በአገር ላይ ሰላም ለማስፈን፤ ጥላቻና ጦርነትን ለማቆም፤ ቂምና ቁርሾ እንዲሽር ማድረጊያ ዋናው መድሀኒት እርስ በእርስ መነጋገር ብቻ ነው። በባህላችንም ችግሮችን ለመፍታት የምንጠቀመው ሽምግልናን ነው። ጸብን በእርቅ ለመደምደም ከሽምግልና የበለጠ መፍትሄ አይኖርም። እናም ከሰዎች መካከል ተጽዕኖ ፈጣሪ፣ ታዋቂና አዋቂ፣ ተወዳጅ፣ አንደበተ ርዕቱእ፣ አስተዋይ ሰው ተመርጦ አንተም አንቺም ተው ባይ ሽማግሌ ይሰየማል። ይሄ ለግለሰቦች ለቡድኖች ብቻ ሳይሆን ለአገርም ያስፈልጋል። በአገርም ጉዳይ ላይ ይሰራል። አገራችን ዛሬ የገጠማትን የሰሜኑን ችግር ለመፍታትም ሆነ በሌሎች አካባቢዎች የሚታዩትን አለመግባባቶች በሰላማዊ መንገድ ለማጠናቀቅ የምክክር ኮሚሽን አቋቁማ ወደ ስራ ገብታለች። ለንግግር ዝግጁ መሆኗንም ደጋግማ አስታውቃለች።
በሰሜኑ የአገራችን ክፍል ችግሮች ሲፈጠሩም ከጦርነት የሚያተርፍ የለምና ወደ ጦርነት አይገባ ችግሮች በሰላማዊ መንገድ ይፈቱ በሚል በተለያዩ ጊዜያት ሽማግሌዎች ወደ መቀሌ አቅንተዋል። የሰላም እናቶች የአገራችንን ሰንደቅ አላማ አንግበው፣ በእንባ እየተራጩ፣ በጉልበታቸው ጭምር ተንበርክከው ለሽምግልና አደባባይ ቆመዋል። ታዋቂና ተጽዕኖ ፈጣሪ ሰዎች ጭምር ሰላም ለህዝባችን ሰላም ለአገራችን ይሁን ብለው ሽምግልናው ተቀባይነት እንዲያገኝ ተማጽነዋል። ሆኖም ከሕወሓት በኩል የተገኘው ምላሽ ሽምግልናውን ያከበረ አልነበረም። መልዕክተኞችን በቅንነት የተቀበለ አልነበረም። በመሆኑም ወደ ተፈራው ጦርነት ተገባ።
ዛሬም ሕወሓት ለሰላም ዝግጁ መሆኑን እያሳየ አይደለም። በማንኛውም ቦታ በማንኛውም ሰዓትና ሁኔታ ለሰላም ለመነጋገር ዝግጁ መሆኑን መንግስት ቢያሳውቅም ሕወሓት ግን ለሰላም መንገዱ አደናቃፊ የሆኑ ቅድመ ሁኔታዎችን እየደረደረ፤ ለሰላም የተዘረጉ እጆችን እየረጋገጠ ይገኛል። ከሰላም ይልቅ የጦርነት ጉሰማን ወደፊት በማምጣት ላይ ነው። ይሄ ለአገርም ለህዝቡም አይበጅም፤ አገር የምታድገው፣ የምታተርፈው ከጦርነት ሳይሆን ከሰላም ነውና የሰላም እጆች ከየትኛው ቦታዎች እንዲዘረጉ ያስፈልጋል። ሽምግልና ለሁለም አትራፊ ነውና በአገራዊ የሽምግልና ባህላችን አገራችን ከመፍረስ፤ ህዝባችንን ከብተና እናትርፍ ሲሉ ሀሳባቸውን ያካፈሉን ለሽምግልና ትልቅ ቦታ የሚሰጡት እናም ለረጅም ጊዜ ሰውና ሰው በማስታረቅ ለሰላም ሰርቻለሁ። በሽምግልናም ረጅም አመት ቆይቻለሁ ያሉን የዛሬው «የወቅታዊ አምድ» እንግዳችን የሰላም አምባሳደሩ አቶ ሙዑዝ ገብረ ህይወት ናቸው።
