
ሀናን ማሕሙድ ትባላለች የባቡልኸይር የበጎ አድራጎት ድርጅት መሥራችና ሥራ አስኪያጅ ናት:: የተወለደችው ሸኖ ከተማ ሲሆን ያደገችው ደግሞ ሸኖ እና አዲስ አበባ መሳለሚያ አካባቢ ነው:: እናቷ ሸኖ ከተማ ላይ በበጎ ሥራ የሚታወቁና ከራሳቸው በላይ ለሌሎች ይጨነቁ እንደነበር ታስታውሳለች፤ ይህም አሁን ላለችበት የበጎ ሥራ ተፅዕኖ እንደነበረው ታስባለች:: የዛሬው የማርች ስምንት ልዩ ዕትም እንግዳ አድርጓታል።
አዲስ ዘመን፡- ባቡል ኸይር እንዴት ተመሠረተ?
ወ/ሮ ሀናን፡- ባቡል ኸይር የተመሠረተው በምኖርበት አካባቢ ባጋጠሙኝ የአስራ ሦስትና የአስራ አራት ዓመት ዕድሜ ያላቸው ሁለት ሴት ታዳጊዎች ምክንያት ነው:: እነዚህ ታዳጊዎች ሁልጊዜ ሳያቸው ከብዙ ጎረምሶች ጋር ምግብ ቤት እየገቡ ይመገባሉ:: ሁሌም ሳያቸው ይገርመኛል ምክንያቱም የትምህርት ቤት ዩኒፎርማቸውን እንደለበሱ ነው የማያቸው በዛ ላይ በዕድሜም ትናንሾች ናቸው::
አንድ ቀን ግን ዛሬ ልጠይቃቸው ይገባል ሳልጠይቅ የማልፈው ነገር አይደለም በሚል ጠርቼ እናንተ በትምህርት ሰዓት ዩኒፎርማችሁን ለብሳችሁ ከዚህ ሁሉ ጎረምሳ ጋር ምንድነው የምታደርጉት? ስላቸው “ከቤት ምንም ሳንቀምስ ነው የወጣነው እናታችን የሆነ ነገር ይዤ እጠብቃችኋለሁ እያለችን ነው ሁሌም ከቤት የምንወጣው” አሉኝ::
ይህን ስሰማ ምንም ነገር ሳናደርግላቸው እነሱ ላይ መፍረዱ ከባድ ስሜት ፈጠረብኝ:: ወቅቱ ገና ሁለት ሴት ልጆችን የወለድኩበት ስለነበር ኢንሻላህ ዕድሜ ከሰጠኝ ሰዎችን በእኩልነት ምንም ነገር ሳይጫንባቸው በፍትሕ የምመግብበት የመመገቢያ ጣቢያ እከፍታለሁ ብዬ ዘየድኩ:: በዛች ቀን ነበር ባቡል ኸይር የታሰበው::
አዲስ ዘመን፡- አመሠራረቱስ እንዴት ነበር?
ወ/ሮ ሀናን፡- በየወሩ የምንገናኝበት የጓደኞች ኅብረት ነበረን፤ ለእነዛ ጓደኞቼ በእኔ የተራ ቀን የገጠመኝን ነገር ነገርኳቸው:: ያገኘኋቸው ታዳጊዎች አንዷ ሙስሊም ናት ሂጃብ አርጋለች፤ አንዷ ክርስቲያን ናት መስቀል አርጋለች፤ አንድ ነገር ማድረግ አለብን ሰው እየተራበ ነው ብዬ ነገርኳቸው:: በዛን ሰዓት ደግሞ የትምህርት ቤት ምገባ አልተጀመረም ነበርና ተማሪ ተራበ ተማሪ እንዲህ ሆነ የሚባል ነገር በጣም እንሰማ ነበር::
እነሱም አዘኑ አለቀሱ ሀሳቤንም በደስታ ተቀበሉ:: ሁሌ ስለጫማ ስለ ቦርሳ፣ ስለመጋረጃና ሌሎች ጉዳዮች ብቻ እያወራሽ አትዘልቂውም ሕይወት የሚባል ነገር አለ ቀብር የሚባልም ነገር አለ:: ተስማሙ እኔም ሳገባ ከቤተሰቦቼ የተሰጡኝ የማልጠቀምባቸው ትልልቅ ወርቆች ነበሩኝ እነሱን አምጥቼ ሰጠሁ፤ ሌሎቹም እንደዛው ወርቃቸውን ግማሾቹም ያላቸውን ነገር አዋጡና ባቡልኸይር ተጀመረ::
አዲስ ዘመን፡- የባቡልኸይር የበጎ አድራጎት ድርጅት ምን ያህል ጊዜ ሆነው፤ ምን ምን ተግባራትንስ እያከናወነ ይገኛል?
