ወደ ርእሰ ጉዳያችን ከመዝለቃችን አስቀድመን ቁልፍ ቃላትን እናስተዋውቅ። በዚህ ጽሑፍ ውስጥ “ኃላፊነት” በስነምግብር ንድፈ ሀሳብ (ethical theory) ስር የሚታቀፈው (Social responsibility) “ማኅበራዊ ኃላፊነት”ና የመሳሰሉት ተዝወታሪ ፅንሰ ሀሳቦች ናቸው። ለተዝወታሪነታቸው ቀዳሚ ምክንያቱ ደግሞ ተዛማጅ፣ ተጠራሪና አብሮ ሂያጅ መሆናቸው ነውና “አንዱን ጥሎ ሌላውን . . .” እንዳይሆን በዚያ መንገድ መሄዱ ስለማያዋጣ ነው።
ይህ የዛሬውን ርእሰ ጉዳይ ይዘን ስንነሳ ጉዳዩ እንደው በቀላሉ፣ በዋዛ ፈዛዛ ሊኬድበት የሚቻል እንዳልሆነ፤ “ሙዝ ላጥ ዋጥ” አለመሆኑንም አውቀን ነው፡፡ ለሰነፍ ጸሐፊም አልጋ ባልጋ እንዳልሆነም ገብቶን ነው፤ እንደ ሌሎች ርእሰ ጉዳዮች ለተሳልቆ የቀለለ፣ ለአሽሙርም የከበደ እንዳልሆነ ተረድተን ነው፤ . . . ነው፤ . . . ነው። በመሆኑም፣ ጉዳዩን ብስል ተቀሊል አድርገን እንደሚከተለው ለታዳሚ፣ አንባቢያን ማቅረቡን መርጠናል፤ ችርስ!!!
እንደ ባለፈው አመት የጠገናው ጎሹ ብያኔ ከሆነ፣ ተጠያቂነት (Accountability) በኃላፊነት ተቀብለን የምንፈፅመው ወይም የምናከናውነው ጉዳይ (ሥራ) ስኬታማ ሲሆን ምሥጋና እና ማበረታቻ የሚቸረንን ያህል ኃላፊነትን በአግባቡ ለመወጣት ባለመቻላችን ለሚፈጠረው ጉድለት ወይም ውድቀት የሚቀርብብንን ትችት (ወቀሳ)፣ የሥነ ምግባር ማስተካከያ እና ህጋዊ ወይም አስተዳደራዊ እርምጃ በፀጋና በቅንነት ከመቀበል አልፎ የሚያስከፍለን ዋጋ የሚኖር ከሆነም ለመክፈል ዝግጁዎች ሆነን የመገኘታችንን አስፈላጊነት የሚነግረን ጽንሰ ሃሳብ ነው።
እኛም እናክልበት፤ ተጠያቂነት ኃላፊነትን መውሰድ ነው፣ ተጠያቂነት ኃላፊነትን መሸከም ነው። ተጠያቂነት ለጠፋው፣ ለወደመው፣ ላልተሠራው፣ መሆን እያለበት ላልሆነው፣ መሆን እየሌለበት ለሆነው ወዘተርፈ ሁሉ “… ተጠያቂው እኔ ነኝ” ብሎ እራስን ለፍርድ ማቅረብ ነው። ተጠያቂነት፣ በማርኪስዝም- ሌኒኒዝም ቋንቋ ሂስን መዋጥ (“እከሌ ሂሱን ውጧል” እንዲል የዘመነ ደርግ ታሪክ) ነው። ተጠያቂነት ከሁሉም በላይ ለራስ ታማኝ ሆኖ ለደረሰው ሁሉ ሙሉ ሀላፊነትን ወስዶ ራስን ማጋለጥ፣ አጥፍቻለሁ፣ አውድሜያለሁ፣ ዘርፌያለሁ፣ የተሰጠኝን ስልጣን ለግል ጥቅሜ አውያለሁ ብሎ መናዘዝ ነው። ተጠያቂነት በሕግ የበላይነት ማመን ነው!!!
