እንደ አገር የራሳችንን ጥለን የሌላን ፍለጋ ላይ ከተጠመድን ሰንብተናል። የትምህርት ሥርዓታችን ደግሞ የዚህ አንድ ማሳያ ነው። እውቀትን ከግብረ ገብነት አዳምሮ ስንት ሊቆችን ያፈራው የቅኔ ትምህርት እንደማይጠቅም ተዘንግቷል። እውቀትን ፍለጋ ከአገር አገር፣ ከመምህር መምህር፣ የሚንከራተቱ የቆሎ ተማሪዎች የእውቀት መሻት በቀላሉ ብዙ ያስከፍላሉ በተባሉ የትምህርት ዓይነቶች መተካት ዕጣ ክፍላቸው ሆኗል።
በዚህም የነተዋናይ ቅኔና ፍልስፍና ዘመኑን አልዋጀም በሚል በምዕራባውያን የትምህርት ሥርዓት ተተክቷል። የአክሱም ሐውልት፣ የላሊበላና የፋሲል ቤተመንግሥት የታነጹበት ጥበብ እንደ አልባሌ ታይቶ አልተጠናም፤ የትምህርቱ አካልም አልሆነም። ለስንት ዘመናት ሲወርድ ሲዋረድ የመጣው የባህል ሕክምናችን የተከተበበትን ብራና ማንበብ የሚያስችል የቋንቋ ትምህርት በዘመናዊው ትምህርት አልተካተትም። በዚህ የተነሳ ምዕራባውያን የእኛን ብራና አገላብጠው ከራሳቸው እውቀት ጨምረው የፈጠሩትን መድኃኒት በውድ ለመሸመት ተገድደናል። ይሄ ደግሞ የራሳችንን ትተን የሌሎችን የመናፈቃችን ውጤት ነው።
ይሄን ስል ግን የተሻለ ነገር ሲገኝ ከራስ እውቀትና እውነት ጋር አናብቦ መጠቀሙና ማላመዱ መልካም አይደለም እያልኩ አለመሆኑ ሊታወቅ ይገባል። ምክንያቱም የተሻለ ሆኖ ሲገኝ የሌላ አገር እውቀትና ሥርዓት መውሰዱ አይከፋም። ለምሳሌ፣ የእውቀት አውድ የሆነውን የትምህርት ሥርዓት እንመልከት። የእኛ የትምህርት ሥርዓት የአገሪቱን ነባራዊ ሁኔታ ከግምት ውስጥ ያላስገባ ከመሆኑም ባሻገር፤ ከራስ አልፈው ለሌላ አገር ልምድ ሊወሰድባቸው የሚገቡ ሥርዓቶችን በሙሉ በመተው ከውጭ በማስገባት ላይ መጠመዳችን የትምህርቱን ነገር ሆድ ይፍጀው አድርጎታል።
በዚህም እንደ ሕዝብ በቀደመው የትምህርት መስመራችን የተሻለ ግብረ-ገብነትና ጥበብን ይዘን የነበርን ማኅበረሰቦች፤ ዛሬ ከውጭ ቀድተን ባመጣነው የትምህርት ሥርዓት ታግዘን በሠራነው ሥራ በየዩኒቨርሲቲው ድንጋይ መወራወር፣ ዱላ መሰናዘር የትምህርቱ አካል እስኪመስል የዩኒቨርሲቲ ተማሪ መለያ ሆነዋል። የትምህርት ጥራቱ በመውረዱ ተማሪዎች ከታች አንስቶ እስከ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ድረስ በኩረጃ መስመር አልፈው ገብተው የሚወጡበት ዕድል ተመቻችቶላቸዋል።
