ታሪክ ሰዎች በተግባር አድርገውትና ሆነውት ያለፉት እውነተኛ የሥራ መዝገብ እንጂ በመለኮት ፈቃድ የሚፈጠር ተዓምር አይደለም፡፡ ታሪክ የፈለጉትን ማድረግና መሆን እንደሚቻል ሰዎች በተግባር ሞክረው ያረጋገጡበት፣ ዛሬን ከትናንት እና ከወደፊቱ ጋር የሚያገናኝ ድልድይ ነው። ትውልድ ሥራ የሚማርበትና የሚለማመድበት ህያው የድርጊት ቤተ ሙከራ ነው እንጂ በሃሳብ ብቻ የቀረ ወይም በቢሆን ምኞት የሚፈጠር በእውነተኛው ዓለም በገሃድ ያልተፈጸመ ልብ-ወለዳዊ ፈጠራ አይደለም፡፡ እናም ታሪክ ዛሬን ከትናንትናና ከወደፊቱ ጋር የሚያገናኝ፣ የአሁኑና መጪው ትውልድ መሆንና ማድረግ እንደሚቻል በወሬ ሳይሆን በድርጊት የሚማርበት ህያው የድርጊት ቤተ ሙከራ ነው፡፡
ከዚህ በመነሳት ራሳችንን ስንመረምር የረጅም ዘመን የነጻነት፣ የአሸናፊነትና የጀግንነት የሚያኮራና ደስ የሚያሰኝ ታሪክ ያለን ሕዝብና ሀገር መሆናችንን እንገነዘባለን፡፡ ከጥንት ከቅድመ ዓለም ጀምሮ እስከ የቅርብ ዘመኖቹ ዓድዋና የፋሽስት ወረራ ለሦስት ሺ ዓመታት በኢትዮጵያ ነጻነት ላይ ደጋግማ በዘመተችው ጣሊያን፣ አስራ ስድስት ጊዜ ሞክራ አስራ ስድስት ጊዜ በተሸነፈችው ታሪካዊ ጠላታችን ግብጽ፣ በዚያድባሬዋ ሶማሊያም ሆነ ክብራችንንና ነጻነታችን ለመድፈር በሞከሩ ማናቸውም እብሪተኛ ኃይሎች በታሪካችን ተሸንፈን የማናውቅ መሆናችንም ለዚህ ሕያው ምስክር ነው፡፡
የአሸናፊነታችንና የድላችን ሁሉ ሚስጥር ደግሞ አንድነታችን ነው፡፡ እጅግ የቅርቡንና በዓለም ላይ ብቻ ሳይሆን በጠቅላላው የሰው ልጅ ፍጡር ዘንድ እንድንከበርና እንድንኮራ ያደረገንን አንዱንና ዋነኛውን የነጻነትና የክብር ታሪካችን በማሳያነት በማንሳት ልጀምር፡፡ እብሪተኞች እንደ ሰው የማይቆጥሩት የጥቁር ሕዝብ “ምንጊዜም የበላይ ነን” ብሎ የሚያምነውን የነጭ ወራሪ በጦር ሜዳ ገጥሞን ለመጀመሪያ ጊዜ ያሸነፍን እናም ለጥቁር ሕዝብ ሁሉ ኩራት የሆነውን ከዚያም አልፎ ለመላው ሰው ልጆች ሁሉ የሰውነት ክብርን ያጎናጸፈውን አኩሪ ታሪክ የሠራነው በአንድነታችን ነው፡፡ ይህም አንድነታችን ለራሳችን ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካውያን ወንድሞቻችንና ለመላው የሰው ዘር በሙሉ፣ ከራሳቸው ከነጭ ዘር የተገኙ ጭቁን ሕዝቦች ሁሉ ለነጻነታቸው እንዲታገሉ ምክንያት፣ ድል አመላካች፣ የአሸናፊነት ምልክት እንድንሆን አድርጎናል፡፡
