እንደምን አላችሁ ልጆች፣ ሰላም ናችሁ? ሳምንቱ እንዴት ነበር፣ ጥሩ ነበር አይደል? ወይስ ጥናትና ቤተሰብን ማገዝ በዝቶባችሁ ቆየ? መቼም ወቅቱ የፈተና ሰዓት ስለሆነ ይህንን ተግባራችሁን እንደማትጠሉት አስባለሁ። ምክንያቱም በትምህርት የተሻለ ለመሆንና ጥሩ ውጤት ለማምጣት ግድ ማጥናት ያስፈልጋል።ንባብ መጀመር ያለባችሁ ገና ትምህርት መማር ስትጀምሩ ቢሆንም ለፈተና ደግሞ ሁሉንም መከለስ ግድ ነው።
እናንተ ደግሞ ይህንን እንደምታደርጉ እርግጠኛ ነኝ።በየቀኑ በማንበብ ተግባር ላይም እንደምትጠመዱ ይሰማኛል።ይህንን ማድረጋችሁ ደግሞ እጅግ በጣም ጥሩ ነው።ለአገራችሁም ለቤተሰባችሁም ኩራት ትሆናላችሁ።ልጆች ለዛሬው ይዘንላችሁ የመጣነው ጉዳይ ብዙዎቻችሁ የምትወዱትና የምትማሩበት ነው።ሁለቱን ንባብ ወዳድ ልጆች እናስተዋውቃችኋለን።ከዚያ በፊት ግን ስለ ንባብ ምንነት ትንሽ እንንገራችሁ።
ማንበብ ከአራቱ የቋንቋ ክህሎቶች አንዱ ሲሆን፤ ጽሑፍን፣ ምልክትን፣ ምስልን ተመልክቶ የመረዳት፣ የመገንዘብ፣ ለመዝናናት ተጨማሪ ዕውቀት ወይም መረጃ ለማግኘት እና ለሌላ ለማስተላለፍ የሚደረግ ሂደት ነው።ለመሆኑ ልጆች የማንበብ ጥቅሙ ምን እንደሆነ ታውቃላችሁ? ጥቂት ነገር እንንገራችሁ።
ንባብ አዳዲስ ነገሮችን ለማወቅ እና ለመዳን፤ የአስተሳሰብ ክህሎት ለማዳበር፤ ለጥናትና ምርምር(አዳዲስ ነገሮች ለማግኘት)፤ ክፉውንና በጎውን ነገር ለመለየት፤ የአስተሳሰብ አድማሳችንን ለማስፋት(ሥነምግባርን ለማስተካከል)፤ በምናደርገው ነገር ሁሉ እርግጠኛ ለመሆንና ጥያቄዎችን ለመመለስ ይጠቅማል።
በተጨማሪም ንባብ ታሪክ እና ትውፊትን ለማወቅ፣ የቀደሙ አባቶቻችን ታሪክ ለመገንዘብ፤ መረጃን ለማግኘትና ሙሉ ሰው ለመሆን፤ ራሳችንን ለማዝናናት፤ አውቀን ለሌሎች ለማስረዳት፤ ጥበበኛ ለመሆን፤ ዓላማና ግብን ለማሳካት፤ ለነገሮች ሁሉ ምክንያታዊ እንድንሆን ያደርገናልም።
ሌላው የንበብ ጥቅም የዓለምን ነባራዊ ሁኔታ ለማወቅና ለመረዳት፤ የሰዎችን ሀሳብ በቀላሉ ለመገንዘብ፤ የአምላክን ጥበብ እና ቸርነት እየተረዱ ለመመሰጥ፤ ለችግሮች መፍትሄ ለማግኘት ያገለግላል።ከዚህም ባሻገር ብዙ መዘርዘር የምንችላቸው ጥቅሞች አሉት።እስኪ እናንተም ትንሽ ተናገሩ? ብዙ መዘርዘር ቻላችሁ አይደል ጎበዞች!!
