ኢትዮጵያን ከዓለም ቀዳሚ ከሆኑ የቱሪዝም መዳረሻ አገሮች መካከል እንድትመደብ በቁርጠኝነት መሥራት ይፈልጋል። ከቅርብ ግዜ ወዲህ መንግሥት ለዚህ ዝግጁ መሆኑን አሳውቆ ከፖሊሲ ማሻሻያ ጀምሮ በርካታ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ። ለተፈፃሚነቱም ሕጎችን በማርቀቅና ስትራቴጂዎችን በመንደፍ ይፋ እያደረገ ይገኛል። ከዚህ ውስጥ ደግሞ ስር ነቀል የአደረጃጀት ለውጥ ማድረግ አንዱ ነው።
እምቅ የቱሪዝም ሃብቶችን በገበያ ልማትና ፕሮሞሽን በማገዝ የጎብኚዎች መዳረሻ እንዲሆኑ ከማድረግ በተጨማሪ አዳዲስ የመስሕብ ስፍራዎችን ማስተዋወቅ ዋንኛ ሥራ ነው። ከዚህ አንፃር በዲጂታል ፕሮሞሽንና በመሰል ስልቶች የቱሪዝም ዘርፉን ለማስተዋወቅ እየተሠራ ነው። ከዚህ ወስጥ መዲናችን አዲስ አበባ ላይም ልዩ ልዩ ሥራዎች እየተሠሩ መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ። ከዚህ ውስጥ በአዲስ ብራንድ ከተማዋን የማስተዋወቅ ስራ ተጠቃሽ ነው።
የኢትዮጵያ መዲና፣ የአፍሪካ ኅብረትና የተለያዩ ዓለም አቀፍ መቀመጫ የሆነችው አዲስ አበባ በተፈጥሮ፣ በቅርስ፣ በታሪክ፣ የማይዳሰሱና የሚዳሰሱ አያሌ የመስሕብ ሃብቶች ባለቤት እንደሆነች ይታወቃል። ከሁሉም በላይ በሆቴልና ሆስፒታሊቲ (ማይስ ቱሪዝም) እንዲሁም በጥቅሉ ለከተማ ቱሪዝም ምቹ ከሆኑ የአፍሪካ መዲናዎች ውስጥ የምትመደብ ነች።
አዲስ አበባ የበርካታ ሐውልቶች፣ ቤተ-መንግሥቶች፣ ሙዚየሞች፣ በከተማው የሚገኙ ፓርኮች፣ የማይዳሰሱ የቱሪዝም ሃብቶች፣ የተፈጥሮ ሃብቶች፣ ዓለም አቀፍና፣ አህጉር አቀፍ ተቋማት፣ የግብይት ቦታዎች፣ የባሕል ምሽት ቤቶች፣ የማይንቀሳቀሱ ቋሚ ቅርሶች የታደለች ከተማ ነች። ይህ ብቻ ሳይሆን በአትሌት ሻለቃ ኃይሌ ገብረስላሴ መሥራችነት 20 ዓመታት በላይ ያስቆጠረው ታላቁ ሩጫ በከተማዋ አዲስ አበባ 10 ኪሎ ሜትር የሩጫ ስፖርት ሌላኛው የቱሪዝም ዘርፉ የመስሕብ ሃብት ነው። የአፍሪካ ኅብረት፣የዓለም አቀፍ ተቋማት መቀመጫ ከ100 በላይ ኤምባሲዎች የሚገኙባት እንዲሁም ከ80 ብሔር ብሔረሰቦች መኖሪያና ወደ 400 የሚደርሱ ቋሚ ቅርሶች መገኛ መሆኗ ለከተማ ቱሪዝም መስፋፋት ተመራጭ ያደርጋታል። የእንጦጦ ተራራ፣ ለተራራ ላይ ሩጫ፣ ለተራራ መውጣት፣ ለአድቬንቸር ቱሪዝም እንዲሁ ምቹነቷን ያረጋግጥላታል።
የአዲስ አበባ ከተማ ባሕል፣ ኪነ ጥበብና ቱሪዝም ቢሮ መዲናዋን የቱሪስት መዳረሻ ለማድረግ እና የአፍሪካ ተመራጭ መዳረሻ እንድትሆን የተለያዩ ተግባሮችን እያከናወነ እንደሚገኝ ይገልፃል። ከዚህ ውስጥ ከያዝነው ዓመት ተጀምሮ ተግባራዊ እየሆነ የሚገኘው “አፍሪቃዊቷ መልሕቅ” (The Vibrant Hub Of Africa) የሚል ስያሜ የተሰጠው የማስተዋወቅ ሥራ ተጠቃሽ ነው። ቢሮው ከዚህ ጋር ተያይዞ እየሠራቸው ከሚገኙ ተግባራት አንዱ በቱሪዝም ዘርፍ ለተሠማሩ አካላት የአዲስ አበባ ከተማን የቱሪዝም ብራንድ ማስተዋወቅ ይገኝበታል።
