ልክ እንደባለፈው ሳምንት ዛሬም እንኳን አደረሳችሁ ብያለሁ… ግዴለም‹‹በየሳምንቱ የሚጨቀጭቀን በጤናው ነው?›› ብላችሁ እንዳትሰለቹ … ‹‹ቸር ተመኝ ቸር እንድታገኝ›› ነውና ነገሩ የመልካም ምኞት መግለጫዬን ተቀበሉ)
ባለፈው ሳምንት በበዓላት ሰሞን ስለታዘብኳቸው አንዳንድ ጉዳዮች (ስለ ከተማውና ነዋሪው ውጣ ውረድና ስለ በዓል ሰሞን የመገናኛ ብዙሃን መሰናዶዎች) አጫውቻችሁ ነበር። ዛሬ ደግሞ ኢትዮጵያን አስተዳድረው ካለፉ ነገሥታት መካከል የአፄ ገላውዴዎስን እና የዳግማዊ አፄ ቴዎድሮስን የፋሲካ በዓል ሰሞን ‹‹ገጠመኞች››ን ላካፍላችሁ ወደድኩ።
ቀደምት የኢትዮጵያ ነገሥታት ልዩ ልዩ በዓላትን የሚያከብሩበት የራሳቸው ልማድ እንዳላቸው ታሪካቸው ያስረዳል። ለአብነት ያህል ነገሥታቱ በዓላትን በዘመቻ (ጦርነት) ላይ እንዳሉ ያሳለፉባቸው ጊዜያትም ብዙ ናቸው። በሌላ በኩል ደግሞ ነገሥታቱ ወደ ሃይማኖታዊ ስፍራዎች (አብያተ ክርስቲያናትና ገዳማት) በመሄድ በዓላትን ያሳልፉም ነበር። ከዚህ በተጨማሪም ነገሥታቱ ዋናው ቤተ-መንግሥታቸው በሚገኝበት በመናገሻ ከተማቸው ሆነው ሕዝቡ በዓላቱን በሚያከብርበት የአከባበር ሥርዓትም ያከብራሉ።
አፄ ገላውዴዎስ ከ1532 ዓ.ም እስከ 1551 ዓ.ም ድረስ ኢትዮጵያን ያስተዳደሩ ንጉሥ ናቸው። አባታቸው አፄ ልብነድንግል ከሞቱ በኋላ የነገሱት አፄ ገላውዴዎስ፣ አብዛኛውን የስልጣን ጊዜያቸውን ያሳለፉት ከግራኝ አሕመድ ጋር ሲዋጉ ነበር። ግራኝ አሕመድ ከምስራቃዊው የኢትዮጵያ ክፍል ተነስቶ ወደ ደጋማው የክርስቲያን ግዛተ-አፄ የሰነዘረው ጥቃት የአፄ ልብነድንግልን መንግሥት ክፉኛ አዳከመው።
በመጋቢት ወር 1521 ዓ.ም ሽምብራ ኩሬ በተባለው ቦታ ላይ በግራኝ አሕመድ ድል የሆኑት አፄ ልብነድንግል እስከ ዕለተ ሞታቸው ድረስ የግራኝ ጦርን ጥቃት በመከላከል ለማሳለፍ ተገደዱ። በመጨረሻም በ1532 ዓ.ም አረፉ።
የአፄ ልብነድንግልን ሞት ተከትሎ ወደ ዙፋኑ የመጡት ልጃቸው አፄ ገላውዴዎስም ከግራኝ አሕመድ ሰራዊት ጋር መፋለም ቀጠሉ። አፄ ገላውዴዎስ ከነገሱ ከሁለት ዓመታት በኋላ ከ1520 ዓ.ም ጀምሮ በአብዛኛው የኢትዮጵያ ክፍል ላይ የበላይነትን ያገኘው ግራኝ አሕመድን ድል አደረጉ። ግራኝ አሕመድም ፍፃሜ ሆነ። አፄ ገላውዴዎስም በግራኝ ጥቃት የወደሙ አብያተ ክርስቲያናት እያሳደሱ ቆዩ።
ይሁን እንጂ ግራኝ አሕመድ ድል ሆኖ ከሞተ በኋላ ባለቤቱ ባቲ ድል ወንበራና ተከታዮቹ የመሪያቸውን ደም ለመመለስና የበላይነትን ለማግኘት ማሴራቸውን
