መረዳዳት የኢትዮጵያውያን መገለጫ የሆነና የእርስ በእርስ ማኅበራዊ መስተጋብራቸውን አጠንክሮ የኖረ ተግባር ነው። መረዳዳት ባይኖር ኖሮ አሁናዊ የኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ የተለየ ይሆን ነበር። በበዓላት ሰሞን በመገናኛ ብዙኃን ከምንሰማቸው ወሬዎች መካከል ‹‹… ህዝበ ክርስቲያኑ በዓሉን ሲያከብር የተቸገሩ ወገኖችን በመደገፍ ሊሆን ይገባል … ህዝበ ሙስሊሙ በዓሉን ሲያከብር አቅም የሌላቸው ወገኖችን በመርዳት ሊሆን ይገባል …›› የሚሉት አገላለፆች ይገኙበታል። እርግጥ ነው፣ ህዝበ ክርስቲያኑም ይሁን ሙስሊሙ በዓላትን ሲያከብሩ የተቸገሩ ወገኖችን መርዳት እንዳይዘነጉ መንገር ተገቢና አስፈላጊ ምክር ነው። በመንግስት ኃላፊዎች፣ ባለሀብቶች፣ ድርጅቶች፣ ወዘተም እንዲሁ በአላትን አስመልክቶ ድጋፎች ሲደረጉ የመረዳዳት ባህሉ እንዲጎልብት ጥሪዎች ይቀርባሉ።
ታዲያ እዚህ ላይ መታወስ ያለበት ነጥብ የማኅበረሰቡ የመረዳዳት ባህል ከበዓላት ሰሞን መሻገር እንዳለበት ማስታወስና ይህ እንዲሳካ ለሚያስችሉ ተግባራት ትኩረት መስጠት ሊሆን ይገባል። በበዓላት ወቅት ህዝቡ መረዳዳት እንዳለበት ከማስታወስ በተጨማሪ ከበዓላት ውጭ ባለው ጊዜም የመረዳዳት ተግባሩን አጠንክሮ መቀጠል እንዳለበት ማስገንዘብም ተገቢ ይሆናል።
ይህ የኢትዮጵያውያን መገለጫ የሆነው የመረዳዳት ባህል በበዓላት ሰሞን ብቻ ተወስኖ እንዳይቀር ለማድረግ የመረዳዳት ባህልን ከአንድ ሰሞን ኹነት የተሻገረ ተግባር አድርጎ መመልከት ያስፈልጋል። በአገራችን በዓላት በደረሱ ቁጥር በርከትና ደመቅ ብለው የምንሰማቸው የእርዳታ ተግባራት ዜናዎች ዘላቂ ሆነው የዜጎች ችግሮችም ትርጉም ባለው መልኩ ምላሽ እንዲያገኙ ወደሚያስገነዝቡ ሃሳቦች ተሸጋግረው መመልከትና ማዳማጥ ይገባል።
የ‹‹ወሎ ቤተ ዐምሐራ የበጎ አድራጎት ድርጅት›› ስራ አስኪያጅ ይርጋለም ታደሰ የመረዳዳትና የመተባበር ተግባራት ከኢትዮጵያውያን የማንነት መገለጫዎች መካከል የሚመደቡ ቢሆኑም ከእርዳታ ይልቅ የዜጎችን ሕይወት በቋሚነት በሚለውጡ ተግባራት ላይ ማተኮር የተሻለ ውጤት እንዳለው ይገልፃል። ‹‹ኅብረተሰባችን ፋታ የማይሰጡ ዘርፈ ብዙ ችግሮች ስላሉበት እንጂ እርዳታን አናበረታታም። ከተለመደው የእርዳታ ተግባር ይልቅ ዘላቂ ውጤት ሊያመጡ በሚችሉ የልማት ስራዎች ላይ እናተኩራለን። እየሰራንም ያለነው በዚህ መርህ ቅኝት ነው። የሰው ልጅ ሕይወት በእርዳታ ይቀየራል ብለን አናምንም›› የሚለው ስራ አስኪያጁ፣ በእርዳታ ላይ የተመሰረተ የኑሮ ዘይቤም ሆነ በዓላትንና ውስን ጊዜያትን ብቻ ጠብቀው የሚከናወኑ የእርዳታ ተግባራት ተመራጭና የሚበረታቱ ስልቶች እንዳልሆኑ ያስረዳል።
‹‹አስተዳደጋችንና የማኅበረሰባችን ነባራዊ ሁኔታ ለመረዳዳት አዲስና ባዕድ አይደለም። መተጋገዝ ጎልብቶ መቀጠል የሚገባው ባህላችን ነው። ይሁን እንጂ ወቅት እየጠበቁ አልፎ አልፎ የሚደረግና ለሚዲያ ፍጆታ ሲባል ብቻ የሚከናወን የመረዳዳት ድርጊት አሳሳቢ እየሆነ መጥቷል። ›› ሲል ያስገነዝባል።