የሰላም አምባሳደር፤ የሰብአዊ መብት እንዲሁም የመልካም አስተዳደር ተሟጋቹ አቶ ሙዑዝ ገብረ ህይወት አሁንም በአገራችን ሰላም እንዲሰፍን እየተንቀሳቀሱ ያሉ ግለሰብ ናቸው። የተወለዱት በትግራይ ክልል ኢሮብ አሲምባ ተራራ በሚባለው አካባቢ ነው። በተወለዱበት ኢሮብ አካባቢ በነበረው ትምህርት ቤት እስከ ሰባተኛ ክፍለ ከተማሩ በኋላ ወደ አዲግራት በመሄድ እስከ አስረኛ ክፍል ተምረዋል። ከዛ የተለያዩ የትግራይ ክፍሎች በመዘዋወር አስራ ሁለተኛ ክፍልን አጠናቅቀዋል። የመንግስት ስራ ከያዙ በኋላ በማታ ትምህርት ክፍለጊዜ ተምረው ዲፕሎማ ብሎም በማኔጅመንት የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ይዘዋል።
የአገራዊ ምክክር ኮሚሽን ላይ በመመረጥ ከአርባ ሁለቱ አንዱ ቀጥሎም ከአስራ አራቱ አንዱ ለመሆን ችለው ነበር። በአገሪቱ ሰላም ለማምጣት አገራዊ መግባባት ላይ እንዲደርስ ምን ስራዎች መሰራት አለባቸው? በሕወሓትና በኢትዮዽያ መንግስት መካከል ስላለው የእርቅ ሁኔታ፤ የትግራይ ህዝብ በወደፊት እጣ ፈንታ ላይ ምን መወሰን እንደሚገባውና በሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ቃለምልልስ አድርገናል፤ መልካም ንባብ።
አዲስ ዘመን፤ በአገሪቱ ውስጥ ያለው ሁኔታ በሰላማዊ መንገድ እንዲፈታ መንግስት ከሕወሓት ጋር የሰላም ምክክር ለማድረግ ኮሚሽን አዋቅሮ የሰላም ድርድሩ በየትኛውም ቦታና በማንኛውም ሰዓት ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን ገልጿል፡፡ በሕወሓት በኩል ደግሞ የሚታየው ነገር ለሰላም ዝግጁ መሆን ሳይሆን ለሰላም ደንቃራ የሆኑ ቅድመ ሁኔታዎችን እያስቀመጡ ነው። ለድርድር የተወከሉት ሰዎችም አልተገለጹም፤ ሕወሓት ፍላጎት እውን ሰላምን መፈለግ ነው ብለው ያስባሉ ? ይህን ሁኔታ እንዴት አዩት?
