ጊዜው እየገሰገሰ፣ ዘመኑም እየዘመነ ዓለማችን ዓለሟን በቴክኖሎጂ እየቀጨች የምትገኝበት ዘመን ላይ እንገኛለን። ቴክኖሎጂው ከወለዳቸው ልጆች ወይም የልጅ ልጆች መካከልም ሚዲያ አንደኛው ነው። የቴክኖሎጂውን መቋደሻ የበለጸጉት አገራት በተለይም ምእራባውያኑ ቢያነሱትም ኢትዮጵያን የመሳሰሉ ታዳጊ አገራትም ዘግይቶም ቢሆን ተቋዳሽ መሆናቸው አልቀረም።
በዘመናችን በተለይም የሚዲያዎችና የፖለቲካ ትስስር ከመቼውም ጊዜ በላይ ፀንቶ የሚታይበት ነው። መድሃኒት ያድናል፣ መድሃኒት ያድናልምና እኛ ግን እንዴት እየሰራንባቸው እንገኛለን? ወይንስ እየሰሩብን ይሆን? የሚለው ጉዳይ አንገብጋቢ ነው።
አንዳንዶቹ ሚዲያዎቻችን አይነኬ ከሆኑ ጉዳዮቻችን ጋር ተቆላልፈው ምንነታቸው የማይለይ አንጃ ግራንጃ ሆነዋል። አንዱ የራሱን ጥቅም ለማብሰል ሲል የሌላውን ሕይወት መማገድ በጣም ቀላል ነገር ሆኗል።
አጃቢ ሰርገኛው ተጫፍረው ሊደምቁ፤
በሰርጉ ቤት ድግስ ጠርሙሶች አለቁ፤
ለትዝብቴ ከብዙ ሚዲያዎች መንደር ባኮበኩብም ለዛሬ ግን ፌስቡክና ግብረ አበሮቹ ውስጥ ስለታጨቁት ንጥረ ክፋትና እንቶ ፈንቶ የአሉባልታ ወሬ ላይ ለማረፍ ወደድኩ። ለቴክኖሎጂው ምስጋና ይግባውና አሁን አሁን ሃሜቱንም አቤቱታውንም በዘመናዊ መልክ በዚሁ መተግበሪያ ማሳልጥ ጀምረናል፡፡
በፌስቡክ ገበያው የብዙዎችን ቀልብ ለመሳብና ብዙ ተከታይ ለማፍራት ሲባል የሌላውን ቆሌ መግፈፍ ፋሽን ከመሆን አልፎ ተለምዷል። በዚያ መንደር ከእውነት ይልቅ ውሸት ነግሷል። “ፌስቡክን ማመን ቀብሮ ነው፡” አለኝ አንዱ ወዳጄ፤ እውነቱን ነው ፌስቡክ ላይ የተለጠፈውን ሁሉ አሜን ብለን ከተቀበልን ከሰውና ከእግዜር ጋር ጨርሰን ከቆመ ግንብ ጋር መጋጨት የምንጀምርበት ጊዜ ሩቅ አይሆንም።
በፌስቡክ አገርና ሰውን ለመገንባት የሚሰሩ እንዳሉ ሁሉ የሞት ድግስ አዘጋጅተው የአገርን ደምና ስጋ የሚመጡ በየጥሻና ጉራንጉሩ ተበራክተዋል። በነሱ የተነሳም መልአኩን ከሰይጣኑ መለየት የተሳነው ሰው ቁጥር እንደ አሸን ፈልቷል። ነገሩ “ፍየል ወዲህ ቅዝምዝም ወዲያ” ሆኗል። መንግስት በአንድ በኩል የተለኮሰን እሳት ለማጥፋት ሲሮጥ የፌስቡክ አርበኛው በሌላ መንገድ እየተሽለኮለከ በአይጥና በድመት አባሮሽ መሃል የሕዝቡ ሰላም ለማደፍረስ ተኝቶ አያድርም።
የፖለቲካ ደም ስሩና መዘውሩ ፌስቡክ የሆነ ይመስል ዘር፣ ቋንቋ፤ ባህልና ሃይማኖት የሁሉም ሰው ስስ ጎን ሆነው ለፌስቡክ አርበኞች ጣፋጭና የማይነጥፍ እንጀራ ሆነዋል።
እነዚህ የፌስቡክ አርበኞች እንደ አይጥ ተሽሎክልከው በሳሳው ጎናችን እየገቡ ነካ ባደረጉን ቁጥር ምንም በሌለበት ተንቀናል፣ተደፍረናል እያለን ቡራ ከረዩ እያልን መጯጯህና መተራመስ ይመጣል።
