የመጀመሪያው አውሮፕላን ወደ ኢትዮጵያ ከገባ ነሐሴ 12 ቀን 93 ዓመት ሞላው። በነዚህ ዓመታትም የአገሪቱ አቪየሽን ዘርፍ ብዙ ውጣ ውረዶችን አሳልፎ ዛሬ ላይ ለትልቅ ስኬት በቅተል። በዛሬው የሳምንቱን በታሪክ አምዳችንም የመጀመሪያው አውሮፕላን ወደ ኢትዮጵያ ሲገባ የነበረውን ኩነት ከሪፖርተር ጋዜጣና ከሌሎች ምንጮች ያገኘነውን መረጃ እንደሚከተለው አጠናክረነዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ በሰማው አዲስ ነገር ተደንቆ ከረመ። ይህ መደነቅ ጉጉት ፈጥሮበታልና ከባዱ የክረምት ብርድ ከቤቱ አላዋለውም። በዚያን ወቅት በተሰበሰበበት አጋጣሚ ሁሉ በከተማው ስለተናፈሰው እንግዳ ነገር ሲያወጋ ከርሟል። ተሰባስቦ ቡና ሲጠጣ፣ በእድርና እቁብ ሰበብ ሲገናኝ፣ ቤተሰብ ሰብሰብ ብሎ ወግ ሲያደራ በቅርቡ ይሆናል ስለተባለው ጉዳይ እያነሳ አጀብ አለ።
በሰማው ነገር እጁን በአፉ የማይጭን ከቶም አልነበረም። ወሬው ሁሉ አዲስ የሚሰማው አስደናቂ ነገር ሆነ። ቀኑ ሲደርስ ንጋት ላይ ተጠራርቶ አጀብ የተባለለትን ነገር ለማየት ወጣ።
ነሐሴ 12 ቀን 1921 ዓ.ም የአዲስ አበባ ነዋሪ የሰማውን ለማመን፤ የተባለውን አዲስ ክስተት ለማረጋገጥ ከ15 ኪሎ ሜትር በላይ አቋርጦ በባዶ እግሩ ወደ ገፈርሳ ሜዳ ተመመ። ነዋሪው ለጉዳዩ አዲስ ነበርና እንኳን አምኖ መቀበል፣ ጭራሽ ለማሰብ ፈጽሞ አይቻለም ያለውን እውነት ለማረጋገጥ በቦታው ተገኘ። ይህ ክስተት ከተከሰተ ያለፈው ነሐሴ 12 ቀን 93 ዓመት ሞላው።
ክስተቱ እንግዳ በመሆኑ የህዝቡ ስሜት የተለየ ነበር። የአገሪቱ ንጉስ ቀዳማዊ አጼ ኃይለሥላሴ ከነሚኒስትሮቻቸው፣ መኳንንቱ፣ መሳፍንቱ፣ ዲፕሎማቶችና የሃይማኖት አባቶች ሳይቀሩ የታደሙበት ነበር። ይሄ ክስተት በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ እጅግ እንግዳ የሆነውን ነገር ይዞ መጣ። ገፈርሳ ከወትሮ በተለየ በአበባ ተሽቆጥቁጣ፣ በዘንባባ ተሞሽራና በሰንደቅ ዓላማ አሸብርቃ አዲሱን ሁነት ለማስተናገድ ትጠባበቃለች።
ይህ ሁሉ ጉጉትና ጥበቃ ያኔ ብዙዎች ‹‹በራሪው የሰይጣን ክንፍ›› ያሉትን አውሮፕላን ለማየት ነው። እዚያ ሜዳ ላይ የተሰባሰበው ሕዝብ በርቀት በሚያያቸው አሞራዎች ሁሉ አዲሱ እንግዳ እየመሰለው ቆየ። ሰማይ ላይ አይኑን ተክሎ ‹‹በራሪው ሰይጣን›› ያለውን የመጀመረያውን አውሮፕላን ለማየት ጓጓ።
