ጥበቃ ሆኜ ልቀጠር ከሰዓት እስኪሆን እየጠበኩ ነው..የድርጅቱ ህንጻ ደረጃ ላይ ቁጭ ብዬ።
በህይወቴ ተመኝቼ የተሳካልኝ ምን እንደሆነ አላውቀውም። እኔ የነካኋቸው ነገሮች ሁሉ እንዳይሆኑ ሆነው የተበጁ ናቸው። ነገሮች ለምን ሌላው ጋ ሰምረው እኔ ጋ ሲደርሱ እንደማይሳኩ ይገርመኛል። ግን በእድለ ቢስነቴ ያዘንኩበት ቀን የለም። በእርግጥ የምፈልጋቸውን ነገሮች ሁሉ ሳጣ የኖርኩ ሰው ነኝ፣ ግን ያጣኋቸው ነገሮች እንዳያሙኝ ሆኜ የቆምኩ ነኝ። ይሄን ብርቱነቴን እንዴት እንዳገኘሁት አላውቅም። ምናልባት ምርጡ አንተ እንዴት ያለው ነው ተብዬ ስጠየቅ ‹ያ ብዙ ነገሮች አልሳካ ብለውት በሳቅ ውስጥ የቆመው እኔ ነኝ› ብዬ እንድመለስ እግዜር ከርህራሄው ትንሽ ቦጭቆ የሰጠኝ ይመስለኛል።
በህይወቴ እድሌን ሁለት ጊዜ ረግሜዋለው..በብዙ ሳቅ ውስጥ ቆሜ እንባ የተናነቀኝ ያኔ ነው እላለው። የመጀመሪያው አባቴን በሞት ሳጣው ነው። አባቴ ታሞ አልጋ ላይ እያለ ዩኒቨርሲቲ ልገባ የሁለት ቀን እድሜ ነበር የቀረኝ። የህይወቴ ትልቁ ጸሎቴ አባቴ ድኖ ማየት ነበር። ግን ዩኒቨርሲቲ በገባሁ በማግስቱ አባቴ ማረፉ ተነገረኝ። አባቴ ከመሞቱ ከደቂቃዎች በፊት የኔን ስም እየጠራ..‹ልጄን ጥሩት፤ አይቼው ልሙት› እያለ እንደነበር ከብዙ ጊዜ በኋላ ነው እናቴ የነገረችኝ። አባቴ ሳያየኝ..የነፍሱን የመጨረሻ ሰዓት ሳላስተውል ተለየኝ።
አባቴን ቀብሬ መቼም ይደርስብኛል ብዬ ባላሰብኩት ብቸኝነትና መከራ ተከብቤ ወደ ዩኒቨርሲቲ ተመለስኩ።በዛ ስብራቴ ውስጥ ሂሩት ከምትባል ልጅ ጋር ተዋወኩ። እድሌን የረገምኩበት ሁለተኛው ምዕራፍ ከዚህ ይጀምራል። ከአባቴ ሞት በኋላ ለብቻዬ የምቀመጥበት አንድ የብቸኝነት አለም ነበረኝ።እዛ አለም ላይ እኔ ብቸኝነቴና እድለ ቢስነቴ ብቻ ነበርን።በዚህ መከራ ውስጥ የሚጎዳኝ ሌላ ሰው ይገባል ብዬ አላሰብኩም ነበር።በዚህኛው እኔ ውስጥ የምትገባ ሌላ ነፍስ ትኖራለች ብዬ አልገመትኩም ነበር።ህልምና እውኔ ተደበላልቀውብኝ ከሰው ልጅ ሁሉ ሌላ ነበርኩ።የምድር ቆይታዬን አጠቃላይ ጉዳት እያስተናገድኩ እንደሆነ ስለማምን ከዚህ በኋላ የሚጎዳኝ ሰውም ሆነ የምጎዳበት አጋጣሚ የለም ብዬ በማመን ውስጥ ነበርኩ።ግን ሂሩት የምትባል ሴት ገባችበት።
የብቻዬ አለም ውስጥ ሽንጠ ረጅሙን ህንጻ ተደግፌ፣ ዛሬም ድረስ በማስታውሳት እንዴት ከወዳጆቿ ተለይታ እዛ ቦታ ብቻዋን እንደቀረች እርግጠኛ ባልሆንኩባት ብሎኬት ላይ ተቀምጨ እኔ አባቴና እናቴ የነበርንበትን የወዲያ አለም እዳስሳለው። ከዛ እምባ..ከዛ ስብራት..