አቶ ሙዑዝ፡- የተወለድኩበት አካባቢ በርካታ የፖለቲካ ቡድኖች የሚንቀሳቀሱበት አካባቢ ነበር። በልጅነቴ ወደ ፖለቲካው እንድቀላቀል ምክንያት የሆነኝ ይህ ነው። በወቅቱ ሌላ ከሕወሓት ጋር የተፈጠረ በምስራቅ ትግራይ ጋሃት የሚባል አንድ ድርጅት ነበር። ያኔ የሁለቱ የፖለቲካ አስተሳሰብን ለማስታረቅ በሚል በሌሊት ወደ ካምፕ በመጠራት አጥፍተዋቸዋል። ይሄ የልጅነት ትዝታዬ ነው። ከዛም ኢህአፓ ጋር ለውይይት ተገናኝተው ተጠፋፍተዋል፡፡ ሌሎችንም የፖለቲካ ፓርቲዎች በተለያየ ጊዜ በሀሳብ አለመግባባት ላይ ሲደረስ በርካታ እኩይ ተግባሮችን እየፈጸሙ አልፈውታል። ከዚህ ከቀደመው የሕወሓት ባህሪ ስንነሳ አሁንም ለሰላም ዝግጁ አለመሆኑን መረዳት ይቻላል። ነገር ግን የሕወሓት የቀደመ ባህሪው ለእርቅ ያልተመቸ ቢሆንም፤ አሁን ግን ለህዝቡ ሲባል አንድ ወደ ሚያደርግ የውይይት ተግባር ውስጥ መገባት አለበት።
በኢትዮጵያ መንግስት በኩል ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ የሚያውቁት ኮሚቴ ተዋቅሮ በይፋ ሥራም ተጀምሯል፡፡ በኢትዮዽያ በኩል ሙሉ ዝግጁነት አለ፤ በሕወሓት በኩል ግን የሰላም ድርድሩን ተቀብለናል ቢሉም እስካሁን ኮሚቴ አላዋቀሩም፡፡ ለድርድሩም ቅድመ ሁኔታዎችን በማስቀመጥ እንዲጓተት የማድረግ ሥራ እየሠሩ ነው የሚገኙት።
ምንም እንኳን ሕወሓት በሽብር ተግባር ገብቶ አገርና ህዝብ እያመሰ ቢሆንም በክልሉ ምንም የማያውቁ ሰላማዊ ዜጎች አሉና ህዝቡ እንዳይራብ እርዳታና መድሀኒት እንዲደርስ እየተደረገ ነው። ይሄም ለነዋሪው በትክክል ይደርሰው ይሆን የሚል ስጋት አለኝ። ሆኖም ቀለቡ ለወገኖቻችንና ለቤተሰቦቻችን የሚደርስ ከሆነ መልካም ነበር። ነገር ግን የሚጓጓዘውን እርዳታ የህዝቡን ህይወት ከመታደግ ይልቅ ለእራሳቸው ሰራዊት ቀለብ እያዋሉት ነው።
እነዚህ ሰዎች ፈጣሪ ካልታረቃቸው በስተቀር በምንም አይነት ሁኔታ ሰላም አይፈልጉም። አሁንም ጦርነት እያወጁ ነው። ጦርነት ደግሞ በአፋቸው ነው እንጂ፤ ምንም ማድረግ እንደማይችሉ ቢገጥሙም እንደማያሸንፉ ያውቁታል። አቅማቸውን አሟጠዋል። እስከ ደብረ ብርሃን ደርሰው ብዙ የትግራይ ወጣትን አስፈጅተው ተመልሰዋል። በቀጣይም ከዚሁ ሽንፈታቸው ውጪ የሚያመጡት ድል አይኖርም። ይሄንን ተረድተው ለህዝቡ ሲሉ ግን አሁንም የሰላሙን መንገድ ቢመርጡ የሚል አስተያየት አለኝ። ጦርነት ህዝብን ጨራሽ ንብረት አውዳሚና አክሳሪ ነው። ነገም ቢሆን የትግራይ ህዝብ ጥያቄ ማንሳቱ አይቀርም፤ አሁንም የትግራይ እናቶች ልጆቻቸውን እየጠየቁ ናቸው። የሚሰጣቸው ምላሽ ግን በግንባር አሉ ከማለት ያለፈ አይደለም።