በበዓላት ሰሞን ብዙ ሰዎች ‹እርዳታ እንሰጣለን› ብለው በመገናኛ ብዙኃን እንደሚታዩም ጠቁሞ፣ የተገባው ቃል ስለመፈፀሙና ስላለመፈፀሙ ግን ማረጋገጫና ተጠያቂነት ሲኖር አይስተዋልም ይላል። ‹ከበጎ ፈቃደኞች ምን ያህል የእርዳታ ግብዓት ተገኘ? ምን ያህሉስ ለተረጂዎች ደረሰ?› የሚሉት ጉዳዮች ተጠያቂነት ሊኖርባቸው ይገባል። የበዓላት ሰሞንን ብቻ ጠብቀው በተደረጉ የእርዳታ ተግባራት ላይ እነዚህ ጉዳዮች ተጠያቂነት ስለማስከተላቸው በእጅጉ አጠራጣሪ ነው። ›› ሲል ያስገነዝባል። ግልፅነትና መተማመን ከሌለ የኅብረተሰቡ የመተጋጋዝ ባህል እንደሚዳከም ጠቅሶ፣ የእርዳታ ተግባራት ኃላፊነትንና ተጠያቂነትን በሚያስከትሉ የአሰራር ስርዓቶች መመራት እንዳለባቸው ያስገነዝባል።
ከዚህ በተጨማሪም፣ የእርዳታ ተግባራት ከበዓላት ሰሞን የተሻገሩ መሆን እንዳለባቸውም ይርጋለም ይጠቁማል። የመረዳዳት ተግባር ከበዓል ሰሞን የተሻገረ እንዲሆን ሕጋዊ አሰራሮችን መከተል እንደሚያስፈልግ የሚገልፀው ይርጋለም፣ ሕግን የተከተሉ አሰራሮች ኃላፊነትን እንደሚያስከትሉ ስለሚታወቅ የእርዳታ ተግባራቱን ስርዓት ባለው መንገድ በመምራት ከአንድ ሰሞን ኹነት ለማሻገር እገዛ እንደሚያደርጉ ያስረዳል። ‹‹የእርዳታ ተግባራት ሕጋዊ በሆኑና መንግሥት ክትትል በሚያደርግባቸው ተቋማት በኩል ከተከናወኑ፣ ተግባራቱ ዘላቂ ለውጥ ለማምጣት ያስችላሉ፤ በአንድ ሰሞን ብቻ የተወሰኑ ከመሆንም ይድናሉ›› ይላል።
እንደ ይርጋለም ገለፃ፣ ‹‹ወሎ ቤተ ዐምሐራ የበጎ አድራጎት ድርጅት›› የሰዎችን ችግሮች በዘላቂነት መፍታት በሚያስችሉ ተግባራት ላይ አተኩሮ ይሰራል። የማኅበሩ ዋነኛ የትኩረት አቅጣጫ በልማት በተለይም፤ በትምህርት፣ በጤናና በቱሪዝም፤ ተግባራት ላይ ቢሆንም በአገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች የተፈጠሩ አለመረጋጋቶች እና የተፈጥሮ አደጋዎች ድርጅቱ በሰብዓዊ ድጋፍ ተግባራት ላይም እንዲያተኩር አድርጎታል። በዚህም በተለያዩ አካባቢዎች በመዘዋወር በርካታ የሰብዓዊ ድጋፍ (የምግብ፣ የአልባሳት፣ የቤት መገልገያና የሕክምና ቁሳቁሶች ድጋፍ) ተግባራትን አከናውኗል። ‹‹በዓልን ጠብቀን ድጋፍ ያደረግንበት አጋጣሚ የለም። ወቅት ጠብቆ የሚበላና የሚጠጣ ነገር ብቻ ከመስጠት ይልቅ ኑሮን በዘላቂነት በሚቀይሩ ስራዎች ላይ ማተኮርን መርጠናል›› በማለት ይናገራል።
ድርጅቱ በመስከረም 2013 ዓ.ም እንቅስቃሴውን የጀመረ ሲሆን፣ ጥቅምት 26 ቀን 2014 ዓ.ም ከኢ.ፌ.ዴ.ሪ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ሕጋዊ እውቅና አግኝቷል። ዋና መስሪያ ቤቱ በአዲስ አበባ ነው የሚገኘው፤ ደሴ እና ወልዲያ ከተሞች ላይ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶች አሉት።