ከብዙ ቆይታ በኋላ ግን የሆነ ድምፅ ከርቀት ወደ ህዝቡ ቀስ በቀስ ይቀርብ ጀመር። ሕዝቡ በየአቅጣጫው ባለ የሰማይ ጥግ በዓይኑ አማተረ። ወቅቱ ክረምት ነው፤ ሰማዩ ዳምኗል። ምንም የሚታይ ነገር ሳይኖር ድምፅ ብቻ ይመጣል። ቆይቶ ግን ድምፁም በጣም እየቀረበና ይበልጥ እየጮኸ መጣ። ያኔ ጉጉቱ ወደ ፍርሀት ተቀየረ።
ከጥቂት ቆይታ በኋላ የክረምቱ ጭጋግ ከተዋጠው ሰማይ፣ ያ ሲጠበቅ የነበረው ‹‹በራሪው የሰይጣን ክንፍ›› ደመናውን ቀዶ ወጣ። ወደ መሬት መቅረብም ጀመረ። ሕዝቡ በድንጋጤ በየአቅጣጫው ይፈረጥጥ ጀመር። ታሪካዊው የመጀመሪያው አውሮፕላን ገፈርሳን ደጋግሞ ዞሮ ድንኳኖቹ ፊት ለፊት ዠርገግ ብሎ አረፈ።
የህዝቡ ትርምስ ቆመ፣ ድንጋጤው ወደ ደስታ ተቀየረ። ገፈርሳም ተደሰተች፣ ፉጨትና ጩኸት በረከተ። ሕዝቡ ካፒቴኑን ተሸክሞ ተቀበለው። ንጉሱ ዘለው ከድንኳናቸው ወጡ። ተስፈንጥረው ካፒቴኑ ላይ ተጠመጠሙበት። ይህ ሁሉ የሆነው የመጀመሪያዋ ፓቴዝ አውሮፕላን ወደ አገራችን በመምጣቷ ነበር።
መንገድ ሳይሠራለት፣ ሐዲድ ሳይነጠፍለት በአየር ላይ ተንሳፎ የመጣው ያ አውሮፕላን የአየር ባቡር የሚል ስም ወጣለት። በዚህ ሁኔታ ነበር የዛሬ 93 ዓመት በኢትዮጵያ የአቪዬሽን ታሪክ የተጀመረው።
ንጉስ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ አቀባበሉን በማስመልከት እዚያው ለተሰበሰበ ህዝብ እንዲህ በማለት ንግግር አደረጉ። “ኢትዮጵያ በጥንት ሥልጣኔዋ ዘመን ከኢየሩሳሌምና ከአረብ፣ ከህንድም መንግሥታት ጋር በንግድና በፖለቲካ ትገናኝ ነበር። አሁንም ያንን ማዕረጓንና ኃይሏን ለመመለስ፣ እንዲሁም የአገር ውስጥ ጉዳያችንን በፍጥነት ለመፈጸም እንዲረዳን ይኼንን የአየር ባቡር አስመጣን…”
ይህ የንጉሡን ንግግር ስንመረምረው የአውሮፕላኑ መምጣት ሁለት ዓበይት አላማዎች እንደነበሩት መረዳት ይቻላል። የመጀመሪያው ብሔራዊ ኩራትን መመለስ ሲሆን በዚያውም ኢኮኖሚያዊ ጥቅምን መቀዳጀት የሚሉ ትልልቅ ዓላማዎች አሉት። ዛሬ ለኢትዮጵያ ኩራት የሆነውና የአህጉሪቱ ታላቁ አየር መንገድ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የዚሁ ዓላማና ጥረት ውጤት ነው።
የመጀመሪያው አውሮፕላን ወደ ኢትዮጵያ የገባበት ዘመን በአገሪቱ የታሪክ ሒደት ውስጥ ከተን ስንመለከተው፣ ከዳግማዊ አፄ ቴዎድሮስ ጀምሮ ኢትዮጵያን የማዘመንና የቀድሞ ክብሯን ለመመለስ ሲደረጉ ከነበሩ ጥረቶች መካከል አንዱ ሆኖ እናገኘዋለን።