ይሁን እንጂ የትንሽነትና ታህተ ሰብዓዊነት፣ የአጥንት ቆጠራና የኢምክንያታዊና ግዑዛዊ መንገኝነት ፖለቲካ መስራችና አቀንቃኝ የሆኑት እንደ ትሕነግና እነሱን የመሳሰሉ አላዋቂዎች ሁለቱንም፤ ታሪክንም አንድነትንም የሚጠሉና ከመጥላትም አልፈው የሚያጥላሉ መሆናቸውን ባለፉት ዓመታት በስፋት ስንስማው የኖርነውና ዛሬም ድረስ የምንታዘበው ሃቅ ነው፡፡ ትሕነጋውያን ሰዎች የፈለጉትን ማድረግና መሆን እንደሚችሉ የሚማሩበትንና በተግባርም መሆናቸውንና መቻላቸውን የሚያረጋግጡበትን ታላቁን የዕውቀትና የሥነ ልቦና ትምህርት ቤት የሆነውን ታሪክን “ተራ ተረት ተረት ነው” በማለትና ዋጋውን በማሳነስና በማጥላላት ትውልዱ ከአኩሪ ታሪኩ ተምሮ የአባቶቹንና የቀደምቶቹን ጀግንነት እንዳይደግም በታሪክ ላይ ሰፊ የጥፋት ዘመቻ ሲያካሂዱ መኖራቸው ይታወቃል፡፡ አንድነትን ደግሞ አሀዳዊነት፣ ብሔር ብሔረሰቦችን የሚውጥ… እያሉ በማጥላላት፣ ያለስሙ ስም በመስጠትና ጥላሸት በመቀባት የኢትዮጵያውያን የነጻነታቸውና የአሸናፊነታቸው ምንጭ የሆነውን አንድነት በኢትዮጵያውያን ዘንድ እንዲጠላና ተቀባይነት እንዳይኖረው ለማድረግ ዘመናቸውን ሙሉ ሲታትሩ ኖረዋል፡፡
ታሪክ ላይ ያለውን ለሌላ ጊዜ እናቆየውና ዛሬ አንድነት ቀን በመሆኑ አንድነትን በሚመለከት ትሕነጋውያንና መሰሎቻቸው በአንድነት ላይ ለዘመናት ሲሰብኩት የኖሩት ትርክት ትክክል መሆን አለመሆኑንና የአንድነትን እውነተኛ ምንነት አመክንዮ (ሎጂክንና) ሳይንስን ዋቢ አድርገን እውነታውን ለመመልከት እንሞክራለን፡፡ ለመሆኑ ግን የመልካም ነገሮች ሁሉ ጠላት የሆነውና የክፋትና የጥፋት አበጋዙ ትሕነግ እንደሚለው እውነት አንድነት ጎጂ ነገር ነውን? እነርሱ እንደሚሉትስ አንድነት ራስን በራስ የማስተዳደር መብት የሚያስቀር፤ ብሔር ብሔረሰቦችን ለመዋጥ በማጭበርበሪያነት የሚያገለግል ነውን? “የውሸት አንድነት” የሚባል አንድነትስ ሊኖር ይችላልን?
ለእነዚህ ጥያቄዎች መልሱ በአጭሩ አይደለም፣ ሊሆንም አይችልም! የሚል ነው፡፡ “ለምን?” ለሚለው አመክንዮአችንን እናቅርብ፡፡ ትሕነጋውያን ለአንድነት ሌላ ስም በመስጠትና ከእውነታው በተቃራኒ ለቃሉ አሉታዊ ትርጉም በመፈብረክ አንድነት ላይ በዚህ መንገድ አዲስ ትርክት ፈብርከው አንድነትን የማስጠላትና የማጥላላት ዘመቻ ውስጥ የገቡበት ምክንያት እነርሱ እንደሚሉት አንድነት ሕዝብን የሚጎዳ ነገር ሆኖ አይደለም፡፡ የራስን በራስ የማስተዳደር መብትን የሚነፍግ፣ ፌዴራላዊ ሥርዓትን የሚያጠፋ፣ ወደ አሃዳዊ ሥርዓት የሚመልስ፣ ብሔር ብሔረሰቦችንም የሚውጥ ስለሆነም አይደለም፡፡ እነርሱም ለሕዝብ አስበው አይደለም እንዲህ ዓይነቱ የሃሰት ትርክት ውስጥ የገቡት፡፡ እውነተኛው ምክንያታቸው ከዚህ ትርክት ጀርባ እነርሱ ማግኘት የሚፈልጉት የራስ ብቻ ተጠቃሚነት ርካሽ የጥፋት ትርፍ ነው፡፡
