እሱ ካለ መድረኩ ይሞቃል ይደምቃል። የተመልካቹን ቀልብ ከመግዛትም አልፎ በስሜት ይሰልበዋል ቢባል ማጋነን አይሆንም። ከጥበብ ተጸንሶ ከጥበበ የተወለደ ያህል በእያንዳንዱ እርምጃው ጥበብን ኖሯታል። የመድረክ ላይ ተዋናይ ብቻ ሳይሆን ድንቅና ምጡቅ በሆኑ ሀሳቦች ቴአትር ይጽፋል፣ ያዘጋጃል። ይህ ሰው ሁሌም ከቴአትር መድረክ አሊያም ከመድረክ በስተጀርባ አይታጣም። ጥበብን ከውስጡ እያፈለቀ አይረሴ የሆኑ ትዕይንቶችና ስሜቶችን ከተመልካቾች ልብ ውስጥ ያሰርጻል። ታላቁ የቴአትር ጥበበኛና ከያኒ ወጋየው ንጋቱ (ወጊሾ)፤ የጥበብን ወግ ማሳየት የቻለ ድንቅ ሰው በመሆኑ የፊተኛውም የኋለኛውም፣ ያየውም ያላየውም ሁሉም ትውልድ በስራው ያስታውሰዋል።
ከአባቱ ከአቶ ንጋቱ ብዙነህና ከእናቱ ከወይዘሮ አምሳለ በየነ በግንቦት ወር 1936 ዓ.ም በአዲስ አበባ ቀበና የተወለደው ወጋየሁ ንጋቱ፤ በኢትዮጵያ የቴአትር ጥበብ ውስጥ ስሙን በወርቃማ ብዕር ማስፈር የቻለ ታላቅ ሰው ነው። የጥበብን ማዕድ ቆርሶ ለሌሎችም ለማቋደስ ያበቃውን የሕይወቱን ምዕራፍ ሲጀመር እንዲህ ነበር፥ በ1942 ዓ.ም በስድስት ዓመቱ አቃቂ በሚገኘው የስዊድን ወንጌላዊት ሚሲዮን ትምህርት ቤት የአንደኛ ደረጃ ትምህርቱን በማጠናቀቅ ቀለማዊ ብቻ ሳይሆን ኪነጥበባዊ እውቀትንም ጭምር ቀስሞ ወጣ። የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱንም በዳግማዊ ምኒልክ እና በተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤቶች በሚከታተልበት ወቅት በውስጡ የነበረችው የጥበብ ጽንስ እየዘለለች ታስጨንቀው ነበርና የሚገላገልበትን መንገድ ይፈልግ ነበር። ከሚመላለስባት ከቀበናዋ ድልድይ የገዘፈ የአዲስ ምዕራፍ መጀመሪያና መሸጋገሪያ የምትሆነውን ድልድይ አጥብቆ መፈለግ የጀመረው ወጋየው ንጋቱ፣ በመጨረሻም በብዙ ተመስጦ ስፍራዋን አገኛት። ባገኛት ድልድይ ሁሉ እየተሸጋገረ ውስጡ የነበረውን እንቁ በግዙፉ የጥበብ አውድማ ላይ በመዝራት ጥበብን አሀዱ አለ።
በትምህርት ቤቶቹ ውስጥ በተለያዩ ጊዜያት በሚዘጋጁ ትርኢቶች ላይ ብቅ እያለ ተሰጥኦውን ያሳይ ነበርና በተማሪዎች ዘንድ ተወዳጅነትን በማትረፍ፣ ገና ትርኢቱ ከመጀመሩ የተማሪው ድምጽ ሁሉ ‹‹ይውጣ ወጊሾ›› የሚል ነበር። የተለያዩ እንስሳትን ድምጽ ያስመስልና ያዝናናቸዋል። በትምህርት ቤት ቆይታውም ከጊዜ ወደ ጊዜ የጥበብ አውዱን እያሰፋ፣ የተደበቁ ልዩ ልዩ ችሎታዎቹም እየተግተለተሉ ከውስጡ መውጣት ጀመሩ።