ወ/ሮ ሀናን፡- የባቡልኸይር የበጎ አድራጎት ድርጅት ከተመሠረተ አምስት ዓመት ሆኖታል፤ ሲመሠረት አንድ መቶ ሃያ ስድስት ሰዎችን በመመገብ ነበር የጀመረው። ምገባውን ለመጀመርና በምገባው መካተት ያለባቸውን ሰዎች ለመለየት ሁለት ወር ፈጅቷል፣ የመጀመሪያ ቀን ወንበር አልነበረንም፣ ድንኳን አልነበረንም እንዲሁ ነበር ሸራ አንጥፈን ስንመግብ የነበረው እንዲህ እንዲህ እያለ በ126 ሰው የተጀመረው አገልግሎቱ ዛሬ ላይ 5ሺህ ሰዎችን መመገብ የሚችልበት ደረጃ ላይ ደርሷል::
አሁን ላይ ከምገባ በተጨማሪ አቃቂ ቃሊቲ ላይ ትልቅ የሥልጠና ማዕከል አለን፤ በልብስ ስፌት እና በጫማ ሥራ፣ በኮምፒውተርና በቋንቋ፣ በምግብ እና ሌሎችም ዘርፎች ሥልጠና እንሰጣለን። ሥልጠናዎቹን በተለይም በእርግዝና ምክንያት ከቤተሰብ ተባረው ለወጡ፣ በልጅ ምክንያት መማርና መሥራት ላልቻሉ፣ በትምህርታቸው ትልቅ ደረጃ ደርሰው በሱስና በተለያየ ምክንያት ጎዳና ለወጡ ሴቶች ሥልጠናውን እንሰጣለን።
በወረዳው አማካኝነት ለሚመጡ እንዲሁም የምገባ ማዕከሉ ተጠቃሚ የሆኑ ወጣት እናቶች በሥልጠና ማዕከል ውስጥ በገነባነው የሕፃናት ማቆያ ልጆቻቸውን አስቀምጠው ሥልጠናውን እንዲወስዱ እያደረግን ይገኛል:: በእስልምና እርጉዝ ሴትንና የምታጠባ ሴትን ምግብ መከልከል አይቻልም። ከምገባው ባሻገር ሠርተው እንዲበሉ ለእነሱ ቅድሚያ እንሰጣለን::
ከወረዳው ብቻ በየስድስት ወሩ 30 ሥራ አጥ ሴቶችን እንቀበላለን አብዛኞቹ በትምህርት ውጤት ያልመጣላቸውና ከስደት ተመላሾች ናቸው:: ሥልጠ ናውን ጨርሰው ሲመረቁ ደግሞ በሠለጠኑበት ሙያ ላይ የተሰማሩ ድርጅቶችን ኃላፊዎች በመጋበዝ የሥራ ዕድል እንዲያገኙ እናመቻቻለን፤ በዚህም ለብዙ ተመራቂዎች የሥራ ዕድል እንፈጥራለን::
ለጋርመንት አስር ሰው እቀጥራለሁ የሚል አለ፣ ሃያ ሰው እቀጥራለሁ የሚል አለ፣ ለኮምፒውተር ሠራተኛ እፈልጋለሁ የሚል አለ:: በአብዛኛው ምርቃታቸው ላይ ሥራ የማግኘት ዕድል አላቸው እስካሁንም አልሀምዲሊላህ 547 ዜጎችን ማብቃት ቀላል አይደለም:: ከእነዚህ ሠልጣኞች 80 በመቶው ሴቶች ናቸው ወንዶችን ማሠልጠን የጀመርነው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ነው፤ ሥልጠናውን የምንሰጠው አካል ጉዳተኛ ለሆኑ ብቻ ነው::
በተጨማሪም ከእኛ ጋር አምስት ዓመት የቆዩ ማንም ለሌላቸው የካንሰር ታማሚዎች ዘመናዊና ምቹ ማቆያ ገንብተን ለሕክምና ክትትል ሆስፒታል እየወሰድን የማስታመም ሥራ እንሠራለን::
አዲስ ዘመን፡- በጎ አድራጎቱ በሥልጠና ካበቃቸው ሴቶች ትልቅ ደረጃ ላይ ደርሰው እንደ ምሳሌ የሚጠቀሱ ይኖሩ ይሆን?