ድርጅቱ ለሚያከናውናቸው ተግባራቱ የሚያስፈልገውን ገንዘብ እያገኘ ያለው በአገር ውስጥና በውጭ አገራት ከሚኖሩ በጎ ፈቃደኞችና ለጋሾች ነው። በተለይም በአረብ አገራት፣ በአሜሪካና በአውሮፓ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ለድርጅቱ ከፍተኛ ድጋፍ ያደርጋሉ። ከኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በተጨማሪ ብዙ ኤርትራውያን ለጋሾም ድጋፍ እያደረጉ ይገኛሉ።
ድርጅቱ አብዛኛውን ገንዘብ የሚሰበስበውም ማኅበራዊ ሚዲያውን፣ በተለይም ፌስቡክንና ቴሌግራምን፣ በመጠቀም ነው። ከሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን እውቅናና ፈቃድ ያገኘ በመሆኑ እያንዳንዱን ግዥ በሕጋዊ መንገድ በመፈፀም አሰራሩን ግልፅ የማድረግ ስርዓትን ይከተላል። ገንዘብ ወጭ ሲደረግም በሁሉም የኮሚቴው አባላት ስምምነት ብቻ እንዲሆን ተደርጓል። ይህም የድርጅቱ ተግባራት ዘላቂ እንዲሆኑና መሰረታዊና ዘላቂ የሕይወት ለውጥ የማምጣት እቅዱን ለማሳካት እንደሚያስችለው ይርጋለም ያስረዳል።
የ‹‹ሐረር የአገር ልጅ በጎ አድራጎት ማኅበር›› መስራችና ስራ አስኪያጅ ተስፋ አለባቸው በበኩሉ የመረዳዳት ተግባራትን ከበዓላት ሰሞን በማሻገር ጠንካራ የመተጋገዝ ባህልን ለማዳበር የሃይማኖት አባቶች በትኩረት መስራት እንደሚኖርባቸው ይጠቁማል። የሃይማኖት አባቶች፣ ምዕመኑ ከበዓል ሰሞን የተሻገረ የእርዳታ ተግባር እንዲያከናውን በንቃት ማስተማር እንዳለባቸውም አስታውቆ፣ ወርሃዊ የሆኑ መርሃ ግብሮችን በማዘጋጀት አጋዥ የሌላቸውን ዜጎች መርዳት ይቻላል ይላል። ምዕመናን በበዓላት ሰሞን በሚከናወኑ የእርዳታ ተግባራት ላይ ብቻ ተወስነው እንዳይቀሩ የሃይማኖት አባቶች ማስተማር እንደሚኖርባቸውም ያስገነዝባል።
ተስፋ እንደሚናገረው፣ በበዓላት ሰሞን ብቻ ያልተወሰነ የመተጋገዝ ተግባር የአብሮነት ስሜትን ይፈጥራል፤ የተቸገሩ ወገኖችም የባይተዋርነት ስሜት እንዳይሰማቸው ያደርጋል፤ መተሳሰብንና ፍቅርን ያጠነክራል። ይህ ዓይነቱ የመረዳዳት ተግባር ለአገር ግንባታ ስለሚኖረው አስተዋፅዖ ሲያስረዳ ‹‹ከበዓላት ወቅት የተሻገረ መረዳዳት ለአገር ግንባታና እድገትም በጎ ሚና አለው። ሰዎች ተቸግረው ወደ ጎዳና ሲወጡ ማኅበራዊ ቀውስ ይፈጠራል። በዓላትን ሳንጠብቅ ሰዎችን የምንረዳ ከሆነ ሰዎቹ ወደዚያ ዓይነት ሕይወት እንዳይገቡ በማድረግ ቀውሱን አስቀድመን መከላከል እንችላለን። ይህም በአገር ግንባታ ላይ አወንታዊ አበርክቶ ይኖረዋል›› በማለት ይናገራል።
ማኅበሩ ዘላቂ የድጋፍ ተግባራትን ለማከናወን በሚያደርገው ጥረት ሰዎችን ወደ ማዕከሉ ጋብዞ የተሰሩ ስራዎችን በማሳየት ወርሃዊና ዓመታዊ ድጋፍ እንዲያደርጉና በሌሎች መልካም ተግባራት ላይ እንዲሳተፉ እያደረገ ይገኛል። በማኅበሩ የሚታገዙ ልጆች በትምህርታቸው ስኬታማ መሆን ችለዋል፤ ስነ ልቦናዊ ድጋፍ ስላገኙ አመለካከታቸው ተለውጦ ስለሌሎች ልጆች ማሰብ ጀምረዋል፤ ከአካባቢያቸው ማኅበረሰብ ጋር ተግባብተው መኖር እየቻሉ ነው።