ለሰላም ድርድር ሲቀረብ ፊት ለፊት ተቀምጦ ይሄ ይደረግልን፤ ይሄ ይሁንልን የሚሉትን ሀሳብ ከሁለቱም ወገን መስማት ሲገባው በቅድሚያ በቅድመ ሁኔታ መንገዱን አጥሮ ለሰላም በራችን ክፍት ነው ማለት ተገቢ አይደለም። ለድርድር ቅድመ ሁኔታ ማብዛት የሰላምን መንገድ እንደመዝጋት የሚቆጠር ነው።
በትግራይ መድሃኒት የለም፤ ምግብ ማግኘት አስቸጋሪ ነው፤ ቢገኝም ዋጋው የሚቀመስ አይደለም። በርካታ የስኳር፤ የደም ግፊት፣ የነርቭ ታማሚዎች ያለ መድሃኒት የማይኖሩ ሰዎች በመድሀኒት ማጣት እንደ ቅጠል እየረገፉ ነው። ለዚህም የትግራይ ህዝብ ይጠይቃል። መንግስት ሊስማማ እንኳን ቢችል ግፍ የተፈፀመባቸው የትግራይ ህዝቦች ለሕወሓት ጥያቄ ማቅረባቸው አይቀረም። አሁን ጦርነት የሚጎስሙት ተሰባብሮ የተጠጋገነ ሰራዊት ይዘው ነው።
ህዝቡ ያለበትን አስቸጋሪ ሁኔታ እንኳን በመሸሽ በጎረቤት ክልሎች አፋርና አማራ በሌላ በኩል ደግሞ ወደ ኤርትራ እንዳይሰደድ እንደ ውሻ ከሁሉም እያናከሱት ይገኛሉ። ያም ሆኖ በየትኛው በኩል ያለው ህዝብ ችግሮችን ይረዳልና ስደተኞችን ከመቀበል አልተቆጠበም።
ሕወሓቶች በአሁኑ ወቅት ለሁለት ከመከፈላ ቸውም በላይ ህዝቡ የሚጠይቃቸውን ጥያቄ ላለመመለስ በቅድመ ሁኔታ ግንብ እያበጁ የሰላምን መንገድ እያደናቀፉ ነው። አሁን ልባቸውን መልሰው ለህዝቡ የሚጠቅመውን የሰላም አማራጭ መውሰድ አለባቸው።
አዲስ ዘመን፤- የሰላም አማራጭ በመንግስት በኩል ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ ቢቀረብም ሕወሓት ቅድመ ሁኔታዎችን አስቀመጧል። እርሶም ሕወሓቶች የቀደመ ታሪካቸውም የሚያ ሳየው ሰላም ፈላጊ አለመሆናቸውን ነው ብለዋል፡ ፡ ድጋሚ ጦርነት ቢመጣ ለትግራይ ህዝብም ሆነ ለተቀረው የአገሪቱ ህዝብ ላይ ምን የሚፈጠር ይመስሎታል?
አቶ ሙዑዝ፡- በአሁን ሰአት ሕወሓቶች በትግራይ የጦርነት ቅስቀሳ እያደረጉ ነው። ከላይ እንደተጠቀሰው እዛው የተራረፉ ምሁራን፤ ሀኪሞች፤ ገበሬዎች የተወሰኑ ከሁሉም የህብረተሰብ ክፍሎች የቀሩ ሰዎች አሉ፤ ከእነዚህ ውጪ ወጣቶቹን አስጨርሰዋል። እነዚህን የተቀሩትን ሰዎችና የተረፉትን የትግራይ ልጆችን ለማስጨረስ እየተዘጋጁ ነው።
ህዝቡ አሁን ላይ ‹‹ የትግራይ ህዝብ ወደ ጨለማ እያስገባችሁን ነው፤ ከአሁን በኋላ ጦርነት አንፈልግም›› በማለት የሕወሓትን የጦርነት ቅስቀሳ መቀበል አቁሟል። ‹‹በሚለዮኖች የሚቆጠሩ ወጣቶቻችንን ጨረሳችሁ ከእንግዲህ ልጆቻችንን አንሰጥም እያለ ነው››፡፡ ነገር ግን አሁን ችግር የሆኑት እነዚህ መሀል ከተማ የተደላደለ ኑሮ ላይ ተቀምጠው፤ ልጆቻቸውን ከጉያቸው ሳያወጡ በውጪ አገራት ያሉት ናቸው የድሃ ልጆችን የሚያስጨርሱት፤ እነሱ በምቾት እየኖሩ ድሃው የትግራይ ህዝብ ላይ የፖለቲካ ቁማር የሚጫወቱት ሀይ ባይ ያስፈልጋቸዋል።
