“ ሰዎች ወደዚህች ዓለም ሲመጡ አራት ዝንባሌዎችን ይዘው ይመጣሉ ። እነርሱም የምጣኔ ሃብት ዝንባሌ (Homo Economicus)፣ የኃይማኖተኝነት ዝንባሌ (Homo Religious)፣ የፖለቲከኛነት ዝንባሌ (Homo Politicus) እና የንድፈ-ሃሳብ ዝንባሌ (Homo Theoreticus) ናቸው። የአንድ መምህርም ተግባሩ ዝንባሌዎቹን ከተማሪው ውስጠ-ልቡና ፈልፍሎ ማግኘት ይሆናል። “ዶክተር እጓለ ገብረ ዮሐንስ ‹‹የከፍተኛ ትምህርት ዘይቤ›› በሚል ርዕስ በ1956 ለንባብ ባበቁት መጽሐፍ ላይ ስለ ትምህርት አስፈላጊነትና ፋይዳ ያስቀመጡት ሃሳብ ነው።
ከላይ በመንደርደሪያነት ያነሳኋቸው የሊቃውንቱ ሃሳብ የመምህር እና የትምህርትን ወሳኝነትና ያለውን ከፍተኛ ፋይዳ ከፍ የሚያደርጉ ናቸው፡፡ የአንድ አገር እድገት ቁልፍም ያለው በትምህርት ዘርፍ ላይ መሆኑን ይጠቁመናል።በአገራችን ባለፉት አስር ዓመታት በመንግሥት ትልቅ ትኩረት ከተሰጡት ዘርፎች መካከል ትምህርት በግንባር ቀደምነት ይጠቀሳል። ከተደራሽነት አንፃር የመንግሥት ከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን ቁጥር በአሁን ወቅት ሃምሳ ሊደርሱ ተቃርበዋል፡፡
በግሉ ዘርፍም ሲቃኝ ደግሞ 150 ስለመድረሳቸው መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡ በሁሉም ደረጃ የትምህርት ተደራሽነቱን ላይ በጎና ሰፊ ስራ ተሰርቷል። ይሁንና ብዛት ላይ ሳይሆን ጥራት ሲጠየቅ መልሱ ቀላል አይደለም፡፡ ከዚሁ እውነታ ጋር በሚናበብ መልኩ የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ በአንድ ወቅት፣ “… የትምህርት ተደራሽነት ማደጉን ሳንረሳ፣ ዘርፉ በእጅጉ በመጎዳቱ ላይ ግን ምንም ክርክር አይኖርም፡፡ በመሠረታዊነት ትምህርትን ማዳረስ አስፈላጊ ቢሆንም፤ ነገር ግን በቂ የትምህርት መሣሪያ፣ አስተማሪና የትምህርት አሰጣጥን ሳይፈጥሩ ሕንፃ እየገነቡ ብቻ ተማሪዎችን መሰብሰብ ችግሩን እንዲፈጠር አድርጓል” ሲሉ መነጋራቸው የሚታወስ ነው፡፡
ኢትዮጵያ የትምህርት ስርዓቱ ብዛትን ተከትሎ የትምህርት ጥራት ጉዳይ መንገድ በመሳቱ፤ በብርቱ ሲታመም እና ሲሰቃይ ቆይቷል፡፡ የአገሪቱ የትምህርት ዘርፍ የገባበትን ገደል ጥልቀት ለመረዳት ደግሞ ብዙ ርቀትን መጓዝ ሳይፈልግ የቅርቡን የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና አስደንጋጭ ውጤት ማስታወስ በቂ ነው፡፡ለፈተናው ከተቀመጡት 980 ሺህ በላይ ተማሪዎች መካከል 30 ሺህ ብቻ ከ50 በመቶ በላይ ውጤት ማግኘታቸው የሚታወስ ሲሆን የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑም የተመዘገበውን ውጤት “አስደንጋጭ” ሲሉ ነበር የገለጹት። ትምህርት ሚኒስቴር በብሔራዊው ፈተና ተደጋጋሚ የሚከሰተውን የፈተና ስርቆት እና ኩረጃን ለማስቀረት የተከተለው አሰራር ደግሞ ተሸፋፍኖ የሰነበተውን ሐቅ አደባባይ ያዋጣ ነበር፡፡
ፕሮፌሰር ብርሃኑ አሁን ለታየው የተማሪዎች የውጤት ማሽቆልቆል ለዓመታት ሲንከባለል የቆየ የበርካታ ችግሮች መገለጫ እና ተሸፍኖ የቆየውን እውነተኛ የትምህርት ሥርዓት ያለበትን ደረጃ ያመለከተ ነው ” ሲሉ ነበር የትምህርት ስርዓቱን ስብራት ያመላከቱት። በእርግጥም በ12ኛ ክፍል ፈተና የተመዘገበው ውጤት እንደ አገር የቱ ጋር እንዳለን ይጠቁመናል። በሌላ በኩል ደግሞ ለችግሩ ቀጣይ መፍትሄ ለማበጀት ያስችላል። በተለይ ለከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የማንቂያ ደውል እንደሚሆን አምናለሁ። ይህን ሁኔታ ዶክተር እጓለ ገብረ ዮሐንስ ‹‹የከፍተኛ ትምህርት ዘይቤ›› መጽሐፍ ላይ፤ “ሰው ከሙሉ የሰውነት ደረጃ የሚደርሰው በትምህርት ነው፣ እነዚህን ነጥቦች ያልተረዳ ማኅበረሰብ ሆነ ሥርዓተ ትምህርት፣ በትምህርት የሚፈለገውን ውጤት ሊያመጣ መቸገሩ አይቀርም፤” ሲሉ ይገልጻሉ፡፡
