
ኢንፌክሽኖች በሰውነት ውስጥ በማንኛውም ቦታ ሊጀምሩና በሰውነታችን በሙሉ ሊሰራጩ ይችላሉ፤ ኢንፌክሽን በሰውነት ውስጥ በሚከሰትበት ቦታ ላይ በመመርኮዝ ትኩሳትና ሌሎች የጤና ችግሮች ይከተላሉ። የሰውነት በሽታ የመከላከል ስርዓት ጠንካራ በሚሆንበት ጊዜ ጀርሞችን በመዋጋት ኢንፌክሽንን ይቋቋማል። አንዳንድ የካንሰር ህክምናዎች በሽታ የመከላከል ስርዓትን ሊያዳክሙ ስለሚችሉ ይህ ሁኔታ ደግሞ ወደ ኢንፌክሽን ሊያመራ ይችላል።
ኢንፌክሽኑ እንዴት እንደሚሰራጭ እና በሰው አካል ላይ የሚያሳድረው ተጽዕኖ እንደ በሽታ አምጪ ተህዋሲያን አይነት ሊለያይ ቢችልም ኢንፌክሽኖች ግን የሚያስከትሉት ጉዳት በቀላሉ የሚታይ አይደለም። በቤተ ዛታ ሆስፒታል የውስጥ ደዌ ስፔሻሊስት የሆኑት ዶክተር ሄኖክ ዘውዱ በኢንፌክሽንና ተያይዘው ሰለሚመጡ በሽታዎች ሰፋ ያለ ማብራሪያ ሰጥተውናል፡፡ እንደሚከተለው ይቀርባል፡፡
የሰውነት በሽታን የመከላከል ስርዓቱ በተላላፊ በሽታዎች ላይ ውጤታማ መከላከያ ቢሆንም በሽታ አምጪ ተህዋሲያን አንዳንድ ጊዜ የሰውነትን በሽታ የመከላከል ስርዓትን በማዳከም አቅምን ሊጠይቅ ይችላሉ። በዚህ ደረጃ ደግሞ ኢንፌክሽን ጎጂ ይሆናል።
አንዳንድ በሽታ አምጪ ተህዋሲያን እምብዛም ተጽእኖ አይኖራቸውም። ሌሎች ደግሞ በሰውነት ውስጥ አሉታዊ ምላሾችን የሚቀሰቅሱ መርዛማ ንጥረ ነገሮችን ያመነጫሉ። የዚህ ልዩነት ደግሞ አንዳንድ ኢንፌክሽኖች ቀላል እና በቀላሉ የማይታዩ ሲያደርጋቸው ሌሎች ደግሞ ከባድ እና ለሕይወት አስጊ እንዲሆኑ አቅም ይፈጥርላቸዋል። አንዳንድ በሽታ አምጪ ተህዋሲያን ህክምናንም ሊቋቋሙ ይችላሉ።
ኢንፌክሽን በሰውነት ውስጥ እንዲሰራጭ ከሚያደርጉ ምክንያቶች መካከል ባክቴሪያዎች፣ ቫይረሶች፣ ፈንገሶች እና ጥገኛ ተውሳኮች የተለያዩ አይነት በሽታ አምጪ ተህዋስያን ይገኙበታል። እነሱ በተለያዩ መንገዶች ይለያያሉ ፣ ከእነዚህም መካከል መጠን፣ ቅርጽ፣ ተግባርና የጄኔቲክ ይዘት ይጠቀሳሉ።
ኢንፌክሽኖች በሰውነት ላይ እንዴት እንደሚሠሩ ለማወቅ የተለያዩ መንገዶች ያሉ ሲሆን ከእነዚህም መካከል ቫይረሶች ከባክቴሪያ ያነሱ በመሆናቸው ወደ ሰውነት ገብተው ሴሎችን ይቆጣጠራሉ።
ጀርሞች የእለት ተእለት ህይወት አካል ሲሆኑ በአየር፣ በአፈር፣ በውሃና በሰውነታችን ውስጥ ይገኛሉ። አንዳንድ ጀርሞች ጠቃሚ የሚሆኑበት አጋጣሚ ያለ ሲሆን ሌሎች ደግሞ ጎጂ ናቸው። ብዙ ጀርሞች በሰውነታችን ውስጥ እና በሰውነታችን ላይ ምንም ጉዳት ሳያስከትሉ ይኖራሉ እና አንዳንዶቹ ጤናማ እንድንሆን ይረዱናል። ኢንፌክሽኑን እንደሚያመጣ የሚታወቀው ጥቂት የጀርሞች ክፍል ብቻ ነው።
ኢንፌክሽን የሚከሰተው ጀርሞች ወደ ሰውነት ውስጥ ገብተው ቁጥራቸው ሲጨምር እና የሰውነት ምላሽ ሲፈጠር ሲሆን ጀርሞች ወደ ሰውነት ውስጥ የሚገቡበት መንገድ ያለው ተጋላጭ ሰው መተላለፍ፣ ጀርሞች ወደ ተጠቂው ሰው የሚዘዋወሩበት መንገድ ተላላፊ በሽታዎች ቫይራል፣ ባክቴሪያ፣ ጥገኛ ወይም የፈንገስ በሽታዎች ሊሆኑ ይችላሉ።
