ናትናኤልና የህልም ግብግቡ ልጆች እንደምን ሰነበታችሁ፤ ደህና ናችሁ አይደል? ሳምንቱን እንዴት አሳለፋችሁት ? በጥናት እንደምትሉኝ እተማመናለሁ። በተለይ ደከም ያላችሁበት የትምህርት አይነት ላይ ለየት ያለ ትኩረት አድርጋችሁ እንደምታነቡ አስባለሁ። ምክንያቱም ለቀጣዩ ውጤታችሁ የተሳካ መሆን ግድ ይህንን ማድረግ ስላለባችሁ። ስለዚህም በደንብ በማጥናት ጥሩ ውጤት ለማምጣት ስሩ እሺ።
ልጆች ዛሬም እንደተለመደው ጎበዝና በሳይንሱ ዘርፍ የተሻለ ነገር ይዞ ለመምጣት የሚጣጣር ተማሪ ይዤላችሁ ቀርቤያለሁ። ልጁ ናትናኤል ዮሐንስ ይባላል። ተወልዶ ያደገው በአዲስ አበባ ሲሆን፤ የዳግማዊ ምኒልክ አጸደ ሕጻናትና መጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት የሰባተኛ ክፍል ተማሪ ነው። ሳይንስ ላይ ልዩ ፍላጎት ያደረበት ተማሪ ነው።
ትምህርቱን የሚማረው ከአያቱ ጋር ሆኖ ነው። በዚህም የአያት ልጅ ቅምጥል እንደሚባለው አይነት የልጅነት ጊዜን ያሳልፋል። በዚያ ላይ አያቱ ባይማሩም የሚያስተምሩትና ያስለመዱት ብዙ ነገር አለ። ከእነዚህ መካከል ሰዎችን መርዳት አንዱ ነው። ‹‹መስጠት ለሰዎች ማድረግ ብቻ ሳይሆን ለራስም ፍቅርን መቀበልም ነው›› የሚል እምነት ያለው ልጅ እንዲሆን አድርጎታል። እምነቱን ደግሞ በተግባር የሚተረጉም ነው። ለምሳሌ በትምህርት ቤት ብቻ ብዙ ነገር ያደርጋል።
አንዱ በምገባ ወቅት ለህጻናቱ የሚያደርገው እንክብካቤ ሲሆን፤ ብዙ ጊዜ ሲሯሯጡ ይደፋባቸዋልና ዳግም ለመጠየቅ ስለሚፈሩ ሳህኑን ሰጥተው ለመውጣት ይገደዳሉ። በዚህ ጊዜ ከእነርሱ እኔ ረሃብን መቋቋም እችላለሁ ብሎ ያስባልና የእርሱን ምሳ ሰጥቷቸው ይወጣል። ደስ የሚል ባህሪ ነው አይደል ልጆች? አያችሁ አንዱ ለአንዱ መኖር እንዲህ ነው። እናንተም ይህንን መልካምነት መገለጫችሁ አድርጉ እሺ።
ናትናኤል በልጅነቱ ነገሮችን ፈታቶ ማየት የሚወድ ሲሆን፤ ውስጣዊ ነገሮች በጣሙን ያጓጉቷል። በተለይ ኤሌክትሮኒክስ ነገሮች እጅግ ከሚስቡትና ከሚፈታታቸው መካከል ይጠቀሳሉ። ይሁን እንጂ ውስጡን ካየ በኋላ በትኩረት ስለሚፈታታቸው ምንም አይነት ስህተት ሳይፈጽም ወደነበሩበት ይመልሳቸዋል። ይህ ስሜቱ ደግሞ ሳይንቲስት እንዲሆን ያስመኘዋል። በተጨማሪም ሜካኒካል ሳይንቲስት መሆን እጅግ የሚማርከው ነገር ነው።
ተማሪ ናትናኤል በመልካም ርምጃችን አጸደ ሕጻናትና የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ሲማር ፍላጎቱን መሰረት ያደረጉ በርካታ ነገሮችን ሠርቷል። እነዚህ ሥራዎቹ ደግሞ የተለያዩ ብቻ ሳይሆኑ ትምህርት ቤቱን ያስጠሩም ናቸው። ናትናኤል እንደሚለው፤ ጊዜው ቅርጻቅርጽ መሥራት ላይ ጥሩ አቅም እንደነበረው ያየበት ነው። ምክንያቱም በወረቀት ጭቃ አቡክቶ በጣም ትልቅ አዞ ሠርቷል። በተጨማሪም ለልጆች መማሪያ የሚሆኑ ከእንጨት የተሰሩ ቅርጻቅርጾችንም ሰርቶ አበርክቷል።