እዛ ያለው ህዝብ በረሃብ አጥንትና ቆዳው ተጣብቆ፤ እናት ሞታ ልጅ የደረቀ ጡቷን እየጠባ፤ እናት ልጆቿ በውሃ እንዲሞላ ትንሽ ምግብ በብዙ ጨው እያበላቻቸው፤ ህይወት በመኖርና በመሞት መካከል ተቀምጦ ባለበት የጦርነት ነጋሪት መጎሰም የሚያዋጣ አይደለም። ይልቅ የሚሉትን ያህል ህዝቡን የሚወዱት ከሆነ ለትግራይ ህዝብ የሚያስቡለት ከሆነ የቀረበላቸውን የሰላም ጥሪ ተቀብለው ወደ ሰላም አደባባይ መቅረብ ይኖርባቸዋል። የኢትዮጵያ መንግስትም የያዘውን ሰላም ማስቀጠል ይኖርበታል። ካልሆነ ግን በተለይም የኢትዮጵያ አንድነት
የሚያሳስባቸው የትግራይ ተወላጆችን በመያዝ ትግራይን ነፃ ማውጣት ተገቢ ነው።
የትግራይ ህዝብም ሰቆቃው ይብቃን በማለት ይህን ቡድን ወደ ሰላም እንዲመጣ ግፊት ማድረግ ይኖርበታል። ያ ካልሆነ ግን ህዝቡ ራሱ የተያዘበትን ልጓም ፈቶ በገዛ አፉ በቃችሁ ሊላቸው ይገባል። የትግራይ ህዝብ ለበርካታ ሺህ ዓመታት በነፃነት ኢትዮጵያዊነቱን አምኖ ኖሯል፤ ወደፊትም ይኖራል። እነሱ ግን ፓርቲ ናቸውና ህዝብን አይወክሉም። የትግራይ ህዝብ ልጆቹን ለእኩይ ተግባራቸው መፈፀሚያ መስጠት የለበትም። ይህ ፕሮፖጋንዳቸው ያለቀ መሆኑን ምላሳቸው ብቻ መቅረቱን በመረዳት በቃ ማለት ይገባዋል።
አዲስ ዘመን፤ ሕወሓት በሚያሰራጨው ፕሮፖጋንዳ የአለም አቀፍ ማህበረሰቡን እያሳሳቱ ነው፤ ሕወሓትን ለሚደግፉ የውጭ ኃይሎችና ለዲያስፖራ የትግራይ ተወላጆች ማስተላለፍ የሚፈልጉት መልእክት ካለ ቢነግሩን?
አቶ ሙዑዝ፡- ከላይ እንደገለፅኩት ውጪ አገር ያሉ ሰዎች በምቾት የሚኖሩ ናቸው፡፡ ድሃውን የትግራይ ህዝብ፣ እየተጎዳ ያለውን የትግራይ ማህበረሰብ በቅርበት አያውቁትም። በፊት ለለውጥ በሚል ለአስራ ሰባት አመታት የትግራይ ልጆች እንደ ቅጠል ረግፈዋል፤ በአሁኑ ጦርነትም አምስት አመት ውስጥ የበርካቶች የሰው ህይወት አልፏል። በሌሎች ክልሎች ያሉ የትግራይ ተወላጆች ከዚህ ቡድን ጋር እንቆጠር ይሆን በማለት እየኖሩ ያሉት በስጋት ነው።
በእርግጥ እነሱን የሚደግፉ አሉ፡፡ በተለያዩ የስራ ዘርፍ የተሰማሩ ከሕወሓት ጎን የቆሙ ትግራዋይ ያልሆኑም በርካቶች ጥቅማቸው የተነካባቸው ሰዎች አሉ። እነዚህ ሰዎች ‹‹ሕወሓት ይመጣል›› ብለው እቅፍ አበባ አዘጋጅተው የሚጠብቁ እንዳሉ ሁሉ፤ ከሌላው ብሔር ብሔረሰብ ጋር በሰላም ለመኖር የሚያስቡ ፍፁም ኢትየጵያዊነት በደማቸው ውስጥ ያሉ ትግራይዋይ በርካታ ሰዎችም እንዳሉ ግምት ውስጥ መግባት ይኖርበታል። ያለ ኢትዮጵያ መኖር የሚያስፈራ ህልም ያህል የሚያሰጋቸው፤ ከኢትዮጵያዊነት መነጠል ማለት የሞት ያህል የሚከብዳቸው ትግራዋይነት ኢትዮጵያዊነት የሚል ትርጉም ብቻ በልባቸው ይዘው ስለ አገር ሰላም ሲፀልዩ የሚኖሩ የአንድነት መምጫው ቀን የሚናፍቃቸው ብዙ የትግራይ ተወላጆች አሉ።
