የሰው ልጅ ህብረት ፈጥሮ እንደ አንድ ልብ አሳቢ እንደ አንድ አፍ ተናጋሪ ሆኖ በተንቀሳቀሰባቸው ጉዳዮች በሙሉ ውጤት ማስመዝገብ እንደሚችል ይታወቃል። የዚህ አይነቱ የንሮ ዘይቤ በተለይ እንደ ኢትዮጵያ የዳበረ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ላላቸው ህዝቦች የኖረ መለያ ነው። ከቅርብ አመታት ወዲህ ግን በተለያዩ ምክንያቶች የሀብረታችን አካሄድ ጥያቄ ምልክት ወስጥ እየገባ መጥቷል። በዚህም በአንድ ወገን የውስጥ ችግሮቻችንን መቆጣጠር ተስኖን ስንገዳገድ በሌላ በኩል የውጪ ጣልቃ ገብነትም ጓዳችን ለመድረስ በቅቷል።
ለመሆኑ የሰው ልጆች ከግለሰብ አስከ ማህበረሰብ የሚኖራቸውን ህብረት ለማጠናከር ምን መስራት ይጠበቃል ስንል የማህበራዊ ሳይንስ አመራርና ባለሙያ የሆኑትን አቶ ዘላለም ይትባረክ አነጋግረን የሚከተለውን ይዘን ቀርበናል። አቶ ዘላለም እንደሚያብራሩት ህብረት ከአንድ በላይ በሆነ ቁጥር ውስጥ የሚፈጠር የሰዎች የሃሳብና የተግባር መገለጫ የሆነ ስብስብ ወይም ቡድን ነው። መተዋወቅ፣ መስማማት፣ መግባባትና አብሮ መሆን ደግሞ ለህብረት መነሻዎች ናቸው።
ህብረት የሰው ልጆችን ከፈለጉት የብልጽግናና የሰላም ማማ የሚያደርስ መንገድም ነው። በጠንካራ የህዝብ ለህዝብና የግለሰቦች ግንኙነትና ህብረት ላይ የተመሰረቱ ሀገራት በቀላሉ የሚደርሱበት የእድገት ደረጃ ለዚህ ዋናው ማሳያ ነው። ህብረት ሰዎች ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ሌሎቸም የጋራ ፍላጎታቸውን ወይም ችግሮቻቸውን በጋራ ለመፍታት እንዲሁም የወደፊት ራዕያቸውን ወይም ህልሞቻቸውን ለማሳካት የሚያደርጉት የእርስ በእርስ ትብብርም ተደርጎ ይወሰዳል።
ጥናቶች እንደሚያመለከቱት ሰዎች ህብረትን የጀመሩት ገና ጥንት በጋርዮሽ ስርዓት ሲሆን ለዚህም ዋናው ምክንያት ራሳቸውን ከጠላት ወይም ከአውሬ ጥቃት ለመከላከል ነው። ከዚያም ጊዜ ጀምሮ (በባህል፣ በሃይማኖት፣ በብሄራቸው፣ በቋንቋቸው፣ በዘራቸው ወዘተ የሚሰባሰቡ ሲሆን) አሁንም ድረስ በተለያዩ ጉዳዩች ከመንደር እስከ አለማቀፋዊነት ድረስ ህብረት እየፈጠሩ ሲሰባሰቡ ይስተዋላል። ከዚህ ወስጥም ትዳር በሁለት ሰዎች የሚመሰረት አንዱ የህብረት አይነት ነው። ይህም በሁለት ተቃራኒና የተለያዩ ሰዎች መሳሳብና መፈላለግ ውስጥ የሚፈጠር የአብሮነት ህብረት ውጤት ነው።
የህብረት ጠቀሜታዎች
• አንዱ ያለውን ለሌለው ያካፍላል። በዚህም ጎዶሎን፣ ክፍተትን ለመሙላት እና ሙሉ ለማድረግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አለው።
