ሚያዝያ 16 ቀን 1979 ዓ.ም – ደራሲና ጋዜጠኛ ብርሃኑ ዘሪሁን አረፈ። ብርሃኑ ዘሪሁን የተወለደው በ1925 ዓ.ም በጎንደር ከተማ ነው። የቤተ-ክህነት ሰው የነበሩት አባቱ በዘመናቸውም የተማሩ ስለሆኑና ለልጃቸው ትምህርት የሚጨነቁ ስለነበሩ አራት ዓመት ሲሆነው የቤተክህነትን ትምህርት መማር ጀመረ። ጎንደር ውስጥ የሚሰጠውን የቤተ-ክህነት ትምህርት ከተከታተለ በኋላ ወደ ዘመናዊ ት/ቤት ገባ። ብርሃኑ መፅሐፍን የሚያነብ ብቻ ሳይሆን እንደ ምግብም የሚጠቀምባቸው ዓይነት ሰው እንደነበር የህይወት ታሪኩ ያወሳል። ብርሃኑን ቀልቡን ከሚስቡት ታሪኮች መካከል ደግሞ የኢትዮጵያ ታሪክ ዋነኛው ነው።
በ1945 ዓ.ም ብዙ ዕውቀቶችን ከገበየበት ከጎንደር ከተማ ወደ አዲስ አበባ መጣ። በአዲስ አበባም ቆይታው ተግባረ ዕድ ት/ቤት ገብቶ የሬዲዮ ቴክኒሻንነት በመማር በ1948 ዓ.ም ላይ በዲፕሎማ ተመረቀ። በምረቃው ወቅት ከተማሪዎቹ ሁሉ አንደኛ ወጥቶ ተሸላሚ የነበረው ብርሃኑ ዘሪሁን ነው። ብርሃኑ ዘሪሁን በተግባረ ዕድ ት/ቤት ሲማር የታላላቅ የዓለማችንን ደራሲያን ሥራዎችን ለማንበብ ዕድሉን አገኘ። የዊሊያም ሼክስፒርን፣ የአሌክሳንደር ዱማስ ፔሬን፣ የቻርልስ ዲክንስን፣ የአሌክሳንደር ፑሽኪንን እና የሌሎችንም ደራሲያን መፃሕፍት አነበበ። በንባብ የተከማቸው ዕውቀቱም በጽሑፍ መውጣት ጀመረ። እዚያው ተግባር-ዕድ ት/ቤት ሲማር የመፅሔት አዘጋጅ ሆኖ ሠርቷል። ተውኔት ጽፎም አሳይቷል።
በ1952 ዓ.ም በመምህርነት ከሚሠራበት ከተግባረ እድ ወደ ማስታወቂያ ሚኒስቴር እንደተዛወረ ‹‹የኢትዮጵያ ድምፅ›› ጋዜጣ ላይ ዋና አዘጋጅ ሆኖ መሥራት ጀመረ። ታዲያ በዚህ ወቅት ጋዜጣዋን ታዋቂ ከማድረጉም በላይ በብዙዎች ዘንድ የሚነበቡ መጣጥፎችን እና ታሪኮችን በመፃፍ ዝነኛ እየሆነ መጣ። ቀጥሎም የአዲስ ዘመን ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ ሆነ። በአጭር ጊዜ ውስጥ ዝነኛ መሆን ቻለ።
በ1958 ዓ.ም አዲስ የታሪክ አብዮት ማቀጣጠል ጀመረ። ‹‹የቴዎድሮስ እንባ›› የሚሰኝ መፅሐፍ አሳተመ። መስፍን ዓለማየሁ ይህን መጽሐፍ ወደ ተውኔት በኢትዮጵያ የቴአትር ታሪክ ከታላላቅ ትያትሮች ተርታ የሚሰለፍ መሆን ችሏል። ብርሃኑ ከአሥር በላይ መጻሕፍትን ጽፏል። ከእነዚህም መካከል «የታንጕት ምስጢር»፣ «ማዕበል የአብዮት ዋዜማ››፣ «ማዕበል የአብዮት መባቻ››፣ «ማዕበል የአብዮት ማግስት»፣ ‹‹ጨረቃ ስትወጣ››፣ ‹‹አማኑዔል ደርሶ መልስ››፣ ‹‹የእንባ ደብዳቤዎች››፣ ‹‹የበደል ፍፃሜ›› የሚሉት ይገኙበታል።ከዚህ በተጨማሪም ‹‹ባልቻ አባነፍሶ››፣ ‹‹ጣጠኛው ተዋናይ››፣‹‹የለውጥ አርበኞች››፣ ‹‹ሞረሽ››ና ሌሎችንም ድንቅ ተውኔቶችንም ጽፏል። ብርሃኑ ዘሪሁን ከደራሲነቱና ከፀሐፌ ተውኔትነቱ ባሻገር ሃያሲም ነበር። የተለያዩ ደራሲያንን ሥራዎችን ፅሑፎችን እየተከታተለ ሂሳዊ መጣጥፎችን ያቀርብ ነበር። ሥራዎቹ በበርካታ የስነ-ጽሑፍና የታሪክ ተመራማሪ በሆኑ ምሁራን ጥናት ተደርጎባቸዋል።
