ሰዎች መሰረታዊ የምግብ ሸቀጣ ሸቀጦችን፣ የግብርና ምርቶችን፣ ወዘተ. ለመሸመት የኑሮ ደረጃቸውንና ገቢያቸውን መሠረት ያደርጋሉ፤ ከሸቀጦቹና የግብርና ምርቶቹ ዓይነት፣ መጠን፣ ጀምሮ የሚሸምቱበት ቦታም እንዲሁ ለየቅል ነው።እንደየአካባቢያቸውም ይወሰናሉ።
ለሚሸምቷቸው ምርቶች ወይም ሸቀጦች ተመጣጣኝ ዋጋ የሚጠየቅበትን፣ ጥራቱንና ደረጃውን የጠበቀ መሆኑን ታሳቢ በማድረግ የገበያ ቦታ አጥብቀው ያስሳሉ።የት ሰራሽነታቸውንም ይመለከታሉ።ለእዚህም ጥሩ ያሏቸውን አማራጮች ያማትራሉ።
በሀገራችን እየተባባሰ የመጣውን የኑሮ ውድነትና የዋጋ ንረት ማምለጥ ያስችላል፤ ትንሽም ቢሆን ለውጥ ያመጣል ብለው ያሰቡትንና እውነትም ጥቂት ለውጥ የታየባቸውን የገበያ ቦታዎች መጎብኘትና ማዘውተራቸው የተለመደ ነው።ደንበኛ የሚለውም ነገር አንድም ከእነዚህ ሁኔታዎች ይመነጫል፡፡
ከእነዚህ ገበያዎች መካከልም የከተሜው የገበያ አማራጭ የሆነው ሱፐርማርኬት አንዱ ነው።ሱፐርማርኬት በርካታ ነገሮች በአንድ ቦታ ማግኘት የሚቻልበት ቢሆንም፣ በሀገራችን ግን ከጥቂቶች በስተቀር አብዛኛው ማህበረሰብ ከእዚህ የገበያ አማራጭ ገብቶ የመሸመት ልምድ የለውም።
ለዚህም ዋናው ምክንያት ሱፐርማርኬቶች ምርቶች በውድ ዋጋ የሚሸጡባቸው፣ መከፈል የሚችሉ ብቻ የሚስተናገዱባቸው ተደርገው ሲታዩ መኖራቸው ነው፤ በትላልቅ ሕንፃዎች ላይ መገኘታቸውን የሚፈሩም ጥቂት አይደሉም፤ የሕንፃ ኪራይ ዋጋን ጭምር ታሳቢ አድርገው የሚሸጡ ተደርገው ስለሚታሰቡም የሚይዙዋቸው ምርቶች ዋጋ የሚቀመስ እንዳልሆነ ተደርጎ ነው የሚታሰበው። ከሌሎች ጊቢያቸው ከፍተኛ የሆኑ የኅብረተሰብ ክፍሎች ቦታ ተደርገውም ይወሰዳሉ።
ይሁንና አሁን አሁን ይህ አመለካከት እየተቀየረ ስለመሆኑ በሱፐርማኬት ገብተው ከገበዩ ወገኖች ይደመጣል።ለወትሮው ዋጋቸው ውድ ነው የተባሉትና ከፍተኛ ገቢ ላላቸው የማህበረሰብ ክፍሎች ብቻ የተፈጠሩ ተደርገው የሚታዩትን የሱፐርማርኬቶች ገበያን ማንኛውም የማህበረሰብ ክፍል እየተቀላቀለው ይገኛል።በተለይ ደግሞ የኑሮ ውድነት አማራጭ ገበያዎችን ግድ ባለበት በዚህ ወቅት ሱፐርማርኬቶች እየተፈለጉ ናቸው።
አዲስ አበባ እንደ አባድር፣ ሸዋና ባምቢስ የመሳሰሉት ሱፐርማርኬቶች ያሏት ብትሆንም አብዛኛውን ሕዝብ በመድረስ በኩል ግን ክፍተት ነበረባቸው።በዚህ የተነሳም ቀደም ብሎ እንደተጠቀሰው ገበያዎቹ የጥቂቶች ተደርገው ይታዩም ነበር።ሱፐር ማርኬቶች ላይ አሁን ለውጦች እየታዩ ናቸው።በተመጣጣኝ ዋጋው ጭምር በማህበረሰቡ ዘንድ እየተለመደ የመጣው የሱፐርማርኬት ገበያ፣ በተለያዩ አካባቢዎች እየስፋፋም ይገኛል።
ባለቤትነቱ የሼክ መሀመድ አላሙዲን የሆነው ሆራይዞን ፕላንቴሽን ክዊንስ ሱፐር ማርኬትን በአዲስ አበባ ከፍቷል፤ ሱፐርማርኬቱ በተለያዩ የአዲስ አበባ አካባቢዎች ቅርንጫፎችን ከፍቶ እየሠራ ሲሆን፣ የግብርናና የኢንዱስትሪ ምርቶችን ለገበያ ያቀርባል።የግብርና ምርቶቹን ከእህት ኩባንያዎቹ ያገኛል።ይህ መሆኑም በንግድ ሰንሰለት መራዘም የሚደርስ የዋጋ ጭማሪን ማስቀረት ይቻላል።ሌሎች በርካታ ሱፐር ማርኬቶችም ገበያውን ተቀላቅለዋል።