በኢትዮጵያ አቨየሽን ታሪክ ስራ የተጀመረው ንጉሰ ነገስቱ በገዟቸው 3 የፈረንሳይ ስሪት ፖቴዝ አውሮፕላኖች ነው። የመጀመሪያውና በጽሑፉ መጀመሪያ ላይ የተጠቀሰው ፈረንሳዊው ሙሴ አንድሬ ማዬ ከጅቡቲ በማብረር ነሐሴ 12 ቀን 1921 ዓ.ም ያረፈችው ናት። አውሮፕላኗም ‹‹ንስረ ተፈሪ›› ተብላ ተሰየመች። ጅቡቲ ቀርተው የነበሩትን ሁለቱን ፖቴዝ አውሮፕላኖች አንዷን ካፕቴን ማዬ ፣ ሁለተኛዋን ደግሞ ጀርመናዊው ካውንት ሼዝበርግ እያበረሩ መስከረም 12 ቀን 1922 ዓ.ም ወደ አዲስ አበባ አመጧቸው።
እነዚህ አይሮፕላኖች ከመጡ በኋላ ‹‹ንስረ አስፋ ወሰን›› እና ‹‹ንስረ መኮንን›› የሚል ስያሜ ተሰጥቷቸው ነበር። ከዚያም የፈረንሳይ ተፎካካሪ የነበረው የጀርመኑ ጀንከርስ (Junkers) አውሮፕላን በባሮን ሻን ኢግል አብራሪነት በከተማዋ ውስጥ ጃን ሜዳ አረፈ። በጃንሜዳ ውስጥ በማረፉ ከፈረንሳዩ አውሮፕላን የበለጠ በርካታ ተመልካች እንዲኖር አድርጐታል።
የመጀመሪያ የአገር ውስጥ በረራ ጀንከርስ አውሮፕላን አዲስ አበባ ከደረሰ አንድ ወር በኋላ ነበር የአገር ውስጥ በረራውን የጀመረው። ያ ጉዞው የመጀመሪያው የአገር ውስጥ በረራ መሆኑ ነው። ያልተሳካው የመጀመሪያው በረራ ሊባልም ይችላል። ጀንከርስ የመጀመሪያ የአገር ውስጥ በረራው ሲሆን ተልዕኮውም የኢሊባቡር ጠቅላይ ገዥ የነበሩትን ራስ ናደውን ለማምጣት ነበር። ይህም አውሮፕላን በኢትዮጵያ በሽተኛ ለማጓጓዝ ሲበር የመጀመሪያው መሆኑ ነው። ራስ ናደው በጽኑ ታመው ነበርና የሚተኙበትን አልጋና ፍራሽ ጨምሮ ወደ ዋና ከተማቸው ጐሬ በረራውን ቀጠለ። ነገር ግን በአየር ሁኔታው አመቺ አለመሆን ምክንያት ተመልሶ ‹‹እንድብር›› አካባቢ ለማረፍ ተገደደ። በማግስቱም ወደ አዲስ አበባ ተመለሰ።
ከ1921 እስከ 1928 ዓ.ም. ድረስ የነበሩት ሰባት ዓመታት የኢትዮጵያ የአቪዬሽን ኢንዱስትሪ ጠንካራ መሠረት የተጣለበት ወቅት ነበር። አውሮፕላን ከማብረር እስከ አውሮፕላን መሥራት፣ ከበረራ ትምህርት ቤት እስከ አውሮፕላን መጠገኛ ጋራዥ (ሀንጋር)፣ ከኢትዮጵያውያን አውሮፕላን ጠጋኞች እስከ ሴት አብራሪዎችን ማፍራት የተቻለበት ወቅት ነበር።