ወ/ሮ ሀናን፡- ብዙ አሉ! አሁን እንኳን ከመጨረሻዎቹ ተመራቂዎች አንዷ ሰበታ አካባቢ የራሷን ጋርመንት ከፍታ እየሠራች ትገኛለች፣ ከዛ በፊትም የተመረቀች ልጅ እንዲሁ ጋርመንት ከፍታ በስሯ 20 ሠራተኛ ቀጥራ እየሠራች ነው:: አብዛኞቹ የራሳቸውን ሥራ ነው የሚሠሩት።
በነገራችን ላይ ሥልጠናው የሙያ ብቻ ሳይሆን ”የማይንድ ሴት”፣ የገንዘብ አጠቃቀምና መሰል ሥልጠናዎችን ያካተተ ነው:: አንዳንዴ ከስደት ተመላሽ ሴቶች ሥልጠናውን ሲያገኙ “ምነው ቀድመን ይሄን ባወቅን ኖሮ እኛም ተጠቅመን ሀገራችንንም እንጠቅም ነበር” ብለው ይፀፀታሉ::
ሥልጠናው አሠልጥኖ ማውጣት ብቻ ሳይሆን እንደሚችሉም ማሳየትን ያካትታል:: ለምሳሌ የሂና ሥራ የሠለጠኑ ሴቶችን በየሠርግ ቤቱ እየላክን ሠርገኞቹ ለሂና ሥራው ሁለት መቶ ብር የሚከፍሉ ከሆነ እነሱን በሃምሳ ብር እንዲያሠሯቸው እናደርጋለን:: በዚህም ልምዱ እንዲኖራቸው በማድረግ ወዲያው የሚለወጡበትን ዕድል እንፈጥራለን።
አንዷ ሠልጣኛችን እንደነገረችኝ፤ በዚህ ሥራ ብቻ በወር እስከ ሃያ ስምንት ሺህ ብር ታገኛለች፤ በየሠርግ ቤቱ እየሄደች ሂና ትሠራለች፤ አሁን ላይ የሂና ጥቅል አውጥታ እየሠራች ነው። ሠልጣኞች የራሳቸውን ሥራ ከጀመሩ በኋላ ምን ማድረግ እንደሚኖርባቸው እናማክራቸዋለን:: ለእኛም ድጋፍ እያደረጉ ያሉ አሉ::
አዲስ ዘመን፡- የካንሰር ታማሚዎችን ማስታመሙስ እንዴት ተጀመረ አሁን ላይ ምን ደረጃ ላይ ይገኛል?
ወ/ሮ ሀናን፡- የተጀመረው ባቡል ኸይር ውስጥ ለምገባ የሚመላለሱ አንዲት እናት ነበሩ። በአጋጣሚ ቤት ይፈርስባቸውና የሚሄዱበት አልነበራቸውም፤ ቤታችን ወስደን እንዳንንከባከብ የምንውለው ቤት አይደለም/በእርግጥ አሁን ላይ የእናቶች ማቆያ የሚሆን ግንባታ ጀምረናል / እንደነዚህ ያሉ በጣም የከፋ ችግር ውስጥ ያሉ ሰዎች ቢያንስ ታክመው የሚውሉበት ቦታ ማቋቋም አለብን ብለን ቤት ተከራይተን ጀመርነው::
ከዛ በኋላ ብዙ የካንሰር ታማሚ እናቶችን ተቀብለን እኛ ጋር ቆይተው የሞቱብንም አሉ:: የካንሰር ሕመም ሕክምናው ከባድ ነው፣ መድኃኒቱ ከባድ ነው፣ ሆስፒታል ማመላለሱም እንደዛው በየሁለት ቀኑ፤ በየቀኑም የሚሄዱ እናቶችና አባቶች አሉ:: እነሱን ለማስተናገድ አገልግሎቱን ጀምረናል፤ ማቆያው እጅግ ዘመናዊ ነው፤ ከበሽታው አኳያ ከመቀመጫ አንስቶ ሁሉም በየግላቸው የሚጠቀሙበትን ቁሳቁስ ያሟላ ነው::