ቫይረሶች ከሴሎች በጣም ያነሱ ናቸው እና በራሳቸው ለመራባት ምንም መንገድ የላቸውም። ወደ ሴሎች ውስጥ ገብተው የራሳቸውን ቅጂ ለመስራት የሴሎችን ማሽኖች ይጠቀማሉ። የባክቴሪያ ኢንፌክሽን ተህዋሲያን አንድ ሕዋስ ያላቸው ፍጥረታት ሲሆኑ መመሪያቸው በትንሽ ዲ ኤን ኤ ላይ የተፃፈ ነው። በሰውነታችን ውስጥ እና በቆዳችን ላይ ጨምሮ ባክቴሪያዎች በዙሪያችን አሉ። ብዙ ባክቴሪያዎች ምንም ጉዳት የላቸውም አልፎ ተርፎም ጠቃሚ የሚሆኑበት ጊዜ አለ። ነገር ግን አንዳንድ ባክቴሪያዎች ሰዎች ህመም ላይ እንዲወድቁ ሊያደርጉ የሚችሉ መርዞችን ይለቃሉ።
የፈንገስ በሽታዎች ልክ እንደ ባክቴሪያ ብዙ ዓይነቶች ሲሆኑ በሰውነት ውስጥ ይኖራሉ። ጎጂ የሆኑ ፈንገሶች በአፍ፣ በአፍንጫ ወይም በቆዳ ውስጥ ወደ ሰውነት ሊገቡ ይችላሉ።
ተላላፊ በሽታዎች በዓለም ዙሪያ በጣም የተለመዱ ናቸው፤ ነገር ግን አንዳንዶቹ ከሌሎቹ የበለጠ የተለመዱ ናቸው። ለምሳሌ በዩናይትድ ስቴትስ በየዓመቱ ከ5 ሰዎች 1ዱ በኢንፍሉዌንዛ ቫይረስ ይያዛል።
ማንኛውም ሰው ተላላፊ በሽታ ሊይዘው ይችላል። በሽታን የመከላከል አቅም ከተዳከመ ወይም አንዳንድ በጣም ተላላፊ በሽታዎች ወዳለባቸው አካባቢዎች ከተጓዙ የበለጠ አደጋ ሊያጋጥምዎት ይችላል።
የታፈነ ወይም የተዳከመ የበሽታ መቋቋም ስርዓት ያለባቸው፣ ለምሳሌ የካንሰር ህክምና የሚያገኙ፣ ከኤችአይቪ ጋር የሚኖሩ ወይም አንዳንድ መድሃኒቶች የሚወስዱ፣ ህጻናት ልጆች፣ እርጉዝ እናቶች እና ከ 60 ዓመት በላይ የሆኑ አዋቂ ሰዎች ፣ በተለመዱ ተላላፊ በሽታዎች ላይ ክትባት ያልወሰዱ፣ ጤና ባለሙያዎች፣ እንደ ወባና ሌሎች በሽታ አምጪ ተህዋሲያን ለሚይዙ ትንኞች ሊጋለጡ ወደሚችሉበት ቦታ የሚጓዙ ሰዎች በኢንፌክሽን የመያዝ እድላቸው ከፍ ያለ ነው።
ተላላፊ በሽታዎች የሚከሰቱት ከውጭ ወደ ሰውነትዎ በሚገቡ የተለያዩ ወኪሎች ሲሆን እነዚህም ውስጥ ቫይረሶች፣ ባክቴሪያዎች፣ ፈንገሶች፣ ጥገኛ ተሕዋስያንና ሌሎችም ይገኙበታል።
ሕዋሳትዎ በወራሪው አካል ሲጎዱ ወይም ሲወድሙ እና የበሽታ መከላከያ ስርዓታችን ለኢንፌክሽኑ ምላሽ ሲሰጥ ምልክቶች ሊታዩ ይችላሉ።
ዶክተር ሄኖክ እንደሚሉት ኢንፌክሽን ማለት የበሽታ አምጪ ተዋህስያን ወይም ጀርም ብለን የምንጠራቸው ነገሮች ወደሰውነታችን ገብተው የሚያስከትሉት ጉዳት ማለት ነው። ኢንፌክሽኖች የተለያዩ መነሻዎች ያሏቸው ቢሆንም ዋነኞቹ ግን ወደሰውነታችን የሚገቡትና ሰውነታችን በአግባቡ ኃላፊነቱን እንዳይወጣ ስራውን የሚያስተጓጉሉት ጀርሞች ናቸው።
