እንደምን አላችሁ ልጆች፣ ሰላም ናችሁ? ሳምንቱ እንዴት ነበር፣ ጥሩ ነበር አይደል? ወይስ ሥራና ጥናት በዛባችሁ? ይህ ከሆነ አይክፋችሁ። ምክንያቱም እነዚህን ተግባራት መከወን ለነገ ተስፋችሁ ትልቅ ጥቅም አለው። ስኬታችሁ ላይም የሚያደርሳችሁ ነውና አትጥሉት። ልጆች ለመሆኑ ስለ አሸናፊነትና ውድድር ምን ያህል ታውቃላችሁ? በውድድር ተሳትፋችሁ አሸናፊ የሆናችሁበትን ቀን ታስታውሳላችሁ? እርግጠኛ ነኝ አዎ ብላችሁኛል። ጎበዝ ስለሆናችሁ ቢያንስ በትምህርት ቤት ተወዳድራችሁ ማሸነፋችሁ እንደማይቀር እገምታለሁ። ስለዚህም የአሸናፊነትን ስሜት ታውቁታላችሁ።
አሸናፊነት ምንድነው? ካላችሁ በራሱ ባህሪይ ነው። የምንለምደውና ሆነን የምንቀጥለው። የሚጀምረው ደግሞ ከአዎንታዊ አስተሳሰብ ሲሆን፤ ቀና ፣ በጎ ፣ ጥሩ ጥሩው የሚታይበት ብቻ ነው። ነገር ግን ሁልጊዜ በአዕምሯችን የሚመላለሰው አልችለውም የሚለው ከሆነ የማይበልጠን እንኳን ቢኖር አናሸንፍም። ምክንያቱም በእኔ አቅም አደረኩት አንልም። ውስጣዊ ደስታም አይኖረንም። ስለዚህም አሸናፊው መልካም ሃሳብ እንጂ ተግባሩ ብቻ አይደለም።
ልጆች አሸናፊ ለመሆን እና ለመባል ደግሞ ውድድር እንደሚያስፈልግ መቼም ታውቃላችሁ። እናም በምንወዳደርበት ጊዜ ውድድሩ ምን እንደሚያስፈልገው ቀድሞ ማወቅ ጠቃሚ ነው። በተጨማሪም ከማን ጋር መወዳደር እንዳለብንም ማወቅ ያስፈልጋል። ለዚህም ሁሌ አንባቢና ጠያቂ መሆን ግድ ነው። የአለመቻል ሥነልቦና በምንም መልኩ አዕምሯችን ውስጥ መቀመጥ የለበትም።
አሸናፊነት በዋነኛነት ትኩረቱን የሚያደርገው ከራሳችን ጋር መወዳደርን ነው። ሆኖም ውድድር ከሌለ ግን መበላለጥ አይመጣምና ከሌሎች ሰዎች ጋር መወዳደር ግድ ነው። አንዱ ደግሞ እንደእናንተ ያሉ ተማሪዎች የሚያደርጉት የትምህርት ውድድር ሲሆን፤ በምታስቆጥሩት ውጤት እንድትበልጡ ትሆናላችሁ። ስለዚህም አንደኛ ለመውጣት መወዳደር ይኖርባችኋል።
ልጆች በውድድር ውስጥ ያለ አሸናፊነት በርካታ ባህሪያት አሉት። የመጀመሪያው ባህሪው ልንደርስበት የምንፈልገውን ማወቅ ሲሆን፤ ለጉዳዩ የጠራ አመለካከት እንዲኖረን የሚረዳን ነው። የመጨረሻ መዳረሻ ግባችንን አስበን እንድንሰራም ያግዘናል። ሩቅ የምናስብም ያደርገናል።
ሌላው የአሸናፊነት ባህሪ ግብን ማስቀመጥና በእቅድ መመራት ሲሆን፤ ግባችንን ተግባራዊ ለማድረግ የተወሰነ ጊዜ፣ ሊለኩ የሚችሉ ተግባራትና ውጤት እንዲኖረን የሚያደርገው ነው። አዎንታዊ አመለካከቶች እንጂ ፍርሀት ጭንቀትንና ውጥረትን በውስጣችን እንዳናስተናግድ የሚያደርግም ባህሪ አለው። ቆራጥና ለነገሮች መሳካት ጠንክሮ መስራትም ሌላው ባህሪይው ነው። ራስን ማወቅም እንዲሁ። በዚህ ምድር አንድም ፍፁም ሰው የለም። ስለዚህም አሸናፊነት ፍፁምነት (ሁሉን አዋቂነት) አይደለምና ደካማና ጠንካራ ጎናችንን አውቀን ጎዶሏችንን እንድንሞላ የሚያደርገን ነው።
