አዲስ አበባ፡- ወደ ትግራይ ክልል የሚላኩ ሰብአዊ ዕርዳታዎች ለማሳለጥ መንግሥት እያደረገ ከሚገኘው ሁሉን አቀፍ ጥረት በተጓዳኝ አሸባሪው ሕወሓት ለጥፋት ዓላማው ሊጠቀምባቸው የሚችሉ ቁሳቁሶች እንዳይተላለፉ በትኩረት እንዲሠራ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን አሳሰቡ፡፡
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ወደ ትግራይ ክልል የሚሄደውን የሰብአዊ ድጋፍ ለማቀላጠፍ የሚደረገውን ጥረት በአፋር ክልል ሰርዶ ኬላ ተገኝተው ተመልክተዋል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን መንግሥት ወደ ትግራይ ክልል የሚላኩ ሰብአዊ ዕርዳታዎች ለማሳለጥ እያደረገ ከሚገኘው ሁሉን አቀፍ ጥረት በተጓዳኝ አሸባሪው ሕወሓት ለጥፋት ዓላማው ሊጠቀምባቸው የሚችሉ ቁሳቁሶች እንዳይተላለፉ በትኩረት እንዲሠራ አሳስበዋል። ባለድርሻዎችም ትኩረት እንዲሰጡም አስገንዝበዋል።
መንግሥት በተለያዩ ክልሎች በሰው ሠራሽ እና የተፈጥሮ አደጋዎች ምክንያት ለተጎዱ ወገኖች ሰብአዊ ድጋፍ ለማድረግ ከተለያዩ ባለድርሻዎች ጋር በመሆን በትኩረት እየሠራ መሆኑን አመልክተው፤ ከዚህም ውስጥ የትግራይ ክልል ነዋሪዎች አንዱ መሆኑን ገልጸው ለተጎጂዎች ያልተገደበ ሰብአዊ ዕርዳታ አቅርቦትን የበለጠ ለማሳለጥ ከዓለም ምግብ ፕሮግራም እና ከሌሎች አጋሮች ጋር በቅንጅት እየተሠራ ነው።
የሰብአዊ ዕርዳታው በቀን እስከ 200 ኮንቮይ ተሽከካሪ በሰርዶ ኬላ ተገቢው የፍተሻ እና ተያያዥ ቁጥጥር ከተደረገበት በኋላ እንደሚላክ በጉብኝታቸው መረዳታቸውን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አቶ ደመቀ መኮንን ገልጸዋል።
ይሁንና በተደረገው ፍተሻም ለሽብር ቡድኑ የጥፋት ዓላማ ማስፈጸሚያ ሊውሉ የሚችሉ፣ ከተፈቀደው የነዳጅ መጠን በላይ ተጨማሪ ነዳጅ እና አንዳንድ ያልተፈቀዱ ቁሳቁሶች ለማሳለፍ ሙከራዎች እንዳሉ መገንዘባቸውን ገልጸዋል።
እንደዚህ ዓይነት ተግባራት ከሰብአዊ አቅርቦት ሕጉ የሚጣረስ በመሆኑ ከሚመለከታቸው አካሎች ሰብአዊ አቅራቢ ድርጅቶች ጋር መንግሥት እንደሚነጋገርበት አስረድተዋል።
በአጠቃላይ መንግሥት ሰብአዊ ዕርዳታውን ለማሳለጥ ከሚያደርገው ሁሉን አቀፍ ጥረቶች ጎን ለጎን ጉምሩክ ኮሚሽን እና ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት ያልተፈቀዱ ቁሳቁሶች ላይ ተገቢውን የቁጥጥር እና ክትትል ሥራቸውን ሊያጠናክሩ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
የአፋር ሕዝብ በሽብር ቡድኑ ወረራ ምክንያት ከቀዬአቸው የተሰደዱ ከአንድ ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ተፈናቃዮችን ይዞ ሳለ መንግሥት ለትግራይ ሕዝብ ሰብአዊ ዕርዳታ ለማቅረብ እያደረገ ለሚገኘው ጥረት ተፈጻሚነት ያሳየው ቀናነት እና ትብብር የሚደነቅ ነው ብለዋል አቶ ደመቀ።
ለዚህም በየደረጃው የሚገኙ አመራሮች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶች እና ሌሎች ማሕበረሰብ መሪዎች እንዲሁም የክልሉ ነዋሪ ሊመሰገን ይገባል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል። በጉብኝቱ የክልሉ ርዕሰ-መስተዳድር አቶ አወል አርባ እንዲሁም ሌሎች የፌዴራልና የክልል ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።
አዲስ ዘመን ግንቦት 28/2014