አራት ኪሎ አካባቢ ከኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት በቅርብ ርቀት በሚገኝ ሕንፃ አንደኛ ፎቅ ላይ ያለው አራዳ ማርትም ሌላው ሱፐርማርኬት ነው።በዚህ ሱፐርማርኬት ሲገበዩ ያገኘናቸው ሸማቾች በመኖሪያ አካባቢያቸው ከሚገኙ የጉልትም ይሁን ሌሎች የገበያ ቦታዎች በተሻለ ሱፐርማርኬቶች ተመራጭ እየሆኑ መምጣታቸውን ይገልጻሉ።መሰል የገበያ አማራጮችን ማህበረሰቡ ቢለምዳቸው መልካም ነው ሲሉም ይመክራሉ።
ከሱፐር ማርኬቱ አትክልትና ፍራፍሬ እየሸመተች ያገኘናት ወይዘሪት ጸሐይ ሞላ፤ በምትሠራበት አካባቢ እንዲህ ዓይነት የገበያ አማራጭ ማግኘት በመቻሏ ደስተኛ ናት፤ ሱፐርማርኬቱ ለመኖሪያ ቤቷ የራቀ መሆኑን ጠቅሳ፣ ለሥራ በወጣችበት ወይም በሥራ መውጫ ሰዓት ወደ ሱፐርማርኬቱ ሄዳ የሚያስፈልጓትን በሙሉ ሸማምታ ወደ ቤቷ እንደምትሄድ ትናገራለች።በመኖሪያ አካባቢዋ ካለው ገበያ ጋር በማነጻጸርም አራዳ ማርት ላይ እያገኘች ያለችው አገልግሎት የተሻለ እንደሆነ ነው የምትጠቅሰው።
ለአብነትም በጉልት ገበያ ላይ ሰዎች የፈለጉትን መርጠው ማንሳት እንደማይችሉና ሱፐርማርኬት ላይ ሲሆን ግን ሸማቹ ጥራት ያለውን ማንኛውንም ምርት በእጁ እያነሳ መርጦ መውሰድ መቻሉንም እንደ አንድ መልካም አማራጭ አድርጋ ትወስደዋለች።በዋጋም ቢሆን በትንሹ ከአንድ ብር ጀምሮ ቅናሽ ያለው መሆኑን ጠቅሳ፣ ሱፐርማርኬት ተመራጭ መሆኑን እየተገነዘበች መምጣቷን ተናግራለች። ከሰፈር ሰፈር ደግሞ ገበያው የሚለያይ እንደሆነ ነው የጠቀሰችው፡፡
እርሷ በምትኖርበት ጀሞ አካባቢ ጉልት ላይ የምርቶች ዋጋ ውድ እንደሆነ ጠቅሳ፣ መርካቶ አካባቢ ቢኬድ ቅናሽ እንደሆነ በንጽጽር ገልጻለች።ይሁንና መሰል ሱፐርማርኬቶች በየአካባቢው ቢኖሩ ማህበረሰቡን በተለያየ መንገድ ማለትም በዋጋም ይሁን በምርት ጥራት የተሻለ ተጠቃሚ እንደሚያደርጉ ነው ያብራራችው።ደህንነቱ በተጠበቀና ምቹ በሆነ ቦታ መገበያየት በራሱ ማህበረሰቡን ተጠቃሚ እንደሚያደርገውም ያስረዳችው፡፡
ከዚሁ ሱፐርማርኬት ሳንወጣ ፍራፍሬ እየሸመቱ ያገኘናቸው ወጣት መሠረት በልሁ እና አሸናፊ ገብሬም እንዲሁ ጉልትን ጨምሮ በአካባቢያቸው ከሚገኘው ገበያ ወይም መደብር ይልቅ ሱፐርማርኬት የተሻለ ስለመሆኑ እየተረዱ መምጣቸውን ይናገራሉ።ምንም እንኳን ደረጃቸውን የጠበቁ ሱፐርማርኬቶች በሁሉም አካባቢዎች ተደራሽ አለመሆናቸውን ጠቅሰው፣ ለአካባቢው ሰው ከአንድ ብር ልዩነት ጀምሮ በጥራት በማቅረብ ሰዎች እንደፈለጉ መርጠው መግዛት መቻላቸው መልካም እንደሆነ ነው የገለጹት።
‹‹በብዙ ሰዎች አስተሳሰብ የሱፐርማርኬቶች ዋጋ ውድ ተደርጎ ይታያል።ሸማቾች ግን ሱፐርማርኬቶችን በሩቅ ሆነው ዋጋቸው አይቻልም ብለው እንደሚሸሹዋቸው ይናገራሉ።ይሁንና ዋጋው እንደሚታሰበው ብዙ ልዩነት የለውም።እንዲያውም የተሻለና ጥራት ያለው ምርት የሚገኘው በሱፐርማርኬቶች ውስጥ ነው›› በማለት የሱፐርማርኬቶችን ተመራጭነት ወጣት መሠረትና አሸናፊ ያስረዳሉ።