አላቆሙም። በአፄ ገላውዴዎስ ግዛት ላይ ጥቃት መሰንዘራቸውን አላቆሙም። በ1551 ዓ.ም ኑር ኢብን ሙቃሒድ የተባለው የግራኝ አሕመድ የእህት ልጅ ሰራዊቱን አስከትቶ ቡልጋን ወረረ። በወቅቱ ጎጃም ውስጥ ቤተክርስቲያን እያሰሩ ነበረ። ንጉሱ ወረራውን ሲሰሙ በንዴት ወደ ሸዋ ገሰገሱ። ነገር ግን ንጉሱ ሙሉ ሰራዊታቸውን ይዘው አልመጡም። መኳንንቶቻቸው ‹‹አሁን ያለን ጦር አነስተኛ ስለሆነ የፋሲካን በዓል ውለን ሰራዊት ጨምረን ብንዋጋ ይሻላል›› ሲሉ ሃሳብ አቀረቡላቸው። ካህናቱም ለንጉሱ ‹‹ፋሲካን አብረን ብንውል ይሻላል›› አሏቸው።
ንጉሱ ግን ‹‹ፋሲካን በሰማይ ቤት ከጌታዬ ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር እውላለሁ›› የሚል ምላሽ ሰጡ። በዕለተ አርብ፣ በስቅለት ቀን ጦርነቱ ተጀመረ። ንጉሱም በተፋፋመው ውጊያ ውስጥ ገብተው እንደተራ ወታደር ሲዋጉ ከተፋላሚው ወገን በተተኮሰ ጥይት ተመቱ። ወታደሮቻቸው እንዳይደናገጡ ቁስላቸውን አስረው ውጊያውን ቀጠሉ። የኑር ኢብን ሙቃሂድ ወታደሮች ተከታትለው መጥተው ደግመው ስለመቷቸው ሕይወታቸው አለፈ። ንጉሱ ከፋሲካ በዓል ቀድሞ በስቅለት ቀን አረፉ።
ንጉሱ ‹‹ይቅርብዎት›› እየተባሉ አሻፈረኝ ብለው ውጊያ ገጥመው በዕለተ አርብ፣ በስቅለት ቀን በመሞታቸው እንዲህ ተብሎ ተገጠመላቸው …
አፄ ገላውዴዎስ ጌታን ተከተለ፣
ፋሲካውን ሳይውል ዓርብ ተሰቀለ።
ጌታውም ሳይረሳው የፋሲካ ለታ፣
አስጠርቶ አበላው ከጧት እስከ ማታ።
አፄ ገላውዴዎስ እንደ ዮሐንስ፣
ባሕር ዳርን ዞሮ ሸዋ ሲመለስ፣
አንፆኪያ ላይ ታዬ ብርሃን ሲለብስ።
ኢትዮጵያን ከ1532 ዓ.ም እስከ 1551 ዓ.ም ድረስ ያስተዳደሩ ንጉሥ አፄ ገላውዴዎስ ታሪካቸው ከፋሲካ በዓል ጋር የተቆራኘ እንዲሆን ያደረገው አጋጣሚ ከላይ በአጭሩ የተፃፈው ታሪክ ነው።
‹‹ዘመነ መሳፍንት›› የተባለው የግዛት ባላባቶች ዘመን ፍፃሜውን እንዲያገኝ፤ ኢትዮጵያን በአንድ ጠንካራ ማዕከላዊ መንግሥት ስር ለማስተዳደር የሞከሩት ንጉሰ ነገሥት ዳግማዊ አፄ ቴዎድሮስም ታሪካቸው ከፋሲካ በዓል ሰሞን ጋር ተያይዞት አለው። ‹‹የአፄ ቴዎድሮስ ታሪክ ከፋሲካ በዓል ጋር በምን ምክንያት ይገናኛል?›› ብላችሁ ከጠየቃችሁኝ … ተከተሉኝ …
ዳግማዊ አፄ ቴዎድሮስ የልጅነት ስማቸው ‹‹ካሣ›› ይባል ነበር። አባታቸው ደጃዝማች ኃይሉ ወልደጊዮርጊስ እናታቸው ደግሞ ወይዘሮ አትጠገብ ወንድበወሰን ይባላሉ። ልጅ ካሣ አባታቸው በሕፃንነታቸው ስለሞቱ ወደ አጎታቸው ደጃች ክንፉ ዘንድ በመሄድ አድገዋል። ለትምህርት በተላኩባቸው ቦታዎችም የአስተዳደር ስራንና የሀገራቸውን የወቅቱን ፈተናዎች ተገንዝበዋል።