በኋላ ላይ የፋሽስት ወረራ በአቬሽን ኢንዱስትሪው ላይ ከፍተኛ ውድመት አደረሰ። በዚያም እጅግ አመርቂ የነበረው ሂደት ተገታ። አገራችን ከፋሽስት ወረራ በ1933 ዓ.ም. ነፃ በወጣች ማግሥት የኢትዮጵያ አየር መንገድ የአገራችን የነፃነት ብሥራት ሆኖ ተቋቋመ። አየር መንገዱ በዚህ ታሪካዊ ወቅት መቋቋሙ ከኋላ የአገሪቱን ቁጭት፣ ከፊት ደግሞ የሕዝቦቿን ራዕይ ተሸክሞ የሚበር አየር መንገድ እንዲሆን አደረገው።
በጸሐፊ ትዕዛዝ አክሊሉ ሀብተወልድ አስተባበሪነት በኢትዮጵያ መንግሥትና በአሜሪካው ትራንስ ወርልድ ኤርላይንስ (TWA) ኩባንያ መካከል በተደረሰ ስምምነት መስከረም 1 ቀን 1938 ዓ.ም በ2 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር የኢትዮጵያ አየር መንገድ በቦርድ ተቋቋመ። የመጀመሪያ ዓለም አቀፍ በረራውንም መጋቢት 30 ቀን 1938 ዓ.ም በአስመራ በኩል በማድረግ ወደ ካይሮ አደረገ።
ከዚህ በኋላ አየር መንገዱ አገሪቱ የምትገኝበትን ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታና የጥንታዊ ቅርስ ባለቤትነት ዕድሎችን እየተጠቀመ በፍጥነት ማደግ ጀመረ። ከተቋቋመ ገና በአራተኛ ዓመቱም ዓለም አቀፍ በረራዎቹን ከካይሮ በተጨማሪ ወደ ጂቡቲ፣ ኤደን፣ ጅዳ፣ ናይሮቢ፣ ፖርት ሱዳን፣ ካርቱም፣ ቦንቤና ካራቺ አስፋፋ።
በኢትዮጵያ የአቪዬሽን ታሪክ ውስጥ አጠቃላይ ኢንዱስትሪውን ሥር ነቀል ወደ ሆነ የላቀ ደረጃ የወሰዱ ሁለት አብዮቶች ተከስተዋል። ሁለቱም አብዮቶች ታዲያ የተከሰቱት በኢትዮጵያ አየር መንገድ የዕድገት ግፊት የተነሳ ነው።
የመጀመሪያው አብዮት የመጣው የኢትዮጵያ አየር መንገድ በ1952 ዓ.ም የቦይንግ ጄት አውሮፕላኖችን ለመግዛት በመወሰኑ ነው። ይህ ውሳኔ አብዮት ያስከተለበት ምክንያት ደግሞ በወቅቱ የነበረውና በጣሊያን የተሠራው የልደታው አየር ማረፊያ፣ አዲስ የሚገዙትን ጄት አውሮፕላኖች የማስተናገድ ብቃት የሌለው መሆኑ ነው። በመሆኑም ውሳኔው ሌላ አዲስ ዘመናዊ አየር ማረፊያ ቦሌ ላይ እንዲሠራ ከማድረጉም በተጨማሪ የቅኝት (Air Navigation) እና የአየር ትራፊክ መቆጣጠሪያ መሣሪያዎችም ከጊዜው ጋር እንዲዘምኑ ምክንያት ሆኗል።
ከአዲሱ ኤርፖርት ግንባታ ጎን ለጎንም አየር መንገዱን ኢትዮጵያዊ የማድረጉ ከፍተኛ ጥረትም የሚዘነጋ አይደለም። የአየር መንገዱን ቁልፍ የሥራ ሒደቶችን (የበረራ፣ የጥገና፣ የሽያጭና የአስተዳደር ሥራዎችን) ከአሜሪካውያን ተረክቦ በኢትዮጵያውያን ባለሙያዎች የመተካቱ ጥረት እየተሳካ ሄዶ፣ በ1963 ዓ.ም. ኮሎኔል ስምረት መድህኔን የመጀመሪያው የአየር መንገዱ ኢትዮጵያዊ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አድርጎ በመሾም ትልቅ እመርታ አስመዘገበ።