ተጠያቂነት ከስግብግብነትና ንዝህላልነት ፅድት ያለ፤ ተጠያቂነት ሁሌ ሰንካላና ሽባ ምክንያቶችን ከመደርደር፤ የእናቴ ቀሚስ አደናቀፈኝን የማይቀበል . . . የላቀ መስዋእትነትን የሚጠይቅ ተግባር ነው። ተጠያቂነት . . . ብዙ ነገር ማለት ነውና ጉዳዩ እዳው ገብስ አይደለም እያልን ነው። ( እኛም፣ ፈረንጆቹ ኃላፊነቱ የማን እንደ ሆነ “who is responsible?” እንደሚሉት ሁሉ ለዚህ ነው “ተጠያቂው ማን ነው?” በማለት ሳናውቅ በስህተት ሳይሆን፣ ስናውቅ በድፍረት የገባንበት። ግን፣ ግን . . . ለዚህ ሁሉ አገራዊም ሆነ አህጉራዊ፣ ወይም አለማዊ ትርምስ፣ ኢኮኖሚያዊ ውድመት፣ ከሁሉም በላይ ለሆነው ሰብዓዊ ቀውስና የሕይወት መጥፋት . . . ተጠያቂው ማን ነው???)
ተጠያቂነት ልክ እንደ መሞገስ ሁሉ መወቀስንም እልል………… ብሎ የመቀበል ፍላጎትና አቅምን ይጠይቃል። ተጠያቂነት የመሪነት ተግባርና ሀላፊነት ነውና ለህዝብና ለሀገር መቆርቆርን የግድ ይላል (ያ ካልሆነ ኃላፊነትን ለመውሰድ አቅም ስለማይኖር)፣ ተጠያቂነት ከኃላፊነት፣ ተጠያቂነት ከእምነት፣ ተጠያቂነት ከአርአያነት . . . ጋር ሳይቀር ትስስሩ ጥብቅ ነው።
ተጠያቂነትን ለመውሰድ የሞራል ልእልናን መላበስ ያስፈልጋል። ከተጠያቂነት ፊት ለመቆም የማይበገር ጀግንነትን የግድ ይላል። ተጠያቂነትን ለመቀበል የመንፈስ ጥንካሬን ይፈልጋል። ተጠያቂነትን ለመውሰድ የተሟላ ሰው መሆንን አጥብቆ ይሻል። ተጠያቂነትን ለመውሰድ በራስ መተማመንን የመፈለጉን ያህል፣ ተጠያቂነትን አለመውሰድ ከሰብእና የመውደቅ ልዩ ምልክት ነው። ተጠያቂነትን ለመውሰድ በራስ ላይ የተሀድሶ ፕሮግራም ማካሄድን ይፈልጋል። ተጠያቂነትን ለመውሰድ ኃላፊነትን ይፈልጋል። ኃላፊነትና ተጠያቂነት በአግባቡ ሥራ ላይ የሚውሉበት ሁኔታ የተመቻቸ ይሆን ዘንድ ተግባርን ይፈልጋል። እንቀጥል . . .
ተጠያቂነትን ለመውሰድ የለየለት ዲሞክራት መሆንን ይጠይቃል። ተጠያቂነትን ለመውሰድ ለሺህ ዘመናት እግር ከወርች አስሮ ከያዘን የከፋ ድንቁርና፣ አስከፊ ድህነትና ረሀብ፤ የእርስ በ’ርስ ተላልቆ . . . ለመገላገል ሀሞተ ኮስታራ መሆንን ሁሉ ይጠይቃል። ተጠያቂነትን መውሰድ ከፖለቲካ ክስረት ለመዳን የሚደረግ ብርቱ ጥረት ነውና ሰው ተኮር ርእዮትን ይፈልጋል። ተጠያቂነትን ለመውሰድ ከአድርባይነትና ሌብነት ተፋ’ቶ የፀረ-ሙስና ትግሉ አካል መሆን ያስፈልጋል። ተጠያቂነትን ለመውሰድ የፈሪሀ እግዚአብሔር በልብ መኖር የግድ ነው። (አሁን ጥያቄው፣ “እነዚህ ሰብእናዎች አሉ ወይ?” ነውና ጉዳዩ ያነጋግራል፤ ያወያያል . . . )