‹‹አሁን ላይ ያላጠጣነው አበባ አያድግም። ከአሁኑ ስንንከባከበው ነው ጥላ የሚሆነን›› የሚለው ተማሪ ናትናኤል፤ ትምህርታችንንም ሆነ ሌሎችን ማገዙ በጊዜው መሆን እንዳለበት ያስረዳል። እርሱም ይህንኑ ነው የሚያደርገው። ጊዜውን በምንም መልኩ ከትምህርት ውጪ ማሳለፍ አይፈልግም። ስኬቱ ላይ የሚያደርሰውን ተግባርም ከመሞከር ወደኋላ አይልም። ሁልጊዜ መሞከር ከምንም በላይ ያስደስተዋል።
በመሞከር ውስጥ አብዝቶ መውደቅ እንዳለም ያውቃልና ወደቅሁ ብሎ ተስፋ አይቆርጥም። ደጋግሞ ይሞክራል። በዚህም ብዙ አዲስ ናቸው የሚባሉ የፈጠራ ሥራዎችን ከውኗል። ከጓደኞቹ ጋር አሁንም የተለያዩ ተግባራትን እየከወነ ይገኛል። አንዱና ዋነኛው ቬንትሬተር ሲሆን፤ በተሻለ መልኩ ለመሥራት እየጣረ እንደሆነም አጫውቶናል።
ልጆች ናትናኤልና ጓደኞቹ ሙቀት በሚያስቸግርበት ወቅት ከውጪ ከምናመጣ በአገር ውስጥ አምርቶ መጠቀም ይቻላል በሚል ተግባሩን እየከወነ የሚገኙ ሲሆን፤ እጅግ የሚደንቅ ጥበብን ለመጠቀም አቅዷል። የመጀመሪያው ገመድ አልባ እንዲሆንና በብሉቱዝ እንዲሠራ ማድረግ ነው። እንደሚሳካላቸውም ያምናል።
ናትናኤል ከተማሪዎች ጋር አብሮ መሥራት የሚያስደስተው ልጅ ሲሆን፤ ይህ ደግሞ የትምህርት አቀባበሉ በጣም ፈጣን እንዲሆንለት አስችሎታል። ሁልጊዜ ከጥናት በኋላ አዳዲስ ነገሮችን እንዲያይም ረድቶታል። በተለይ የጀመራቸው ሥራዎች ካሉ እነሱን ለማጠናቀቅ የማይቆፍረው ድንጋይ አይኖርም። ዩቲውብና መሰል ማህበራዊ ድረገጾችን በርብሮ መረጃ እንዲያገኝ ያግዘዋልም።
ሌላው የናትናኤል ልዩ ባህሪ ትምህርቱን የሚያጠናው ብዙ ጊዜ ከትምህርት ቤት ከገባ በኋላ መሆኑ ነው። ምክንያቱም ቤተሰብ ቤት ውስጥ ካለ ሀሳቡን ሰብስቦ ማንበብ አይችልም። ስለሆነም እነርሱ ሳይመጡ መጀመሪያ የቤት ሥራውን ያስቀድምና ከዚያ ወደ ጥናቱ ይገባል። ዛሬ የተማረውን ዛሬውኑ ለማጥናትም ይሞክራል። ስለዚህም ለነገ የሚለው ነገር የለውም።
ትምህርትን አብዝቶ የሚወድና ብዙ ጊዜውን ለጥናት የሚሰጥ ቢሆንም ከትምህርት ጊዜና ከጥናት ውጪ ደግሞ የተለያዩ ነገሮችን መሥራት ያስደስተዋል። አያቱን ማገዝ፤ እግር ኳስ መጫወትም ይወዳል። ከሁሉም በላይ ግን የፈጠራ ሥራዎቹን የተሻለ ለማድረግ የሚያስፈልገውን ተግባር መከወን ይማርከዋል። እናም ጊዜው የሚያልፈው ይህንን በማድረግ እንደሆነም ነግሮናል። ልጆች እናንተም በትምህርታችሁ ውጤታማ እንድትሆኑ ጊዜያችሁን በአግባቡ መጠቀም አለባችሁ። በተለይም ልዩ ትኩረታችሁ መሆን ያለበት ትምህርትና ትምህርታችሁ ብቻ መሆን ይገበዋል። ጊዜው ደግሞ ሰኔ በመሆኑ ለፈተና ልዩ ዝግጅት ማድረግ ይኖርባችኋል በርትታችሁ አጥኑ። ለዛሬ ይዘንላችሁ የቀረብነው ልጅ ደግሞ ይህንን በሚገባ ያሳየ በመሆኑ ከእርሱ ተማሩ። በሚቀጥለው አምድ እስከምንገናኝ መልካም ሰንበት ይሁንላችሁ!!
ጽጌረዳ ጫንያለው
አዲስ ዘመን ሰኔ 5 ቀን 2014 ዓ.ም