ቸገር ያለ ጊዜ ሲያጋጥም ሀሳብም አብሮ ቸገር ማለቱ የግድ ነው። በመሆኑም፣ ቸገር ያለ ጉዳይ ሲያጋጥም ደግሞ የባሰውኑ ሁሉም ነገር ቸገርገር ይልና ነገር አለሙ ሁሉ ድብልቅልቅ ይላል። ያኔ ወደ ኋላ መለስ ብሎ ማሰብ የግድ ይሆንና ይመጣል። የነገሮችን፣ ክስተቶችን … ታሪካዊ ዳራ መፈተሽ የማይታለፍ ሆኖ ከተፍ ይላል።
በርእሳችን ላይ ትኩረት የሰጠነው ”በፍፁም አይደገምም!” (Never Again) እዚህ እንደ ጠቀስነው ጉዳዩ ቀላል አይደለም። ይዘቱ እንደ ቅርፁ ሳይሆን ከዛም በላይ የተራመደ፤ የሰውን ልጅ ሁሉ በአንድነት አንድ (ቢያንስ በጊዜው) ያደረገ፤ በታሪክ መዝገብ ላይ በወርቅ ቀለም የተፃፈ፤ የነበረውን የአለም ታሪክ ባልነበረ መልኩ ይቀይረዋል ተብሎ የተጠበቀ የአለም መንግስታት ውሳኔ (እና የቃል ኪዳን ሰነድ) የነበረ ውል ነው። ለምን?
እንደሚታወቀው፣ ሁለተኛው የአለም ጦርነት የሰውን ልጅ ቅርጥፍ አድርጎ የበላ ጦርነት ነው። ታሪኩን በገራገር ቋንቋ እንደ ወረደ ስናስቀምጠውም፣ ”ከ1932 ዓ.ም. እስከ 1937 ዓ.ም. ድረስ የተደረገ ታላቁ አለም አቀፍ ጦርነት ነው፤ በዚህ ጦርነት መጨረሻ የአክሲስ ሃያላት ማለትም ጀርመን፣ ጣልያንና ጃፓን ተሸነፉ። በጠቅላላ አለም ዙሪያ 70 ሚልዮን ሕዝብ በጦርነቱ ጠፉ። ከ20 ሚልዮን ህዝብ በላይ ለከፋ የአካል ጉዳት ተዳረገ። ከጦርነቱም በኋላ አሜሪካና ሶቭየት ኅብረት የዓለም ዋና ኃያላን ሆኑ። በሁለተኛው የአለም ጦርነት ወቅት ዋናው ተዋናይ ሂትለር ነበር።” የሚል ሆኖ ነው የምናገኘው።
በዚህ ምክንያት የአለም መንግስታት አንድ ነገር (ስምምነት?) ላይ መድረስ እንዳለባቸው ተገነዘቡ። በመሆኑም አንድ ድምዳሜ ላይ መድረስ ያለባቸው መሆኑንም ተረዱ። ያ ከላይ የጠቀስነው በሁለተኛው የአለም ጦርነት ሳቢያ የደረሰው ሰብአዊና ቁሳዊ ውድመት መደገም የሌለበት መሆኑን አመኑ። በዚሁ ምክንያትም ”መቸም አይደገምም” (Never Again) ሲሉ ተማማሉ። ”መቸም አይደገምም!!!” አሉ፣ የእምነት ቃላቸው፣ የአንገት ማተባቸው እስኪመስል ድረስ።
እውቁ የፊዚክስ ሊቅ አልበርት አንስታየን ”በሶስተኛው የአለም ጦርነት አሸናፊው ማን ይሆናል ብለህ ትጠብቃለህ?” ተብሎ ሲጠየቅ ”እሱን ተውትና የአራተኛውን ልንገራችሁ” ይላል። ”እሺ እሱን ንገረን” ሲባል ”በዛን ጊዜ ማንም አይኖርም፤ አይተርፍ” ብሎ መለሰ። ይህም እነሆ በጦርነት ታሪክ መዝገብ ላይ ተጠቃሽ ጥቅስ ሆኖ ተመዝግቦለት ይገኛል። ይህ የአንስታየን ምሁራዊ ትንበያ፣ ገና ያኔውኑ ”መቸም፣ መቸም አይደገምም” (Never Again) የሚለው የመሪዎች ምህላ ”ፌዝ” መሆኑ እንደገባው ያሳያልና እውነትም አንስታየን ሊቅ ነበር።
