የአማርኛው መዝገበ ቃላት ዓባይን ዋና፣ አባት ሲል ይገልጸዋል። ከዚህ እውነት በመነሳት ዓባይ ማለት ዋና ማለት እንደሆነና አባት ማለት እንደሆነ እንደርስበታለን። ይህ ስም የስሞች ሁሉ በኩር፣ የክብሮች ሁሉ ቁንጮ ነው። ይህ ስም የእኛ ስም ነው። ይህ ስም የኢትዮጵያውያንን ባህልና ታሪክ ተንተርሶ ነፍስ የዘራ ነው። ይህ ስም እትብቱን ከእትብታችን ቀላቅሎ፣ ጥቁርነትን ለብሶ፣ ታሪክና ሥልጣኔዓችንን ተጋርቶ ከጉያችን መንጭቶ የሚፈስ ነው። ታዲያ አባት ቢባል ምን ያንስበታል? ዓባይ ዋናችን ነው፤ ከዚህ ውጪ ምንም ሊሆን ዓይችልም። ለዘመናት በአቅምና በኢኮኖሚ ችግር አባትነቱን ግብጾች ቀምተውን በራሳችን ታሪክ ባይተዋር አድርገውን ነበር። ለዘመናት በእኛ አባትነት ግብጽን ጨምሮ የታችኞቹ ተፋሰስ ሀገራት ሲያጌጡና ከፍ ሲሉ ነበር። ዘመን ተቀይሮ ይሄኛው ትውልድ በአቅምም በኢኮኖሚም በርትቶ ዓባይን ሊገድብ ሲነሳ ግብጾች አባታችንን አንሰጣችሁም ወልደን ያሳደግነው ልጃችን ነው ሲሉ አመጹብን። አባታችንን ላይሰጡን ብዙ ተሟገቱን፣ ብዙ ዋሹ ይሄ ትውልድ ግን የዋዛ አልነበረምና አባቱን መለሰ..ዓባይንም ገደበ።
እናም ዓባይ የጋራ ስማችን ነው… መታወቂያችን። ኢትዮጵያዊነት የወል ስም ካለው ዓባይ ነው። በብዙ ነገር ተለያይተን በዓባይ ጉዳይ ላይ ግን ዓንድ ነን። ምክንያቱም ዓባይ በጋራ የጻፍነው የጋራ ታሪካችን ስለሆነ። በኢትዮጵያ ምድር እንደ ዓባይ በጋራ ጀምረን በጋራ ልንጨርሳቸው የሚገቡ በርካታ ነገሮች ዓሉ። መለያየት ያበላሻቸው፣ እኔነት ያጸለማቸው በጣም ብዙ ጉዳዮች አሉን። እኚህ ጉዳዮቻችን ተጀምረው እንዲያልቁ፣ ስኬትና ከፍታ፣ እድገትና ስኬት እንዲሆኑን በአንድነት መቆም አለብን። ዓባይ የአንድነታችን ውጤት ነው። ዓለም በተነሳብን ጊዜ፣ ኃያላኖቹ ለግብጽና ሱዳን ወግነው በተነሱብን ጊዜ አንድ ላይ ነበርን። በብዙ ልዩነት ውስጥ አብረን ነበርን። ይሄን ነው የኢትዮጵያዊነት ቀለም የምላችሁ። ይሄን ነው የጋራ ስማችን የምላችሁ። ይሄ አንድነት ዛሬ ላሉብን ችግሮች አስፈላጊ ነው። ዓባይን በጋራ እንደገነባነው ሁሉ በጋራ የምንወጣቸው በርካታ ሀገራዊ እንከኖች አሉብን። አንድነትምን ያክል ኃይል እንደሆነ ዓባይ ምስክራችን ነው። የዓባይ ግድብ፣ የዓባይ ምስጢሩ የአንድነታችን ውጤት ነው።