የከተማዋ የቱሪዝም ብራንድ “አፍሪቃዊቷ መልሕቅ”(The Vibrant Hub Of Africa) በሚል መሰየሙም ይታወቃል። ከዚህ ጋር በተያያዘ የባሕል፣ ኪነጥበብና ቱሪዝም ቢሮ በስሩ ለሚገኙ ለክፍለ ከተማ ባለሙያዎች እና በቱሪዝም ዘርፍ ለተሰማሩ ባለድርሻ አካላት በከተማዋ የቱሪዝም ብራንድ እና በማይስ (mice) ዙሪያ ስልጠና መስጠቱም የሚታወስ ነው።ይህን መረጃ ከወሰድን በኋላ ኃላፊነታቸውን ያስረከቡት የቢሮው የቱሪዝም ዘርፍ ኃላፊ እጩ ዶክተር ደስታ ሎሬንሶ ጉዳዩን አስመልክተው ለዝግጅት ክፍላችን በሰጡት አስተያየት እንደተናገሩት የቱሪዝም ዘርፉ በዕውቀት መመራት ስለሚገባው በዘርፉ ለሚሠሩ ባለሙያዎች የአቅም ግንባታ ስልጠና መስጠት አስፈላጊ መሆኑን አንስተዋል። አዲስ አበባ ያላትን እምቅ ሀብት ለቱሪስቱ ለመሸጥ ከተማዋን በብራንድ ማስተዋወቅ እንደሚገባ ታምኖበት ወደ ሥራ መገባቱን ነግረውናል።
እጩ ዶክተር ደስታ ሎሬንሶ ረዘም ላሉ ዓመታት ኢንዱስትሪውን ያውቁታል። እርሳቸው እንደሚሉት፤ ቱሪስቶች በኢትዮጵያ የመስሕብ ስፍራዎችን ለመመልከት፣ የባሕል ፌስቲቫሎች ላይ ለመገኘት ወደ አገር ይመጣሉ። ከዚህ ጋር ተያይዞ አስጎብኚ ድርጅቶች እና በቱሪዝም ዘርፉ ላይ በሆቴልና ሆስፒታሊቲ ላይ የተሠማሩ ባለድርሻ አካላት ለጎብኚዎች የአገሪቱ መዲናና የአፍሪካ ኅብረት መቀመጫ የሆነችውን አዲስ አበባ እንዲያሳዩ መሠራት ይኖርበታል።
“ከቅርብ ግዜ ወዲህ በከተማዋ እንደ አንድነት ፓርክ፣ እንጦጦ፣ሳይንስ ሙዚየም እና ወዳጅነት ፓርክን የመሳሰሉ የውጪ ቱሪስቶች እንዲመለከቱት መሥራት ያስፈልጋል” የሚሉት እጩ ዶክተሩ፤ በከተማዋ የሚገኙ የኢትዮጵያን ታሪክና ቅርስ የያዙ ሙዚየሞችን ጎብኝተው ከመሄድ ባሻገር የቱሪዝም ምርቶችን እንዲሸምቱና ምጣኔ ሃብቱን እንዲያነቃቁ ማድረግ ተገቢ መሆኑን ያነሳሉ። ለዚህ ደግሞ የአዲስ አበባ ከተማን በአዲስ ምልክት የማስተዋወቅ (ብራንድ) የመፍጠር ተግባር ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ ይገልፃሉ።
የአዲስ አበባ ከተማ ቱሪዝም ዘርፍ የቱሪዝም ማኅበራትን፣ የሆቴል ባለቤቶችን፣ የቱሪስት ትራንስፖርት አሽከርካሪዎችን ስልጠና እየተሰጠ መሆኑን የሚገልጹ እጩ ዶክተሩ፤ እነዚህ አካላት ፍትሐዊ በሆነ ክፍያ፣ በኢትዮጵያዊ ጨዋነትና መስተንግዶ አገልግሎት እንዲሰጡ ምክረ ሃሳብ እንደሚሰጥ ይናገራሉ። ከዚህ ባሻገር አፍሪካዊቷ መልሕቅ የሚለውን “ብራንድ” ቱሪስቶች እንዲያውቁትና ከተማዋን በአዲስ ምልክትና መነቃቃት አስተዋውቆ የቱሪዝም መዳረሻ እንድትሆን ተግባራዊ እንቅስቃሴ ውስጥ እንደተገባ ይገልፃሉ።