ልጆች ስለ አሸናፊነትና ውድድር ያነሳነው ያለምክንያት አይደለም። በሂሳብ ትምህርት እንደ አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር “በኢትዮ ማት ኦሎምፒያ “የተማሪዎች ውድድር ላይ ሁለት ዙሮችን አሸናፊ ሆኖ ሦስተኛውን ዙርም ለማሸነፍ እየተጣጣረ ስላለና የአሸናፊነትን ባህሪ ስለተላበሰው ተማሪ ልናወጋችሁ ፈልገን ነው። እንግዳችን ናታን ፍሬዘር ይባላል። የቤዛ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የአራተኛ ክፍል ተማሪ ነው። በትምህርቱ በጣም ጎበዝ አንደኝነቱን ማንም ነጥቆት የማያውቅ ነው።
ናታን የመጀመሪያ ውድድሩን የጀመረው ከትምህርት ቤቱ ተመርጦ ሲሆን፤ ካሉ ጎበዝ ተማሪዎች ጋር ተወዳድሮ የላቀ ውጤት አምጥቷል። ያንን ካለፈ በኋላ ደግሞ ሁለተኛ ውድድሩን ዳግማዊ ምኒልክ ትምህርት ቤት ላይ አድርጓል። እዚያም በከፍተኛ ውጤት ማሸነፍ ችሏል። ለዚህ ደግሞ ያበቃው ንባብ ወዳድነቱ ፤ ትምህርቱን በደንብ መከታተሉና የቤት ሥራውን ሳይሰራ ትምህርትቤት አለመሄዱ እንደሆነ ይናገራል።
ልጆች ናታን ገና የ 10 ዓመት ልጅ ቢሆንም ንባቡ አዳዲስ ነገሮችን እንዲሞክር ስለሚገፋፋው አልችለውም የሚለው ነገር የለም። በተለይ ፍላጎቱ የጠፈር ተመራማሪ መሆን ነውና ለዚያ የሚያበቃውን ነገር መሞከር በጣም ያስደስተዋል። ክረምትንም ቢሆን ትምህርት ስለሌለ በዚህ ሁኔታ እንደሚያሳልፍ ነግሮናል።
ናታን በጣም የሚገርመው ከትምህርቱ ጎን ለጎን ቤተሰብን ያግዛል። ሳይታዘዝ ጭምር በጠዋት ተነስቶ ቤት ያስተካክላል። አልጋውንም የሚያነጥፈው ራሱ ነው። አሁን ግን ይህንን እገዛውን በመጠኑ ቀንሷል። ምክንያቱም ለሦስተኛ ዙር ፈተና መዘጋጀት አለበት። ፈተናው የሚሰጠው በኮከበፅብሃ ትምህርትቤት ሲሆን፤ ሁሉን ዝግጅት የተደረገው በኢትዮ ማት ኦሎምፒያ አማካኝነት እንደሆነ ነግሮናል።
ይህ ውድድር በጠቅላላ ስድስት ፈተናዎች ያሉበት ሲሆን፤ ናታን ሦስተኛውን ዙር ለመፈተን እየተዘጋጀ ነው። በስድስቱም አሸናፊ እንደሚሆን ያምናልም። ምክንያቱም ለዚያ የሚያበቃውን በቂ ዝግጅት እያደረገ ነው። የፈተናው ዋና ትኩረት ሒሳብ ላይ ቢሆንም አጠቃላይ ትምህርቱን በደንብ ማጥናትና የተሻለ ውጤት ማምጣት ካልተቻለ ማለፍ እንደማይችል ያውቃልና ለትምህርቱም ልዩ ትኩረት ይሰጣል።
‹‹ አሸናፊነት በራስ መተማመንን ይሰጣል። የተሻለ ተማሪ ለመሆንም ያስችላል። ከሁሉም በላይ ሁልጊዜ አዲስ ነገርን ያስገኛል›› የሚለው ናታን፤ ተሸላሚና አሸናፊ ለመሆን የተገኙ እድሎችን መጠቀምና ልምዶቹን ቀምሮ ለሌላው ጊዜ መዘጋጀት ወሳኝ እንደሆነ ያነሳል። ሁልጊዜ አሸናፊነትን እያሰቡ መራመድም ተገቢ እንደሆነ ይመክራል። ልጆች እናንተው የናታንን ምክር ሰምታችሁ አሸናፊ ሁኑ፤ ነጋችሁንም አሳምሩ በማለት ለዛሬ አበቃን።
ጽጌረዳ ጫንያለው
አዲስ ዘመን ሰኔ 12/2014