በዓባይ ጉዳይ ግብጾች ተኝተው አያውቁም። ዛሬም የውሸትና የፖለቲካ ሸሮችን እየጎነጎኑ ተስፋችንን ሊነጥቁን እያሴሩብን ነው። ትውልዱ ግን በአባቱ የማለ፣ በአባቱ ቀልድ የማያውቅ ሆኖ በግብጽና ሱዳም ጩኸት ውስጥ ታሪክ እየሠራ ይገኛል። ይሄ ትውልድ ከእንግዲህ ወደ ኋላ የማይል ነው። ዋናውንና አባቱን ለባዕድ ሰጥቶ በድህነትና በኋላ ቀርነት መኖር አይፈልግም። አይደለም በዓባይ ጉዳይ ወደኋላ ሊል ቀርቶ እነዛ በአቅም ማነስ በግብጾች የበላይነት ያለፉት የአባቶቹ ዘመናት እንኳን የሚያስቆጩት ናቸው። ግብጾች የነጠቁንን አባታችንን ማስመለስ የዚህ ትውልድ የቤት ሥራው ነው። ለዘመናት በአባታችን በዓባይ ግብጽ ስታጌጥ ኖራለች። ከእንግዲህ ዓባይ የእኛ ነው። ካባ ለብሶ፣ ዘውድ ጭኖ ትንሳኤውን ሊያሳየን እነሆ ከአፋፍ ደርሷል። ኢትዮጵያውያን በአንድ ያዜምንለት፣ በአንድ የዘፈንለት ዓባይ ሊሞሸር ዋዜማ ላይ ነው። ጨለማዎቻችን ሊነጉ፣ ተስፋዎቻችን ብርሃን ሊያዩ…ኢትዮጵያ ልትስቅ እነሆ ትንሽ ብቻ ይቀራል።
ዓባይ የገነት መቀነት ነው። ወገቧን ሸብ ያደረገችበት። ገነት ያጌጠችው ዓባይን ተደግፋ፣ ዓባይን ጠምጥማ ነው። ዓባይ የኤዶም ገነት ክንብንብ ነው..አንገቷ ላይ ጣል ያደረገችው። ዓባይ እምነታችን፣ ጽናታችን፣ የአንድነታችን ክር ነው። ዓባይ ተስፋችን፣ ትንሳኤያችን፣ የከፍታችን ማማ ነው። በዓባይ ግድብ ተስፋን የሰነቁ፣ ነገን አሻቅበው የሚያዩ አያሌ ነፍሶች በኢትዮጵያ ምድር አሉ። እኚህ ነፍሶች እኔና እናተ ነን። እኚህ ነፍሶች መጪው ትውልዶች ናቸው። ከምንበላው ላይ ቀንሰን፣ ከሌለን ላይ ገምሰን ነው ከዘመናት ኩብለላው የመለስነው። ዓባይ በተፈጥሮ ውልደት ከከበቡንና ታሪክና ባህላችንን ከወረሱ እሴቶቻችን አንዱና ዋነኛው ነው። በዚህ ርስታችን ማጌጥ ያለብን እኛ እንጂ ግብጾች ዓይደሉም። ከዚህ ህብስታችን መብላት ያለብን እኛ እንጂ ሱዳኖች አይደሉም። ኢትዮጵያውያን ክፉዎች አይደለንም። እውነትን ሽተው ለተጠጉን ካለን ላይ ማካፈል የለመድን ሕዝቦች ነን። እኛ አብረን እንብላ ስንል ግብጽና ሱዳን ለብቻችን ካልበላን እያሉ ነው። ይሄ ትውልድ ርስቱን አሳልፎ መስጠት አይፈልግም። ከበሉ አብረውን ይብሉ ካልበሉ ግን በርስታችን ላይ የመጠቀም ሙሉ መብት አለን..ዓባይን ገድበን የመጠቀምና የመልማት መብት።
