እንደ ትናንቱ ናት.. እንደዛ ቀደሙ። አንገቷ ተሰብሮ፣ አይኖቿ አዘቅዝቀው ከመሬት ተወዳጅተዋል። ቀና የሚያረጋት ክንድ ትሻለች። ግን የነኳት ክንዶች ሁሉ ለዝቅታዋ ምክንያት ሆነው ያለፉ ናቸው።
ሰው ለሌሎች የሚተርፈው ለራሱ ሲበቃ ነው ትላለች ግን በእውነቷ ውስጥ ኖራ አታውቅም። አይደለም ለሌሎች ልትተርፍ ቀርቶ ለራሷ ያልበቃች ምናምንቴ የሆነች ያክል ይሰማታል።
ቀና የምትለው አንድ ጊዜ ነው.. ዝግ ያለ፣ ቀርፋፋ ኮቴ ስትሰማ.. እና ደግሞ ያ ኮቴ የአንድ አዛውንት መሆኑን ስታውቅ። ቀና የምትለው አንድ ጊዜ ነው.. የአዛውንቱ ሰላላ እጅ ፊቷ ላይ ሲያርፍ። ሊያነሳት አቅም የሌለው ጎስቋላ ክንድ ሲተሻሻት።
መኖር መሯት ዝቅ ባለችበት ሰሞን ኮቴ ሰማች። ቀርፋፋ ኮቴ። ዘመን የፈጀ በሚመስል ዝግታ አንገቷን በቀስታ ቀና አደረገች.. በምርኩዝ የሚሄዱ.. ሽበታም ሽማግሌ በተደነቃቀፈ እርምጃ ወደ እሷ ሲያዘግሙ ተመለከተች። እዚህ ጋ ቀና ትላለች.. እዚህ ጋ አድራሻውን የማታውቀው አዲስነት ይዋሃዳታል።
ሽማግሌው ቀና ባለችበት በዘመን ያጌጠ ጎስቋላ እጃቸውን ወጣት ፊቷ ላይ አሳረፉት። ቀና የምትለው አንድ ጊዜ ነው.. እንዲህ እንደ አሁኑ አዛውንት እጃቸው ፊቷን ሲነካው።
‹እንዴት ነሽ? ዝግ ብለው ጠየቋት።
‹ያው ነኝ› ዝግ ብላ መለሰችላቸው።
‹እንደ መቼው?
‹እንደ ትናንቱና እንደዛ በፊቱ›
‹እና አሁንም በሞት ነው የምትጽናኚው..? ጠየቋት።
‹አዎ በሞት ነው የምጽናናው። ማንም ያልሞተውን ሞት መሞት እፈልጋለሁ። መከራዬን በሞት መርሳት ምድር ላይ የቀረኝ የመጨረሻ ሃሳቤ ነው› ስትል ተናገረች።
አዛውንቱ ዝም ብለው ሲያደምጧት ቆይተው። ‹በሕይወትሽ ውስጥ ሞትን የሚያስንቅ፣ መኖር የሚያስናፍቅ እንዴት አዲስ ነገር አጣሽ? ሲሉ ለጆሮ በሚጥም ዝግታ ጠየቋት። ዝግ ሲሉ ያምራሉ.. የሽምግልና ውበታቸው ዝግታ እስኪመስል ድረስ።
‹የኔ ሕይወት ስትሰራ አዲስ ነገር እንዳይኖራት ተደርጋ ነው። ህሊና የምትባለው ሴት ወደምድር ስትመጣ ለመከራ ብቻ ታስባ ነው› ሳግ ባነቀው ድምጽ ተናገረች።
‹አንቺ አልሽ..እኔም አንቺም ሌላውም ሰው አንድ አይነቶች ነን። ከአዲስ ነገር ጋር የተሰራ ሕይወት የለንም። አዲስ ነገራችን በአዲስ ሃሳብ፣ በአዲስ የኑሮ ዘይቤ የሚመጣ ነው። እንደ ትናንቱ ማሰብ፣ እንደ ትናንቱ መኖር እስካላቆምሽ ድረስ አዲስ ነገርሽ ላይ መድረስ አትችይም።
ግራ ተጋብታ ታስተውላቸው ጀመር። እስከዛሬ ሊያነሷት የሞከሩ ክንዶች ሁሉ የደቆሷት ናቸው። የእኚህ አዛውንት ክንድ ግን በጉስቁልና ውስጥ የማይቻል ሆኖ አገኘችው።
‹ይሄ አመለካከት ከውስጥሽ እስካልወጣ ድረስ አዎ ለመከራ ነው የተፈጠርሽው። መጽሃፉ ‹ሰው ከአፉ ፍሬ መልካምን ይበላል› ይላል። እየበላን ያለንው የአፋችንን ፍሬ ነው። አሁን ካለሽበት ትንሽ ፈቀቅ በይ..
