ልጆች እንዴት ናችሁ፤ እረፍቱ እንዴት ይዟችኋል? መቼም አሪፍ ነው እንደምትሉኝ አምናለሁ። ምክንያቱም በተለያየ መልኩ ክረምትን ከቤተሰቦቻችሁ ጋር እያሳለፋችሁ እንደሆነ መገመት አያቅተኝም። በዚያው ልክ ግን ቤተሰባችሁን በተለያየ ነገር እያገዛችሁ ነው አይደል? ይህንን ያላደረጋችሁ ካላችሁ ጥሩ አይደለም። ለእናንተ እነርሱ የማያደርጉት ነገር የለም። ስለዚህም ውለታቸውን በምትችሉት ሁሉ መክፈል የምትችሉበት ጊዜ ደግሞ ይህ የእረፍት ወቅታችሁ ስለሆነ ማገዝ አለባችሁ።
ልጆች ዛሬ ምን ይዤላችሁ እንደመጣሁ ታውቃላችሁ? አፋር ሄጄ ነበርና ጎበዞቹን የአፋር ልጆች ተሞክሮ ነው የማቀርብላችሁ። በተለይም ረፍታቸውን በምን አይነት ሁኔታ እያሳለፉ እንደሆነ ይነግሯችኋል። ከእነርሱ የምትወስዷቸው ብዙ ተሞክሮዎች አሉና በሚገባ አንብቡት እሺ? ጎበዞች!
መጀመሪያ ያናገርኩት ተማሪ አሊ መሀመድ ይባላል። በአፋር ክልል በዳርሳጊታ አንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቤት የሰባተኛ ክፍል ተማሪ ነው። እናትና አባቱ በመለያየታቸው የተነሳ እናቱን የሚያግዛቸው እርሱ ብቻ ነው። እናቴ ስትቸገር ማየት አልፈልግም በሚል ትምህርቱን ጭምር ለእርሳቸው ሲል አቋርጦ ነበር። በዚህም እርሱ እርሳቸውን ለማገዝ የማይቆፍረው ድንጋይ አልነበረም። አንዱ ባጃጅ መንዳት ነው።
ልጆች አሊን ስታዩት በጣም ትንሽ ልጅ ነው። ነገር ግን በከተማዋ ጎበዝ ከሚባሉት አሽከርካሪዎች ውስጥ ይመደባል። በጣም ጎበዝ ሹፌር ነው። ብዙ ጊዜውን ለሥራው ከመስጠቱ አንጻር በትምህርቱ ውጤታማ አልነበረም። በዚህም ከምወድቅ ትንሽ እናቴን ላግዝና የተሻለ ገቢ ሳገኝ ተመልሼ እማራለሁ በማለት ወስኖ ትምህርቱን አቋርጦ እናቱን ሲያስተዳድር ነበር። ሆኖም ትምህርቱን በማቋረጡ ሁልጊዜም ይቆጭ ነበር።
መማር ያለውን ጠቀሜታ በደንብ ይረዳልና አሁን ወደ ትምህርቱ ተመልሶ የሰባተኛ ክፍል ትምህርት ማጠቃለያ ፈተናውን ወስዷል። ገና ባልጠነከረ ጉልበቱ ባጃጅ እየነዳ ቤታቸውን ሲደጉም ጎበዝ እንደሆነ እንጂ ዝቅተኛ ስሜት ተሰምቶትም አያውቅም። ትምህርቱ ላይ ብቻ የሚያተኩር ቢሆን ኖሮ ሁሉንም እንደሚበልጣቸውም ያምናል። እናም ልጆች የመማር ሙሉ እድል ካላቸው ትምህርታቸው ላይ ልዩ ትኩረት ማድረግ እንደሚገባቸው ይመክራል። በተመሳሳይ ለቤተሰባቸው የሚያደርጉትና የሚችሉት ነገር ካለ ለጉልበታቸው ሊሳሱ እንደማይገባም ያወሳል።
ተማሪ አሊ ባጃጅ ነድቶ በሚያገኘው ገቢ ብቻ አይደለም ቤተሰቡን የሚያግዘው በቤት ውስጥ ሳይቀር የተለያዩ ሥራዎችን በመሥራት ያግዛቸዋል። ምክንያቱም ሴት ልጅ ስለሌላቸው በዚህ ማገዝ ግዴታው እንደሆነ ያምናል። እናም ለምሳሌ፡- ወጥ ይሰራላቸዋል፤ ከሰልም ያቀጣጥላል፤ ልብስ ማጠብና ገበያ መላላክም የእርሱ ኃላፊነቶች ናቸው። በተጨማሪም የቤት ጽዳት ላይም በጣም ጎበዝ ነው።
‹‹ልጆች የእኔ እጣ ባይደርሳቸው ደስ ይለኛል። ምክንያቱም ከጓደኞቼ ተለይቼ ትምህርቴን በማቋረጥ መማር ባለብኝ ጊዜ እንዳልማር ሆኛለሁ። እንደልብ የምፈልገውን እንኳን ለማሟላትም እቸገራለሁ። በዚህ ውስጥም ቢሆን ግን ለመማር መጣሬን አደንቀዋለሁ። ምክንያቱም ተመልሼ መማር ችያለሁ›› ይላልም። ስለዚህም ለእናንተ የሚመክረው ነገር ልጆች ሁልጊዜም ቢሆን ለትምህርታቸው ትኩረት መስጠት እንዳለባቸው ነው።