ጀርሞች ስንል ባክቴሪያዎች ፈንገሶች ፓራሳይቶችና ሌሎችም ሊሆኑ ይችላሉ የሚሉት ዶክተር ሄኖክ፤ እነዚህ ኢንፌክሽን አምጪ ነገሮች መነሻቸው የተለያየ ሲሆን በተለይም ሰውነታችን ውስጥ ገብተው ወረው በሽታን ከማስከተላቸው ጋር በተያያዘ መከሰቻቸውም የቅርብ አካባቢያችን ሊሆን እንደሚችል ያብራራሉ።
ኢንፌክሽን መነሻ ምክንያቶቹ ይለያዩ እንጂ በሰውነታችን ውስጥ ከገቡ በኋላም ቢሆን የተለያዩ የሰውነት ክፍሎቻችንን ሊያጠቃ የሚችል ነው፤ ለምሳሌ ለውጪው ችግር የተጋለጡ የሰውነት ክፍሎች እንደ ቆዳ፣ በጉንፋን አማካይነት የአየር መተላለፊያ ቱቦዎቻችን የበሽታ የመከላከል አቅማችን ሲወረድ ደግሞ የውስጥ አካላቶቻችንን እንደ ጉበት ጣፊያ መግል መያዝ ሊከሰቱ ይችላሉ።
እዚህ ላይ ግን ልብ ሊባል የሚገባው ነገር የሰዎች በሽታን የመከላከል አቅም የሚቀንሱ በርካታ ምክንያቶች አሉ፤ ከነዚህ መካከል ደግሞ የስኳር በሽታ፣ ኤች አይ ቪ ኤድስና ሌሎችም አቅምን ሊያሳጡ ይችላሉ፤ እነዚህ ባሉበት ሁኔታ ደግሞ ጀርሞች ወደሰውነታችን ከገቡ ለኢንፌክሽን የመጋለጣችን መጠን እንዲጨምር ከመሆኑም በላይ ለተባባሰ ችግርም የመጋለጥ እድላችን ሰፊ ነው እንደ ዶክተር ሄኖክ ገለጻ።
ኢንፌክሽን መምጫው ጀርም ይሁን እንጂ የቆዳ ንክኪዎች የሰውነት ፈሳሾች እንደ ምራቅና ሌላም የሰዎችን አይነምድር መንካት የተበከለ ምግብና መጠጥ በመጠቀም በሽታ አምጪ ጀርሞችን የታቀፈ አየርን ወደውስጣችን መሳብ ሊሆን ይችላል ፤ በመሆኑም ኢንፌክሽኖች መምጫቸው ብዙ እንደሆነ ሁሉ ከሰው ወደሰውም ለመተላለፍ መንገዳቸው ብዙ ነው።
በአገራችን በጣም የተለመዱት የኢንፌክሽን አይነቶች የመተንፈሻ አካል ኢንፌክሽኖች ሲሆኑ፤ የሚቀሰቀሱበት ምክንያት እንደ ጉንፋን ሳይነስ ቶንሲልና ሌሎችም የተለመዱ ሲሆኑ በተጨማሪነት የተቅማጥ ህመመም ተከትሎ የሚመጣው የአንጀት ኢንፌክሽን ተጠቃሽ ነው ብለዋል።
እነዚህ የተለመዱ አይነት የኢንፌክሸን አይነቶች ጉዳታቸው ለተባባሰ ችግር የማጋለጣቸው መጠንም እንደ ሰው የሚለያይ ሲሆን፤ በተለይም ህጻናት በተለያዩ ህመሞች ምክንያት በሽታ የመከላከል አቅማቸው የተዳከሙ ሰዎች እንዲሁም አረጋውያንን በተፈጥሮ በሽታን መቋቋም የማይችሉ ሰዎች ላይ ጉዳታቸው የበረታ ይሆናል።
ለምሳሌ በቫይረሶች ምክንያት የሚመጣው የቶንሲል ህመም ብዙዎችን ለተባባሰ ችግር የሚዳርግ እየዳረገም ያለ የህመም አይነት ነው፤በተለይም እንደእኛ በማደግ ላይ ባሉ አገሮች ውስጥ በባክቴሪያ ምክንያት የሚመጣው የቶንሲል ህመም በብዛት የሚስተዋል ሲሆን የሚያስከትለው ችግርም ሰፊ ነው።
ይህ የቶንሲል ህመም ደግሞ በተገቢው ሁኔታ ህክምና ካላገኘ መግል የመያዝ አካባቢውን ሁሉ የማወክ አልፎ ተርፎም መተንፈስ አለማስቻል ይስተዋልበታል። ባስ ሲልም ወደልብ የኩላሊት የመገጣጠሚያ የማጅራት ገትር የነርቭ ህመሞችን ያስከትላል።