የሁለቱኛ ደረጃ ትምህርቱን እንዳጠናቀቀም በ1955 ዓ.ም ቀደም ሲል የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ወዳቋቋመው ‹‹ኪነ ጥበብ ወትያትር›› ወይም የአሁኑ ‹‹ባህል ማዕከል›› በመግባት ከጓደኞቹ ከአባተ መኩሪያ እና ደበበ እሸቱ ጋር እንቅስቃሴ ማድረግ ጀመረ:: በዚህ ጊዜም የትወናና የተውኔት ዝግጅት አቅሙን ከፍ የሚያደርግለትን አንድ መሠረታዊ ስልጠና፣ በወቅቱ የማዕከሉ ኃላፊ በነበሩት ፍሊፕ ካፕላን አማካኝነት በመውሰድ ወደተግባር ቀየረው። ከዚህ በኋላ ታዲያ ወጋየው ንጋቱ በጥበብ ቅኝት ውስጥ በመግባት በተውኔት ዝግጅትና በትወናው ስራዎቹን እያከታተለ ድንቅ ተሰጥኦውን አቀጣጠለው። ሮሚዮ እና ጁሌት፣ ጠልፎ በኪሴ፣ የከርሞ ሰው፣ መድሃኒት ቀምሰዋል፣ ዳንዴው ጨቡዴ፣ የዋርካው ስር ምኞት፣ ላቀችና ድስቷ በተባሉ ትርጉምና ወጥ ተውኔቶች ላይ አብይ ሚናዎችን ይዞ በመጫወት አንቱታን ማትረፍ ቻለ።
ይሄ ገና የጥበብ ህይወቱ ጅማሬ እንጂ መጨረሻ እንዳልሆነ ስለቆጠረው በስራዎቹ ሳይኮፈስ በጥበብ ላይ ጥበብን፣ በእውቀት ላይ እውቀትን ለመጨመር የማይቆፍረው ጉርጓድ አልነበረም። ትጋትና ጥረትም መገለጫዎቹ ነበሩ። ይህንን የተመለከቱት የቅርብ ኃላፊዎቹ በ1959 ዓ.ም ከደበበ እሸቱ ጋር ወደሀንጋሪ ቡዳፔስት በመሄድ የስነ-ተውኔት ሙያን ለሁለት ዓመታት ያህል እንዲማር አደረጉት። ጥበብና እውቀትን ለተጠማው ወጋየው ይህ ትልቅ እድል ነበርና ከዚያ እንደተመለሰ ሌሎች በሮችም ተከፈቱለት። እሱም የጥበብን ካባ ደርቦ በክብር ሰተት ብሎ ወደ አዳራሹ ገባ። በሬዲዮና በቴሌቪዥን አጫጭር ተውኔቶችን ማቅረብ ጀመረ። በተለይም በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ለተመልካች እንግዳ የሆኑ አስማተኛው፣ ቁንጫ፣ ባሉን፣ ቀለም ቀቢው፣ የተዘጋ በር እና የመሳሰሉ ድምጽ አልባ (ማይም) ተውኔቶችን ማቅረብ በመጀመሩ ተደናቂነትን እያተረፈ መጣ።
ስኬት በቀላሉ የማይመጣ እልህ አስጨራሽ የሕይወት ውጣውረዶችን ማለፍ የሚጠይቅ እንደመሆኑ፣ እሱም ከዚህ ትግል ውስጥ ነጥሮ መውጣት ግዴታው ነበር። ይህንንም አደረገው። እየገጠሙት የነበሩትን ችግሮች እንደ መሰላል እየተጠቀማቸው በብልሃት የስኬት ጫፍ ላይ መድረስ ቻለ። ታዲያ ወጋየሁ አንድ ግሩም ባህሪው፣ ከደረሰበት ከፍታ ትንፋሹን ሳብ አድርጎ እንደገና ወደሌላኛው ምዕራፍ ለመሸጋገር ይጥራል እንጂ ፈጽሞ ጨረስኩኝ አያውቅም። ስኬቶቹ ለእርሱ መሰላል እንጂ ሰገነት አይደሉምና አሁንም ሌላ እይታ…ሌላ ጉዞ…ሌላ ከፍታ… ሌላ ስኬት ይሄ ነው የእርሱ ማንነት።
