ሰላ ልጆች እንዴት ሰነበታችሁ፤ የክረምት ጊዜው ሊገባደድ ነው አይደል? መቼም ቶሎ ሳያልቅ ማድረግ ያለባችሁን ነገር እያደረጋችሁ እንደሆነ አስባለሁ፡፡ በተለይም ቤተሰብን ማገዙና ለአዲሱ ዘመን መዘጋጀት ላይ ትልልቅ የሚባሉ ተግባራትን እየከወናችሁ እንደቆያችሁም ይሰማኛል፡፡ ምክንያቱም ጳጉሜ ከገባ በኋላ በፍጥነት መስከረምን እንቀበላለን፡፡ ይህ ሆነ ማለት ደግሞ እንደምታውቁት አዲሱን የትምህርት ዘመናችሁን በአዲስ መልክ ትጀምራላችሁ፡፡ ስለዚህም ይህ ከመሆኑ በፊት ልዩ ዝግጅቶች ያስፈልጋችኋልና የክረምቱን ወቅት መጠቀም ይጠበቅባችኋል፡፡ ያላጠናቀቃችሁት ነገርም ካለ በዚህች 13ኛ ወር ማጠናቀቅ አለባችሁ፡፡
ዛሬ ልጆች ስለዚህች ወር ምንነት ልናግራችሁ ፈልጌያለሁ፡፡ ብዙዎቻችሁ ትርጓሜውን ጭምር እንደምታውቁት እገምታለሁ፡፡ በዚያ ላይ ምንም የማታውቁም ትኖራላችሁ፡፡ ስለዚህም ለምታውቁት ትውስታ ለማታውቁት ደግሞ እውቀት ይሆናችኋልና ልንገራችሁ፡፡ ጳጉሜን በኢትዮጵያ ዘመን አቆጣጠር ውስጥ ትልቅ ቦታ ያላትና ዘመን ቀያሪ ወር ነች፡፡ ኢትዮጵያ በዓለም አደባባይ ብቸኛ ያደረገች መገለጫም ነች፡፡ ምክንያቱም እንደኢትዮጵያ ዘመን አቆጣጠር ዓመታት ሁሉ በአራት መደባት ይዞራሉና እነርሱን በሚገባ የምታስረዳም ነች፡፡ እነዚህ ዘመናት በሐዋርያት ስሞች የተሰየሙ ሲሆኑ፤ ዘመነ ማቴዎስ፣ ዘመነ ማርቆስ፣ ዘመነ ሉቃስ (ተጨማሪ የጳጉሜ ቀን የሚቀበለው) እና ዘመነ ዮሐንስ ይባላሉ።
ልጆች ጳጉሜን ጳጉሜ ስያሜዋን ያገኘችው ‹‹ኤፓጉሜኔ›› ከሚለው የግሪክ ቃል ነው፡፡ “ኤፓጉሜኔ” ማለት ደግሞ ጭማሪ ማለት ነው፡፡ በግእዝ ቋንቋ ተውሳክ እየተባለ ይጠራልም፡፡ ይህም እንደላይኛው ተጨማሪ ማለት እንደሆነ የኢትዮጵያ የስነፈለግ ሊቃውንት
ይናገራሉ። ጳጉሜን የኢትዮጵያ 13ኛ ወር ፀጋ መገለጫ ስትሆን፤ ልዩ ተደርጋ ትታያለች፡፡ ምክንያቱም አውሮፓዎች እንደኢትዮጵያ ጳጉሜን ለብቸዋ አድርገው አይቆጥሯትም። በወር ላይ ተጨማሪ አድርገው ይደምሯታል እንጂ፡፡ ማለትም የወርን ቁጥር እንደ ኢትዮጵያን በአንድ አይነት ቀን ሠላሳ አድርገው ሳይሆን አንዳንድ ወራቸው ላይ ሰላሳ አንድ በማድረግ በመጨመር ያካትቷታል፡፡
ልጆች የኢትዮጵያ ሊቃውንት ግን ሠላሳ ያደረጉበት የራሱ ምክንያት አላቸው፡፡ ጳጉሜን የወር ተጨማሪ ሳያደርጉ የዓመት ተጨማሪ ያደረጉበትም እንዲሁ፡፡ ሊቃውንቱ ጳጉሜን እንደ ዓመት ማጠቃለያ፣ እንደ ዘመን መፈጸሚያ አድርገው የሚያስቧት የአቷማትና በዓላት እንዲሁም ሌሎች መሰረታዊ ነገሮችን የምትለይላቸው ስለሆነች ነው፡፡
ጳጉሜን በሁለት ዘመናት መካከልም እንደ መሸጋገሪያ የምትታይ፤ ከሌሎች ወሮች በተለየ ቀኖቿ መጠን የሚቀያየሩ ብቸኛ ወር ናትም። ስለሆነም በኢትዮጵያ ዘመን አቆጣጠር ጳጉሜን ከነሐሴ በኋላ 13ኛ ወር ትባል እንጂ፣ በውስጧ የያዘቻቸው የቀናት ቁጥር በአንድ ሳምንት ካሉ ቀናት ያነሱ ናቸው። ለመሆኑ ልጆች ይህቺ የዘመን ድልድይ የሆነች ወር አንዳንዴ