ከተጀመረ ሦስት ዓመት አካባቢ ሆኖታል፤ ግን ለማንም አስጎብኝተነው አናውቅም፤ እኔ በታማሚዎቹ ቦታ ላይ ብሆን በዛ ሁኔታ ውስጥ ሆኜ ሰው ሚዲያ ላይ ቢያወጡኝ ምን ይሰማኛል፤ በእኔ ላይ ሊሆን የማልፈልገውን በሌላ ሰው ላይ ማድረግ ይከብደኛል:: ለእንደዚህ ያሉ ሕመምተኞች ትኩረት መስጠት አለብን እኔን እንደ ሀናን ብትጠይቂኝ ግዴታ ባቡልኸይርን ብቻ መጥታችሁ ጎብኙ አልልም።
ጎረቤቶቻችሁን እዩ የታመሙ፣ ቤት የቀሩ፣ የቅርብ ዘመዶቻችሁን እዩ አብዛኛውን ሰው ስታዩ ወንድሙ ወይ አጎቱ ጥሩ ደረጃ ላይ ይሆንና እሱ ጎዳና ላይ ነው:: የቅርብ ሰዎቻችንን ማየት ስንችልም ነው ችግር የሚፈታው፤ በተለይ አሁን ላይ በደንብ ዘንጦ መጥቶ ራሱ ኑና ቤቴን እዩ ተርቤያለሁ የሚለን ብዙ ነው፤ እነዚህ ሰዎች ዘመድ ነበረኝ ጥሩ ደረጃ ላይ ያለ ግን ስልኬን እንኳን አያነሳም የሚሉን ናቸው:: ነገ እኛም እዛ ሰውዬ ቦታ ላይ ላለመሆናችን ምንም ዋስትና የለንም::
አዲስ ዘመን፡- በጎ አድራጎት ርኅራሄን ይጠይቃል ለዚህ ደግሞ ሴት መሆንሽ ምን ያህል አስተዋፅዖ አድርጓል?
ወ/ሮ ሀናን፡- በጣም ብዙ አስተዋፅዖ አድርጓል፤ ሴት ስትሆኚ የቤትሽን ጉድለት የምታውቂው አንቺ ነሽ፤ አቅሙ ኖሮሽ ራሱ ብዙ ነገር ይጎድልብሻል:: ለምሳሌ ባቡል ኸይር የበጎ አድራጎት ድርጅት ባሉ የኃላፊነት ቦታዎች ላይ በሙሉ ሴቶች ናቸው ያሉት፤ ለዚህም ነው ድርጅቱ ስኬታማ የሆነው ብዬ አስባለሁ:: የእያንዳንዱን ሰው ጉዳይ በጥልቀት ያውቃሉ፣ ስለ አንድ ሰው ብትጠይቂያቸው ሙሉ ታሪኩን ይነግሩሻል::
አዲስ ዘመን፡- ሴቶችን በኃላፊነት ቦታው ላይ በሙሉ የማስቀመጡ ጉዳይ እንዴት ታሰበ?
ወ/ሮ ሀናን፡- እንደነገርኩሽ ሴቶች ብዙ ነገሮችን በጥልቀት ያያሉ፣ አብዛኞች ናቸው፤ ወንድ አያዝንም ማለቴ አይደለም፣ የዚህ በጎ አድራጎት ተጠቃሚዎች 80 በመቶው ሴት ከመሆናቸው አኳያ የመቆርቆር አዝማሚያም ታይባቸዋል::
አዲስ ዘመን፡- ሴት መሆን በራሱ ተጓዳኝ ኃላፊነቶች አሉት ከበጎ ሥራው ጋር እንዴት እያስኬድሽው ነው?