በውጭ አገራት ላሉ ለትግራይ ተወላጆች የማስተላልፈው መልእክት ‹‹ የሚሻላችሁ ብታርፉ ነው። ትግራይ ለብቻዋ አገር መሆን አትችልም። ዝም ብላችሁ የትግራይን ልጆች እያሰጨረሳችሁ ነው፡፡ እያለቁ ያሉት የትግራይ ልጆች እንጂ አሜሪካ ያሉ የባለስልጣን ልጆች አይደሉም፡፡ እያለቁ ያሉት የትግራይ ልጆች እንጂ ጉያችሁ የደበቃችኋቸው ልጆቻቸሁ አይደሉም። ›› ማለት እፈልጋለሁ፡፡
የፈለጉትን እየበሉ ሶፋ ላይ ቁጭ ብለው ሲያሻቸው የተንጣለለ አልጋ ላይ ተኝተው እየተናገሩ ነው፡፡ እዚህ ግን ደም ይፈሳል፤ እነሱ እየተንከባለሉ እየጠረጉ ያሉት የአሜሪካን አስፓልት ነው። ለስሙ ለኢትዮጵያ አንድነትና ክብር የተማሩ ናቸው፡፡ ለአገሪቱ አንድነት ማሰብ አለባቸው። በረሃብ በጦርነት ለሚያልቀው ለትግራይ ህዝብ ማሰብ አለባቸው።
እዛ ሆኖ የሚፎክረውና ትግራይ ውስጥ እየተጎዳ ያለው ማህበረሰብ አንድ አይደለም። የትግራይን የአንድነት ታሪክ ማበላሸት አይገባም። በርካቶች በኢትዮጵያ ውስጥ ሆነው አገራቸውን እያገለገሉም ቢሆን በሁለት ቢላ የሚበሉ ነውረኞችም አሉ። ለሁሉም የሚበጀው አገር አንድ የምትሆንበትን መንገድ መከተል ነው። አገር ከመፍረስ ስትድን ሌሎች ችግሮችን ቀስ እያሉ መፍታት ይቻላል።
አንዳንዶች የአገርን ሀብት ለሽፍታ አሳልፎ የሚሰጡ መኖራቸው በጣም ይገርመኛል። አገር ለሚያፈርስ ኃይል እገዛ ማድረግ ያስተዛዝባል። እነዚህ እኩይ አላማ ይዘው የሚንቀሳቀሱ ሰዎች ትግራይ ክልል እንጂ አገር መሆን እንደማትችል አውቀው ይሄንን አስተሳሰብ ከልቦናችሁ ውስጥ አውጡ እላለሁ።
በማንኛውም አካባቢ እና በውጪ አገር ለሚኖር ለትግራይ ተወላጅ ማስተላለፍ የምፈልገው መልዕክት በትግራይ ክልል ሰላም የሚኖረው አንድም ሕወሓት ወደ እርቅ ሲመጣ ወይም ደግሞ ከምድረ ገፅ ሲጠፋ ነው። ይህ እንዲሆን በተቻለ መጠን ሕወሓት ላይ ግፊት ማድረግ ይገባል።
መናገር የቻለ፤ መደመጥ የሚገባው፤ በተለያዩ መድረኮች ሊታይ የሚችል የትግራይ ተወላጅም ሆነ የትግራይ ህዝብ ተቆርቋሪ ሕወሓቶች ያለ ምንም ቅደመ ሁኔታ ወደ ሰላም ድርድሩ መቅረብ እንደሚገባቸው ግፊት ሊያደርግ ይገባል። ይህ የሰላም ማጣት ሁኔታ በረዘመ ቁጥር እየተከሰተ ያለው ሰብኣዊ ጉዳት ከቁጥጥር ውጪ ሊሆን እንደሚችል በማሰብ የግድ አንደኛ አማራጭ ሊሆን የሚገባው የሰላም መፍትሄ ነው እላለሁ።