ሁለተኛው አብዮት ደግሞ ርዕይ 2025 (እ.ኤ.አ.) ነው። ይህ ርዕይ ልክ እንደ 1952 ዓ.ም. ውሳኔ ሁሉ በአዲስ አበባ ኤርፖርትና በአየር ትራፊክ ቁጥጥሩ ላይ ሥር ነቀል ለውጥ እንዲመጣ ያስገደደ ክስተት ብቻ ሳይሆን፣ የአየር መንገዱንም የውስጥ አደረጃጀት ከመሠረቱ እየቀየረ ያለ ውሳኔ ነው።
እ.ኤ.አ በ2010 የተቀረፀው ይህ የ15 ዓመት የዕድገት መርሐ ግብር አየር መንገዱን ወደ ሰባት የተለያዩ የትርፍ ማዕከልነት በማዋቀር ወደ ግዙፍ የአቪዬሽን ግሩፕ ኮርፖሬትነት እያሳደገው ይገኛል። በዚህም አየር መንገዱን እ.ኤ.አ. በ2025 በ112 አውሮፕላኖች 18 ሚሊዮን መንገደኞችንና 710,000 ቶን ጭነቶችን ወደ 92 ዓለም አቀፍ መዳረሻዎች በማጓጓዝ በዓመት አንድ ቢሊዮን ዶላር ትርፍ ላይ ለመድረስ አልሟል። በእርግጥ አየር መንገዱ በአሁኑ ወቅት የዓለም አቀፍ መዳረሻዎችን ብዛት በመጨመር ከዕቅዱ ቀድሞ ማሳካት ችሏል።
ይህ የአየር መንገዱ ርዕይ የአዲስ አበባ ዓለም አቀፍ ኤርፖርትን በሁለት ዙር፣ በ2004 ዓ.ም በ1.1 ቢሊየን ብር እና በኋላም በአምስት ቢሊዮን ብር፣ ግዙፍ የማስፋፊያ ፕሮጀክቶች ውስጥ እንዲገባ ከማድረጉም ባሻገር፣ የኢትዮጵያ ኤርፖርቶች ድርጅት በአዲስ አበባ አቅራቢያ ሌላ ግዙፍ የኤርፖርት ከተማ የመገንባት ውሳኔ ላይ እንዲደርስ ምክንያት ሆኗል። በአየር ትራፊክ ቁጥጥሩ ላይም ከፕሮሲጀራል ቁጥጥር እጅግ ዘመናዊ ወደሆነው የራዳር የአየር ትራፊክ ቁጥጥሩ እንዲቀየር ምክንያት ሆኗል። ዛሬ ላይ የኢትዮጵያ አየር መንገድ እንደ ቦይንግ B787 እና ኤርባስ A350 ያሉ ዘመናዊ አውሮፕላኖች ባለቤት ሆኗል። በሌሎች አየር መንገዶች ላይም እያደረገ ያለው ኢንቨስትመንትም የዚሁ ራዕይ 2025 አካል ነው።
በሄደበት የዓለም ጥግ ሁሉ በኩራት የአገራችን አምባሳደር የሆነው አየር መንገዳችን፣ የአገራችንን የቀድሞ ‹‹ማዕረጓንና ኃይሏን መመለስ›› የሚለውን ታሪካዊ ተልዕኮ በብቃት እየተወጣ ይኼው ዛሬ ላይ ደርሷል።
ተገኝ ብሩ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 15 ቀን 2014 ዓ.ም