የተበላሸ የትምህርት ስርዓት የሚያደርሰውን ጉዳት ተረድቶ በፍጥነት መፍትሄ መፈለግ እንደሚበጅ መረዳት ይገባል። ከዚህ አኳያ መንግሥት ችግሩን በሚገባ የተገነዘበው ይመስላል። ምክንያቱም በሁሉም ደረጃ የትምህርት ስርዓቱን ስብራት ለመጠገን እያደረገ ያለው እንቅስቃሴ ይሄንኑ ይናገራልና። በተለይ በአገር አቀፍ ደረጃ የትምህርት ስርዓቱ ውድቀት ማሳያ በመሆን በሚጠቀሰው በከፍተኛ የትምህርት ላይ ስር ነቀል ለውጥ ለማምጣት ጥረት እየተደረገ ስለመሆኑ መካድ አይቻልም። በዚህ ረገድ መንግሥት የትምህርት ዘርፍ ያጋጠመውን ስብራት ለመጠገን በርካታ ስራዎች እየሰራ እንደሚገኝ ይታወቃል።
ከእነዚህ መካከል ደግሞ የዩኒቨርሲቲ መውጫ ፈተና ይጠቀሳል። ትምህርት ሚኒስቴር ከአንድ ዓመት በፊት በ2015 ዓ.ም ጀምሮ የዩኒቨርሲቲ የመውጫ ፈተናው በሁሉም የመንግሥትና የግል ዩኒቨርሲቲዎች ለመስጠት መወሰኑ ይታወሳል። በዚህ ሁሉ ተስፋ የታጠረው የዩኒቨርሲቲ መውጫ ፈተናው በመጪው ሐምሌ ወር በሁሉም ዩኒቨርሲቲዎች መሰጠቱ እርግጥ ሆኗል። የመውጫ ፈተና እንደ ማሌዢያ፤ ጃፓንና ቻይና የመሳሰሉ አገራት ያሉ ተማሪዎች ራሳቸውን የሚገመግሙት የዩኒቨርሲቲው የመውጫ ፈተና እየወሰዱ እንደሆነ መረጃዎች ያመላክታሉ። እነዚህ አገራት ምን ያህል እንዳለፉና እንደወደቁ ራሳቸውን ይፈትሻሉ።
ይህም ድርጊት ተማሪዎች ጉድለታቸውን አውቀው እንዲጠነክሩ ይረዳቸዋል። በኢትዮጵያ ውስጥም ይህ ዓይነት ልምድ ቢኖር የትምህርት ጥራቱ የተሻለ እንደሚሆን አያጠራጥርም። በተለይ የትምህርት ሥርዓታችን ከታችኛው ክፍል ጀምሮ በኩረጃ የዋዠቀ እንደሆነ ትችት የሚቀርብበት እንደመሆኑ፤ የመውጫ ፈተና መሰጠቱ አሁን ላይ ያለው ትውልድ ራሱን እንዲፈትሽ መጭው ትውልድ ደግሞ በጥንቃቄ ለመማር ያስችላል ተብሎ ይጠበቃል። የመውጫ ፈተና ተግባራዊ መሆን ለቁጭቱ ተገቢ ምላሽ የሰጠ እርምጃ እንደሆነ ሁሉ ተግባራዊነቱም በከፍተኛ ትምህርት ላይ ያሉትን ክፍተቶች ለይቶ ማወቅ ወደ ጥራት መንገድ ለመጓዝ ያስችላል፡፡ ይህን አይነቱን ተስፋ ያዘለ አዲስ አሰራር ሲመጣ ተግባራዊነቱን ከመደገፍ ባሻገር ለውጤታማነቱ አብሮ መሰለፍ ያስፈልጋል።
በአሁን ወቅትም ሁሉም በየፊናው ለፈተናው ስኬትና ያማረ ውጤት እየተጋ ቢሆንም በ12ተኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ውጤት ታሪክ ራሱን እንዳይደግም በሁሉ ረገድ ቀድሞ መዘጋጀት የሚጠይቅ ነው፡፡ በተለይ የቅድመ ምረቃ ተማሪዎች ለመውጫ ፈተናው በስነ- ልቦናም በእውቀት ደረጃ በመዘጋጀት ራሳቸውን ለፈተናው ብቁ አድርገው መቅረብ ይኖርባቸዋል። ተማሪዎች የመውጫ ፈተና ዓላማው የተባለሸውን የትምህርት ስርዓት ለማስተካከል የተወሰደ መፍትሄ መሆኑን በማመን በተረጋጋ መንፈስ ዝግጅታቸውን ማድረግ ይጠበቅባቸዋል። ዩኒቨርሲቲዎችም የመውጫ ፈተናው ተማሪዎች ብቻ ሳይሆን ዩኒቨርሲቲዎች የራሳቸውን አቅም ጭምር የሚፈትሹበት ትልቅ አጋጣሚ እንደሆነ ሊረዱም ይገባል። ይህን መሰረት ባደረገ መልኩ አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት በማድረግ የመውጫ ፈተናው በስኬት ማጠናቀቅ እንዲቻል ሀገራዊ ኃላፊነታቸውን ሊወጡ ይገባል
ዳንኤል ዘነበ ።
ይህ አምድ በተለያዩ ፖለቲካዊ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ዜጎች ነፃ ሀሳባቸውን የሚሰጡበት ነው። በዓምዱ ላይ የሚወጡ ጽሁፎች የዝግጅት ክፍሉን አቋም አያመለክቱም።
አዲስ ዘመን ሰኞ መጋቢት 4 ቀን 2015 ዓ.ም