በአለም አቀፍ ደረጃ ዳቦ ለሰው ልጅ እጅግ አስፈላጊና ጠቃሚ ከሆኑ መሠረታዊ የምግብ ዓይነቶች አንዱ ነው። ጥንታዊና እጅግ ተወዳጅ ‹‹one of the world’s oldest and most beloved foods›› ተብሎም በበርካቶች ዘንድ ይንቆለጳጰሳል። በነጋ በጠባ ከብዙ ቢሊየኖች ደጅና ጓዳ የሚዳረሰውና በገበያ ላይ ሲኖር የመኖር ሕልውናን የሚያረጋግጠው ዳቦ፣ሲታጣም ‹‹bread riots›› በመፍጠር ሥልጣንን እንደ ወተት የሚንጥ ፖለቲካ አዘል ተወዳጅ ምግብ ነው። በየትኛውም የዓለም ጥግ ተወዳጅ የሆነው ዳቦ ዋነኛ ግብአት ደግሞ ስንዴ ነው። በዓለም አቀፍ ደረጃም የተለያዩ አገራት ስንዴን ያመርታሉ። ከራሳቸው ተርፈው ለሌሎች ይተርፋሉ።
ዓለማችን በተለያዩ ወቅቶችና ክስተቶች የስንዴ ምርት ማግኘት አልሆን ብሏት ጎተራዋ ደርቆ ያውቃል። ይህን ተከትሎም የስንዴ ፖለቲካ ‹‹wheat politics››ን በተደጋጋሚ አስተናግዳለች። በአሁን ወቅትም በስንዴ ፖለቲካ እየታመሰች ትገኛለች። ምክንያቱ ደግሞ የዳቦ ቅርጫት የሚባሉትና ከዓለም የስንዴ ምርት የውጭ ንግድ ከ28 በመቶው በላይ ወይንም አንድ ሦስተኛ የሚሆነው ፍላጎት የሚያቀርቡት ዩክሬንና ሩስያ ከየካቲት አጋማሽ 2014 ዓ.ም ጀምሮ ወደለየለት ጦርነት መግባታቸው ነው።
በሁለቱ አገራት ጦርነት ምክንያት የስንዴ ዋጋ በአስራ ሶስት ዓመታት ውስጥ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ ንሯል። ቀውሱም በበርካታ ሀገራት የምግብ እጥረትን በማስከተል ረሀብና ተቃውሞን ሊቀሰቅስ ይችላል የሚል ስጋት አሳድሯል። የቀውሱ ተጽእኖም በተለይም በሁለቱ አገራት ምርቶች ላይ ጥገኛ በሆኑት አገራት በርትቷል። ከሳውዲ አረቢያ እስከ ተርኪዬ፣ ከሱዳን እስከ ባንግላዴሽ፤ ከፓኪስታን እስከ እስራኤል፣ ከአዘርባጃን እስከ ቬትናም፣ ከኢንዶኔዥያንም እስከ ግብፅ እንዲሁም ሌሎች አገራት የስንዴ ጎተራቸው ባዶ ሆኗል።
አብዛኞቹ አገራትም የስንዴ እጥረት በርትቶባቸው፤ በብዙ መቶ ሚሊዮኖች ለሚሆኑ ዜጎቻቸው ዳቦ ለማቅረብ ተቸግረዋል። ይሄን ለተመለከተ የዳቦ ጥያቄ አመጽን በተግባር የተመለከቱባቸውን ግብጽና ሱዳንን በመመልከት‹‹የሆድ ነገር ሆድ ይቆርጣል፣ የዳቦ ነገር ጊዜ አይሰጥም›› በሚል እጥረቱ የሕዝብ አመጽን አባብሶ ወደ መንግሥት ግልበጣ ሊያመራ ይችላል በሚል ስጋት ውስጥ ገብተዋል።