ከዚሁ ከጦርነትና እርስ በርስ መተላለቅ ጉዳይ ሳንወጣ አንድ ሌላ ተጠቃሽ ጥቅስን እናንሳ። እሱም የእውቁ የቀድሞው የኩባ ፕሬዚዳንት ፊደል ካስትሮ ንግግር ነው።
ካስትሮ ”የሚያስፈልገው የሀሳብ ጦርነት (Battles of Ideas) እንጂ የቴክኖሎጂ ጦርንት አይደለም። እንደ አለመታደል ሆኖ ግን አለም ምርጫው ያደረገው ሁለተኛውን ነው። ይህ ደግሞ ውጤቱ የከፋ እንጂ በፍፁም ለሰው ልጅ የሚመቸው አይሆንም” ነበር ያሉት። ይህ ጉዳዩ በተነሳ ቁጥር ሳይጠቀስ የማይታለፈው የካስትሮ ጥቅስ ዛሬ ላይ ሆኖ ለተመለከተው ያንኑ፣ ከላይ የጠቀስነውን ”መቸም፣ መቸም አይደገምም” (Never Again) በሚገባ የተረዳና የማይተማመን ጓደኛ በየወንዙ ይማማላል እንዲሉ፣ ገና ከመነሻው እማይረባ ብቻ ሳይሆን እማይሰራ መሆኑን አስቀድመው የተረዱ ስለመሆናቸው ጥሩ ማሳያ ነው። (እዚህ ላይ ጉዳዩን አፍሪካዊ እናድርገውና የአፍሪካ ህብረት በ2023 የመደበኛ ስብሰባውን መሪ ቃል ”በ2020 በአፍሪካ የነፍጥ ድምፆችን ጭጭ ማድረግ” የሚል የነበረ ሲሆን፤ መሪዎቹም ጉባኤውን ያጠናቀቁት በየአገራቸው ይህንኑ ተግባራዊ ለማድረግ በመስማማት መሆኑን አስታውሰን እንለፍ።)
በግልፅ መነጋገር ያስፈልጋልና ዛሬ ”መቸም፣ መቸም አይደገምም” (Never Again) የሚለው የማይረቡ ጓደኛሞች ምህላ፤ በ”ይደገም፣ ይደገም …!!!” ተተክቷል የሚሉ አጥኚዎች ቁጥራቸው እየበዛ ብቻ ሳይሆን ወደ መድረክም በብዛት እየመጡና ተከታዮችንም እያበዙ እንደሚገኙ ማረጋገጫው ብዙ ነው።
አስተያየት ሰጪዎቹ ”Again and A gain” ያሉት፤ እኛ በሙዚቃ ኮንሰርት ሙድ ”ይደገም፣ ይደገም …!!!” ያልነው እንደው ዝም ብለን ”ዘፈን ለማሞቅ” ወይም ጨዋታ ለማሳመር አይደለም፤ መሬት ላይ ያለው እውነታ፣ እየሆነና እየተደረገ ያለው ድርጊት … ይህንኑ ስለሚያረጋግጥ ብቻ ነው።
ልብ እንበል፤ ከሁለተኛው የአለም ጦርነት ከተጠናቀቀና ”መቸም አይደገምም” (Never Again) ምህላ ከተፈፀመ በኋላ ምን ምን ተግባራት ተፈፀሙ? ብለን ብቻ እንጠይቅ። መልሱንም ምን ያልተፈፀመ ነገር አለን? ለዛውም ”ይደገም ይደገም …!!!” በሚመስል መልኩ ሆኖ ነው የምናገኘው።