ከዚህ በተጨማሪም በሱፐርማርኬቶች ውስጥ ዋጋ ስንት ነው? ብሎ መጠየቅና መከራከር አለመኖሩ በራሱ ጊዜን መቆጠብ የሚያስችልና ተመራጭ የሚያደርጋቸው ነው ሲሉ ያብራራሉ።የሁሉም ምርቶች ዋጋ በግልጽ በጽሑፍ የቀረበ ሲሆን፣ ሸማቹ የፈለገውን እና የመረጠውን በሚፈልገው መጠን ገዝቶ ይወጣል።ይህ ደግሞ ሊበረታታና በማህበረሰቡ ዘንድም ሊለመድ የሚገባው የገበያ አማራጭ ነው ይላሉ።
አራዳ ማርት ለአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች ለየት ያለ አሠራር ይዞ ስለመቅረቡ የአራዳ ማርት ባለቤት አቶ ታምራት ዘውዴ ይገልጻሉ፤ ድርጅቱ ከሌሎች የገበያ ቦታዎች በተመጣጣኝ ዋጋ ኅብረተሰቡ ዘንድ ለመድረስ ሲነሳ ማህበረሰቡን ቤተሰብ በማድረግ መሆኑን ይናገራሉ።የምርቶቹ ዋጋ መንግሥት አማራጭ ብሎ ካቀረባቸው የእሁድ ገበያዎች ሳይቀር የአንድ ብር ቅናሽ እንደሚኖረው፣ አልያም እኩል ዋጋ የሚኖርበት ጊዜ እንዳለ ነው የሚያብራሩት።
አራዳ ማርት ከተጀመረ ዘጠኝ ወራትን ብቻ ያስቆጠረ እንደሆነና በዚህ ጊዜ ውስጥም ከጠበቁት በላይ አገልግሎት እየሰጠ እንደሆነና በአሁኑ ወቅትም በአማካኝ በቀን ከ250 እስከ 300 ሰው እያስተናገደ መሆኑን ያብራራሉ።ሱፐርማርኬቱ የሸቀጦች ዋጋ እየናረ ባለበት በዚህ ወቅት ጥራት ያለውን ተፈላጊ ምርት መጠነኛ በሆነ ቅናሽ ይዞ መቅረቡ ተመራጭ እንዳደረገው አቶ ታምራት ይገልጻሉ፡፡
ለዋጋ ውድነት ዋናው በመሀል የሚኖረው ደላላና ረጅሙ ሰንሰለት ስለመሆኑ አቶ ታምራት ይናገራሉ።ሱፐርማርኬቱ የግብርና ምርቶችን በቀጥታ ከአምራቹ እንደሚያመጣና መጠነኛ ትርፍ አግኝቶ ለሸማቾች እንደሚያቀርብ ነው ያብራሩት።ረጅሙን ሰንሰለት በማሳጠር እንዲሁም አግባብ ያልሆነ ጭማሪ አለማድረግ የዋጋ ንረትን ለማረጋጋት ያስችላል ይላሉ።
በቀጣይም ተደራሽነትን ለማስፋት ቴክኖሎጂን በመጠቀም ቤት ለቤት የማድረስ ሥራ እንደሚጀምሩ የተናገሩት አቶ ታምራት፤ በተለይም አዲስ አበባ ከተማ ላይ መሰል የቢዝነስ ሞዴል ተግባራዊ ማድረግ ለማህበረሰቡም ሆነ ለመንግሥት ጠቃሚ እንደሆነ ነው አስታውቀዋል።ሰዎችን ለመድረስ የግድ ወጪ አውጥቶ በየአካባቢው ሕንፃ መከራየት የግድ እንዳልሆነና ቴክኖሎጂን በመጠቀም ቅርንጫፎችን ማስፋትን አቅደዋል።
በሌላ በኩል ደግሞ የኑሮ ውድነትን ለመቆጣጠር ሌሎች አማራጮች ተደርገው በመንግሥትም በሕዝቡም የተያዙት የህብረት ሥራ ማህበራት ናቸው።ማህበራቱ በሸማቾች የህብረት ሥራ ማህበራት በኩል በተመጣጣኝ ዋጋ የኢንዱስትሪና የግብርና ምርቶችን ለሸማቾች እያቀረቡ ይገኛሉ።በአዲስ አበባ የህብረት ሥራ ማህበራቱ ሚና እየሰፋ ሲሆን፣ የከተማ አስተዳደሩ ለማህበራቱ ገንዘብ በተዘዋዋሪ ፈንድ በመስጠትም በማህበራቱ ይበልጥ እንዲሠራ እያደረገ ያለው።
