላለች:: የአገር ውስጥ ሲባል ያለው አመለካከትና የሚሰጠው የዋጋ ግምት ዝቅተኛ መሆን የለበትም፤ መራከስም የለበትም:: ዘርፉ ራሳችንን ካስከበርን ነው ማደግ የሚችለው ትላለች::
ከዚህ ባሻገር የፋሽን ተደራሽነትን በማስፋት ረገድ ሚዲያ ትልቅ ሚና እንዳለው የምትገልጸው ዲዛይነሯ፤ ፋሽን እይታ ነው፤ በአይን የምናየው ነገር በጫማ፣ በልብስ፣ በሜካፕ እና በማንኛውም ነገር ሊገለጽ የሚችል በመሆኑ ሲታይና ሲወደድ ተደራሽነቱ ሊሰፋ ይችላል:: ኅብረተሰቡም በአገራችን አልባሳት እንድንኮራ ሊያበረታታን ይገባል ነው የምትለው፤ የፋሽን ላይ የምንሠራ ባለሙያዎችም እርስ በርስ እየተበረታትን ከሄድን የማናድግበት ሁኔታ የለም ትላለች::
ዲዛይነር ሀና ኃይሌ በበኩሏ ውበትና ፋሽን ተያያዥነት ያላቸው ነገሮች መሆናቸውን ገልጻ፤ ፋሽን ላይ ትኩረት አድርጎ ተሠርቶ ውበት ላይ ካልተሠራ ትርጉም የለውም ነው የምትለው:: ውበት ላይ የመሥራትን አስፈላጊነትም ጠቁማለች:: የፋሽን ሙያው እንዲያድግ በዘርፉ የተማረ የሰው ኃይል ማፍራት እንደሚያስፈልግ የምትገልጸው ሀና፤ የውበትና የሙያ ማሰልጠኛ ተቋም በማቋቋም የወንድና የሴት ፋሽንን በዘመናዊ፣ ባህላዊ መልኩ እያስተማረች ፋሽንን ተደራሽ በማድረግ ላይ ትገኛለች::
የፋሽንን ተደራሽነት ለማስፋት በተማሪዎች ምረቃ ቀን እያንዳንዱ ተማሪ ሥራውን መድረክ ላይ እንዲያቀርብ ዕድሉን ይሰጠዋል ነው ዲዛይነር ሀና የምትለው፤ በዚህ ያለፉ ባህላዊም ሆነ ዘመናዊ ልብሶችን ዲዛይን እያደረጉ ውጤታማ የሆኑ፣ የየራሳቸውን የፋሽን ሥራ የጀመሩ እና በፋሽን ዙሪያ የሚሠሩ ተማሪዎች እንዳሉም ትገልጻለች::
በአሁኑ ሰዓት ሙያው በጣም ተፈላጊ ስለሆነ ተማሪዎቻችንን ከብዙ ድርጅቶች ጋር በማገናኘት የራሳቸውን መክፈት የሚፈልጉ እንዴት መክፈት እንዳለባቸው ስልጠና እንዲያገኙ ይደረጋል:: በዚህ መንገድ ሁሉም ሙያውን የተማሩ በሙያው እንዲሰማሩ ስለሚደረግ ተምሮ ጨርሶ የሚቀመጥ አይኖርም ትላለች::
ቀደም ሲል ፋሽንም ሆነ ውበት ሲባል ምን ትኩረት አይሰጠውም፤ አማራጭ ሲታጣ የሚገባበት ዘርፍ አድርጎ የማሰብ የአመለካከት ችግር ይስተዋል እንደነበረ ትጠቅሳለች:: ፋሽን ለመማር በቅድሚያ የሚያስፈልገው ፍላጎት መሆኑን የምትገልጸው ሀና፤ አሁን የሰው ፋሽን የመማር ፍላጎት እየጨመረ ዲግሪና ማስተርስ ያላቸው ሰዎች ሁሉ በተጨማሪነት እየተማሩት እንደሚገኙም ጠቅሳለች::
‹‹ውስጤ የነበሩ የምፈጥራቸውና ዲዛይን የማደርጋቸው ነገሮች እኔ ጋ ብቻ እንዲቀሩ ስላልፈለግኩ ነው ወደ ማስተማሩ ሥራ የገባሁት›› የምትለው ሀና፤ የማስተማር ሥራ ከጀመረች 15 ዓመታትን እንዳስቆጠረችም ትናገራለች:: በተለይ ሴቶች ላይ ብዙ መሥራቷን ገልጻ፤ በዘርፉ ላይ የሚያጋጥሙ ተግዳሮቶች ብዙ ሊኖሩ ይችላሉ፤ ተግዳሮት ገጠሞኛል ብሎ ሥራ ማቆም ግን አይታሰብም፤ መቀጠል ያስፈልጋል ስትል አስገንዝባለች::
ወርቅነሽ ደምሰው
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 23/2015