ተጠያቂነት ለደረሰው ውድመት፣ ድቀት፣ ለተፈፀመው ወንጀል፣ ሙስና . . . ሁሉ “ተጠያቂው ማን ነው?” ሲባል “እኔ” የማለት ሰብዓዊ ልእልናን ይፈልጋል።
ቀደም ሲል የጠቀስናቸው ጸሐፊ (ጠገናው) “‘በኃላፊነትና በተጠያቂነት አምላክ አትግደሉን፣ አታስገድሉን፣ አታገዳድሉን፣ አታሳዱን፣ አታሰድዱን፣ በርሃብና እርዛት አለንጋ አታስገርፉን፣ ወዘተ’ እያሉ ከመማፀን የባሰ ትውልዳዊ ውድቀት የለም።” በማለት ለንባብና ታሪክ ያበቁትን ሃሳባቸውንም እዚህ ማስቀመጡ ከታሪካዊ ኃላፊነት አኳያ ተገቢ ይሆናልና አድርገነዋል።
ኃላፊነት (Responsibility) እንደ ግለሰብ ወይም እንደ ቡድን ወይም እንደ ማህበረሰብ ወይም እንደ መንግሥት የሚጠበቅብንን ትክክለኛ ጉዳይ (ተግባር) ሁሉ ተፈፃሚ አድርገን የመገኘታችንን እና የማይጠበቅብንን እና ትክክል ያልሆነ ነገር ደግሞ አድርገን ያለመገኘታችንን አስፈላጊነት የሚገልፅ ጽንሰ ሃሳብ ነው።
እንደሚታወቀውና እንደተለመደው ዓለማችን ቅጣንቧሯ በጠፋባት ጉዳዮች ሁሉ መንግሥታት ከእግር ጥፍር እስከ ራስ ጠጉራቸው ድረስ ያገባቸዋል። በመሆኑም፣ “. . . የለሁበትም” ማለት አይቻላቸውም እና፣ በአንድ ሀገር ውስጥ ተጠያቂነት ይሰፍን ዘንድ መስራት የእነሱ ተግባርና ኃላፊነት (ግዴታ) ነውና፣ ሕዝብ “ለደረሰው ውድመት፣ ጥፋት፣ ሰብዓዊ መብት ጥሰት . . . ወዘተ ተጠያቂው ማን ነው?” ብሎ ሲጠይቅ “. . . ተጠያቂው እከሌ ነው።” ማለት የእነሱ ሙሉ ሃላፊነት ነውና፣ የተጠያቂነት ስርአት መዘርጋት የእነሱ ቀዳሚ አጀንዳ ነውና . . . ወደ መንግሥታዊ ሰነዶች፤ በተለይም (አሾልቀንም ቢሆን) ወደ ውስጥ እናይ ዘንድ (አለ/የለም ብለን የምንወዛገብ ካለን) ወደ ራሳችን ሰነዶች እናዝግም።
በየም አማካሪ ተቋም የተዘጋጀው፣ በትግራይ ክልል (የትግራይ ሴቶች ማህበር የማህበረሰብ አገልግሎት መመዘኛ ካርድ (2001 አ.ም)) ሥራ ላይ እንዲውል የተደረገውና “የማህበረሰብ ተሳትፍ ውጤት መመዝገቢያ ካርድ ተመራጭ የማህበራዊ ተጠያቂነት መሳሪያ ነው። . . . ብቃት፤ ጥራት፤ አስተማማኝነትና ቅልጥፍናን” ይለካል የሚለው መመሪያ (ሰነድ) “ተጠያቂነት”ን “ስልጣን ላይ የተቀመጡ ሰዎች የሚያከናውኑት ሥራ (ተግባር) ሁሉ ተጠያቂ የሚሆኑበትና ኃላፊነትን እንዲወስዱ የሚገደዱበት ሂደት (ሥርዓት) ነው።” ሲል ይፈታዋል። (ያነሳነው ችግር መሬት ላይ ስለመኖሩ አንዱ ማሳያ መሆኑን ልብ ይሏል።)