“በቱሪዝም ዘርፍ በአመራርነት ላይ እንደመጣሁ አዲስ አበባ ከተማን ‘በከተማ ቱሪዝም’ ምን ዓይነት አቅም እንዳላት ለማጥናት ሞክረናል” የሚሉት እጩ ዶክተር ደስታ፤ በውስጧ ከባሕል፣ ከተፈጥሮ፣ ከታሪክና ከቅርስ አንፃር ያለውን እምቅ አቅም በዝርዝር ለማወቅ ጥረት መደረጉን ይናገራሉ። ከተማዋን ሌሎች አፍሪካ ሀገራት መዲናዎች መስተካከል የማይችሉ መሆናቸውንና አዲስ አበባ በተሻለ የአፍሪካ ዋና ከተማ መሆን የሚያስችላት ታሪካዊም ሆነ ሌሎች በርካታ አመክንዮዎች መኖራቸውን ማረጋገጥ እንደተቻለም ነው የሚናገሩት። የአፍሪካ ኅብረት መቀመጫና የተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት መቀመጫ እንደ መሆኗ ይህንን የቱሪዝም ዘርፉን ለማሳደግ እንደ እድል ለመጠቀም በር ከፋች መሆኑን ይገልፃሉ።
በእነዚህ ገፊ ምክንያቶች “የአፍሪካ መልሕቅ” (The Vibrant Hub of Africa) የሚል ብራንድ እንዲቀረፅና የፕሮሞሽንና የገበያ ልማት ሥራ ተግባራዊ እንዲደረግ ውሳኔ ላይ መደረሱን እጩ ዶክተር ደስታ ሎሬንሶ ይናገራሉ። በመዲናዋ ውሕድ ማንነት ባሕል፣ የብሔር ብሔረሰቦች መቀመጫ፣ የብዙ ክብረ በዓላት፣ ታሪኮች፣ ቅርሶች፣ የዓድዋና የኔልሰን ማንዴላ ሙዚየም ግንባታ ሂደት ጨምሮ በርካታ የመስሕብ ስፍራዎች መኖራቸው ቱሪዝሙን ለማሳደግ እድል የሚሰጥ መሆኑን ይገልፃሉ። የሀገርና አህጉር መልክ ያላት ዋና ከተማዋ ያላትን መልካም እድሎች ተጠቅሞ በብራንድነት ማስተዋወቅ ተገቢ መሆኑን ይናገራሉ።
አዲስ አበባ የአፍሪካ ዋና ከተማ እንደሆነች አፍሪካውያን አንዲገነዘቡትና ከዚያም ባለፈ ልክ እንደራሳቸው ለመላው ዓለም የሚያስተዋውቋት ልትሆን እንደሚገባ የሚናገሩት እጩ ዶክተሩ፤ አዲስ አበባ ወደ ሌሎች የመስሕብ ስፍራዎች የሚሄዱ ጎብኚዎች የትራንስፖርት መሸጋገሪያ ሳይሆን የምትጎበኝና የራሷ መልክ ያላት ከተማ እንድትሆን በሰፊው መሠራት ይኖርበታል ይላሉ። ይህ እንቅስቃሴም በአዲስ አበባ ባሕል ኪነ ጥበብና ቱሪዝም ቢሮ ተግባራዊ እየተደረገ መሆኑን ይናገራሉ።
አዲስ አበባ ውስጥ በርካታ የከተማ ልማት ሥራዎች እየተሠራ መሆኑን የሚናገሩት የቱሪዝም ባለሙያው፤ የፅዳት፣ የአረንጓዴ ልማት፣ የፓርክ፣ የወንዝ ዳርቻ ፕሮጀክቶች ከእነዚህ የልማት ሥራዎች ውስጥ እንደሚካተት ይገልፃሉ። ይሄ ደግሞ የመዲናዋን የቱሪዝም ሃብትነትና ገፅታ በተመሳሳይ እየቀየረው እንደሆነ ይናገራሉ። ይህን ሃብት ይዞ አዲስ አበባን በተለያዩ የኮንፍረንስ ቱሪዝም፣ ሁነቶች፣ ፌስቲቫሎች እንዲሁም ለልዩ ልዩ የኢንዱስትሪው ግብአቶች በማዋልና በማስተዋወቅ መነቃቃት መፍጠር ተገቢ እንደሆነ ይናገራሉ። በዚህም ዓለም አቀፍ ቱሪስቶች ከተማዋን እንደ አንድ የቱሪዝም መዳረሻነት እንዲመለከቷት ማድረግ እንደሚያሻ ይናገራሉ።