በሄደባቸው ጉዞዎች ሁሉ ልዩ ልዩ ክህሎቶቹን ማዳበር በመቻሉ በ1962 ዓ.ም ወደ ሀገር ፍቅር ቴአትር በመምጣት የቴአትር ክፍሉ ኃላፊ፣ አዘጋጅ፣ ተዋናይ ከመሆኑም ባሻገር ሌሎች ወጣቶችም የእርሱን ፈለግ እንዲከተሉ በማስተማርና ልምዱን በማካፈል ሁለጉብ አገልግሎት መስጠት ችሏል። ከዚህ በኋላ ወደ ኢትዮጵያ ሬዲዮ ተዘዋወረና በመዝናኛ ፕሮግራም አቅራቢነትና በዜና አንባቢነት እየሰራ ለአራት ዓመታት ቆየ። በመቀጠልም ወደ ብሄራዊ ቴአትር በመግባት ዳግም ፊቱን ወደ ትወና አዞረ። በብሄራዊ ቴአትር ቆይታውም የበጋ ሌሊት ራዕይ፣ ትግላችን፣ ደመ መራራ፣ ደማችን፣ ሀሁ በስድስት ወር፣ ሞረሽ፣ አጽም በየገጹ፣ ጸረ ኮሎኒያሊስት፣ እናት ዓለም ጠኑ፣ የአዛውንቶች ክበብ፣ ዋናው ተቆጣጣሪ፣ ፍርዱን ለእናንተ፣ ጴጥሮስ ያቺን ሰዓት፣ ክራር ሲከር፣ ሀምሌት፣ ሊየር ነጋሲ፣ የድል አጥቢያ አርበኛ፣ ዘርዓይ ደረስ፣ ገሞራው፣ አሉላ አባነጋና እና እናት ነሽ በተሰኙት ተውኔቶች ላይ የተለያዩ ገጸ-ባህሪያትን እየወከለ ተጫውቷል:: ከነዚህ ተውኔቶች በአንዳንዶቹ በዋና አዘጋጅነትና በተዋናይነትም ሰርቷል::
ታዋቂው ጸሃፊ ዘነበ አብርሃ ስለ ወጋየሁ ንጋቱ የመድረክ ላይ ችሎታው በጣም ይገረም ስለነበረ ‹‹የመድረኩ ኮከብ›› በተሰኘ ርዕስ ሲጽፍ ስሜቱን በእነዚህ ቃላት አስፍሮታል፤ ‹‹ለመጀመሪያ ጊዜ ያየሁትም ቀልቤን የወሰደውም የታዋቂውን ባለቅኔ የጸጋዬ ገብረመድህንን ‘ጴጥሮስ ያቺን ሰዓት’ ቴአትር ሲሰራ ነው። ወጣትነቱም አይሎ ነው መሰል እንባዬን መግታት ተሳነኝ። ደግነቱ አዳራሹን የሞላው ታዳሚ ሁሉ ይነፈርቃል›› በማለት ወጋየሁ በአቡነ ጴጥሮስ ተመስሎ ሲጫወት የፈጠረበትን ስሜት ይገልጻል። ወጋየሁ እንደዚህ ነው! ገጸባህሪያቱን መስሎ ሳይሆን ሆኖ ነው የሚሰራው። የሱን ቴአትሮች በመድረክ ላይ የመታደም እድል ያገኙ የቴአትር ተመልካቾች በአንድ ድምጽ ይህንኑ ችሎታውን ይመሰክሩለታል። ወጋየሁ መሆን እንጂ መምሰል ፈጽሞ አይሆንለትም።
ወጋየሁ ንጋቱ ከሚታወቅባቸው ዘርፈ ብዙ ችሎታዎቹ አንደኛው በሬዲዮ ያቀርብ የነበረው የመጽሃፍት ትረካ ነው። በመጽሃፍት ዓለም ፕሮግራም በሬዲዮ ከተረካቸውና አድናቆትን ካተረፉለት መጽሃፍት መካከል የሀዲስ አለማየሁ ፍቅር እስከ መቃብር፣ የብርሃኑ ዘሪሁን ሶስት መጽሃፍ ማዕበል፣ የአብዮት ዋዜማ፣ የአብዮት መባቻ እና የገበየሁ አየለ ጣምራ ጦር ከተደራሲያን አዕምሮ የማይጠፉ የትረካ ችሎታውን ፍንትው አድርጎ ማሳየት የቻለባቸው መጽሀፍት ናቸው። ከሁሉም ግን በሀዲስ አለማየሁ ፍቅር እስከ መቃብር ላይ የነበረው ችሎታና የትረካ አቀራረብ የተለየ ነበር። በወቅቱ መጽሀፉ ተተርኮ እንዳለቀ ሀዲስ አለማየሁ ለወጋየሁ እንዲህ ሲሉ ተናገሩት ‹‹እኔ ከጻፍኩት ይልቅ አንተ በህዝቡ አዕምሮ የሳልከው ይበልጣል›› የሚል የአድናቆት አስተያየት ሰጥተውታል::