“ማህበራዊ ተጠያቂነት”ን በተመለከተ ደግሞ ወደ ሀረሪ ክልል ሄደን ሀሳብ እንምዘዝ። በቅርቡ (ከታኅሳስ 7-8/2015 ለሁለት ቀናት) የሀረሪ ክልል ገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ቢሮ በጉዳዩ ላይ ከሚመለከታቸው ጋር ሲመክር “ማህበራዊ ተጠያቂነት ፕሮግራም ትግበራ” ማህበራዊ ተጠያቂነት ዜጎች በማንኛውም ደረጃ በሚገኝ የመንግሥት አገልግሎት ተሳትፎ የሚያደርጉበት ሂደት ሲሆን፤ በተሳትፎውም የመንግሥት አገልግሎት ግልፅ፣ ተጠያቂነት ያለበት፣ ውጤታማ የሆነ፣ መልካም አስተዳደርን በማስፈን የመንግስት አስተዳደር እንዲሻሻል እንደሚያደርግ እና በተጨማሪም የአንድ ሀገር ዜጎች መብታቸውንና ግዴታቸውን በውል እንዲረዱ በማድረግ ንቁና ነፃ የሆነ ዴሞክራሲያዊ ማህበረሰብ መፍጠር” የሚያስችል የተመሰከረለት ብቻ ሳይሆን የተጨበጨበለት አሰራር መሆኑን፤ እንዲሁም፣ “በአጠቃላይ ማህበራዊ ተጠያቂነት የመንግሥት አገልግሎት ከሙስና የፀዳና ውጤታማ እንዲሆን በማስቻል በአንድ ሀገር ውስጥ ሁለንተናዊ ልማት እንዲረጋገጥ ማድረግ” መሆኑም ጮክ ብሎ ይነግረናል። ይህንን የመሰለ ወርቃማ (ሳይንሳዊ) ብያኔ ይዞ “እልል በቅምጤ” አለማለት አይቻልምና እልል በቅምጤ ስንል ቆመን ነው።
“ማህበራዊ ተጠያቂነት ፕሮግራም ዜጎች ችግሮቻቸው እንዲፈቱ ለመንግስት ጥያቄ የሚያቀርቡበት የአሠራር ስርአት ነው” ከሚለንና ጉዳዩን በባለቤትነት ከያዘው፣ ከወደ ገንዘብ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ሹክ እንደሚለን ከሆነ “ፕሮግራሙ መሰረታዊ የአገልግሎት ማሻሻያ ስር ያለ ፕሮግራም ሆኖ ሁለቱን አካላት በማወያየትና ግልጸኝነት በመፍጠር አገልግሎቱን ለማቀላጠፍ በሚያስችል መልኩ የሚፈፀም ተግባር ነው።” ይህ እውነት ከሆነ፣ መሬት ላይ ካለ፤ አሁንም እልል በቅምጤ . . . የማይል ካለ እሱ ራሱ ተጠያቂ ነውና እጁን በማውጣት “እኔ” ሊል፣ ኃላፊነቱን ሊወስድ ይገባል።
ከላይ የጠቀስነውና በየም አማካሪ ተቋም የተዘጋጀው ሰነድ በበኩሉ “ማሕበራዊ ተጠያቂነት ስንል ተጠያቂና ኃላፊነት የሚሰማው አስተዳደርን መገንባት የህብረተሰብ ተሳትፍ ላይ የተመሰረተ አካሄደ ነው።” ሲል ደስ በሚሉ ቃላት ይፈታዋል። አሠራሩንም “ህብረተሰብ ተሳትፎ ቁጥጥር ላይ የተመሰረተ ሲሆን፣ የሚጠቀምበት ዘዴም ማሕበራዊ ክትትል (ቁጥጥር) ና የዜጎችን ሪፖርት በመጠቀም ነው። መመዝገቢያ ካርዱ እንደዜጎች ሪፖርት ሁሉ፣ ማህበራዊና ሕዝባዊ ተጠያቂነትንና ኃላፊነትን ለአገልግሎት ሰጪዎች የሚያስገነዝብ መሣሪያ ሲሆን፤ አካሄዱና መሠረቱ በህብረተሰቡ የታችኛው ደረጃ ላይ የቁጥጥሩን መረብ የዘረጋ ነው።” ይለናል። እንደዚህ ሰነድ ከሆነ “የለሁበትም” ማለት ድሮ ቀረ ማለት ነውና “ሙሽራዬ ቀረ”ን ለመጀመሪያ ጊዜ ደፍራ የዘፈነችው፣ የአበባ ደሳለኝ “. . . የለሁበትም” ዜማ ሥራውን ጨርሶ ከተሰቀለበት ወርዷል ማለት ነውና ደስ ይላል። ካልሆነ ግን አልወረደም ማለት ነውና በሌላ ድምፃዊያን ሊደገምና ሊደጋገም የሚገባው ግጥምና ዜማ ነው ማለት ነው።