ሱዳንና ግብጽ የከፉብንን ያክል እኛ ለነሱ ከፍተን አናውቅም። ከትናንት እስከዛሬ አብረን እንልማ፣ አብረን እንደግ እንዳልን ነው። ነገር ግን ወልደው ባሳደጉት የክፋት ሃሳቦቻቸው ከጀመርነው የእድገት ጎዳና ሊያደናቅፉን ብዙ ለፍተዋል አሁንም እየለፉ ነው። በተለይ ዓባይን ለመገደብ በተነሳንበት ሰሞን ከግብጽና ከወዳጆቿ እንዲሁም ከዓለም ዓቀፉ ማሕበረሰብ የደረሰብን ጫና ቀላል የሚባል አልነበረም። አሁንም አልተኙም..የተሳሳተ መረጃዎችን በማሰራጨት፣ በዓባይ ጉዳይ ያለንን አንድነት ለማላላት በርካታ ሴራዎችን በመጎንጎን ላይ ናቸው። እኛ ግን አሁንም በዓባይ ጉዳይ ላይ አልቆምንም.. አልተለያየንም፣ አንድ ላይ ነን። በተለይ የመጀመሪያውን የውሃ ሙሌት በጀመርን ሰሞን፣ በተለይ ሁለተኛውን የውሃ ሙሌት ጀምረን ኃይል ማመንጨት ስንጀምር የሆኑት መሆን እንዲህ በቀላሉ የሚገለጽ አልነበረም። አሁንም ሶስተኛውን የውሃ ሙሌት ተከትለው የተሳሳተ መረጃዎችን በማሰራጨትና ከምዕራባውያን ወዳጆቻቸው ጋር እያሴሩብን ነው።
እኛ ግን ያው እንደትናንቱ ነን። የግብጽን የሀሰት ወሬ ችላ ብለን ስለ ዓባይ ጎንበስ ቀና እያልን ነው። እኛና ግብጽ አይሁድንና ክርስቶስን ነን። በዛ በጎለጎታ፤ በርባን ተፈቶ ክርስቶስ ሲሰቀል ብዙዎች ደስ ብሏቸው ነበር። አሁንም የግብጽ ወዳጆች ኢትዮጵያ ከሥራ ግብጽ እንድታተርፍ የሚፈልጉ ናቸው። ይሄ ግን አይሆንም ምክንያቱም ትውልዱ ትንታግ ትውልድ ነው። በዚያ ጊዜ ከአይሁድ ጫጫታ ይልቅ ጲላጦስን ያስፈራው የክርስቶስ ዝምታ ነበር። እኛም የግብጾች ጩኸት ምናችንም ነው። እንደ ክርስቶስ ዝም ብለን በግብጽና ሱዳን ተንኮል ላይ ተረማምደን ትንሳኤያችንን እናያለን። ዓባይ እኮ አባታችን ነው.. እናቱ ደግሞ ኢትዮጵያ ናት። ከአብራኳ ወጥቶ፣ በአብራኳ አድጎ የበለጸገ ልጇ። ታዲያ አባዬ ብለን ብንጠራው ማነው የሚያገባው? ዛሬም ነገም መቼም ዓባይ የእኛ ነው። ለሚወዱን በፍቅር ለተጠጉን እናጋራዋለን። ዓባይን ከመገደብና በዓባይ ላይ ከመጠቀም የሚያግደን ምንም ምድራዊ ኃይል የለም።