ይህ ደግሞ በዚሁ ዕድል ያለፉና ከሞራልም ከእውቀትም ልዕልና ያልደረሱ «ተማርን ባይ ተመራቂዎችን» ለሌላ ጥፋት በትምህርት ዘርፉ እንዲገቡ ዕድል ሰጥቷቸዋል። ለዚህም ነው ዛሬ ላይ እውቀትና ክህሎትን በሚያስገኝ መልኩ ትምህርት እንዲሰጥ እና ተማሪዎችም አቅማቸው ተመዝኖ ወደተሻለ ደረጃ እንዲሸጋገሩ ከማድረግ ይልቅ፤ እነሱው ባለፉበት የኩረጃና የፈተና ስርቆት መስመር እንዲያልፉ እያደረጉ ያሉት። ጉዳዩ ከፖለቲካና ከሌሎችም እኩይ ፍላጎት ጋር ሲዳመር፤ ትውልዱ እውቀት እንዲያገኝ ከመጣር ይልቅ የተሠረቀ የፈተና መልስ በመስጠት ለማሳለፍ የሚኬድበት ርቀት ችግሩን ከድጡ ወደ ማጡ አድርጎታል።
ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የማህበራዊ ሚዲያዎችን መስፋፋትና ለበርካታ ዓመታት የለፉ ተማሪዎች ሕይወት ላይ የፖለቲካ አቋማቸውን ማሳየት በቀለላቸው ግለሰቦች ምክንያት ፈተናዎች ተሰርቀው ተሰራጭተዋል፤ ያልተሠረቁ ፈተናዎችም ተሰርቀዋል በሚል በተፈታኝ ተማሪዎችና በቤተሰቦቻቸው ብሎም ለፈተናው ባዘጋጇቸው መምህራን ሞራል ላይ ውሃ የሚያፈሰው የፈተና መሠረቅ ወሬ ተበራክቷል። በዚህም መንግሥት በርካታ ብር ቢያሳጣውና እንደ ቴክኖሎጂ አፋኝ ቢያስቆጥረውም ኢንተርኔትን በመዝጋት የፈተና ስርቆትን ለመከላከል ሲጥር ቆይቷል።
ይሄ ሁሉ የመጣው የራሳችንን ጥለን የሰውን በመሻታችን ነው፤ በዚህ ሥርዓት ያለፉ የተወሰኑ መምህራን የእኔ ያሉትን ለመጥቀም ሌላው ቢጎዳም ቅር አይሰኙም። ለፈተናው ስኬታማነት ታምነው ኃላፊነት የተሰጣቸው የጸጥታ አካላት፣ የፈተና አውጪም ሆኑ ፈተናው ሕትመት ላይ ሳለ በሥራ አጋጣሚ የሚያገኙ አካላት የእኔ ወገን ይጠቀም ሲሉ የእኛ አይደለም ያሉትን ወገን የጎዱ እየመሰላቸው የእኔ ያሉትን መልሰው እውቀት አልባ በማድረግ የኩረጃ ጥገኛ እያደረጉት ይገኛሉ። በዚህ እኩይ ተግባራቸውም ከታች ያሉ ተማሪዎችም ነገ በነሱ ጊዜ ፈተና እንደሚሰረቅ ግማሹ ተስፋ በማድረግ ለመስረቅ ከአሁኑ ትምህርቱን ችላ ሲል የተቀረው ፈተና ተሰርቆ የስንት ዘመን ልፋቴን ውሃ ይበላው ይሆን በሚል ስጋት ለቁዘማ ተዳርጓል።
ታዲያ በዚህ የእኔ ወገን ይጠቀም ባዮች ምክንያት በተሰረቀ ፈተና ሳያውቁ አወቁ የተባሉ ዜጎች ነገም ይሄንኑ ልምዳቸውን በማስቀጠል በጥረታቸው ወደየ ስኬታቸው ለመድረስ የሚተጉ ዜጎችን ዕድል በመንጠቅ ሥራውን ለመቆጣጠር ያገኙትን ዕድል ለመጠቀም አያመነቱም። በሚሰማሩበት የሥራ መስክም ደንበኛን ማጉላላት፣ ለበሽተኛ የተሳሳተ መድኃኒት መስጠት፣ ፍትህ ማዛባት፣ አባጣ ጎርባጣ የበዛው አስፋልት መሥራት መገለጫቸው ሆኖ ይታያል፤ ከዚህ አልፈውም አገር ዘራፊ፣ የእኔና የእነሱ የሚል መደበቂያ ፈጥረው አንዱን ጠቅሞ ሌላውን ለመጉዳት የሚተጋ የተዛነፈ እሳቤና ተግባር ባለቤት ሆነው ይገለጣሉ።