አዲስ ዘመን፡- እርሶ የአገር ሽማግሌ ነኝ ብለዋል የሰላሙ መንገድ እንዴት ይሁን ይላሉ? እስኪ ምክሮዎትን ለግሱን፡፡
አቶ ሙዑዝ፡- የሰላም ጉዳይ መነሳት የሚችለው ቅድሚያ ሰላም የሚል ህዝብ ሲኖር ነው። የሰላም ዋጋው ከምንም ጋር አይወዳደርም። የሰላም ዋጋ በምንም መስፈርት አይተመንም። የሰላምን ዋጋ የሚረዳው በጦርነት ውስጥ ያለ ህዝብ ብቻ ነው። ጦርነት ህዝብ ይጨርሳል፤ ጦርነት ኢኮኖሚ ያደቃል፤ ጦርነት የአገርን ኢኮኖሚ አቀጭጮ የአገርን እድገት ወደ ኋላ ይመልሳል። ጦርነት ያፈናቅላል፤ ህዝብን ከህዝብ ይለያያል። ጦርነት ካለ እንኳን ሀብት ንብረት የራስ አካልም የራስ ስለመሆኑ ዋስትና የለም።
የጦርነትን አስከፊነት በዘመናችን ያስተናገድናቸው በርካታ ጦርነቶች ካደረሱብን ጥፋቶች መገንዘብ ሳንችል አንቀርም። ጦርነት ለምድር ፍጥረታት ለሰዎች፣ ለእፅዋቱ እና ለእንስሳቱም በአጠቃላይ ለሁሉም አይጠቅምም፤ አውዳሚ ነው። በጦርነት የሚታመሱ የዓለም አገራትን አይተናል። ወደፍርስራሽነት ተለውጠዋል። ከሞት የተረፉት ዜጎቻቸው ለስደት ተዳርገዋል። እኛም ይሄንን እያስተናገድን ነው፤ ስለዚህ ከሌላውም ከራሳችንም ስህተት መማር አለብን።
ስለዚህ ሕወሓቶች አማራጫቸውን ሰላም ማድረግ አለባቸው። ሰላማዊ ቦታ ተቀምጠው የሚያጋግሉ አርፈው መቀመጥ አለባቸው፡፡ ከሰላም በላይ ቅድሚያ የሚሰጠው ነገር የለም። ኢትዮጵያ በክብር እንድትኖር፤ የለፋንበት፣ መስዋዕትነት የከፈልንበት የአባይ ግድባችን እንዲያልቅና አገራችን በእድገት ጎዳና እንድትጓዝ ለሁሉም ሰላም ያስፈልጋል።
አበባ ጉንጉን አዘጋጅተው፤ ሹርባ ተሰርተው፤ ከበሯቸውን ፀሃይ አስመትተው ሕወሓትን ለመቀበል የሚጠብቁ ሰላም ጠሎች ለሰላም ቅድሚያ ሰጥተው በእኩልነት አገራችን ኢትዮጵያ ውስጥ አንድንኖር ለማድረግ የበኩላቸውን ጥረት ማድረግ ይገባቸዋል።
ሌላው የምክክር ኮሚሽን በተቻለው ፍጥነት ሰላም ወደ ማምጣቱ ስራ መግባት ይኖርበታል። ምክንያቱም በተለያየ ቦታ ሰው እያለቀ ይገኛል። ሕወሓት ደግሞ በጣም መጥፎ ነው። በቤኒሻንጉል፣ በኦሮሚያ፣ በጋምቤላ፣ በሱማሌና በተለያዩ አካባቢዎች ለሚፈጠሩት የሰላም መደፍረሶች የእነሱ እጅ እንዳለበት መገንዘብ ይኖርብናል። ስለዚህ መላው የኢትዮጵያ ህዝብ ርብርብ ማድረግ የሚገባው ይህን ቡድን ወደ ሰላም ማምጣት ላይ መሆን አለበት።
አዲስ ዘመን፡- የትግራይ ህዝብ ከኢትዮጵያ ዊነቱ ተለይቶ በአንድ ክልል አስተሳሰብ ውስጥ እንዲታጠር ለማድረግ እየሠሩ ይገኛሉ፤ እዚህ ላይ ምን አስተያየት አለዎት?