ሌላው ያናገርኩት ልጅ አብዱል ሀሰን ሲሆን፤ እንደ አሊ ሁሉ የሰባተኛ ክፍል ተማሪ ነው። የሚማረውም በዳርሳጊታ አንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቤት ነው። በትምህርቱ መካከለኛ ተማሪ ሲሆን፤ አሁን ተሸላሚና ጎበዝ ተማሪ ለመሆን ተግቶ በማጥናት ላይ ነው። በተለይ ትምህርቱ ማለቁ ለዚህ እድል እንደሚሰጠውም ይናገራል። ምክንያቱም ሰፊ ጊዜ ስለሚኖረው ከጨዋታ ይልቅ ማጥናቱ ላይ ያተኩራል። በዚያው ልክ ቤተሰቡንም ከማገዝ ወደኋላ አይልም።
እናቱ አዛውንት ሲሆኑ፤ በሸቀጣሸቀት ንግድ ላይ ተሰማርተው ለእርሱ የሚያስፈልገውን ያሟሉለታል። እናም አሁን በአለችው ጊዜ ከጥናቱ ጎን ለጎን ማድረግ የሚፈልገው እናቱን ማገዝ ነው። ለአዲሱ ዘመን ብዙ የሚያስፈልጉት የትምህር ቁሳቁስም ስለሚኖር እነርሱን ለመሸፈን እንደሚሯሯጥም አጫውቶናል።
አማን ኑሩ ሰይድም እንዲሁ የሰባተኛ ክፍል ተማሪና በዳርሳጊታ አንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቤት ተማሪ ሲሆን፤ የእረፍት ጊዜውን በምን አይነት ሁኔታ እንደሚያሳልፍ ነግሮናል። እርሱ ዶክተር መሆን ይፈልጋል። ለዚህም ትምህርቱን በሚገባ ያጠናል። ለዚያ የሚያበቃውን ነገርም ከአሁኑ ጀምሮ እየሰነቀ እንደሆነ አጫውቶናል።
እነ አማን በጦርነት አካባቢ ውስጥ ስለነበሩ እንደሌላው ክልል ተማሪዎች ትምህርታቸውን አላጠናቀቁም። እኛ ያገኘናቸው ጊዜም ፈተና ላይ ነበሩ። እናም በአካባቢያቸው ችግር ቢበዛም ውጤታማ መሆን እንዳለበት ያምናልና በፈተና ውስጥ ሆኖ ያነብ እንደነበር ነግሮናል። አሁን በወሰዱት ፈተናም የተሻለ ውጤት እንደሚያመጣ ይናገራል። ምክንያቱም ዶክተር ለመሆን ጎበዝ መሆን ያስፈልጋል ባይ ነው።
ልጆች አማን ዶክተር መሆንን ለምን እንደሚፈልግ ታውቃላችሁ? በጦርነቱ የተጎዱ በርካታ ሰዎችን በማየቱ እንደነዚህ አይነት ሰዎችን አክሞ መፈወስ ስለሚፈልግ ነው። ከዚያ ውጪ በትምህርት ቤት ውስጥ ችግኝ መትከል ይወዳል። ይህንንም ብዙ ጊዜ ይተገብረዋል። አሁን በዚህ ክረምት እንኳን በርካታ ችግኞችን ተክሏል። ከዚህ ቀደም የተከላቸውም እንደጸደቁለት ነግሮናል።
አማን ልዩ ችሎታ ያለው ልጅም ነው። ማለትም በስዕል ሙያ የተዋጣለት ነው። ለዚህም ማሳያው በትምህርት ቤቱ ውስት ከእንጨትና ከካርቶን ቀራርጾ የሰራቸው የመማሪያ ቁሳቁሶች ናቸው። ፊደላትን በካርቶንና በእንጨት ሰርቶ የሰጠ ጎበዝ ተማሪ ነውም። ልጆች ሶስቱም ልጆች በጣም ጎበዞችና አስተማሪ ሕይወት ያላቸው እንደሆኑ በደንብ እንደተገነዘባችሁ አስባለሁ። እናንተም ከእነርሱ ተምራችሁ ያላችሁን ችሎታ በማውጣት ትምህርት ቤታችሁንና ቤተሰባችሁን ማገዝ አለባችሁ እሺ? በሉ በሚቀጥለው በሌላ ጉዳይ ላይ ሌሎች ልጆችን ይዤላችሁ እስከምቀርብ ለዛሬ በዚህ እናብቃ ። መልካም ሳምንት ተመኘሁ!!
ጽጌረዳ ጫንያለው
አዲስ ዘመን ሐምሌ 24 ቀን 2014 ዓ.ም