ባሳለፍነው ሳምንት አንድ አዲስ ፓርቲ መመስረቱን ተከትሎ በአገራችን የሚንቀሳቀሱ ፓርቲዎች ቁጥር 108 ደርሷል። የፓርቲዎች ቁጥር እንዲህ የበዛው አብዛኞቹ የፖለቲካ ፓርቲዎች የውስጥ ዴሞክራሲ ስለሌላቸው የሀሳብ ልዩነት ተፈጥሮ አለመግባባት በተከሰተ ቁጥር አኩራፊው በጓሮ በር እየወጣ አዲስ ፓርቲ ስለሚያቋቁም ይመስለኛል።
እያንዳንዱ አኩራፊ አዲስ ድርጅት ከሚያቋቁም ምርጫ ቦርድ ፖለቲካኞች እንደ እግር ኳስ ተጫዋቾች ከአንዱ ፓርቲ ወደሌላ ፓርቲ መዘዋወር እንዲችሉ የሚያደርግ የሕግ ማዕቀፍ ቢያዘጋጅ መልካም ነው። የፖለቲካ ፓርቲዎች ክልልንና ቋንቋን መሰረት አድርገው መደራጀታቸውም ቁጥራቸው እንዲያሻቅብ ያደረገ አብይ ምክንያት ነው ብዬ አምናለሁ።
በዚሁ ከቀጠልን ከክልል ወረድ በማለት ከተማን፣ አለፍ ሲልም መንደርን እንወክላለን የሚሉ ፓርቲዎች ብቅ ማለታቸው አይቀሬ ነው። ስለዚህ የዱከም ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ዱዴፓ)፣ የጨርቆስ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ጨዴፓ) የፍልቅልቅ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ፍዴፓ)፣ የውቅሮ ዴሞራሲያዊ ፓርቲ (ውዴፓ)፣ የጅግጅጋ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ጅዴፓ) እና ሌሎችም ተመሳሳይ የፖለቲካ ፓርቲዎች ይኖሩናል ማለት ነው። መች በዚህ ብቻ ያበቃል፣ ሌሎች ሰዋዊ ፍላጎቶችን መሰረት ያደረጉ ፓርቲዎችም ከች ይላሉ። ለምሳሌ እ.ኤ.አ. በ1994 ሩሲያ ውስጥ የቢራ አፍቃሪያን ፓርቲ ተቋቁሞ በይፋ ተመዝግቦ ነበር።
ዓላማውም የቢራ አፍቃሪያንን መብት ማስከበር ነው። በተያያዝነው መንገድ ከተጓዝን እኛም አገር የጫት ቃሚዎች ፓርቲ የማይመሰረትበት ምክንያት አይታየኝም። ባስ ሲልም በሃይማኖት፣ በፆታና በሙያ መስክ የተደራጁ ፓርቲዎችን ልናይ የምንችልበት እድል ሊኖር ይችላል። ታዲያ እንዲህ እንዲህ እያለ ከቀጠለ በአገራችን የሚንቀሳቀሱት ፓርቲዎች ቁጥር በፓርላማው ወንበር ልክ 547 ሊደርስ ይችላል። መንግሥት ለእነዚህ ሁሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጽህፈት ቤት ለመስጠት ካሰበ አዲስ የቤት ልማት ፕሮግራም መጀመር ሳይኖርበት አይቀርም። ለፓርቲዎች ጽህፈት ቤት መገንባትአስቸጋሪ ነው።
ምክንያቱም አንድ አዳራሽ ውስጥ ለሰዓታት ተቀምጠው እንኳን መግባባት ስለማይችሉ አንድ ብሎክ ላይ በጋራ መኖር አይሆንላቸውም። ስለዚህ ፓርቲዎቹ በሚንቀሳቀሱበት አካባቢ ለአንድ ፓርቲ አንድ ብሎክ መገንባት ግድ ይላል። ግርም ድንቅ የሚለው ነገር ደግሞ በቤተ ዘመድ ርብርብ የተመሰረተ ፓርቲ ሳይቀር በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ደጋፊዎች አሉኝ ማለቱ ነው።
በቅርቡ አንድ ሰው እንደተናገሩት፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች አለን እያሉ በሚጠቅሱት የደጋፊ ብዛት ከተሰላ የአገሪቷ ህዝብ ቁጥር ሁለት መቶ ሚሊየንን ይሻገራል። የፖለቲካ ፓርቲዎች ቁጥር መብዛት የማያሳስባቸው ይልቁንም በርካታ ጥያቄዎች ላሏት አገር 108 ፓረቲዎች ሲያንሱ ነው ብለው የሚሞግቱ ወገኖች አሉ። ሌሎች ደግሞ ሳር ቅጠሉ የፖለቲካ አዋቂና ተንታኝ በሆነበት ዘመን 108 ፖለቲካ ፓርቲዎች በዝተዋል በሚል ማለቃቀስ ተገቢ አይደለም ይላሉ። እንደነዚህ ሰዎች እምነት፣ አገሪቷ ያላት ህዝብ በሙሉ ፖለቲከኛ ሆኗል። እናም እያንዳንዱ ዜጋ ባለው የፖለቲካ አረዳድና ንቃት ልክ ከታሰበ በሺ የሚቆጠሩ ፓርቲዎችም በቂ አይሆኑም።
በርግጥ አንዳንድ ጊዜ የፖለቲካ ፓርቲዎች ቁጥር መብዛት ለዜጎች መልካም ዕድል ይዞ ሊመጣ ይችላል። ጀርመን ውስጥ እ.ኤ.አ. በ1998 የተቋቋመ ኤፒፒዲ የተባለ ፖለቲካ ፓርቲ ድምፅ ለሚሰጡት ዜጎች የቢራ ግብዣ ያደርግ ነበር። ማን ያውቃል እኛም አገር ከተፎካካሪዎቹ ልቆ ለመገኘት ሲል ድምፅ ለሚሰጡት ዜጎች የ 1 ወር የቤት ኪራይ የሚከፍል ፓርቲ ሊያመጣ ይችላል። ከ108ቱ ፓርቲዎች አንዳንዶቹ ምርጫው ሲቃረብ ምርጫ ቦርድን ፕራንክ ለማድረግ እንደተመዘገቡ ገልፀው ራሳቸውን ከምርጫው ያገልሉ ይሆናል።
አውስትራሊያ ውስጥ The Sun Ripened Warm Tomato የተባለ ፓርቲ የአውስትራልያን ምርጫ ኮምሽን ፕራንክ ለማድረግ በህጋዊ መንግድ የተቋቋመ ነበር። ፓርቲው ለተወሰነ ጊዜ ሲንቀሳቀስ ቆይቶ ምርጫ ኮምሽኑን ፕራንክ ካደረገ በኋላ ሩጫዬን ጨርሻለሁ ብሏል። እኔ የምለው አገር ያለ ፖለቲካ ፓርቲዎች አትኖርም? እንዴታ አሳምራ ነዋ ! የካናዳ ሰሜን ምዕራብ ክፍል፣ ቫቲካን፣ ኩዌት፣ ባህሬንና ማክሮኒዢያ የፖለቲካ ፓርቲ የሌላቸው አገራት ናቸው። አንዳንዶቹ እንዲያውም ለተቀረው የዓለም ህዝብ ምሳሌ መሆን የሚችሉ ዲሞክራሲ የሰፈነባቸው አገራት እንደሆኑ ይነገርላቸዋል።
አዲስ ዘመን መጋቢት 20/2011
በየትናየት ፈሩ