በዚህ የቀን ሙሉ ትካዜዬ ውስጥ ከተደገፍኩት ህንጻ አናት የተማሪዎች ኮቴና ድምጽ፣ ሳቅና ቧልት ይሰማኝ ነበር። የሆነ ሰዓት ላይ፣ በሆነ በተመጠነ እርምጃና እንቅስቃሴ ወደዚያ ወደዚህ ስል የምሰማው አንድ ኮቴ ነበር።በሆነ ሁናቴ የሚራመድ ሰበር ሰካ..ማቅ በለበሰች በነፍሴ ነፍስ ውስጥ የሚያረብብ ዳና አንዱ ትውስታዬ ነበር። ይሄ ኮቴ ጠዋት ወደ ክፍል ሲገባ ረፋድ ከክፍል ሲወጣ እንደገናም ከሰዓት ክፍል ገብቶ ሲወጣ ለነፍሴ እጅግ የቀረበ ዜማ ሆኖ ተለማመድኩት። አንድ ቀን..ተክዤ በተቀመጥኩበት ይሄው ኮቴ ካለሁበት መጣ።ምንም እንዳይማርከኝ ሆኜ ለመኖር የተሰናዳሁ ሰው ነበርኩ…ለዛ ኮቴ ቀና ስል ከአንዲት ጠይም ሴት ጋር አይን ለአይን ተጋጨሁ።
ምንም አይነት ቅጥያ ሳትጨምር ‹ሂሩት እባላለው› ስትል እጇን ዘረጋችልኝ።
‹ናሆም› ስል እጆቿን በመጨበጥ መለስኩላት። እውነት እላችኋላው በዛ ቅጽበት የተሰማኝ አዲስነት ነበር።የአንዲት ሴት እጅ በዘላለሜ ውስጥ በትካዜ ላኖረው ቃል የገባሁለትን እኔን ሲቀይረው መኖር ትርጉሙ ጠፋኝ። በዛ ቅጽበት ከእንግዲህ አትረባም ያልኩት እኔ ተስፋ ሲያለመልም ህይወት ድንግርግር አለችኝ።ያ እጅ ሁሌ የምሳለመው የካህን እጅ ሆኖ ልቤ እንዲቀመጥ ለራሴ ቃል ገባሁ።ያ እጅ እንዳይጥለኝ..ከአባቴ እጅ ቀጥሎ በመተማመን ወደህይወት ደባለኩት።እንዲያ ባለው አጋጣሚ ከሂሩት ጋር ተዋወቅን።እኔ ከተወችኝ ለሞት በሚያበቃ ስሜት ወደድኳት..እሷ ግን እንዲያው ነበረች። መሻሬን ስታውቅ ችላ አለችኝ።
ልቧን ካራራው ብዬ አንድ ቀን እንደማፈቅራት ነገርኳት። ለምን እንደቀረበችኝ ግልጽ ባለ አማርኛ እንዲህ ስትል አስታወቀችኝ..‹የቀረብኩህ አሳዝነህኝ ነው..ሁሌ ወደክላስ ስገባና ከክላስ ስወጣ ብቻህን አዝነህ ሳይህ የሆንከው ነገር እንዳለ በመረዳት ነው የቀረብኩህ..እኔ አሁን ላይ ለፍቅር ዝግጁ አይደለሁም› አለችኝ።ከአባቴ ሞት ቀጥሎ በሂሩት ተሰበርኩ። አባቴንና ሂሩትን ሳስብ ሁለት ሞትን ሞቼ ሰው የሆንኩ ያህል ይሰማኛል።ከዛ በኋላ ባሉት ጊዜያቶች ውስጥ እድሌ እየካበ ሲንደኝ፣ እየጠገነ ሲሸርፈኝ አሁን ካለሁበት ደረጃ ላይ አድርሶኛል።
ከተመረኩ ሶስት አመት አልፎኛል..የሄድኩባቸው አንዳቸውም ድርጅቶች ስሜን ለጥፈውት አላየሁም። በእርግጥ ውጤቴም እዚህ ግባ የሚባል አይደለም ግን ደግሞ ከኔ ያነሰ ውጤት ያላቸው ወዳጆቼ ስራ ተቀጥረው አይቻለው። ከኔ በቀር ሁሉም ጓደኞቼ በስራ አለም ላይ ናቸው። ሁለት ጓደኞች ብቻ አሉ እንደ እኔ በጡረታ የተገኘ የእናታቸውን እንጀራ እየበሉ ቤት የተቀመጡ። እኔስ በእድለቢስነቴ ነው ስራ ያጣሁት የእነሱ ግን ጥጋብ ነው..አዲስ አበባ ውስጥ ያልገቡበት የስራ ቦታ የለም።ግን ከወር በላይ መቆየት አይችሉም። መጀመሪያ የጽሁፍ ማስጠንቀቂያ ይሰጣቸዋል..ከዛ በሳምንቱ የማስጠንቀቂያ ደብዳቤ ይደርሳቸዋል፣ በዛው ሳምንት መሰናበቻ ደብዳቤ ይደርሳቸዋል። አመላቸው ጉድ ነው።እነሱን ሳይ ከኔም የባሰ እድለቢስነት አለ እንዴ እላለው።ሁሉም በራሱ አጋንት ውስጥ ነው..