ይኸውም ትሕነጋውያን “የአሃዳዊነት መሳሪያ ነው” በሚል በሃሰት አንድነትን የሚወነጅሉትና እንዲጠላ የሚያደርጉት ለብሔር ብሔረሰቦች ራስን በራስ የማስተዳደር “መብት” እና ለሕዝቦች “እኩልነት” አስበውና ተቆርቁረው ሳይሆን ይህንን ሽፋን አድርገው የራሳቸውን ጥቅም ለማስቀደም ነው፡፡ ትሕነጋውን በአንድነት ላይ የዘመቱት ሁሌም እነርሱ ብቻ የበላይ ሆነው ለመኖር የሚፈልጉ ጊዜ ያለፈበት የ“እኔ አውቅልሃለሁ” የክፋት ፖለቲካ መስራችና አራማጅ በመሆናቸው በለመዱት የ“ጨቋኝ-ተጨቋኝ” የሃሰት ፍረጃ ትርክታቸው ራስን በራስ በማስተዳደር ሽፋን ሕዝብን ለመከፋፈልና ሕዝብን አለያይተው፣ በጠላትነት አቧድነው ተከፋፍሎ የተዳከመ ሕዝብን ያለ ተቃውሞ በበላይነት ለመግዛት ነው፡፡
እነርሱ እንደሚሉት አንድነት በምንም ተዓምር የብሔር ብሔረሰቦችን መብት ሊጨፈልቅ አይችልም፤ “የውሸት አንድነት” የሚባል ነገርም የለም፡፡ “ውሸት” የሚሆነው እነርሱ እንደሚያደርጉት ለብሔር ብሔረሰቦች መብት በመቆርቆር ሽፋን የራሱን የበላይነት ለማምጣት አብረው የሚኖሩ ሕዝቦችን የሚከፋፍለው የሀሰት “ተቆርቋሪነት” ነው፡፡ ይህም ለብሔር ብሔረሰቦች ያዘኑ በመምሰል የራስን የበላይነት ለማስፈን የሚደረግ ድብቅ ሴራ ነው፡፡ እናም የሕዝቦችን ራስን በራስ የማስተዳደር መብት የሚነፍገውና ማንነታቸውን የሚጨፈልቀው መደጋገፍንና መተባበርን መሰረት ያደረገውና ለእኩልነት በጋራ የሚሰራው አንድነት ሳይሆን የራሱን ጥቅም ብቻ ለማስጠበቅና በሌሎች ላይ የበላይ ሆኖ ለመኖር “አንድነትን እያጥላላ” ሕዝብን ከፋፍሎ አዳክሞ ለመግዛት የሚሞክረው የትሕነጋውያን የጥቅምና የክፋት እኩይ ፖለቲካ ነው፡፡
አንድነትማ የተራራቀውን ያቀራርባል፣ የተቃቃረውን ያስማማል፣ በልዩነቱ ምክንያት አብሮ መኖር አቅቶት የተለያየውን አንድ ያደርጋል፣ በብዙነቶችና በልዩነቶች ስምምነት በጋራ ጉዳዮች ደግሞ ሕብረት እንዲፈጠር ሕዝቦች በፍቅርና በሰላም አብረው እንዲኖሩ ያደርጋል እንጂ እንዴት አድርጎ መብትን ያፍናል? እንዲያውም “የአንዲት ሀገር ዕድገትና ታላቅነት የሚለካው በሕዝቦቿ አንድነት ነው” እንዲሉ ታላቁ ንጉሠነገሥት አጼ ቴዎድሮስ ስምምነትና ሕብረት የጋራ ዕድገትና ብልጽግና ይፈጥራል እንጂ እንዴት አንድነት ጭቆናን ይወልዳል?
እናም እላችኋለሁ ትሕነግና የትሕነግ ጀሌዎች የቱንም ያህል ትርጉሙን ለማጣመም ቢሞክሩ፣ እንዲጠላ ቢጥሩ እውነታውን መቀየር አይችሉም፡፡ በሃሰት ፕሮፓጋንዳና በዘመቻ ብዛት አይለወጥም፡፡ አንድነትን የሚጠላም አያገኙም፡፡ ምክንያቱም ዛሬም ነገም ወደፊትም አንድነት አጥፊ ሆኖ አያውቅምና፡፡ አንድነት ያው አንድነት ነው ሌላ ትርጉም የለውም፡፡ አንድነት እውነተኛ ትርጉሙ ሕብረት ነው፣ ሕብረትም ኃይል ነው፡፡ ኃይል ደግሞ በፊዚክስ ሕግ የማይጠፋ፣ የማይፈጠር- ከትውልድ ወደ ትውልድ እየተሸጋገረ ፀንቶ የሚኖር ማለት ነውና! ኢትዮጵያም በአንድነቷ ለዘላለም ትኖራለች!
ይበል ካሳ
አዲስ ዘመን ጳጉሜን 5 ቀን 2014 ዓም