አቶ ሙዑዝ፡- የሚፈልጉት ትግራይ ለብቻዋ አገር እንድትሆን ነው፡፡ በዚህም ብቻ ሳይበቃ ኢትዮጵያ እንድትገነጣጠልም ፍላጎት አላቸው። ቀደም ሲል ጅቡቲ፤ ኤርትራ የኛ አገር አካል ነበሩ፤ ሀምሳ አመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ሌላ አገር ሆኑ። ኃይልና ጥንካሬ የሚኖረው አብሮ በመሆን ነው። ትግራይም ከኢትዮጵያ ጋር በመሆን እንጂ ብቻዋን በመሆን አታተርፍም።
ትግራይ ተገንጥላ እንድትኖር ለሚፈልጉት ‹‹በምንም አይነት ትግራይ አትገነጠልም፤ ተገንጥላም አገር አትሆንም›› በማለት ላሳስብ እወዳለሁ። ሁለተኛ እነሱ እንደሚያስቡት ከወሎ መሬት ቆርሰው ከአፋር መሬት ቆርጠው፤ ከኤርትራ መሬት ቆርሰው አገር ለማድረግ ያስባሉ፤ ይሄንን ደግሞ በአስራ ዘጠኝ ሰማኒያ ሶስት ዓመተ ምህረት ኢትዮጵያ ከመምጣት እዛው ማድረግ ይችሉ ነበር። ምክንያቱም ትግራይ በእጃቸው ነበረች። አልቻሉም፤ አሁንም ይሄ እንደማይሆን ያውቁታል።
አሁን ሀሳባቸው በሁመራ በር ተከፍቶ በሱዳን በኩል ግብፅ ኢትዮጵያ መጥታ አገር እንድትረብሽ የማድረግ ሴራ ነው። እነዚህ ኢትዮጵያን አፈራርሰው ትግራይ ለብቻዋ ትኑር ሲሉ በርካታ ሤራዎችን እየሰሩ ናቸው። ለምሳሌ ባለፈው ሰዎች እስር ቤት ይገቡ በነበረ ጊዜ ያልሆነ ጥቆማ በመስጠት ሁሉም ትግራዋይ መንግስትን እንዲጠላ የማድረግ ሴራ ሲሠሩ ነበር። ሕወሓቶች ባልና ሚስት መካከል ገብተው እርስ በእርስ የሚያሰልሉ ናቸው። ለተንኮል ሲሆን እጃቸው ረጅም ነው።
የትግራይ ህዝብ ግን ሀሳቡን ሰብስቦ ለአሁኑም ሰላም፤ ለወደፊትም ከታሪክ ተወቃሽነት ለመዳን ትግራዋይነት ኢትዮጵያዊነት መሆኑ ላይ ምንም አይነት ድርድር ውስጥ ሳይገባ ለሰላም በተቻለው አቅም ጥረት ማድረግ አለበት። እነዚህንም ኃይሎች ወደ ሰላም መድረክ እንዲመጡ ግፊት ማድረግ ይገባዋል።
አዲስ ዘመን፡- ስለነበረን ቆይታ በዝግጅት ክፍሉ ስም ከልብ አመሰግናለሁ።
አቶ ሙዑዝ፡- እኔም አመሰግናለሁ።
በአስመረት ብስራት
አዲስ ዘመን ሐሙስ ነሐሴ 19 ቀን 2014 ዓ.ም