ታዲያ ይሄን ትውልድ አምካኝ የፈተና ስርቆትና መኮራረጅን ለመከላከል የሚያስችሉ በዚህ ዓመት የተለያዩ ርምጃዎች የተወሰዱ ሲሆን፤ ለምሳሌ፣ የዘንድሮ የ12ኛ ክፍል ፈተና ከዚህ ቀደም ከነበረው አራት የፈተና ኮድ ወደ 12 ኮድ ከፍ እንዲል ሆኗል። ተማሪዎች እንደ ቀድሞው በትምህርት ቤቶች ሳይሆን በዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ ፈተናውን እንዲወስዱ ተደርጓል። ፈታኞቹም የዩኒቨርሲቲ መምህራን ሲሆኑ፤ ፈተናው የሚሰጥበት ዩኒቨርሲቲ መምህር ራሱ በሚያስተምርበት ዩኒቨርሲቲ የማይፈትን መሆኑና በፈተና ስርጭትና በጥበቃ ረገድም ሙሉ በሙሉ ከክልሎች ጣልቃ ገብነት ነፃ ተደርጓል።
ተማሪዎቹ ወደመፈተኛ ዩኒቨርሲቲያቸው ከገቡ በኋላ ውጭ ካለ አካል ጋር በአካልም ሆነ በሌሎች የመገናኛ ዘዴዎች ምንም ግንኙነት እንዲኖራቸው ስለማይደረግ ተረጋግተው ፈተናውን መውሰድ እንደሚያስችላቸው ታምኖበታል። ሂደቱም በተማሪዎቹ ስነ-ልቦና ላይ ጫና እንዳያሳድር አስፈላጊው ዝግጅት የተደረገ ሲሆን፤ በዚህ መልኩ ከመስከረም 30 ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮ በመሰጠት ላይ ያለው አገርአቀፍ ፈተናም በእስካሁን ሂደቱ የፈተና ኩረጃና ስርቆትን ከመከላከል አንጻር የተነገረ ችግር አለመኖሩ ለውጥኑ በስኬት መጓዝ አንድ ማሳያ ሆኖ የሚጠቀስ ነው።
ይህ ደግሞ በቀጣይ ተማሪዎችም ሆኑ ወላጆች የትምህርት ዓላማው ፈተናን ከማለፍና ከመውደቅ የዘለለ መሆኑን አውቀው ለእውቀትና ሰብእና መገንባት የሚሠራ ትውልድ መፍጠር ላይ ማተኮር እንደሚገባ አመላካች ነው። ለዚህ ታዲያ አሁን የተጀመረው ጅምር ቢረፍድም ከመቅረት ይሻላል እንዲሉ፤ ዛሬ የ12ኛ ክፍል አገር አቀፍ ፈተና የሚወስዱ ከ976 ሺህ በላይ ተማሪዎች በሰላም ፈተናቸውን ሲያጠናቅቁ፤ ነገ በእውቀት የሚመራት አገር ስለምትኖረን ሰላማዊነቷም በዚያው ልክ የተጠናከረ ይሆናል። ምክንያቱም፣ የሚያውቀው ከማያውቀው በትክክለኛ ወንፊት የተለየባት አገር፤ ዩኒቨርሲቲዎቿ በድንጋይ ወርዋሪ ከመሞላት ይልቅ ለአገር በሚበጁት አንባቢና አሰላሳይ ዜጎች መፍለቂያ ይሆናሉ። ያኔ ከዩኒቨርሲቲዎች የሚነሱ ጥያቄዎች ብቻ ሳይሆኑ ከዩኒቨርሲቲዎች የሚወጡ ተማሪዎች ባለ ህልም፣ አገር እና ሕዝብ አሻጋሪ ይሆናሉ።
ከትዝታ ማስታወሻ
አዲስ ዘመን ሐሙስ ጥቅምት 3 ቀን 2015 ዓ.ም