ችግሩም ከዩክሬንና ከሩስያ በሚመጣ እህል ላይ ጥገኛ ለሆኑ የአፍሪቃ ሀገራት ራስ ምታት ሆኖ ታይቷል። መረጃዎች እንደሚያመላክቱትም ከሁለቱ አገራት ወደ አፍሪካ ይገባ የነበረውን እህል በአፍሪካ ሀገራት መካከል በሚካሄድ ንግድ ብቻ መተካት የሚቻል አይደለም። ይህም በርካቶችን አስደንግጧል። የቀውሱ ውጤትም በአደባባይ ለመታየት ጊዜ አልፈጀበትም። 90 በመቶ የሚሆነውን የስንዴ ፍላጎቷን ከሁለቱ አገራት በምታስገባው ግብፅ የዳቦ ጋጋሪዎችም የዱቄት ዋጋ በጣም ውድ ሆነብን ሲሉ ተደምጠዋል። ከዩክሬን 60 በመቶ የሚሆነውን የስንዴ ምርት የምታስገባው ሊባኖስም ጭንቅ ውስጥ ናት። አፍ አውጥታ እርጥባን እስከ መጠየቅ ደርሳለች። በዩጋንዳ ተራ የሚባለው ዜጋ ዳቦ መግዛት የማይችልበት ደረጃ ላይ ደርሷል።
በዓለም አቀፍ ደረጃ በርካታ አገራትም ጊዜያዊ የሚሉትን መፍትሄ በመሞከር ላይ ተጠምደዋል። የዳቦና ስንዴ ውጤቶችን የገበያ ዋጋ ከመተመን አንስቶ ስንዴ ፍለጋ የቀረባቸውን በር እያንኳኩ ናቸው። የስንዴ ምርት ከአገር ውስጥ ፍጆታ ባሻገር ወደ ሌሎች አገሮች እንዳይሸጥ ከልክለዋል። ለዳቦ ስንዴ ዱቄት ድጎማ በጀት መድበዋል።
ምንም እንኳን ሁለቱ አገራት ስንዴ ምርቱን ለመላክ ፈቃደኛ መሆናቸውን ብንሰማም፣ ቀወሱ ግን እንዲህ በቀላል መፍትሄ ያገኛል ብሎ ማሰብ ሞኝነት ነው። ሌላው ቀርቶ የሁለቱም አገራት መሬቶች ሳይታረሱ ፆማቸውን ያደሩ መኖራቸው በሚቀጥለው የምርት ዘመን የሚሰበሰብ ምርት አይኖርም። ይህ ደግሞ የዓለማችንን የምግብ ዋስትና የባሰ ስጋት ውስጥ እንደሚጥለው እርግጥ ነው። ሁኔታውም ስንዴ ከነዳጅ ጋር የሚገዳደር ቀጣይ የዓለማችን ተፅዕኖ ፈጣሪ ሀብት እንደሚያደርግም የበርካቶች ግምት ነው።
የጦርነቱን መዘዝ ላስተዋለና ውጤቱን ለፈተሸ ኢትዮጵያስ እንዴት ትሆን ይሆን? የሚል የስጋት ጥያቄ መጠየቁ አይቀሬ ነው። እንደሚታወቀው፣ ኢትዮጵያ ከሰሃራ በታች ከፍተኛ መጠን ያለው ስንዴ አምራች አገር ነች። ስንዴ ለማምረት ምቹ የሆነ የእርሻ ስነ- ምኅዳር (suitable Agro ecology) እና በስንዴ ዙሪያ የሚመራመሩ የእህል ሳይንቲስቶች እና ልምድ ያላቸው ምሁራን ያላት አገር አላት። ይሁንና ኢትዮጵያ ብዙ መቶ ሚሊዮን ዶላር እያወጣች ስንዴ ከዩክሬንና ሌሎች አገራት ገዝተው ወደ አገር ውስጥ ከሚያስገቡ የአፍሪካ አገሮች አንዷም ናት። ከዓመት ዓመት የሕዝብ ቁጥሯ በእጅጉ እየጨመረ መምጣቱም የአገሪቱ ስንዴን በተለያዩ መንገዶች በስፋት የመጠቀም ፍላጎት እና ምርቱን ለመግዛት የምታወጣውን ወጪ ሰ ማይ ሰቅሎታል።፡