አንዳንድ ውሸቶች ሲቆዩ ወደ እውነት ይቀየራሉ። በተለይ ውሸት ፈጣሪ ግለሰቦችና ፖለቲከኞች ሲኖሩ እውነት ክብር ያጣል። የዓባይ ጉዳይ በግብጽ ላይ እንደዚህ ነው። ለዘመናት ያለማንም ከልካይ ተጠቀሙበት ከዛም የእኛ ብቻ ነው፣ የሚመነጨውም ከግብጽ ምድር ነው ሲሉ ማመን ጀመሩ። ማመን ብቻ አይደለም ያላመኑትን ማሳመን ጀመሩ። ትውልዱ እውነትን ሽሮ ዓባይ የግብጻውያን እንደሆነ አምኖ እንዲቀበል ብዙ ለፉ። ለልጆቻቸውም ስለ ዓባይ ውሸት ነገሩ። በዚህ አላበቁም በዓባይ ጉዳይ ላይ የትምህርት ሥርዓት ገንብተው ልጆቻቸውን ስለዓባይ ውሸት ማስተማር ጀመሩ፤ ዓባይ የእኛ ነው ሲሉ። ዓሁን ለግብጻውያን ዓባይ ማለት ከግብጽ የሚመነጭ፣ ለግብጽ ህልውና የተሰጠ አምላካዊ ስጦታ ነው። ይሄ በዘመናት የውሸት አሉባልታ ውስጥ የተፈጠረ እውነት ነው። ዓባይ የኢትዮጵያውያን ነው። ውልደቱ፣ እድገቱ ከሰከላ ማህጸን ነው። ዓሁን ትግላችን በግብጻውያን ልብ ውስጥ የታተመውን የውሸት እውነት ፍቆ ከተቻለ ዓባይ የግላችን እንደሆነ ማሳየት ካልተቻለ ደግሞ ዓባይን በጋራ እንድንጠቀመው ማድረግ ነው።
በግብጽ ምድር ለዓባይ የተዘፈነውን ያክል ለማንም አልተዘፈነም። ዛሬም ድረስ የጉዳያቸው አንደኛ ነው። ብሄራዊ ክብራቸው፣ ታሪካዊ ህልውናቸው አድርገውት ለዘመናት ኖረዋል። ይሄ የውሸት ትርክት በዚህ በእኔና በእናንተ ተሽሮ ዓባይ የእኛ ነው ስንል ተነስተናል። ትግላችንም ፍሬ አፍርቶ እየገደብንው እንገኛለን። ከመገደብም አልፈን ሶስተኛውን የውሃ ሙሌት በማጠናቀቅ ላይ ነን። የሚቀረን በአንድነት የገነባንውን፣ በአንድነት የደከምንለትን የህዳሴ ግድባችንን እልል ብሎ መመረቅ ነው። የሚቀረን በጋራ ትንሳኤዔያችንን ማጣጣም ነው። የሚቀረን እንደ ህዳሴ ዓይነት ሌሎች ግድቦችን መሥራት ነው። በነገራችን ላይ ግብጻውያን ዓባይን የህልውናቸው መሰረት ያደረጉበትን ብዙ ማስረጃዎችን ማየት እንችላለን። ግብጽ ውስጥ በዓባይ የሚምሉ አሉ። ግብጽ በየዓመቱ ከአምስት ሺ በላይ የሶስተኛ ዲግሪ ተማሪዎችን ታስመርቃለች በጣም የሚገርመው ደግሞ እኚህ ሁሉ ተማሪዎች የመመረቂያ ጽሁፋቸውን የሚሠሩት በዓባይ ወንዝ ላይ መሆኑ ነው። ግብጽ ውስጥ ዓባይ ለብዙ ተማሪዎች የመመረቂያ ጽሁፍ ሃሳብ ነው። ይሄ ማለት ግብጾች በዓባይ ዙሪያ ምን ያክል ርቀት እንደተራመዱ የሚያሳይ ነው። አሁን ጊዜው የእኛና የዓባይ ነው። በዓባይ ላይ የግብጽ የበላይነት አክትሟል። ዓባይ ወደ እናቱ ተመልሷል።