አምስት ቀን ፤ ሲሻት ደግሞ ስድስትና አልፎም ሰባት ቀናትን እንደምትይዝ ታውቃላችሁ? አዎ ይህ እንዴት ሆነ ካላችሁ ደግሞ መልሱ ይህ ነው፡፡ ዓመቱን በሰላሳ ቀን ስንከፋፍለው የሚተርፉ ቀናት ይኖራሉ፡፡ እነዚህን ቀናት በመሰብሰብ 13ኛ ወር አድርገን እናከብራታለን፡፡ በተጨማሪም ዓመቱ በአውደ ፀሐይ ሲለካ 365 ቀናት ከ15 ኬክሮስ ከ6 ካሊኢት ሲሆን፤ በጨረቃ ሲለካ ደግሞ 354 ቀናት ከ22 ኬክሮስ ከአንድ ካልኢት ከ36 ሳልሲት፤ ከ52 ራብዒት፤ ከ48 ሀምሲት ነው፡፡ እናም 60 ኬክሮስ አንድ ቀን ይሆናልና እነዚህ ቀናት ተደማምረው የጳጉሜን የቀን ብዛት እንወስናለን፡፡
ጳጉሜ ሰባት የምትሆነው በየ600 መቶ ዓመት አንድ ጊዜ ሲሆን፤ በየዓመቱ የተወሰነ ሰከንድ እየተደመረ ከስድስት መቶ ዓመት በኋላ ሙሉ አንድ ቀን ይሆናልና ተጨማሪ ቀናት ይፈጠራሉ፡፡ ስለዚህም በተከታታይ አምስት ብለን የቆጠርነውን ስድስት ከዚያም ሰባት ናት እንድንል እንሆናለን፡፡ አዲስ ዓመት በጁሊያን ካሌንደር አቆጣጠር በኦገስት 29 ወይም 30 የሚጀምር ሲሆን፤ በአንድ ዓመት ውስጥ 12 ባለሠላሣ ቀናት እና አንድ ባለ አምስት (ስድስት በአራት ዓመት) 31 ቀናት ያሉባቸው ወራት የመፈጠራቸው ምስጢርም ይኸው ነው።
ልጆች ኢትዮጵያ በራሷ ቀመር ጊዜን የምትቆጥር አገር ነች የምትባለው በዘመን ውስጥ ጳጉሜን ለብቻ ይዛ በመቀጠሏ ሲሆን፤ በዘመን አቆጣጠር ውስጥ ከዕለት በታች የምንቆጥርባቸው ስድስት መለኪያዎችን መሰረት አድርጋም ትለካለች፡፡ እነሱም ኬክሮስ፤ ካልዒት፤ ሳልሲት፤ ራብኢት፤ ሃምሲትና ሳድሲት ናቸው፡፡ ከዚህ አንጻር 60 ኬክሮስ አንድ ዕለት በማለት እንቆጥረዋለን፡፡ እንደምታውቁት 1 ኬክሮስ 24 ደቂቃ ነው፡፡ ስለዚህም በዚህ ቀመር የምትሰራው ጳጉሜን አምስት ሆና ቆይታ በአራት ዓመቱ አንዴ ስድስት፤ በየስድስት መቶ ዓመቱ ደግሞ ሰባት ሆና ብዙ ነገሮቻችን እንድንወስን ታደርገናለች፡፡
ይህቺ ወር ታላለቆቹ ማለትም 30 ቀን የያዙት ወራቶችን ጭምር የምትበልጥ እንደሆነችም እስካሁን ካነሳነው መረጃ አንጻር መገንዘብ ትችላላችሁ፡፡ ማለትም እነርሱ 30 ቀናትን ይዘው ምንም ሳይፈጥሩ እርሷ ግን ሳምንት የማይሞላ ቀንን ይዛ ልደትን፣ የዓመቱን ሰርግና ሌሎች በዓላትን ትወስናለች። ስለዚህም የትንሽ ትልቅ ቀን ናትና በደንብ እወቋት በማለት ሀሳቤን ቋጨሁ፡፡ በሚቀጥለው ጊዜ ደግሞ አዲስ ዓመት ላይ ስለምንገናኝ ስለ አዲስ ዓመትና ዝግጅታችሁ እንነጋገራለን፡፡ ለዛሬ መልካም ሰንበት ይሁንላችሁ በማለት ተሰናበትሁ፡፡ ሰላም!
ጽጌረዳ ጫንያለው
አዲስ ዘመን ነሃሴ 29/2014