የግዛት ባላባቶች በቡድን ተከፋፍለው ለስልጣን ደም ሲፋሰሱ የወቅቱ የኢትዮጵያ ሁኔታ ካሣን እረፍት ነሳቸው። ኢትዮጵያን በአንድ ጠንካራ ማዕከላዊ መንግሥት ስር ለማስተዳደር ማሰብ ጀመሩ። አስበውም አልቀሩም።
በየጊዜው የተጠመደባቸውን ሴራ በብልሃትና በጀግንነት በማለፍ የግዛት ባላባቶችን ድል አድርገው ‹‹ዳግማዊ አጤ ቴዎድሮስ ንጉሰ ነገሥት ዘኢትዮጵያ›› ተብለው ዘውድ ደፉ። አንድነቷ የተጠበቀች ኢትዮጵያን ለመምራትም እንቅስቃሴዎችን ማድረግ ጀመሩ።
ይሁን እንጂ የወቅቱ የኢትዮጵያ ማኅበረ-ፖለቲካዊ ስሪትና ዓለም አቀፋዊ ሁኔታዎች ከንጉሰ ነገሥቱ ባህርያት ጋር ተደምረው ዓላማቸውን እንዳሰቡት ሊሳኩ አልቻሉም። በአገር ውስጥ ከራሳቸው መኳንንትና ንግስና ከሚፈልጉ ባላባቶች እንዲሁም ከኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክርስቲያን ካህናት ጋር የገቡበት ውዝግብ ያሰቡትን ማሳካት አላስቻላቸውም።
ለስልጣኔ ትልቅ ጉጉት የነበራቸው ንጉሱ፣ ‹‹መሳሪያ የሚሰሩ ባለሙያዎችን ላኩልኝ›› ብለው ወደ አገር ቤት የመጡ እንግሊዛውያንን በተፈጠረ ውዝግብ ወደ ወህኒ ቤት መወርወራቸው ውድቀታቸውን የበለጠ አፋጠነው።
እንግሊዝ ዜጎቿን ለማስፈታት በጀኔራል ናፒዬር የተመራ ጦር ወደ ኢትዮጵያ ላከች። ዳግማዊ አፄ ቴዎድሮስም የጦር መሪያቸውን ፊታውራሪ ገብርዬ ከሞቱበት ጦርነት ቀደም ብሎ ለእንግሊዙ የጦር አለቃ ጀኔራል ናፒዬር ‹‹መቼም ክርስቲያን ነህና ለመግደፊያ አንድ ሺ በጎችን ልኬልሃለሁ፤ ከፈለግህ ጦሙ ሲገደፍ ትገጥመኛለህ›› የሚል ስጦታና መልዕክት ልከው ነበር።
የእንግሊዝ ጦር ከንጉሰ ነገሥቱ ጦር ጋር ከመዋጋቱ በፊት ሚያዝያ 3 ቀን 1860 ዓ.ም በዕለተ ዓርብ፣ በስቅለት ቀን ከንጉሱ ታማኝ የጦር መሪ ከነበሩት ከፊታውራሪ ገብርዬ ጦር ጋር ገጥሞ ፊታውራሪ ገብርዬ ሞቱ።
ንጉሱም አምርረው አለቀሱ። ‹‹ላልጨርሰው አልጀመርኩትም›› ያለው ናፒየርም በፋሲካ ማግሥት (በማዕዶት – በፋሲካ ማግሥት የሚውለው ሰኞ ‹‹ማዕዶት›› ይባላል)፣ ሚያዝያ 6 ቀን 1860 ዓ.ም በንጉሱ ላይ ጥቃት ከፈተ። ንጉሰ ነገሥቱም ‹‹በጠላት እጅ ከመውደቅ …›› ብለው በሽጉጣቸው ራሳቸውን አጠፉ። ገብርዬ በስቅለት፤ቴዎድሮስ በማዕዶት (በፋሲካ ማግሥት) ይችን ዓለም ተሰናበቱ።
‹‹አርባ ጦም ተጡሞ፣ ፋሲካ ሲደርስ፣
በአፈር ገደፉ አሉ፣ የሀበሻው ንጉስ›› ተብሎም ተገጠመላቸው።
ሁለቱ ኃይለኛ ነገሥታት፣ አፄ ገላውዴዎስ እና ዳግማዊ አፄ ቴዎድሮስ በፋሲካ በዓል ሰሞን ጋር ያላቸው ቁርኝት በአጭሩ ይህን ይመስላል።
በድጋሜ እንኳን አደረሳችሁ … መልካም በዓል!
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 16/2011
በአንተነህ ቸሬ