ያቺ ቀን፣ አዕምሯቸው በትዕቢት አብጦ፤ ልባቸው ክፋት አምጦ፤ መንፈሳቸው ተንኮልን አብሰልስሎ ለዓመታት የትግራይን ህዝብ ሲጠብቅ በኖረው የመከላከያ ሰራዊት ላይ የክህደት እና የጭካኔ ተግባር የፈፀሙባት ዕለት ነች። የአገርን ልብ እንደሰው ልብ ያደሙበት። አዎ! ያቺን ዕለት እኛ ኢትዮጵያውያን መቼም ቢሆን አንረሳትም – ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም ውድቅት ላይ የሰሜን እዝ ጀርባውን በከሃዲው አሸባሪው ትህነግ የተወጋበትን ቀን።
አሸባሪዎቹ ትህነጎች፣ መንገዳቸው የጨለማ ስለነበር የት ጋር ሊሰናከሉበት እንደሚችል አላወቁም፤ ከዛ ይልቅ ከውልደታቸው ጀምሮ የተጠናወታቸው እብሪትና እብሪቱ የወለደው ጀብደኝነታቸው ዋጋ ወደሚያስከፍላቸው የፍጻሜያቸው መጀመሪያ ወደሆነው ስህተታቸው ገቡ።
ለበርካታ ዓመታት ጥላ ከለላ ሆኖ ሲጠብቃቸው፣ በጉልበቱ ሲያገለግላቸው በነበረው የመከላከያ ሰራዊታችን ላይ ጥቃት በመሰንዘር አንድም ለስልጣን የቱንም አይነት ዋጋ እንደሚከፍሉ፤ ስልጣን ለእነሱ ከአገር እና ከህዝብ በላይ መሆኑን በተጨባጭ አስመሰከሩ። በእጅጉ ዘግናኝ እና መራራ በሆነው የክህደት ተግባራቸው በኢትዮጵያውያኑ ልብ ውስጥ የነበራቸውን እንጥፍጣፊ ቦታ አሟጠው ከመሬት ደባለቁት። በሰሩት ግፍም ከንቱነታቸው በአደባባይ ተገለጸች።
የአሸባሪው ትህነግ ትዕቢትና እብሪት ጠማማውንና ክፉውን መንገድ እንዲከተል አስገድዶት የሕዝብ ልጅ በሆነው በአገር መከላከያ ሰራዊት ላይ እጁን ማንሳቱ የገዛ አካሉን በገዛ ሳንጃው በጭካኔ እንደወጋውና እንደቆረጠው ተቆጥሯል። አስቦበት እና አቅዶበት የታመነበትን ወገኑን አድብቶ ማጥቃቱ ግን እንደ መሻቱ ሊሳካላት የፈለገውን ሊያሳካለት አልቻለም። እውን ለማድረግ የቋመጠለት ሕልም አልተሳካለትም።
ጀግናው የመከላከያ ሰራዊታችን በከዳተኛው ቡድን ከጀርባው በተወጋበት ቅጽበት በወቅቱ የቡድኑ ቃል አቀባይ የነበረው ሴኩቱሬ ጌታቸው፣ አስነዋሪ ድርጊታቸውን ያለምንም ሃፍረት በሰራዊቱ ላይ ‹‹መብረቃዊ ጥቃት›› መፈጻማቸውን መናገሩ የክህደታቸውን ጥግ የሚያሳይ ነበር። ይሁንና ከሃዲው ሴኩቱሬ፣ ‹መብረቃዊ ጥቃት› ያለው ድምፁ ሳይደበዝዝ ላይነሳ ማሸለቡን ታሪክ ዘግቦት አልፏል።
በባንዳው የተከዳው የአገር መከላከያ ሰራዊት ከቸገራቸው ጎን በመቆም የሚስተካከለው አልነበረም። ከሁለት አስርት ዓመት በላይ በትግራይ ሲቆይ ጊዜውን በቀበሮ ጉድጓድ አገርን ከጠላት ለመታደግ፣ በአርሶ አደሩ ማሳ አንበጣ ለማባረር እንዲሁም የደረሰ ሰብል ለመሰብሰብ ሕይወቱንም ጉልበቱንም ሰስቶ አያውቅም፤ ካለው አካፍሎ ትምህርት ቤት፣ ጤና ጣቢያና መሰል በጎ ተግባር ሲሰራ የቆየ፤ ዜማው ህዝባዊነት፤ መገለጫም ህዝባዊነት ነበር።
በቡድኑ የአደባባይ ክህደት የመላው ኢትዮጵያዊ ልብ ተሰብሯል። ስንቶቹን የአገር ኩራት በግፍ መነጠቃችንን ስንሰማ አምርረን እንደ አንድ ልብ አልቅሰናል። ሉዓላዊነታችን ተወጋ የሚል መረጃ ሲደርሰን አንጀታችን ተንሰፍስፏል። ጉዳታቸው አሳምሞናል።
እርግጥ ነው የባንዳው ዓላማ የቀለሞች ኅብር የሆነችውን ታላቋን ኢትዮጵያ ለማፍረስ ነበር። ለእርሱ ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያዊያነት ዛሬም ቢሆን አይገባውም። ኢትዮጵያዊነት እንደ አለት ጽኑ መሆኑን ከቶ አያውቀውም።