በእኛ አገር የኑሮ ሁኔታችን ንጽህናን የመጠበቅ ግንዛቤያችን ብዙም ያደገ ባለመሆኑ በተለይም የቶንሲል ኢንፌክሽን በልጆችም ሆነ በአዋቂዎች ላይ በተደጋጋሚ የሚከሰት በሽታ ነው ያሉት ዶክተር ሄኖክ፤ ይህንን ህመም በአስፈላጊው ልክ መታከም ደግሞ የሚጠበቅ ነው።
ኢንፌክሽን በጣም ህጻናት በሆኑ በሽታ የመከላከል አቅማቸው እጅግ በደከመና በተለያዩ በሽታዎች ውስጥ ባሉ ሰዎች ላይ በአዛውንቶች እንዲሁም በተፈጥሮ በሽታን የመቋቋም አቅም በሌላቸው ሰዎች ላይ አቅማቸው የጠነከረ ነው። በደም ውስጥ ኢንፌክሽን ገባ ማለት ደግሞ ቀን ጠብቆ በመላው ሰውነት ላይ ይሰራጫል ይህ ሆነ ማለት ደግሞ ተሰራጭቶ ከሚሄድባቸው ቦታዎች መካከል አእምሮ ወይም የነርቭ ክፍል ሊሆን ይችላል። በዚህ ጊዜ ደግሞ በታማሚው ላይ ሰውነትን ለማዘዝ ከመቸገር ጀምሮ እንደ ማጅራት ገትር የኩላሊትና የልብ ህመም ሁሉ ሊያስከትል ይችላል ማለት ነው።
ኢንፌክሽኖችን ለመከላከል ትልቁ መደረግ የሚገባው ነገር በአግባቡ የግል ንጽህንን መጠበቅ፤ የምናበስለውን ምግብ በአግባቡ መስራት ለምግብ መስሪያነት የምንጠቀምባቸውን እቃዎች ንጽህናም በተገቢው ሁኔታ ማጽዳት ምግብ በሚቀመጥበት ወቅት በአግባቡና ደህንነቱ በተጠበቀ ሁኔታ መሆኑን ማረጋገጥ ከችግር የሚያድን ሲሆን ሌላውና ወሳኙ ነገር ደግሞ ክትባቶችን መከተብ ነው።
ሰዎች የተለያዩ ህመሞች ሲሰሟቸው ነው ወደህክምና የሚመጡት በዚህን ጊዜ ደግሞ አስፈላጊው የደምና ሌሎች ምርመራዎችን እንዲያገኙ ይደረጋል ከዚህ በኋላ ኢንፌክሽኑ የትኛው የሰውነት ክፍላቸው ላይ ነው ያለው የሚለውን በአግባቡ ከተለየ በኋላ አስፈላጊውን ህክምናና መድሃኒት በመስጠት ግለሰቡ ካለበት ችግር እንዲያገግም ይሆናል።
ነገር ግን ህመም እየተሰማቸው ወደህክምና ተቋም የማይሄዱ ሰዎች ኢንፌክሽኑ በደማቸው ውስጥ ተሰራጭቶ መላ ሰውነታቸውን እንዲቆጣጠረው ከዛም አለፍ ሲል የተባባሰ የጤና ችግር ውስጥ እንዲገቡ ምክንያት ሊሆን ስለሚችል ማንኛውም ሰው ምንም ዓይነት ህመም ሲሰማው በፍጥነት ወደህክምና ተቋም ቢሄድ መፍትሔው ቀላል መሆኑን ዶክተር ሄኖክ ያብራራሉ።
በሌላ በኩል ሰዎች አመመኝ በሚል ሰበብ ብቻ ተገቢውን ምርመራ ሳያደርጉ ምንም ዓይነት ጸረ ተዋህሲያን (አንቲባዮቲክ) መድሃኒቶችን መውሰድ የለባቸውም። ምክንያቱም ጸረ ተዋስያን (አንቲባዮቲክ) መድሃኒቶች ተደጋግመው በተወሰዱ መጠን የማዳን ሃይላቸው እየተዳከመ ከመምጣቱም በላይ አላስፈላጊ ችግር ውስጥም የሚያስገቡ በመሆናቸው ከፍተኛ የሆነ ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል።
ከሁሉም በላይ ሰዎች ጤናማ ኑሮን መኖር ከፈለጉ የግልና የአካባቢን ንጽህና በአግባቡ መጠበቅ የግድና መሰረታዊ መሆኑን ዶክተር ሄኖክ መክረዋል።
እፀገነት አክሊሉ
አዲስ ዘመን የካቲት 25 ቀን 2015 ዓ.ም