የዶክተር ዐቢይ አመራር ወደ ሥልጣን ከመጣ በኋላ ታሪክ ለመቀየርም፣ የስንዴ አመራረት ዘዴዋን ለማሻሻል እና የውጭው ዓለም የስንዴ ጠባቂነት ስሜትን በመፋቅ በአገር ቤት ስንዴ በስፋት የሚመረትበትን መንገድ ለመቀየር እየተሠራ ይገኛል። ወደ ሌሎች አማራጮች በመሄድ የመሠረታዊ ምግብ አቅርቦት መንገድን በመከተል፤ የስንዴ አምራችነትና ተጠቃሚነት አቅምን በማሳደግ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ጉዞው ተጀምሯል። በዚህም በከፍተኛ ሥፍራዎች በዝናብ ላይ ተተኩሮ ከሚካሄደው የስንዴ ማምረት ተግባር በተጓዳኝ፤ አገሪቱ ያላትን የውሃ ሀብት በመጠቀም በቆላማ አካባቢዎች በግል ባለሀብቶች ስንዴ በመስኖ እንዲለማ ማድረግ ተጀምሯል።
‹‹Another man’s bread will not fill your belly›› የሚል አንድ የአረቦች አባባል አለ። የሌላ ሰው ዳቦ ሆድህን አይሞላልህም ማለት ነው። ኢትዮጵያም ይህ አባባል ጠንቅቆ ገብቷታል። ‹አይመጣምን ትታ፤ ይመጣልን በማሰብ፣ ‹‹የሰው ወርቅ አያደምቅ›› ብላ የራሷን መንገድ ጀምራለች። በስንዴ ምርት የራሷን ፍላጎት ከማሟላት አልፋ ስንዴን ለዓለም አቀፍ ገበያ ለማቅረብ ተጨባጭ ሥራዎችን በመሥራት ላይ ትገኛለች። ጉዳዩን አስመልክተው ኔሽን ላይ ሀተታ ጽሑፍ ያቀረቡት የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ፕሬስ ሴክሬታሪያት ቢልለኔ ስዩም፣ ኢትዮጵያ የስንዴ ፍላጎቷን አሟልታ ስንዴን ለውጭ ገበያ የማቅረብ ውጥኗ የጫወታውን ህግ የሚቀይር ነው›› ማለታቸው የሚታወስ ነው።
በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የበጋ ስንዴ ልማት የመጀመሪያው ምዕራፍ ብቻ ከ405 ሺህ በላይ ሄክታር መሬት በዘር ተሸፍኖ 16 ነጥብ 2 ሚሊዮን ኩንታል የስንዴ ምርት ማግኘት ተችሏል። በሁለተኛው ምዕራፍ ደግሞ ከ208 ሺህ ሄክታር መሬት 8 ነጥብ 35 ሚሊዮን ኩንታል የስንዴ ምርት መሰብሰቡ ከግምት ውስጥ ሲገባ፤ ኢትዮጵያ ስንዴን ኤክስፖርት የማድረግ ውጥን ስኬታማ እንደሚሆን ማረጋገጫ ነው።
በመሆኑም፣ በኢትዮጵያ በግብርናው ክፍለ ኢኮኖሚ ዘርፍ እየተሠራ ያለውን ሥራ ዜጎችን ከዓለም የስንዴ ዋጋ ግሽበት ብቻ ሳይሆን አገርን ከስንዴ ጋር ተያይዞ ከሚመጣ ጫና ማዳን የሚያስችል ነው። ነገሮች እንደታቀዱ በትኩረት ተይዘው ከተጓዙ ደግሞ ለጎረቤት አገራትም እንተርፋለን። እናም ለዚህ ዕቅድና ግብ መሳካት እያንዳንዱ ዜጋ የሚችለውን ሁሉ ማድረግ አለበት።
ታምራት ተስፋዬ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 5 ቀን 2014 ዓ.ም