አሸባሪው ትናንትም የነበረው መሰረት የባንዳነት ነው። ዛሬም የሚያንጸባርቀው ያንኑ ባንዳነቱን ነው። ምክንያቱም እሱ ይመቸው እንጂ የትግራይ ሕዝብ ሆነ የተቀረው የኢትዮጵያ ሕዝብ ለእርሱ ምኑም አይደለም፤ በተከፈለው እና በተገባለት ቃል ልክ አገሩንና ሕዝቡን እያዋረደ ራሱን ከሰገነት ላይ ማስቀመጥ ሕልሙ ነው።
አገራችን ኢትዮጵያ ከዚህ ከሃዲ ቡድን የጥፋት እና የባንዳነት ተልእኮ የተነሳ በርካታ ፈተናዎችን ለማሳለፍ ተገዳለች፤ አሁንም እንደተገደደች ነው። ይህም ሆኖ ግን የቀደመ ታሪኳ ሆነ አሁን እየሆነ ያለው እውነታ የሚመሰክረው ከፈተናዎች በላይ የመሆን አቅም ባለቤት መሆኗን ነው። ከሁሉም በላይ ሉዓላዊነቷን ለመድፈር የሚቀላውጠውን የትኛውንም ኃይል ማዋረድ የቀደመ ማንነቷ ነው።
ሉዓላዊነቷን አደጋ ውስጥ ሊያስገባ የሚችል የትኛውም ፈተና ቢከባት፣ ዓለም አቀፍ ጫና ቢበረታባት በፍጹም አንገቷን አያስደፋትም። ይልቁኑ ከወትሮው በተለየ ሁኔታ አንድነቷን እንደ ብረት አጽንቶ የሚያቆማት አገር ነች። ይህን ደግሞ የ50 ዓመት የክህደት ልምድ ያለው አሸባሪው ትህነግ ቀርቶ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ጠንቅቆ የሚያውቀው ጉዳይ ነው።
ዛሬ ትናንት አይደለም፤ የከሃዲው ትህነግ ጀምበር ጠልቃለች። መብራቱም ጠፍቷል። እስካሁንም ድረስ ‹ከፋፍዬ በትኛቸዋለሁ› ያላቸው ኢትዮጵያውያን በተለይ ደግሞ በእርሱ የአገዛዝ ዘመን ያደጉ ወጣቶች ሕልሙን ቅዠት በማድረግ በኩል ግንባር ቀደም ተሰላፊ መሆናቸውን በተግባር አሳይተውታል።
መሸሸጊያ ያደረገውም የትግራይ ሕዝብ ‹በቃኸኝ› ሲል ከጀግናው መከላከያ ሰራዊታችን ጎን በመቆም በእነርሱ ዘንድ አለመፈለጉን በተግባር እያሳየው ነው። የቡድኑ መዝገቡ ሲገለጥ የሚነበበው ኹከትና ሽብርተኝነት በመሆኑ ራሱ በቆፈረው ጉድጓድ እየገባ ነው።
ቡድኑ በሰሜን ዕዝ ላይ የፈጸመው ግፍ ከክብደቱ የተነሳ ሐዘኑን፣ እንኳን የሰው ልብ ምድር ልትሸከመው የሚከብዳት ነው። ይህ ግፍ የተሞላበት ክህደት በጀግናው መከላከያ ሰራዊታችን መፈጸሙን ለመዘከር በተዘጋጀ መድረክ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር እና የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ ዶክተር ዐቢይ አሕመድ፣ ‹‹ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም በግፍ የተገደለው ወታደር ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያም ተገድላለች፤ በእለቱ የተጨፈጨፈው ሰራዊቱ ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያ ህዝብም ጭምር ነው›› ማለታቸው የሚታወስ ነው።
ታድያ ይህ ክፋት መቼም ቢሆን በማንም ላይ እንዳይደገም ትውልድ በአግባቡ ሊገነዘበው ይገባል። የአሸባሪው ትሕነግ ግፍ አምና የታወሰው ‹‹አልረሳውም፤ እኔም የኢትዮጵያ ሰራዊት ነኝ” በሚል መሪ ሃሳብ ነበር፤ ዘንድሮም ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ምን ‹‹መቼም አንረሳውም›› በሚል መሪ ሐሳብ እየተከበረ ይገኛል።
የሽብር ቡድኑ በሰራዊቱ አባላት ላይ የፈጸመው ይህ ክህደት ሆነ አሰቃቂ ግፍ ሊረሳ የሚችል አይደለም። ይህ አይነቱ በአገርና በህዝብ ላይ የሚፈፀም ክህደት ዳግም እንዳይፈጸም የዚህ ትውልድ ብቻ ሳይሆን የመጪውም ትውልድ ኃላፊነት ነው፤ ለዚህም ነው ዛሬ ላይ ሆነን ‹‹መቼም አንረሳውም›› የምንለው!
ወጋሶ
አዲስ ዘመን ሐሙስ ጥቅምት 24 ቀን 2015 ዓ.ም