
– ግድቡ እስኪጠናቀቅ ድጋፋቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉም ተናግረዋል
አዲስ አበባ፦ የሁለቱ ተርባይኖች ሃይል ማመንጨት ለጠላት ሽንፈት ለኢትዮጵያውያን ደግሞ ትልቅ ድል መሆኑን የአዲስአበባ ነዋሪዎች ገለጹ። ግድቡ እስኪጠናቀቅ የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው እንደሚቀጥሉም ተናግረዋል።

አራት ኪሎ አካባቢ ያገኘናቸው አቶ ጌታነህ ይገዙ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት በሰጡት አስተያየት፣ የተርባይኖቹ ስራ መጀመር ኢትዮጵያውያን ድል ያገኙበት ብቻ ሳይሆን ጠላቶች ስለኢትዮጵያውያን እንዲያውቁና እንዲረዱ የሚያደርግ ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያ ሕዝብም አንድ የሚያደርጉት ጉዳዮች ላይ በአንድነት እንደሚሰራና ለጋራ ጉዳዮች በጋራ እንደሚቆም የሚሳይ መሆኑን የኢትዮጵያ ጠላቶች ሊረዱትና ሊገነዘቡት ይገባል ያሉት አቶ ጌታነህ፣ ያለብንን ውስጣዊ ችግር ፈትተን ካደጉት ሀገራት እኩል የምንሆንበት ጊዜ ቅርብ ነው ሲሉም ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ሕዝቦች የአንድነት መገለጫ አርማ የሆነው የህዳሴ ግድብ ሁለት ተርባይኖች ኃይል ማመንጨት በመጀመራቸው ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ እንኳን ደስ አላችሁ በማለት ሃሳባቸውን የጀመሩት ደግሞ ወይዘሮ ሸዋጌጥ ሰይፈ ናቸው።
የህዳሴው ግድብ የሁላችንም አሻራ ያረፈበት፣ ከጨለማ የሚያወጣን የጋራ ብሄራዊ ሀብታችንና የጥንካሬያችን መገለጫ ነው ያሉት ወይዘሮ ሸዋጌጥ፤ እኛ ኢትዮጵያውያን ያለማንም ጣልቃ ገብነት በራሳችን ጉልበት፤ በራሳችን የሰው ሃይል እራሳችንን ችለን እዚህ በመድረሳችን እጅግ ልኮራ ይገባል ብለዋል።
የህዳሴ ግድቡ የሁሉም ኢትዮጵያውያን አሻራ ያረፈበት ፕሮጀክት እንደመሆኑ መጠን በቀጣይም ሕዝቡ የፕሮጀክቱን ቀሪ ስራ ለማጠናቀቅ የተጀመረውን ተሳትፎ አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አሳስበዋል።
ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሁለት ተርባይኖች ኃይል ማመንጨት በመጀመራቸው መደሰታቸውን የገለጸው ደግሞ ወጣት ተስፋዬ ብርሃኑ ነው።
ሁለቱ ተርባይኖች ሃይል ማመንጨት መጀመራቸው መብራት የማያገኙ አካባቢዎች መብራት የሚያገኙበት ጊዜ ሩቅ አለመሆኑን የሚያመለክት ነው ያለው ወጣት ተስፋዬ፣ ሀገራችን በኢኮኖሚ፣ በማሕበራዊና በፖለቲካዊ መስኮች ለውጥ እንድታመጣ ያስችላታል ብሏል።
የኢትዮጵያ ጠላቶች አላስፈላጊ የሆኑ ድርጊቶቻቸውን ትተው ሰላማዊ በሆነ መንገድ ችግሩን ለመፍታት መሞከር ይኖርባቸውል ያለው ወጣ ተስፋዬ፤ ከዚህ ውጪ የሚደረግ ድርጊት ከጠቀሜታው ይልቅ ጉዳቱ ይበልጣል ሲልም ተናግሯል። ኢትዮጵያ ግን በሁሉም አማራጮች አሸናፊ እንደምትሆን ሊገነዝቡት እንደሚገባም አሳስቧል።
ሌላው አስተያየት ሰጪ አቶ አያሌው አሰፋ በበኩላቸው፣ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ውስብስብ ችግሮችን አልፎ ኃይል ማመንጨት መጀመሩ ኢትዮጵያውያን በአንድነት የማንሻገረው ችግር እንደሌለ ማሳያ ነው ብለዋል። ሕፃን አዋቂ ሳይል ሁሉም ያለውን አውጥቶ ያስገነባው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ለዚህ ደረጃ መብቃቱ የሚያኮራ ተግባር መሆኑንም ገልጸዋል። “እኛ ኢትዮጵያውያን በራሳችን ማንኛውንም ልማት እውን ማድረግ እንደምንችል ከዓድዋ ድል ቀጥሎ ታላቁ ህዳሴ ግድብ ህያው ምስክራችን በመሆኑ ኮርቻለሁ” ብለዋል።
የግድቡ ሁለት ተርባይኞች ኃይል ማመንጨት ከመጀመራቸውም በላይ አንድነታችንን ለማጠናከር፣ ብሄራዊ መግባባት ለመፍጠርና ሀገርን በጋራ ለማልማት ትልቅ አቅም ይሆነናል ብለዋል።

ወጣት ሶስና አፈወርቅ በበኩሏ፣ የህዳሴው ግድብ ሁለት ተርባይኖች ኃይል ማመንጨት መቻላቸው ሀገራዊ ዲፕሎማሲውን ለማጠናከር፣ የውጭ ጫናውን ለማቃለልና አንድነታችንን ለማጠናክር ያግዛል ብላለች።
የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በተለይም ለወጣቱ ዘርፈ ብዙ ተስፋዎችን የሰነቀ የኢኮኖሚ መሰረታችን በመሆኑና ለፍሬ መብቃቱ ድርብ ደስታ መሆኑን ገልጻለች።
የግድቡን ግንባታ ለማስተጓጎል ተባብረው ይሰሩ የነበሩ አንዳንድ የውስጥና የውጭ ኃሎችን ያሳፈረ፤ ወዳጆቻችንን ደግሞ ደስታ ያጎናፀፈ ልዩ ቀን ነው ስትልም ተናግራለች።
የህዳሴ ግድብ ከዚህ ደረጃ ለመድረሱ ዋነኛው ሚስጥር የኢትዮጵያ ሕዝቦች በአንድነት መቆም ነው” ያሉት አቶ ዘላለም ምሬሳይ፣ ግድቡ እስኪጠናቀቅ ሕብረተሰቡ ድጋፉን አጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባው ገልጸዋል።
የህዳሴ ግድቡ ሙሉ በሙሉ እስኪጠናቀቅ የጀመሩትን ድጋፍ አጠናክረው እንደሚቀጥሉም ነዋሪዎቹ ተናግረዋል።
ሳሙኤል ወንደሰን
አዲስ ዘመን ነሐሴ 6 /2014