በየትኛውም መስፈርት ቢታይ የኢትዮጵያ ግድብ መሥራት ግብጽና ሱዳንን አይጎዳም ይጠቅማቸዋል እንጂ። ግን ውስጣቸው ያስቀመጡት የኔነትና የብቻ ሃሳብ ስላለ ዓባይን መጋራት አይፈልጉም። ይሄ ሃሳብ ምን ያክል እውነት እንደሆነ ለማየት ጥቂት ምሳሌዎችን ላስቀምጥ። ካቻምና የመጀመሪያ የውሃ ሙሌት ስናከናውን ካጠቃላዩ የውሃ ይዘት 4 ፐርሰንት ብቻ ነበር የተጠቀምነው። ቀጥለን በዓመቱ አምና ማለት ነው 13 ፐርሰንት ብቻ ነው ለሙሌት የተጠቀምነው ይሄ ማለት በመጀመሪያው ሙሌት 96 ፐርሰንቱ በሁለተኛው ሙሌት ደግሞ 87 ፐርሰንቱ ውሃ ወደ ግብጽና ሱዳን ፈሷል ማለት ነው። ከዚህ እውነት በመነሳት የውሃ እጥረት ይፈጠራል፣ ተፋሰስ ሀገራት ይራባሉ የሚሉት የግብጽና የሱዳን አሉባልታ ውሸት መሆኑን እንደርስበታለን። ምንም አይደለም የግብጽና ሱዳን ስጋት የኢትዮጵያን ብልጽግና ከመፍራት የመነጨ ነው። ኢትዮጵያን ከመፍራት፣ ብልጽግናዋን ከመስጋት የመነጨ የበታችነት ስሜት ነው። ኢትዮጵያ ሀገራችን ከህዳሴ ግድባችንና ከዚህ በኋላም በምትገነባቸው ግድቦች የምታገኘው የኃይል፣ የኢኮኖሚ፣ የፖለቲካ፣ የሥልጣኔ፣ የዘመናዊነት ጸጋ ስጋት ሆኗቸው ነው ዛሬ ላይ ይሄን ሁሉ ችግር እየፈጠሩ ያሉት።
የሶስተኛውን የውሃ ሙሌት ተከትሎ እንኳን የተለያዩ የውሸት ዜናዎች ከግብጽ ሚዲያ እየተሰሙ ነው። አንድ ጋጤጠኛ በራሱ የዩቲዩብ ገጽ ላይ ግድቡ እየተሰነጣጠቀ ነው፤ ሕዝቡ አሁን ላይ ስለ ህዳሴ ግድብ ማሰብ አቁሟል የሚል ከእውነት ውጪ የሆነ የሀሰት ወሬዎችን ሲያራግብ ነበር። ከሰሞኑ ግብጽ ስለ ህዳሴው ግድብ የሚመለከታቸውን ሀገራት ጋብዛ በህዳሴው ዙሪያ እየተወያየች ነው። እውነቱ እኛጋ ነው ያለው። የህዳሴ ግድባችን ከሃሳባችን ያልወጣ፣ ከሃሳባችን የማይወጣ የህልውናችን ማህተም ነው። ጠላት ያው ጠላት ነው ጥሩ ነገር አያወራም። ገና ከዚህ በኋላም የተለያዩ የውሸት ወሬዎችን እንሰማለን። ከእኛ የሚጠበቀው እንደ ክርስቶስ ዝም ብለን እየሠራን ወደ ትንሳኤያችን መጓዝ ነው። ዓባይ አባታችን ነው፤ የሚያስቆመን ማንም የለም። የግብጾች ህልውና እንደመሆኑ እኛም ህልውና ነው። በዓባይ ግድብ ላይ መቶ ሃያ ሚሊዮን ድሃ ሕዝቦች ተስፋን ቋጥረዋል። እምነትን ጥለዋል። በዓባይ ግድብ ላይ መጪው ትውልድ ኩራትና ብኩርናን በዛሬዎቹ እኛ ላይ ጥሏል። ታዲያ ዓባይ እህል ውሃችን ቢሆን ምን ይገርማል?
በትረ ሙሴ መልከ (ኢትዮጵ)
አዲስ ዘመን ሐምሌ 5 ቀን 2014 ዓ.ም