ሰነዱ ይህንን ይበል እንጂ፣ ልክ በ2Pac “Brenda’s Got a Baby” ዜማ እንደ ተብጠለጠለው ማህበራዊ ኢ-ፍትሀዊነት (social injustice) ማለት ነው፣ ዘመናችን ነገረ ሥራው ሁሉ ቁርጥ የድምፃዊት አበባ ደሳለኝን “የለሁበትም” አይነት ነው “. . . እኔ የለሁበትም” (ኧረ በፈጠረን፣ ይህንን የአበባ ደሳለኝን ጉደኛና ማህበራዊ ሂስ (Social criticism) ሰጪ ዜማ እናዳምጥና ከዚህ ጽሑፍ ጋር በማያያዝ መታዘብ ያለብንን (እንደ ማህበረሰብም እራሳችንን) እንታዘብ።)
ኪነጥበብ የእውኑ ዓለም ነፀብራቅ ነው እንዲሉ፣ በሴቭ ዩር ጀነሬሽን ኢትዮጵያ እና የባለሙያዎች ህብረት ልማት (ፓዴት) በጋራ ሲያከናውኑት በነበረው “ማህበራዊ ተጠያቂነት ፕሮግራም ሁለት” አማካኝነት ቀርቦ የነበረው፣ በዚሁ ጉዳይ ላይ የሚያጠነጥነውና በምህረት ማስረሻ የተዘጋጀው “ከመጠየው . . .” ቴያትርም በተለያዩ የአገሪቱ ወረዳዎች መድረኮች ለእይታ የበቃው ይህንኑ የሚያረጋግጥ ሆኖ ነው። (እዚህ ላይ የጋሽ መሀሙድን “ማን ይሆን?” እንዳለ ለአድማጭ ትተን መሆኑን ማስታወስ እንፈልጋለን። “ኧረ ማ’ነው . . .?”)
የሰዎችን (ተጠያቂዎችን) ከተጠያቂነት ሽምጠጣ፣ ፍርጠጣና እግሬ አውጭኝ እንደ ጋዜጠኞች አሳምሮ የሚያውቅ ያለ አይመስለኝም። በሚዲያ ቀርቦ የተሠራ ያልተሠራውን፤ የለማ የወደመውን፤ ሀላፊነቱ የ(እነ)ማ እንደሆነ፣ ተጠያቂውስ ማን እንደሚሆን (ሊሆን እንደሚችል) መናገርን እንደ ጦር የሚፈራው ብዛቱ ከሰማይ ኮኮብ፣ ከምድር አሸዋ እንደሚበልጥ የሚያውቁት እነሱ ብቻ ናችው። (ጋዜጠኛን ለነገ ቃለመጠይቅ ቀጥሮ ስልኩን እስከወዲያኛው የሚዘጋውን ባለሥልጣን ቤቱ ይቁጠረው እያልን ነው።)
እየቀጠረ የሚጠፋው፣ ስልኩን እስከ ወዲያኛው የሚጠረቅመው፣ የእጅ ስልኩ ሲያጓራ (እንደ ስልኩ ሁኔታ ሲንጫረር) ባልሰማ ጆሮውን በጥጥ የደፈነው፣ ጠያቂውን እያየ ላለመጠየቅ (በአላየሁም) አንገቱን አዙሮ የጎድን የሚሄደው . . . (ጥራት የለውም እንጂ) ብዛቱ ተቆጥሮ አያልቅም። መረጃ መስጠት ማለት አንገት ላይ ወደሮ ማጥለቅ የሚመስለው፣ ቃለመጠይቅ ማድረግን “በራስ እጅ ራስ ላይ ካቴና ማስገባት ነው” በማለት በእምነቱ የፀናውን ወዘተርፈ ቤቱ ይቁጠረው እንጂ ሌላ ምንም ማለት አይቻልም። የዚህ ሁሉ ድምር ውጤት ደግሞ ከተጠያቂነት ለማምለጥ መሆኑ ሲታሰብ ጉዳዩ እስከ ወዲያኛው ያሳዝናል (ልክ እየሄድንበት እንዳለው መንገድ ማለት ነው)።