ዛሬም ተስፋ አስቆረጧት። በሞት ላይ አስጨከኗት። ተሰናብቻቸው እሞታለሁ ብላ ነበር.. እጃቸው ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ጉንጭዋ ላይ ሲያርፍ ተመልክታ ወደሞት ልትሄድ ተጠናቃ ነበር። መኖር የምትጀምረው እሳቸው ፊት ስትቆም ነው። ብዙ ሞቶችን በእሳቸው ሰላላ ክንድ ረታለች። ብዙ መከራዎችን፣ ብዙ ተስፋ መቁረጦችን የመላዕክት በሚመስል ዝግ ባለ ንግግራቸው አልፋለች። ግን ያጣችውን.. ያልደረሰችበትን አዲስ ነገሯን ሊሰጧት አልቻሉም። ከአጠገቧ ሄድ ሲሉ መሞት ትጀምራለች። ከአጠገቧ ሸሸት ሲሉ ወደደሮነቷ ትመለሳለች። ሞትን ማፍቀር.. ተስፋ መቁረጥን የሙጥኝ ማለት ትጀምራለች።
‹እርሶ የህይወቶን ዘጠና አመት እንዴት እንዳለፉ ሊነግሩኝ ይችላሉ? ስትል አዲስ ነገር ሽታ ጠየቀቻቸው። አንድም ቀን ስለራሳቸው እንዲነግሯት ጠይቃቸው አታውቅም። አንድም ቀን ከማድመጥ ባለፈ ምንም ነገር ጠይቃቸው አታውቅም። ዛሬ ጠየቀቻቸው.. ምናልባት ዘመን ካሾረው ከታሪካቸው ዳና ስር አዲስ ነገሯን ታገኝ ይሆናል.. ምናልባት ደግሞ ለአንዴና ለመጨለሻ ጊዜ ትኖር ይሆናል። በጆሮዋ ብቻ አይደለም በመላ ሴትነቷ ልታደምጣቸው ተሰናዳች።
እያዩዋት ወደ ራቀ ኋላ ኮበለሉ። በሃሳብ፣ በትካዜ የዘጠና አመትን የዘመን ድር ወደኋላ እያጠነጠኑ ተከዙ። የሕይወታቸውን እልፍ ዘመን አፈር አራግፈው ተረኩላት። ‹እኔ ጎዳና ተወልጄ ህጻናት ማሳደጊያ ውስጥ ነው ያደኩት። እስከዛሬ ድረስ ወላጆቼን አላውቃቸውም። በሃያ አምስት አመቴ ሁሉ ነገሬ ያደረኳት የመጀመሪያ ፍቅረኛዬ ከዳችኝ። በሰላሳ አመቴ ባልሰራሁት ወንጀል ተከስሼ ሃያ አመት ታስሬ በሃምሳ አመቴ ከእስር ቤት ወጣሁ። ከእስር ቤት መልስ ሚስት አገባሁ። ሚስቴ እጅግ መልካም ሴት ነበረች። ፈጣሪ በከንቱ ለባከነው ዘመኔ መካሻ እንድትሆነኝ የሰጠኝ ነበር የመሰለኝ። ግን ምን ያደርጋል በተጋባን በሶስት አመታችን ሚስቴ በሞት ተለየችኝ። ግን አሁንም እስቃለሁ። እውነት ለመናገር በሕይወቴ ካጣሁት ነገር ሁሉ በላይ የሚስቴ በሞት መለየት ነበር የጎዳኝ ግን ምንም እንደማላደርግ ሲገባኝ በመከራዎቼ ላይ መሳቅ ጀመርኩ። ከዛ በኋላ ባለው እድሜዬ አግብቼ ለመውለድ ብዙ ሞክሬ ነበር ግን አልተሳካልኝም። እናም አሁን ብቻዬን አለሁ.. ግን እስቃለው›።
