አዲስ አበባ፡- በደቡብ ክልል ሰባት ዞኖችና ሦስት ልዩ ወረዳዎች ውስጥ በ334 ሺህ 760 ሄክታር ማሳ ላይ አዲሱ መጤ ተምች መከሰቱን የደቡብ ክልል ግብርና ቢሮ ገለጸ።
የደቡብ ክልል ግብርና ቢሮ የግብር የአዝዕርት ልማትና ጥበቃ ዳይሬክተር አቶ ወንድማገኝ ኃይለማሪያም ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደተናገሩት፣ በክልሉ በሚገኙት 7 ዞኖችና 3 ልዩ ወረዳዎች በ334 ሺህ 760 ሄክታር ማሳ ላይ አዲሱ መጤ ተምች ተከስቷል።
አዲሱ መጤ ተምች የተከሰተባቸው ሰባቱ ዞኖች ደቡብ ኦሞ፣ ጋሞ፣ ኮንሶ፣ ጎፋ፣ ካምባታ ጣምባሮ፣ ስልጤና ጌዴኦ እንደሆኑ የገለጹት አቶ ወንድማገኝ፣ ደራሼ፣ አሌና ባስኬቶ ደግሞ የተምች ወረርሽኙ የተከሰተባቸው ሶስቱ ልዩ ወረዳዎች መሆናቸውን ተናግረዋል።
በክልሉ በያዝነው የበልግ ወቅት በሰባት ዞኖች በአገዳ ሰብሎች ከተሸፈነው ማሳ 322 ሺህ 204 ሄክታር ላይ የተምች ወረርሽኝ ተከስቷል።
የተምች ወርርሽኙም በነፍሰ ወከፍ በ28 ሺህ 219 የአርሶ አደሮች ማሳ ላይ መከሰቱን የገለጹት አቶ ወንድማገኝ፣ በጾታ ስብጥርም 26 ሺህ 953 በወንድ እና ሶስት ሺህ 158 የሴት አርሶ አደሮች ማሳ ላይ ተከስቷል ብለዋል።
በመከላከል ሥራ ላይ 10 ሺህ 73 ሄክታር ማሳ ላይ የተባይ ቁጥጥር ስራው ተከናውኗል ሲሉ የተናገሩት አቶ ወንድማገኝ፣ በአራት ሺህ 556 ሄክታር ማሳ ላይ አራት ሺህ 556 ሊትር ፈሳሽ ፀረ-ተባይ ኬሚካል በመርጨት እንዲሁም በአምስት ሺህ 517 ሄክታር ላይ ደግሞ ማሕበረሰቡ ተባዩን በእጅ ለቅሞ በመግደል የመቆጣጠር ስራ ተሰርቷል ብለዋል።
እንደ አቶ ወንድማገኝ ገለጻ፣ በዘንድሮ በልግ ወቅት የዝናብ ሁኔታ በመጠንም ሆነ በሥርጭት ያልተስተካከለ በመሆኑ በተለይም በደረቅ ቆላማ አካባቢዎች የተባዩ ክስተት ምቹ ሁኔታ እየፈጠረ ነው።
አቶ ወንድማገኝ አክለውም፣ በቀጣይም የተባዩ ክስተት ሊቀጥል ስለሚችል ሁሉም አካባቢዎች የአሰሳና ቅኝት ሥራውን አጠናክሮ በመቀጠል የባህላዊ የመከላከል ዘዴን መሠረት በማድረግ የቁጥጥር ሥራውን አጠናክሮ መቀጠል ያስፈልጋል ብለዋል።
ሙሳ ሙሐመድ
አዲስ ዘመን ሰኔ 7 /2014