ወ/ሮ ሀናን፡- ኋላፊነቱ ትንሽ ከባድ ነው፤ ቤት ገብተሽ የፈለገ ነገር ቢኖርሽ አያገባኝም ብለሽ አትቀመጪም:: እኔ ባለትዳርና የአምስት ልጆች እናት ነኝ እኔ አብዛኛውን ጊዜ ወይ ባቡል ኸይር ነኝ ወይ ቤቴ ነኝ:: እውነት ለመናገር በማይጠቅም በማይጎዳ ነገር ጊዜዬን አላሳልፍም ።
ጓደኛም ስይዝ ወይ ጠቅላላ እውቀት ኖሮት ከዛ ሰው የምጠቀመው ነገር ካለ፣ ወይ ጥሩ የዲን እውቀት ኖሮት ይሄ ነገር ሀላል ነው፣ ይሄ ነገር ሀራም ነው እንዲህ አርጊ እንዲህ አታርጊ ብሎ የሚመክረኝ ካልሆነ ዝም ብሎ ጊዜውን አልባሌ ነገር ላይ ከሚያሳልፍ ሰው ጋር ብዙም ቁርኝት የለኝም:: ወይ ለባቡል ኸይር ወይ ደግሞ ለቤቴ ነው ጊዜዬን የማጠፋው ስለዚህ በተቻለኝ አቅም አቻችላለሁ፤ ቤተሰቦቼም ይረዱኛል ብዬ አስባለሁ::
አዲስ ዘመን፡- በተለይ ዓላማን ከማሳካት አኳያ ለሌሎች ሴቶች የምታስተላልፊው መልዕክት ካለ ?
ወ/ሮ ሀናን፡- ሴት ልጅ ካሰበችበት ዓላማዋን ታሳካለች:: አሁን ላይ እንደማየው ሴት ልጅ ትዳር ላይ ጠንካራ መሆን አለባት፤ ሕይወት በራሱ የሴት ልጅን ጥንካሬ ይጠይቃል። ቤት ማስተዳደር፣ ልጅ ማሳደግ፣ የቤት አጋዦችሽን ሳይቀር መምራት አንድን ተቋም የመምራት ያህል ነው:: ያ ሳይሆን ሲቀርና ምን አታገለኝ ስትይ ትዳር ይፈርሳል፣
ምንም ጥርጥር የለውም ጠንካራ መሆን ግድ ነው፤ ሕይወትን ካልተጋፈጥን ቶሎ ነው የምንሰበረው፣ መጋፈጥ መቻል አለብን። ደግሞም እኛ ጠንክረን የሠራነው ነገር በእርግጠኝነት ይሳካል:: ብልሆች ነን፣ ሰው መጉዳት አንፈልግም፣ አርቀን ነው የምናስበው፣ እያንዳንዱ ሥራችን በርኅራሄ ውስጥ ነው፣ በአዛኝነት ውስጥ ነው፤ አንድ ሌባ እንኳን እንደሰረቀን እያወቅን ርቦት ይሆናል ብለን እንተዋለን፤ በዛ ውስጥ ደግሞ ጥንካሬ አለ መተዋችንን ትቶ አላህ የሚጨምርልን ነገር አለ::
እኛ ጋር እንዳየሽው ብዙ ወጣት እናቶች ትዳራቸውን ትተው፣ ልጆቻቸውን ለባላቸው ትተው ይወጣሉ፣ እሱም ልጆቹን ትቶ ይወጣል፤ልጆቹም ጎዳና ይወጣሉ፤ ይህ የሚሆነው ደግሞ ትዕግስት ከማጣት፣ ሥራ ላይ ካለመጠንከር ነው። ቤታችንን በጥንካሬ ከመራን በውጪም ስኬታማ ለመሆን አያቅተንም::
ከዚህ ውጪ በዚህ አጋጣሚ ማስተላለፍ የምፈልገው መልዕክት፤ ኑና ባቡል ኸይርን ጎብኙ፤ ዓለም ባንክ ቤተል አካባቢ ለእናቶች ብቻ የሚውል ማረፊያ፣ ማሠልጠኛና ሌሎች ብዙ ነገሮችን ያካትታል ማዕከል እያስገነባ ነው:: 0909969696 የባቡል ኸይር ስልክ ነው፤ ደውሉና በተቻላችሁ አግዙን፤ ብዙ ጊዜ ርዱን ስለማይል ብዙ ሰው ሀብታም ድርጅት እንደሆነ ያስባል፤ ነገር ግን ባቡል ኸይር ምንም ኖሮት ሳይሆን ከልመና ይልቅ ሰው ራሱ በበጎ ፍቃድ ሲረዳ ጥሩ ነው በሚል ሃሳብ የተጀመረ እና የሌሎችን ድጋፍ የሚፈልግ። የማዕከሉ ግንባታ እንዲሳካ ስላለ ሁላችሁም እንድትሳተፉ እንድትረባረቡ ጥሪዬን አቀርባለሁ::
ነፃነት ዓለሙ
አዲስ ዘመን ቅዳሜ የካቲት 29 ቀን 2017 ዓ.ም