ፖለቲካችን ከጀበና ላይ እንዳለ ቡና ሁሉም ቀድቼ ካልጠጣሁ እያለ ሲወዘውዘው መልሶ እየደፈረሰ መስከን ተስኖታል። እያንዳንዳችን ጋር ያለው የፖለቲካ አቋም በደንብ መብሰል ይቀረዋል። ከነፈሰው ጋር እየነፈስን አቋማችን እንደ ፔንዱለም ወዲያና ወዲህ እየዋዠቀ ማንነታችን ብቻ ሳይሆን ምንነታችንም የማይጨበጥና እንደ እስስት ልውጥውጥ የሚል ሆኗል። ዛሬ “እኔ ከመንግስትና ከኢትዮጵያ ህዝብ ጎን ነኝ!” የሚል መፈክር አንግበን ሰላማዊ ሰልፍ ወጥተን ስንጨርስ ነገ ደግሞ መልሰን “መንግስት አለ እንዴ!” እንላለን። ከነገ በስቲያ ደግሞ “ህዝብ አለ እንዴ!” ማለታችን አይቀርም።
ፖለቲካዊ መስተጋብራችን ሳናውቀው ከስሜታችን ጋር ተዋህዶ ውሃ መልክ ይዟል። ውሃ ከፍሪጅ ሲገባ ከበረዶነት አልፎ የጠጠረ ድንጋይ ይሆናል። እሳትን ሲያገኝም ከእሳቱ በላይ የሚያቃጥል ትንታግ ከመሆን አልፎ ወደ እንፋሎትነት ይቀየራል። የአብዛኞቻችን ፖለቲካም እንዲሁ ነው ከበረዶው ጋር ተባርደን፣ ከሞቀው ጋር ተሟሙቀን፣ ከጨሰው ጋርም እንጨሳለን። አንዱ ከመሬት ተነስቶ ‘በሬ ወለደ’ ሲለን “ኧረ እኔም እኮ ወተቱን ጠጥቻለሁ” እያልን በአሉባልታ ወሬ ቅመሟን ጠብ ማድረግ አመል ሆኖብናል።
ማህበራዊ ሚዲያዎቻችን ደግሞ ለዚህ ምቹ ናቸው። የማንም መፈንጫ ሆነዋል። እጅግ በጣም ብዙ ያልተማሩ የሚመስሉ ‹‹ምሁራን›› አስተዋውቆናል። አንዱ የቀበሌ ሊቀመንበር የመንደሩን ነዋሪ ለስብሰባ ጠርቶ ድንገት ከመንገድ ላይ ወዴት እየሄድክ ነው ቢሉት “ያልገባኝን ላልገባቸው ላስረዳ እየሄድኩ ነው” አለ ተብሎ ይቀለድ ነበር። አንዳንዶቹ ልክ እንደዚህ ናቸው፤ ያልተማሩትን ሊያስተምሩን፣ ያልተረዱትንም ሊያስረዱን በኔ ይሁንባችሁ ብለው ያስገቡንና የነብር ጭራ አሲዘውን “በል እግዜር ካንተ ጋር ይሁን!” ብለውን እልም ይላሉ። ትልቁ ችግር ደግሞ አብዛኛው ማህበረሰባችን ፖለቲካ የማይወድ(የማይገባው) ፖለቲከኛ መሆኑ ነው። ድንገት የሆነ ቦታ በአጋጣሚ ከአጠገባችሁ ቁጭ ብሎ ጆሯችሁ እስኪደማ ልባችሁ ፍስስ እስኪል ይህን የፖለቲካ ወሬ በአናት በአናታችሁ ፍትፍት አድርጎ ካጠገባችሁ በኋላ “እና አንተስ?” ስትሉት “አይ እኔ እንኳን ፖለቲካ አይመቸኝም።” ብሏችሁ እርፍ! ታዲያ የዛኔ በትዝብት አይናችሁ ግርፍ አድርጋችሁት ታልፋላችሁ።
ባላመንበት ነገር እየኖርን እኛው ተዋናይ እኛው ተመልካች እየሆንን ነገሩ ሁሉ ‘አንቺው ታመጪው አንቺው ታሮጪው’ ሆኗል። እንደ ረቂቅ ስዕል የተወሳሰበውን የአገራችንን ፖለቲካ መንግስትና ህገ መንግስት ብቻ አይፈታውም። ከማንም በላይ መፍትሄው እኛ ጋ ነው። እኛ ሕዝቦች፣ እኛ ዜጎች በአገራችን ጉዳይ ብዙም አይናፋር፣ ብዙም ደግሞ አይናውጣ ሳንሆን ትክክለኛውን ነገር በትክክለኛው ሰዓት ለአገራችን እናድርግላት። ሲመሽ ወደ ማታ ማንም አያየኝም ብለን ከማይገባን አድረን፤ አደራ! ኋላ ሲነጋ እርስ በእርስ እንዳንተዛዘብ ቀልባችንን ከሰወሩ መጥፎ ርዕሰ ጉዳዮች ወጥተን ኢትዮጵያን እናስባት።
ሙሉጌታ ብርሃኑ
አዲስ ዘመን ሰኞ ታኅሣሥ 10 ቀን 2015 ዓ.ም