ሌላው የሚያሳዝነው የተጠያቂነት አለመኖር በመኖር ይተካ ዘንድ የሚቀረጥፈው በጀት ነው። በሰኔ 2010 ዓ.ም ለአየር የበቃ የኢዜአ ዜና “የኢትዮጵያ ማህበራዊ ተጠያቂነት ፕሮግራም ሁለት ከአየርላንድ፣ ከኦስትሪያና ከዓለም ባንክ በሚገኝ የገንዘብ ድጋፍ ከ2003 ዓ.ም ጀምሮ በአገሪቱ ሁሉም ክልሎች በሚገኙ 223 ወረዳዎች ላይ በአገልግሎት ሰጪዎችና ተገልጋዮች መካከል በመሆን ዜጎች ተገቢውን አገልግሎት እንዲያገኙ የግንዛቤና የሥልጠና ሥራ ሲሠራ ቆይቷል።” (ዜናው “የማህበራዊ ተጠያቂነት ሁለት ከ2003 ጀምሮ ለሰባት ዓመታት ሲተገበር የቆየ ሲሆን፤ ሶስተኛውን ምዕራፍ በ2011 ዓ.ም ለመጀመር በዝግጅት ላይ መሆኑም ተገልጿል።”ም ብሏል) ይህንን “የገንዘብ ድጋፍ” (ብድር ካልሆነ) በየዙሩ ስናሰላና የተጠያቂነት አለመኖርን ድምር ውጤት ስናስብ ነው እንግዲህ የችግሩ ሁለተኛ ጥፋት (ኤሊያስ ተባባል “ገንዘቡም ያልቅና . . .” እንዳለው) ድቅን የሚልብን። ግን ግን፣ ይህ ሁሉ ገንዘብ ወጥቶበት ለውጥ መጥቷልን? (እዚህች ጋ የሰዎቹን ሀሳብ መዋስ ያስፈልጋል – “ይህ ራሱን የቻለ ጥናት ይፈልጋል” የምትለዋን መሹለኪያ ቀዳዳ።)
የእኛ ጥያቄ “ውጤቱስ?” ቢሆንም፣ መልሱን ሳንጠብቅ (ለ“ሆድ ሲያውቅ ዶሮ ማታ” ትተን) ኢትዮጵያ (ከላይ “በሀገሪቱ ሁሉም ክልሎች በሚገኙ 223 ወረዳዎች”ን ልብ ይሏል) ምን ያህል በተጠያቂ አልባነት ተሰንጋ እንደተያዘች በመረዳት ብቻ ወደሚቀጥለው፤ መውጫ በራችን እንጠጋ።
አንተ፣ ወንድምም ሆንክ እርስዎ አዛውንቱ፣ ሌሎቻችሁም፣ “እንዴት ሶስቱ ጎምቱ ተቋማት፣ ሕግ አውጭው (The Legislative)፣ ሕግ አስፈፃሚው (The Executive) እና ሕግ ተርጓሚው (The Judiciary) ባሉበት አገር ተጠያቂነት አፈር ከድሜ ይበላል?” እያላችሁ የምትጠይቁ ሁሉ፣ ይህ ጽሑፍ መልስ የሚሰጥ ባለመሆኑ ከወዲሁ ይቅርታ እየጠየቅን፣ ለምትሰጡን ማብራሪያ ከወዲሁ እስከ ወዲያኛው እናመሰግናለን፤ በማጠቃለያችንም ጉዳዩን እንጠቀልለዋለን።
አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ፣ “ተጠያቂው ማን ነው?” በሚል ርእስ ወደ እዚህ ውይይት ስንገባ “እኔ” በማለት እጁን የሚያወጣ ሰው እናገኛለን ብለን አይደለም። እንደሌለ እናውቃለንና “እኔ”ን አንጠብቅም። የዚህ ጽሑፍ አላማ “እስከ መቼ?”፣ “ተጠያቂ አልባነት እስከ መቼ መደበኛ አሠራር ሆኖ ይቀጥላል?” የሚለውን ማስረፅና አፋጣኝ መፍትሄ ይፈለግ ዘንድ ማሳሰብ ነውና በዚሁ እንሰናበታለን።
ቸር እንሰንብት!!!
ግርማ መንግሥቴ
አዲስ ዘመን የካቲት 16 ቀን 2015 ዓ.ም