ሰመራ፦ በሆቴልና ቱሪዝም ዘርፍ ለሰለጠኑ የአገር ውስጥ ባለሙያዎች ዕድል አለመሰጠቱ አገሪቷ ከዘርፉ የምታገኘውን የውጭ ምንዛሬ የውጭ አገራት ባለሙያዎችን በመቅጠር እንድታባክን እያደረጋት መሆኑን የቱሪዝም ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተርና የሆቴል አስተዳደር ተመራማሪና አማካሪ አቶ ይታሰብ ስዩም ተናገሩ።
አቶ ይታሰብ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ በኢትዮጵያ ከአሥር ዓመታት በላይ በዘርፉ ልምድ ያላቸውና እስከ ባለአምስት ኮከብ ሆቴሎችን የመምራት አቅም ያላቸው የአገር ውስጥ ባለሙያዎች ቢኖሩም አብዛኞቹ ትላልቅ ሆቴሎች ከውጭ አገራት ባለሙያዎችን እያስመጡ ይቀጥራሉ።
ይህ አካሄድ ዜጎችን የሥራ ዕድል እንዳያገኙ ከማድረጉም በላይ አገሪቷ በዘርፉ የምታገኘውን የውጭ ምንዛሪ የውጭ አገራት ባለሙያዎችን በመቅጠር መልሳ እንድታጣው ያደርጋታል ብለዋል።
በኢትዮጵያ የሆቴልና ቱሪዝም ዘርፍ ለአገሪቱ ኢኮኖሚያዊ እድገት የበኩሉን ሚና እንዲጫወት ለማስቻል በሙያው ለሰለጠኑ የአገር ውስጥ ባለሙያዎች ዕድል ሊሰጣቸው እንደሚገባም አስተያየታቸው ሰጥተዋል።
ኢትዮጵያ ለቱሪዝም ዘርፉ ልዩ ትኩረት በመስጠትና ዜጎችም ዘርፉ በሚፈጥረው የሥራ ዕድል ተጠቃሚ ለማድረግ በሆቴልና ቱሪዝም ዘርፍ አሁን ላይ እስከ 15 በሚደርሱ የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች በመጀመሪያ ዲግሪ ባለሙያዎችን እያሰለጠነች ትገኛለች ያሉት ተመራማሪው፤ አብዛኞች ትላልቅ ሆቴሎች ለአገር ውስጥ ባለሙያዎች ዕድሉን በመንፈግ የውጭ አገራት ባለሙያዎችን እየቀጠሩ እንደሚገኙም አስረድተዋል።
እነዚህ ከውጭ አገራት የሚመጡ ባለሙያዎች ከአገር ውስጥ ባለሙያዎች አንጻር እዚህ ግባ የሚባል የተለየ ልምድና ብቃት እንደሌላቸው ጠቅሰው፤ በአገሪቱ ውስጥ በሚገኙ ኮሌጆችና ዩኒቨርሲቲዎች የሚሰለጥኑ ሙያተኞች ከአሥር ዓመታት በላይ የሥራ ልምድ ያላቸውና እስከ ባለአምስት ኮከብ ሆቴሎችን ማስተዳደር የሚችሉ መሆናቸውም አብራርተዋል።
ለምሳሌ በአንድ ትልቅ ሆቴል ውስጥ ከሚሠሩ ከአምስት መቶ በላይ የአገር ውስጥ ባለሙያዎች የሚያገኙት ደመወዝ ስድስት ወይም ሰባት የሚሆኑ የውጭ ባለሙያዎች ከሚያገኙት ደመወዝ ያነሰ ነው ያሉት አቶ ይታሰብ፤ እነዚህ የውጭ ባለሙያዎች ወደ ኢትዮጵያ ሲመጡ የተለየ እውቀትና ችሎታ ይዘው ከሆነም የአገር ውስጥ ባለሙያዎችን አሰልጥነው መመለስ አለባቸው ሲሉ አሳስበዋል።
እንደ አቶ ይታሰብ ገለጻ፤ ዓለም አቀፍ ሆቴሎች በኢትዮጵያ ሥራ ከጀመሩ ከሃያ እስከ ሠላሳ ዓመት ቢሆናቸውም በምክትል ሥራ አስኪያጅ ደረጃ እንኳን የአገር ውስጥ ባለሙያዎችን ማፍራት አልቻሉም። በሆቴሎች ሼፎች፣ የምግብና የመጠጥ ኃላፊዎችን ጨምሮ ሌሎች የየዘርፉ ኃላፊዎች የውጭ አገራት ባለሙያዎች ናቸው።
ከሦስት ዓመታት በፊት ኢንስቲትዩቱ አንድ ጥናት አካሂዶ እንደነበር አስታውሰው፤ በሆቴልና ቱሪዝም ተቋማት የሰለጠነ ባለሙያ ቁጥር ከ26 በመቶ አይበልጥም፤ አብዛኛው ሥራ የሚሠራው በዘርፉ ባልሰለጠኑና በማይመለከታቸው ሰዎች ነው ሲሉ ገልጸዋል።
የአገልግሎት ጥራት ይሻሻል ከተባለ ዘርፉ በሰለጠኑ ባለሙያዎች ሊመራ ይገባል ሲሉ ጥሪ ያቀረቡ ሲሆን፤ ለቱሪዝም ዘርፉ ትኩረት ተሰጥቶት ከተሠራበት ለአገሪቱ ኢኮኖሚ እድገት ትልቅ አስተዋጽዖ ሊኖረው እንደሚችልም ጠቁመዋል።
የአገር ውስጥና የውጭ ኮሌጆችና ዩኒቨርሲቲዎች ባለሙያዎችን ለማፍራት እየሠሩ ይገኛሉ ያሉት ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ፤ ኢንስቲትዩቱ ለጉዳዩ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ እንደሚገኝና ወደፊትም አጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።
ባለሙያው ስለኢትዮጵያ የቱሪዝም ዘርፍ ያለበትን ሁኔታ ሲገልጹ፤ አገሪቷ በቱሪዝም ዘርፍ እምቅ አቅም አላት ያሉ ሲሆን፤ ከዚህ ዘርፍ መጠቀም ባለባት ልክ እንድትጠቀም የባለድርሻ አካላት ቅንጅት ወሳኝ መሆኑንም አስገንዝበዋል።
አገሪቷ ያሏትን እምቅ ሀብቶቿ ለማስተዋወቅና የተሻለ ውጤት እንዲመጣ ውጤታማ የማስተዋወቂያ ዘዴዎችን መጠቀምና ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት በቅንጅት እንዲሠሩ ማድረግ ጊዜ የማይሰጠው ጉዳይ መሆኑንም አስረድተዋል። አክለውም፣ እስካሁን ባለው ሁኔታ አብዛኞቹ ሥራዎች የሚሠሩት በተናጠል ስለሆነ ገንዘብና ጊዜ እንዲባክን ምክንያት ሆኗል ብለዋል።
አብዱረዛቅ መሐመድ
አዲስ ዘመን ሰኔ 28 /2014