ሊቢያ አፈር ነህና …. እንደ ተባለው ሁሉ አፈር ሆናለች፣ ሶሪያ ከ”አለች” ይልቅ! ”የለችም” በሚባለው ደረጃ ላይ ነች፣ ናጄሪያ ቦኮ ሀራም ሲፈልግ የሚያርሳት፣ ሲፈልግ የሚቆፍራት አገር ነች፤ ደቡብ ሱዳን … ዝም ነው። ሩዋንዳ . . . ምን ሆኖ ነበር? (ባህላዊው ድምፃዊ ”… ምን ልበላችሁ (2 ጊዜ)/ ታውቁት የለም ወይ በ’የቤታችሁ” እንዳለው ነው)፤ አፍጋኒስታን … ቆጥረን አንጨርሰውም። ወዳለንበት ወቅታዊ ሁኔታ እንመለስ።
ያለንበት ሁኔታ ከአለማችን ሰላማዊው ቀጣና ይልቅ ሰላም ያልሆነው እየበዛ ያለበት ነው። ያለንበት ሁኔታ ከተስፋ ይልቅ ተስፋን የሚያጨልም የሚመስል ነው። ያለንበት ሁኔታ ፍርደ ገምድሉ በዝቶ ፍርድ የናፈቀበት፤ ፍትህና ርትእ ከነበሩበት የተሰደዱ እስኪመስል ድረስ ለሽታ እንኳን የታጡበት ነው።
ያለንበት ሁኔታ የሰው ልጅ ወጥቶ ለመግባት አይደለም ሳይወጣም እንኳን መኖር ያልቻለበት ነው። ያለንበት ሁኔታ ”ወንድም በወንድሙ ላይ …” እንዲሉ ወንድም በወንድሙ ላይ የተነሳበት ነው። ያለንበት ሁኔታ ”መቸም፣ መቸም አይደገምም” (Never Again) ወደ ”ይደገም፣ ይደገም …!!!” የተቀየረበት፤ ተቀይሮም ስራ ላይ ”በስፋት” እያዋለ ያለበትና ”ተጠናክሮ የቀጠለበት” ነው። ያለንበት ሁኔታ … (ኢትዮጵያ ሳትቀር ”መቸም መቸም አይደገምም” (Never Again) በማለት የቀይ ሽብር ሰማእታት ሀውልትን ብትገነባም)፤ … ያለንበት ሁኔታ …
ከላይ ”ፍርደ ገምድል”ነትን በተመለከተ አንስተናልና እሱን አስመልክተን አንድ ሀሳብ ብቻ ጣል አድርገን ጽሑፋችንን እንቋጭ።
በብዙዎቻችን እንደታመነውና ጉዳዩ የሚመለከታቸውም በመረጃና ማስረጃ አስደግፈው እንደ ሚነግሩን፤ ”ፍርደ ገምድል”ነት የዘመኑ ፋሽን ሲሆን፤ የዳቦ ስሙም ”Both-side-ism” ይባላል።
እንደ ተመራማሪዎቹ ብያኔ ”Bothsidism” ማለት ሁለት ተፋላሚ ወገኖችን እኩል አድርጎ የማየት፣ ጥፋተኛውን ለይቶ ”አንተ ጥፋተኛ ነህ” ማለት አለመቻል፤ ሲያስፈልግ ሁለቱንም እኩል ጥፋተኞች አድርጎ የማየት፣ ሲያስፈልግ ደግሞ ሁለቱንም ’ትክክል ናችሁ’ ብሎ የመበየን … አዲስ የፖለቲካ ፈሊጥ ነው፤ አላማውም በእጅ አዙር የራስን ጥቅም ማስከበርና ለዚህም ሁለቱን ተፋላሚ ወገኖች ጭዳ (የጦስ ዶሮ) የማድረግ የዘመኑ ”ብልጦች” አካሄድ ነው።
እዚህ ላይ ግን አንድ ነገር ማንሳትና ለውይይት አቅርቦ መሄድ ያስፈልጋል። እነዚህ ሁለት ተፋላሚዎች፣ ለ”Bothsidism” ኢሰብአዊ ፍልስፍና አራማጆች ጥቅም ሲባል ጭዳ እየሆኑና የሚሆኑ ወገኖች መቼ ነው የሚነቁትና ሕዝባቸውን ከሰላምና ፀጥታ ስጋት ነፃ የሚያደርጉት የሚለው ነው ! መልካም ጊዜ።
አዲስ ዘመን ሰኔ 24 ቀን 2014 ዓ.ም