በአንድ ወቅት ከዜና ቱሪዝም ጋር ባደረገው ቃለመጠይቅ እንዴት የተዋጣለት ተዋናይ መሆን እንደቻለ ሲጠየቅ ወጋየሁ የሰጠው ምላሽም ‹‹… የስቴጅ ዓይኔን የከፈተው … ተስፋዬ ገሠሠ ነበር። የድራማ መምህሬ፤ የተውኔት አባቴ እርሱ ነው›› ሲል ለጥበብ አባቱ ያለውን ክብር ገልጿል። ይህን ውለታውንም ሳይረሳም እሱም ያለውን እውቀትና ክህሎት ለሌሎች ተተኪ ባለሞያዎች በማስተማር እና በማካፈል የወጣት ባለሞያዎችን የመድረክ ዓይን በመክፈት መልሷል። በ1967፣ በ1969 እና በ1970 ዓ.ም ብሔራዊ ቴአትር በሰጠው የተዋንያን ስልጠና አስተማሪ በመሆን የሚጠበቅበትን አስተዋጽኦ አበርክቷል። በዚህ ወቅት ተማሪዎቹ ከነበሩት ውስጥ እነ ሲራክ ታደሰ፣ ዓለምጸሐይ ወዳጆ፣ ተክሌ ደስታ፣ መዓዛ ብሩ፣ ዓለምጸሐይ በቀለ፣ ዓይናለም ተስፋዬ፣ ኃይሉ ብሩና የመሳሰሉት ተጠቃሽ ናቸው።
ወጋየሁ ለእስር የተዳረገበት አንድ አጋጣሚም ነበር። ይኸውም በ1966 ዓ.ም በብሄራዊ ቲያትር ውስጥ በነበሩት የውስጥ አለመግባባቶች ጸጋዬ ገብረመድህን ከብሄራዊ ቴአትር እንዲነሱ ብዙ የቴአትር ቤቱ ሠራተኞች ሠልፍ በመውጣት ተቃውሞ በሚያሰሙት ጊዜ፣ ሌላ የፖለቲካ ዓላማ ያላቸው ተደባልቀው ነበርና ‘ከስንዴ ጋር የተገኘህ ሰሊጥ አብረህ ተወቀጥ’ ሆኖበት እሱም እንደጸረ-አብዮተኛ ተቆጥሮ ለተወሰኑ ወራት ታስሮ ተፈቷል። ጸረ-አብዮተኛ ተብሎ በታሰረበት በዚያው መንግስት ደግሞ በ1977 ዓ.ም ከባህል ሚኒስቴር ሠራተኞች መካከል ምስጉን ሠራተኛ ተሰኝቶ ተሸልሟል።
ወጋየሁ ቴአትርን የኖራት፣ ያከበራትና ያስከበራት ድንቅ ልጇ እንደነበረ የማይካድ ሀቅ ነው። በመጨረሻዎቹ የሕይወት ማብቂያ ዘመኑ ግን እንግዳ የሆኑ ስሜቶችን ማስተናገድ ጀምሮ ነበር። ምን እንደሆነ ማንም አያውቅም። እሱም ለማንም አይናገረውም፣ ብቻ ስለ አንድ ጉዳይ ያስባል፣ ይተክዛል፣ ሆድ ይብሰውና በሆነ ባልሆነው መናደድ፣ መበሳጨት ከዚያም መጠጣት ያበዛል። ውስጡን የረበሸውን ሚስጥር ምን እንደሆነ ለማንም ሳይናገረው ህዳር 6 ቀን 1982 ዓ.ም ባደረበት ህመም ሳቢያ፣ በ46 ዓመቱ የሞት መልአክ ነብሱን ነጠቃት። ማንም ሊነጥቃቸው የማይችላቸው ስራዎቹ ግን ትዝታና ትውስታ ሆነው ለዘለዓለም ይኖራሉ።
በሙሉጌታ ብርሃኑ
አዲስ ዘመን ጥር 7 ቀን 2015 ዓ.ም