የሌላ ሰው ታሪክ የሚነግሯት ነበር የመሰላት። እሷን ከሞት ለማዳን ሲሉ ዓለም ላይ ያልተፈጠረ ታሪክ ፈጥረው እየነገሯት መሰላት። ይሄን ሁሉ መከራ ችለው ሰው መሆናቸው አስደነቃት። ተገርማ ሳታበቃ ወደ እሷ የሚምዘገዘግ ዝግ ያለ ድምጻቸውን ሰማችው።
‹ብዙ ችግሮችን በልጅነቴ አሳልፌአለሁ። ወጣትነቴም እንደነገርኩሽ ከነውር የራቀ አልነበረም። በጉልምስና እድሜዬም ተሰብሬአለው። አዲስ ነገሬ በሳቄ ውስጥ እንዳለ ስለማምን እስቃለሁ። ሰዎች፣ አጋጣሚዎች ደስታችንን እንዳይወስዱብን ነው መጠበቅ ያለብን። ችግሮቻችን ሳቃችንን እንዲያሸንፉብን መፍቀድ የለብንም። ለአንድ ሰው ቤተሰቡን እንዳለማወቅ ስብራት አለ ብዬ አላስብም። እኔ በዛ ውስጥ ነው ያለፍኩት። ግን እስቃለሁ። የምስቀው ሳልሰበር ቀርቼ አይደለም፣ የቆምኩት ተስፋ መቁረጥ ሳይጎበኘኝ ቀርቶ አይደለም እጅ አልሰጥም ብዬ እንጂ። በሳቄ ችግሮቼ አቅም እንዲያንሳቸው ያደረኩት እኔ ነኝ። ለመታመም፣ ለመሞት፣ ተስፋ ለማጣት እንደ እኔ ቅርብ አልነበረም ግን መከራዎቼን ስቄባቸው አሸነፍኳቸው። ልጄ ሞት ይሞታል.. ሞትሽን ግደይው እንጂ አትሙቺለት›። ሲሉ አስተዋሏት።
ምን እንደምትል ጠፋት። እሞታለሁ ብላ ነበር። ከእንግዲህ አልኖርም ብላ ነበር። ዓለም ደህና ሰንብች ብላ በሞት ልትጽናና ተዘጋጅታ ነበር። ሽማግሌው አሸነፏት.. ሃሳብ ላይ እያለች ጉንጩዋ ላይ የሆነ እጅ አረፈባት። ከሃሳቧ ባነነች.. በሴትነቷ ምስራቅ ላይ ጸሀይ ወጣች። መከራዋን ጥላ እንደ አዲስ የተፈጠረች ይመስላታል።
እጃቸውን ከጉንጭዋ ላይ አንስተው፣ ትክ ብለው አስተዋሏት። በነፍሷ ውስጥ ነፍስ ተፈጥሮ አዩ። ከእንግዲህ አይደርሱባትም.. የማትሞት አዲስ ነፍስ በመፍጠራቸው እየተደሰቱ ምንም ሳይሏት ትተዋት ሄዱ።
አላቀረቀረችም.. ቀና ያለችባቸውን እነዛን አዛውንት እጆች ናፈቀች። ለዋሉላት ውለታ ሁሉንም ልትሆንላቸው ተከተለቻቸው።
በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵ)
አዲስ ዘመን ጥር 19 ቀን 2015 ዓ.ም