• ህብረት የጥንካሬ ምንጭ ነው። በማህበራዊ የኑሮ ውጣ ወረድ የሰው ልጅ ብቻውን ለመከወን የሚከብዱትን ነገሮች እንደ እቁብ፣ እድርና በገጠሩ የአገራችን ክፍል የምናያቸው እንደ ደቦ፣ ወንፈልና የመሳሰሉትን፤ በመጠቀም ኑሮውንና የገጠመውን ችግር በቀላሉ ለመፍታት ያስችለዋል።
• በተናጠል ከምናስመዘግበው ውጤት ይልቅ በህብረት
የምናመጣው የላቀ ይሆናል፤ አንድ ማህበረሰብ እንደ ሀገር ራሱን ችሎ ለመቆም ሀይልና ሀብት ያስፈልገዋል። እነዚህን ነገሮች የሚያሟላው በሚፈጥረው የፖለቲካ፤ የንግድ ወይንም የሃይማኖት ህብረት ሊሆን ይችላል።
የህብረት ሳንካዎች
• አንደኛ ነኝ፣ እኔ/እኛ ብቻ እና ያለ እኛ/ እኔ አይሆኑንም የሚሉ ጉራ አዘል ትርክቶች፤
• የሌሎችን አስፈላጊነት እውቅና አለመስጠት፤
• ራስን አለማወቅ እና የበዛ የራስ ወዳድነት ፤
• እሱኮ/ እነሱኮ የሚል የጅምላ ፍረጃ፤
• ሃላፊነት በአግባቡ መወጣት አለመቻል። ለምሳሌ የትዳርን ህብረት ብንመለከተው በሁለቱ ሰዎች ሃላፊነትን መወጣት አለመቻል ምክንያት ሲፈርስ እንመለከታለን።
• ጥርጣሬ (አለማመን)፣ ይህ ማለት ካለ በቂ መረጃና መነሻ ምክንያት የግለሰቦችን አልያም የአንድን ቡድን እንቅስቃሴ በጥሩ ጎኑ አለመመልከትና ይህንን መነሻ በማድረግ ምላሽ መስጠት ማለት ነው።
• የጋራ ተጠቃሚነትን (lose –win) ያላረጋገጠ ህብረት ወይም (lose- lose) እንጠፋፋ አይነት አስተሳሰብ ይዞ ህብረትን መመስረት ለውጤታማነት የማያበቃና ለወድቀት የሚዳረግ ነው። በመሆኑም ከዚህ ይልቅ የጋራ ተጠቃሚነት (win-win) እና ሰዎች እንዲረዱ በቅድሚያ ህብረቱ ለጋራ ተጠቃሚነት የተፈጠረ መሆኑን በሚገባ ማስገንዘብ መቻል።
ለህብረት መጠናከር መሰረታዊ ምሰሶዎች
1. የእያንዳንዱን ሰዉ ከምንም መስፈርት ውጭ አስፈላጊ የሚሆንበት ግዜ እንደሚኖር አምኖ መቀበል።
2. የሰዎችን ድርሻ አስተዋጽኦ አሳንሶ አለመመልከት።
3. ለብቻ የሚሰራ ነገር በሙሉ ውጤቱ አመርቂ እንደማይሆን መገንዘብ።
4. ተግባቦትን ማጠናከር ይህም ማለት በመነጋገር፣ በመወያየትና በመመካከር ውሳኔን ማስተላለፍ ወደ ተግባርም መግባት።
5 ልዩነትን ማክበር፤ ጥንካሬ የሚጎለብተው ከተመሳሳይ ሃሳብ ሳይሆን ከልዩነት ወስጥ በሚመነጭ አዲስ ሀሳብ ነው። ዓለም እዚህ የደረሰችው በልዩነት ውስጥ ያለውን ልዩ ልዩ ሃሳብ በመጠቀም እና ለጋራ ግብ ወይም ዓላማና ራዕይ በጋራ በመቆም መሆኑን መዘነጋት የለበትም። አለበለዚያ ልዩነትን በመቀበል ለእድገት ለሰላምና ለአብሮነት መጠቀም ይገባል።
6. የጋራ አሸናፊነትንና ተጠቃሚነትን ማሰብ መቻል፤ በዚህም ከእኔነት ወደ እኛ ወደ ሚል መሸጋገር ማለት ነው።
ራስወርቅ ሙሉጌታ
አዲስ ዘመን ግንቦት 3/2013