ወደዋናው ሃሳባችንና የልጆቹ ጉዳይ ስንገባ መጀመሪያ ያነጋገርናት ልጅ ማርካን ዘላለም ትባላለች።በሐዋሳ ከተማ የምትኖር ሲሆን፤ በቦናፋየር ትምህርት ቤት ትማራለች።በጣም ጎበዝ የአራተኛ ክፍል ተማሪ ነች።ለዚህ ያበቃት ደግሞ ንባብ ወዳድነቷ እንደሆነ ትናገራለች።በተጨማሪም እርሷ የምታስተባብረው ቡድን ኃላፊ መሆኗም ብዙ እንደተቀማት ነግራናለች።ምክንያቱም እነርሱን ለማስረዳት ስትጥር የማታውቃቸውን ነገሮች እንድትመረምርና ጠይቃ እንድትረዳ ትሆናለች።
ልጆች ሌላው የማርካን ልዩ ባህሪ ወንድሟን እየተከፈላት ማስጠናቷ ነው።በሚከፈላት ገንዘብ ደግሞ ምን እንደምትገዛ ታውቃላችሁ? መፀሐፍትን ነው።ይህ የሚሆነው ደግሞ ለሁለት ነገር ሲሆን፤ የመጀመሪያው ለራሷ ልታነባቸው የምትፈልጋቸውን ትገዛለች።ከዚያ በኋላ ደግሞ እርሷ ወይም ጓደኞቿ ለልደት ተጠርተው ከሆነ የምታበረክትላቸው ነው።በምንም ተአምር ከመጽሐፍ ውጪ ስጦታ ለማንም አትሰጥም።
ለዚህ ምክንያቷ ምን መሰላችሁ? መጽሐፍ የማይሰበሩ፣ የማይጠፉና ከአዕምሮ የማይሰወሩ ልዩ ማስታወሻዎች መሆናቸውን ስለምታምን ነው።ማርካን በጣም የሚገርመው ከመፀሐፍት ጋር በተያያዘ ድንቅ ተግባር ከውናለች።ይህም ለአብርሆት ቤተመጸሐፍት የሚሆን 67 መጽሐፍ በራሷ ገንዘብ ገዝታ ከወንድሟ ጋር በመሆን ማበርከቷ ነው።ጓደኞቿም ቢሆኑ በዚህ ተግባር ላይ እንዲሳተፉ አነቃቅታለች።እንደውም የእርሷን መፀሐፍ ስታስረክብ የእነርሱንም ጨምራ እንደነበር አጫውታናለች።
ልጆች ማርካን ማንበብን የጀመረችው ገና አንደኛ ክፍል ከመግባቷ በፊት ነው።ለዚህ ደግሞ መሰረት የሆኗት አባቷ ናቸው።እርሷ የምትወዳቸውን ጭምር ለይተው ስለሚያውቁ መType equation here.ሐፍ እየገዙ ይሰጧታል።በዚህም ብዙ ጊዜ የታሪክና የሳይንስ መጽሐፍት ላይ ልዩ ትኩረቷን አድርጋ ታነባለች።ስለአገሯ ጠንቅቃ ለማወቅም የማታነበው አገራዊ መጸሐፍት እንደሌለም ነግራናለች።በተጨማሪ ለትምህርት አጋዥ የሆኑ ፊልሞችን ማየት ያስደስታታልም።ነገር ግን ይህንን የምታደርገው በእረፍት ጊዜዋ እንደ ሆነም ታነሳለች።
ማርካን ሌላም ተሰጥኦ አላት።ይህም ስነጽሁፍ በተለያየ ቋንቋ ትጽፋለች።በተለያዩ ፕሮግራሞች ላይም ታነባለች።ቋንቋ መማር በጣም የምትወድ ሲሆን፤ አሁን ላይ ፈረንሳይኛ ቋንቋን ለማወቅና ለመማር የተለያዩ ቪዲዮችን እንደምታይም አጫውታናለች።
ማርካን ተማሪዎች ጎበዝ የሚሆኑት መጀመሪያ ስነምግባር ሲኖራቸውና ሰዎችን ሲያከብሩ ነው ትላለች።እርሷም ብትሆን መምህሮቿን፣ ወላጆቿንና ከእርሷ የሚበልጡትን ሁሉ እንደምታከብርም ነግራናለች።ለልጆችም የምትመክረው ሰው አክባሪና አንባቢ ሁኑ የሚለውን ነው።
ናታን ዘላለም የማርካን ታናሽ ወንድም ሲሆን፤ የሦስተኛ ክፍል ተማሪ ነው።እርሱም ልክ እንደማርካን በጣም ጎበዝ ተማሪ ሲሆን፤ ማንበብም በጣም ይወዳል።እንደውም ከንባብ ጋር ተያዞ አንድ የሚለው ነገር አለ።‹‹ ሁሉም ሰው የራሱ ድርሻ አለው።ለተማሪ ድርሻው ደግሞ ማንበብ ብቻ ነው።ይህ ደግሞ ለትምህርታቸው የላቀ ሚና ይኖረዋል።እናም አንባቢ መሆንን አጥብቀው ሊይዙ ይገባል።›› የሚል ነው።
ትምህርት ቤታቸው ማንበብን በጣም የሚያበረታታ እንደሆነ የነገረን ናታን፤ በሳምንት አንድ ቀን ክፍለጊዜ ተመድቦላቸው ቤተ መጸሐፍት ገብተው እንደሚያነቡ አጫውቶናል።በተጨማሪም ቤታቸው የፈለጋቸውን መጽሐፍ ይዘው በመሄድ የማንበብ ባህላቸውን እንዲያዳብሩም ይበረታታሉ።ከዚያ ውጪ ራሳቸው ቤተሰብ ከሚሰጣቸው ገንዘብ ላይ እየቆጠቡም ይገዛሉ።ስለዚህም ቤታቸውም ሆነ ትምህርት ቤት ውሏቸውን ከመጽሐፍት ጋር እንደሚያደርጉም ነው የነገረን።ልጆችም ይህንን ቢያደርጉ መልካም ነው ይላል።
ልጆች እነ ማርካን በጣም ጎበዝ ናቸው አይደል? እናንተም እንደነእርሱ ጎበዝ መሆን ከፈለጋችሁ የመከሯችሁን ተግባራዊ አድርጉ።ለዛሬ ይህንን ያህል ካልናችሁ ይበቃል።በቀጣይ በሌላ ታሪክ እስክንገናኝ ቸር ሰንብቱ!!
ጽጌረዳ ጫንያለው
አዲስ ዘመን ሰኔ 19/2014