ሚያዝያ 16 ቀን 1992 ዓ.ም – ገጣሚ፣ ፀሐፊ ተውኔት፣ ደራሲ፣ ሃያሲ፣ ተርጓሚ፣ መምህርና የስነ ጽሑፍ ተመራማሪ ደበበ ሰይፉ አረፈ። ደበበ ሰይፉ ሐምሌ 5 ቀን 1942 ዓ.ም ከበጅሮንድ ሰይፉ አንተንይስጠኝ እና ከወይዘሮ የማርያምወርቅ አስፋው ባለውለታው፣ የማንነቱ መገኛ፣ የዕውቀቱ መፍለቂያና መድመቂያ መሆኗን በግጥሙ ባሞካሻት ይርጋለም ከተማ ተወለደ። መዝሙረ ዳዊትን እንዲሁም የአንደኛና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱንም ይርጋለም ከተማ በሚገኘው ራስ ደስታ ት/ቤት ከተማረ በኋላ ወደ አዲስ አበባ በመዛወር የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን በኮከበ ፅባህ ቀዳማዊ ኃ/ሥላሴ ት/ቤት አጠናቀቀ። በትምህርቱ የላቀ ውጤት እያስመዘገበ ቀዳማዊ ኃ/ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ (የአሁኑ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ) ገባ። የጀመረውን የቢዝነስ ትምህርት ትቶ ወደ ስነ-ጽሑፍ ትምህርት ክፍል ተዛወረ።
በ1965 ዓ.ም ከዩኒቨርሲቲው የኢትዮጵያ ቋንቋዎችና ስነ-ጽሑፍ ተቋም በመጀመሪያ ዲግሪ በማዕረግ ተመረቀ። ከአምስት ዓመታት በኋላም በእንግሊዝኛ ስነጽሑፍ ሁለተኛ ዲግሪውን በማዕረግ ተመረቀ። ደበበ በልጅነቱ መጽሐፍትን አንብቦ አይጠግብም ነበር ይባላል። እስከ ግንቦት 1985 ዓ.ም ድረስ በዩኒቨርሲቲው በመምህርነትና በተመራማሪነት አገልግሏል። ከምርምር ሥራዎቹም መካከል … ‹‹የትያትር ጥበብ ከጸሐፊ ተውኔት አንፃር››፣ ‹‹ደራሲው በአብዮት አውድ››፣ ‹‹ዋዜማ ጦርነት ግጥሞች››፣ ‹‹ሕዝባዊ ስነ-ግጥም››፣ ‹‹Profile of Peasantry in Ethiopian Novels››፣ ‹‹A Critical Analogy of Ethiopian Novels››፣ ‹‹Foreign Scholars on Amharic Novels››፣ ‹‹The Need for Marxist Approach in the Teaching of Literature›› የሚሉትና ሌሎች ሥራዎቹ ይጠቀሳሉ።
ከተውኔት ሥራዎቹ መካከል ደግሞ ‹‹እናትና ልጆቿ››፣ ‹‹ከባህር ወጣ ዓሣ››፣ ‹‹ሳይቋጠር ሲተረተር›› እና ‹‹የሕፃን ሽማግሌ›› የሚሉት ተጠቃሽ ናቸው። ‹‹ክፍተት››፣ ‹‹እድምተኞቹ››፣ ‹‹ጋሊልዮ ጋሊሊ››፣ ‹‹ማክቤዝ›› እና ‹‹ፓሪስ ኮሚዬን›› የተባሉ ሥራዎቹ ደግሞ ለኢትዮጵያ ትያትር ዘርፍ ያበረከታቸው የትርጉም ሥራዎቹ ናቸው። ለሕትመት ከበቁት የደበበ መጽሐፍት መካከል ደግሞ ‹‹ማርክሲዝምና የቋንቋ ችግሮች›› (1971)፣ ‹‹የትያትር ጥበባት ከጸሐፊ ተውኔት አንፃር›› (1973)፣ ‹‹ፅጌሬዳ ብዕር›› (ከሌሎች ደራስያን ሥራዎች ጋር – 1977)፣ ‹‹የብርሃን ፍቅር – ቅጽ 1›› (1980) እንዲሁም ‹‹ለራስ የተፃፈ ደብዳቤ (የብርሃን ፍቅር ቅጽ 2)›› ተጠቃሽ ናቸው።
ገጣሚ፣ ፀሐፊ ተውኔት፣ ደራሲ፣ ሃያሲ፣ ተርጓሚ፣ መምህርና የስነ ጽሑፍ ተመራማሪ ደበበ ሰይፉ ከግንቦት 1985 በኋላ የማስተማር ሥራውን አቁሞ ለሰባት ዓመታት ያህል ከቤት ዋለ። ሲያሰቃየው የነበረው የመገጣጠሚያ አካላት ያለመታዘዝ ችግር በተወለደ በ50 ዓመቱ ሚያዝያ 16 ቀን 1992 ዓ.ም ለሕልፈት ዳረገው። ስርዓተ ቀብሩም ሚያዝያ 17 ቀን 1992 ዓ.ም በቅዱስ ዮሴፍ ቤተ-ክርስቲያን ተፈፀመ። በወቅቱም በርካታ የሕትመት መገናኛ ብዙኃን ስለደበበ ታላቅነት ደጋግመው ጽፈዋል።
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 18/2011
አንተነህ ቸሬ