ዶክተር ተስፋዬ ዘለቀ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የአገር ልማት ጥናት ኮሌጅ የምርምርና ስርፀት ተባባሪ ዲን ናቸው። በአዲስ አበባ ከተማ ስለ “አካታች” ቱሪዝም ጥናታዊ ጽሑፍ የሠሩም ናቸው። አዲስ አበባን በአዲስ ምልክት ከማስተዋወቅና የመስህብ ሃብቶቹን የማልማትና አዳዲስ መዳረሻዎችን ከመፍጠር ጎን ለጎን በከተማዋ ያለው የቱሪዝም ኢንዱስትሪ እድገት እንዲያሳይ ተግባራዊ ስራዎች መከናወን እንዳለባቸው ምክረ ሃሳብ ይሰጣሉ።
“በአዲስ አበባ ውስጥ እየተነቃቃ ያለውን የቱሪዝም እንቅስቃሴ በዘላቂነት ለማስቀጠልና እድገቱን ለማረጋገጥ የአቅም ግንባታ ሥራዎች ያስፈልጋሉ” የሚሉት ዶክተር ተስፋዬ በዋናነት ግን በታችኛው መዋቅርና መስሕቡ በሚገኝባቸው ወረዳዎች አካባቢ በከፍተኛ ሁኔታ አደረጃጀቱ ሊፈተሽ እንደሚገባ በሠሩት ጥናታዊ ጽሑፍ ላይ አመላክተዋል። ይህን መሥራት ከተቻለ ወጣቶችን፣ ሴቶችና የተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍሎችን አደራጅቶ ከዘርፉ ተጠቃሚ የሚሆኑበትን መንገድ መዘርጋት እንደሚቻልና የከተማዋን የቱሪዝም መስሕቦች በዓለም አቀፍ ደረጃ ማስተዋወቅ እንደሚገባ ምክረ ሃሳባቸውን ይሰጣሉ። ከአደረጃጀት አንፃር መፈተሽ ያለበት ጉዳይን ሲያነሱ ከቅርብ ግዜ ወዲህ የባሕልና ቱሪዝም ዘርፍ መለያየቱንና ይሄም እስከታችኛው የወረዳ መዋቅር ድረስ መውረድ እንደሚኖርበት በማሳያነት ይገልፃል። ይህ ተግባራዊ ከሆነ የአዲስ አበባ ከተማን በብራንድነት ከማስተዋወቅ ባሻገር አካታች የሆነ የቱሪዝም እድገትን መገንባት፣ ምጣኔ ሃብታዊ ተፅዕኖውን ከፍ የማድረግ እድሉ ከፍተኛ መሆኑን ይገልፃሉ።
እንደ መውጫ
ቱሪዝም በበርካታ የበለፀጉ አገራት ቀዳሚ የምጣኔ ሃብት ምንጭ ነው። ይህንን መንግሥታቸው ብቻ ሳይሆን ሁሉም ዜጎች በቅጡ ተገንዝበውታል። ለምሳሌ ያህል ፈረንሳይ (ፓሪስ)፣ ጣሊያን (ሮም)፣ ግብፅ (ካይሮ)፣ ከቱርክ (ኢስታንቡል) እና ሌሎችም ሀገራት ከቱሪዝም እጅግ ከፍተኛ ሃብት በማጋበስ የስልጣኔ መንገዳቸውን አልጋ በአልጋ ማድረግ ችለዋል። ይሁን እንጂ ከቀደም ባሉት ዘመናት ሃብቶቻቸውን ለቀሪው ዓለም በማስተዋወቅ (ለገበያ ምቹ በማድረግ) ሰፊ ትግል አድርገዋል። በተለይ ታሪካቸውን፣ የቀደመ ሥልጣኔን፣ የሕንፃ ጥበባቸውን፣ የተፈጥሮ ሃብቶቻቸውን ለሰሚውም ሆነ ለተመልካቹ ምቹና አዝናኝ እንዲሆን አድርገው አሰናድተዋል። በቱሪዝም ሃብቶች ጥበቃና ልማት ዙሪያም እጅግ አስደናቂ ሥራዎችን ሠርተዋል። አሁንም ድረስ እየሠሩ ይገኛሉ። ይህ አያሌ ጎብኚዎችን እንዲያስተናግዱ፣ የአገር መልካም ገፅታ እንዲገነቡ አስችሏቸዋል። ከምንም በላይ ግን ጠንካራ የምጣኔ ሃብት ባለቤት ሆነዋል። በጭስ አልባ ኢንዱስትሪው የማይነጥፍና የማይጎድፍ ሃብትና ስምን ገንብተዋል። በኢትዮጵያ ዋና መዲና አዲስ አበባም ሆነ በመላው አገሪቱ ተመሳሳይ ተግባር እና ጠንካራ ሥራ ያስፈልጋል።
ዳግም ከበደ
አዲስ ዘመን ጥር 28 ቀን 2015 ዓ.ም