ከሶስት አመት ስራ ማጣት በኋላ ጥበቃ ሆኜ ልቀጠር ከህንጻው መግቢያ ደረጃ አንዱ ላይ ተቀምጬ ከሰዓት እስኪሆን እጠብቃለው።ጥበቃ ሆኜ ማለፌም ይገርመኛል..እድለቢስነቴ ከላዬ ላይ ጮሆ ሊወጣ እያጣጣረ ይመስለኛል።አባቴን ያሳጣኝና ሂሩትን የነጠቀኝ እድለቢስነት ከዚህ በኋላ ቢወጣ ባይወጣ ምን ሊጠቅመኝ ስል በውስጤ እመልሳለው።ደረጃው ላይ ተቀምጬ ኮቴ ሰማሁ.. ቁልቁል የሚወርድ ኮቴ።የጫማው ኮቴ ደረጃው ላይ ሲያርፍ የሚፈጥረው ስሜት እድለቢስነቴን አስረሳኝ።የማን እግር ይሆን እንዲህ በተዋበ እርምጃ የሚረግጥ? የማን ጫማ ይሆን እንዲህ ባማረ አካሄድ ዜማ የሚፈጥር? እያልኩ ወንድ ይሁን ሴት በማላውቀው ሰው ርምጃ ተደንቄ መጠበቅ ጀመርኩ።
ኮቴው እየቀረበኝ መጣ..ከላይ የሚወርድ የሆነ ሰው እንደሆነ ተገለጠልኝ።ኮቴው እኔ በተቀመጥኩበት የደረጃ መረማመጃ ላይ ሲደርስ ሴት መሆኗን ተረዳሁ..ደስ የሚል ጠረን የቀላቀለ ሴትነት ከላይ ወደታች ተዋሃደኝ። ለመተላለፊያ እንዲሆናት ስል ሰፋ አድርጌ ከያዝኩት ቦታ ነቅነቅ ብዬ ጥጌን ያዝኩ። ደስ በሚል እርምጃ በአጠገቤ አለፈች። አይኔ ጀርባዋ ላይ አረፈ..ሂሩት ነበረች ብል ማን ያምነኛል? አዎ ሂሩት ነበረች.. እንዳልከተላት የሚያደርግ ለሶስት አመት የታመቀ ቅያሜ ነበረኝ..ከተቀመጥኩበት ተነስቼ መጨረሻዋን አየሁት። መጨረሻዋ ውጪ ቆማ ከምትጠብቃት ቀይ መኪና ውስጥ መግባት ነበር።በመኪናዋ ስትሄድ አየኋት..
ድርጅቱ የአባቷ ነበረ..ለጥበቃ ከተወዳደሩት ስም ዝርዝር ውስጥ የኔን ስም ተመልክታ ልታገኘኝ እንደመጣች ተነገረኝ..
የድርጅቱ ስራ አስኪያጅ ነበረች..የመጀመሪያ ቀን ዩኒፎርም ለብሼ በጥበቃነት በር ላይ እንደቆምኩ ከሳምንት በፊት ያየኋት ቀይ መኪና ወደግቢው ስትገባ በር ከፈትኩ። ሂሩት ናት..አላወቀችኝም።አንድ አይነት ለብሼ፣ ኮፍያ አድርጌ..አላየችኝም።
ነፍሴ ተጨነቀች..ስራውን ልተው አልተው በሚል ሃሳብ ቀን ሙሉ ዋልኩ።ለማፈቅራት ሴት ድርጅት ጥበቃ ሆኖ መስራት..ምንም ይሁን እሰራለው ስል ወሰንኩ።
የሆነ ቀን ሂሩት አወቀችኝ..
ወንድነቴ ውስጥ እኔ የማላውቀው ዲያቢሎስ ያለ ይመስለኛል።
በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵ)
አዲስ ዘመን የካቲት 24/2015