‹‹እየተባባሰ የመጣውን የኑሮ ውድነትና የዋጋ ንረት ለማረጋጋት መንግሥት ይጠቅማሉ ባላቸው የህብረት ሥራ ማህበራት በኩል እየሠራ ይገኛል፡፡›› የሚሉት በኢትዮጵያ ህብረት ሥራ ኮሚሽን የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ወይዘሮ አያልሰው ወርቅነህ፤ በተለያዩ ሸቀጣ ሸቀጦችና በግብርና ምርት አቅርቦት ዙሪያ ያለውን ችግር ለመፍታት የህብረት ሥራ ማህበራት አማራጮች መሆናቸውን ይጠቅሳሉ። መንግሥት ከመቼውም ጊዜ በበለጠ የህብረት ሥራ ማህበራትን እየተጠቀመ መሆኑንም ነው የሚገልጹት።ማህበራቱ ካላቸው ጉልህ ሚና አንጻር የገበያ ተደራሽነታቸውን ለማስፋትም በርካታ ሥራዎችን በማከናወን የድርሻውን እየተወጣ ይገኛል።
በመሆኑም በምርት አቅርቦትና ግብይት ላይ ከፍተኛ ድርሻ ካላቸው አምራቾችና ሸማቾች ህብረት ሥራ ማህበራት፣ መንግሥታዊ ድርጅቶች፣ ኢንዱስትሪዎች፣ አስመጪዎች፣ አቀናባሪዎችና ታላላቅ ግዢ ከሚፈጽሙ ተቋማት ጋር ቀጥተኛ የግብይት ትስስር መድረኮች በማመቻቸትና ግብይት እንዲፈጸም የውል ስምምነቶችን በማድረግ የግብርናና የሸቀጥ ምርት አቅርቦት ችግር እንዲፈታ ጥረት በማድረግ ላይ ነው፡፡
አሁን እየታየ ያለው የኑሮ ውድነት በአገር ውስጥ ካለው ችግር በተጨማሪ በውጭ ዓለም ያለው ውጥረትም እንደምክንያት የሚጠቀስና ችግሩን ይበልጥ እንዳባባሰው የጠቀሱት ዳይሬክተሯ፤ ዜጎች በእጅጉ እየተፈተኑበት ያለውን የኑሮ ውድነት ለማረጋጋት እርምጃዎች እየተወሰዱ መሆናቸውን ይናገራሉ፡፡
ከእነዚህም መካከል ጤናማ የግብይት ሥርዓትን በማስፈን አምራችና ሸማቹን በቀጥታ ለማገናኘት በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ንግድ ቢሮ አማካኝነት የተጀመረው የእሁድ ገበያ የዋጋ ንረትን ለማርገብ ብሎም ገበያን ለማረጋጋት ጉልህ ድርሻ እየተጫወተ ይገኛል።
ወራት ያስቆጠረው የእሁድ ገበያ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ማህበረሰብ በሚኖርበት አካባቢ ከአስር በማይበልጡ ቦታዎች ነው የተጀመረው።በአሁኑ ወቅት የክልል ከተሞችን ሳይጨምር በአዲስ አበባ ከተማ ብቻ 50 በሚደርሱ አካባቢዎች ግብይት በቋሚነት እየተካሄደ የሚገኝ ሲሆን፣ ኅብረተሰቡ ዘንድ ይበልጥ ለመድረስ በቅርቡ ቅዳሜን ጨምሮ ገበያው እንዲኖር እንደሚደረግ ተጠቁሟል።
ለዚህም ትልቅ ድርሻ ያላቸው የህብረት ሥራ ማህበራትን ማጠናከርና ለኅብረተሰቡ ተደራሽ ማድረግ ዋነው ጉዳይ ነው።በተለይም በከተሞች የሚስተዋለውን የምርት እጥረትና የሸቀጦች ዋጋ ንረትን ለማረጋጋት ማህበራቱ ከመቼውም ጊዜ በተለየ የጎላ እንቅስቃሴ እያደረጉ ይገኛሉ።ይህም ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
ፍሬሕይወት አወቀ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 27 ቀን 2014 ዓ.ም