ወይዘሮ መቅደስ ገብረወልድ የ‹‹አሻጋሪ ኮንሰልተንሲ›› እና የ‹‹አሻጋሪ በጎ አድራጎት ድርጅት›› መስራችና ስራ አስኪያጅ ናቸው። በበጎ አድራጎትና በማኅበረሰብ ስራም (Social Work) በንቃት ይሳተፋሉ። ከበዓል ሰሞን ያለፈ የእርዳታ ተግባር አስፈላጊ ስለመሆኑ ሲናገሩ፣ ‹‹ለበዓል ብቻ የሚራብና የሚታረዝ ማንነት የለንም። ትዝ ባለን ጊዜ ብቻ ሳይሆን ኃላፊነታችንን መወጣት እንዳለብን ታሳቢ አድርገን መስራት ይገባናል። ተረዳድቶ መኖር የደግነት ብቻ ሳይሆን የህልውና ጥያቄም ሊሆን ይገባል›› ይላሉ። ስራ መስራትና መፍጠር የሚፈልግ ትውልድ እንዲኖር ማድረግ እንደሚገባ ይናገራሉ፤ ዘላቂ የመረዳዳት ተግባር ለእዚህ እገዛ እንደሚያደርግ ጠቅሰው፣ ለማኅበረሰብም ሆነ ለአገር ግንባታ አወንታዊ አስተዋፅኦ እንደሚያበረክት ወይዘሮ መቅደስ ይገልፃሉ።
የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ በአንድ ወቅት ‹‹ያለንን ማካፈል የባህላችን አንድ አካል ሆኖ የዘለቀ ዕሴት ነው። እጦት ለገጠማቸው ማካፈል ዐሥር እጥፍ መልሶ የሚያሸልም ተግባር ነው። ከበዓል ሰሞን ባሻገር በቀጣይነት የመስጠት ተግባራችንን ማስፋት በእኩልነት ተደራሽ የሆነ ማኅበረሰብን ለመፍጠር ከሚያስችሉ ግብአቶች አንዱ ነው። በተለያየ የኑሮ ደረጃ የሚገኙ ሁሉ ማዕድ ማጋራትን እንዲያሰፉ አበረታታለሁ›› የሚል መልዕክት አስተላልፈው ነበር። አዎ፣ የመረዳዳት ባህልን ከአንድ ሰሞን ድርጊት አሻግሮ ዘላቂ ለማድረግ ‹‹ያለንን የማካፈል›› መርህን በሚገባ መረዳት ያስፈልጋል። ያለንን በማካፈል መርህ የምናምን ከሆነ የተቸገሩ ወገኖችን ለማገዝ የበዓላትን ሰሞን መጠበቅ አያስፈልገንም። ያለውን በማካፈል መርህ የሚያምን ሰው መተጋገዝ ጊዜና ቦታ የማይገድበው በጎ ተግባር እንደሆነ ጠንቅቆ ያውቃል።
ዛሬ በሌሎች የተረዳና የተደገፈ ነገ ሌሎችን መርዳቱና መደገፉ አይቀርም፤ ዛሬ ያለውን ያካፈለ ሰው በእርሱ ማካፈል የሌሎች ችግር እንዲቃለል ከማድረጉ በተጨማሪ ሌሎችም ያላቸውን ለሌሎች እንዲያካፍሉ ትምህርት ይሰጣል። ያለንን የማካፈል መርህ እንዲህ ዓይነት አካሄዶችን በመገንባት መረዳዳትን ዘላቂ ለማድረግ ያስችላል።
የመረዳዳት ባህል ትርጉም የሚኖረውም ውስን ጊዜያት እየተጠበቁ በሚከናወኑ የመተጋገዝ ስራዎች ሳይሆን፣ ቀጣይ በሆኑ የመደጋገፍ ተግባራት ነው። ዘላቂ የሆነና ያለንን በማካፈል መርህ ላይ የተመሰረተ የመረዳዳት ተግባር ወንድማማችነትን/ እህትማማችነትን ያጎለብታል፤ መተማመንንና መከባበርን ያዳብራል፤ በጋራ ለማደግ ጠንካራ መሰረት ይሆናል። እነዚህ እሴቶች ለአገር ሰላም ትልቅ አወንታዊ አስተዋፅዖ ያበረክታሉ። በአጠቃላይ ዘላቂ የሆነ የመረዳዳት ባህልና ተግባር በመተማመንና በመከባበር ላይ የተመሰረተ አገር እንዲኖር ትልቅ ሚና ይጫወታል።
አንተነህ ቸሬ
አዲስ ዘመን ዓርብ ሚያዝያ 13 ቀን 2015 ዓ.ም