ልጆች! ሰላም ናችሁ፤ ትምህርቱስ እንዴት ነው? በጣም ጥሩ። ጎበዝ ተማሪዎች ለመሆን ከክፍል ተማሪዎች የመጀመሪያውን ደረጃ ለማግኘት የየዕለቱን ትምህርት በዕለቱ እያጠናችሁ አይደል! አዎ ብላችሁ ምላሽ እንደምትሰጡ አምናለሁ። በጣም ጎበዞች። ልጆች የየዕለቱን ትምህርት በየዕለቱ በአግባቡ ማንበብ ስኬታማ ያደርጋል። ነገር ግን የየዕለት ጥናታችሁን ሳታጠኑ ጊዜያችሁን በጨዋታ ብቻ የምታሳልፉ ከሆነ ጎበዝም ሆነ ህልም ያለው ተማሪ መሆን አንችልም። እናም የምትፈልጉት ነገር ለመሆን ካሰባችሁ መጀመሪያ አንባቢና ለትምህርታችሁ ልዩ ትኩረት የምትሰጡ ልጆች መሆን አለባችሁ።
ሁሉም ሰው ከልጅነቱ ጀምሮ መሆን የሚያስበውን ምኞቱን ለማሳካት ትኩረት ሰጥቶ ነው የሚሠራው። እናንተም መሆን ለምትፈልጉት ነገር ዛሬ ላይ መትጋትና መልፋት ይጠበቅባችኋል። መነሻውን ሳያሳምር የቀረ ተማሪ መድረሻው አያምርም። ስለሆነም ዛሬ ላይ መሆን የምትፈልጉትን ለማሳካት ጥሩ ተማሪ ልትሆኑ ይገባል። ያ ደግሞ የሚመጣው የተማሩትን በየቀኑ ለነገ ሳይሉ ማንበብ ሲቻል ነው። በተጨማሪም ከትምህርት ገበታ ላይ ባለመቅረት፤ የተሰጠን የቤት ሥራ በአግባቡ መሥራት እንዲሁም በክፍል ውስጥ መከታተል ከምንም በላይ ያስፈልጋል። የዚህን ጊዜ ልዩ ችሎታችሁን እንድትረዱም ጭምር ትሆናላችሁ።
ይህንን የሚያደርግና ብዙ የፈጠራ ሥራዎችን እያከናወነ ለህልሙ መሳካት የሚተጋን ልጅ ታሪክ ለዛሬ ልንነግራችሁ ወደናል። ልጁ በዳግማዊ ምኒልክ አጸደ ሕፃናትና የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርትቤት የሰባተኛ ክፍል ተማሪ ነው። ሀብታሙ መሰለ ይባላል። ልዩ ችሎታውን ሲፈልግ ከሁሉም በላይ ከኤሌክትሮኒክስ ሥራ ጋር በተገናኘ የሚከውነው ተግባር እጅጉን ያስደስተዋል። እናም ይህንን ችሎታውን ለማዳበር ሰፈራቸው ላይ የኤሌክትሮኒክስ መሸጪያና መገጣጠሚያ ስለነበር እዚያ በመሄድ የተለያዩ ልምምዶችን ያገኝ ነበር። ይህ ልምዱ ደግሞ የአገኘውን ሁሉ እንዲፈታታና ዳግም ወደነበረበት እንዲመልስ አስችሎታል። ከቤት አልፎም ጎረቤትን ጭምር የሚያግዝበት ዕድልንም ሰጥቶታል።
ሀብታሙ ዛሬ ላይ የሰባተኛ ክፍል ተማሪ ቢሆንም ይህንን ችሎታውን ያወቀው ግን ገና በትንሽነት ዕድሜው ነው። ይህ ደግሞ በየቀኑ ችሎታው እየጎላ እንዲመጣ አግዞታል። በተለይም ከኤሌክትሪክ ጋር በተገናኘ የማይፈታው ችግር እንዳይኖር አድርጎታል።
ሀብታሙ ሙከራውን ማንም ቢመታውና ቢቆጣውም አያቆምም። ምክንያቱም በመሞከር ውስጥ አዲስ ነገር እንደሚገኝ ያምናል። እንዲያውም ከዚህ ጋር ተያይዞ አንድ ገጠመኝ አለው። ይህም ቤታቸው ውስጥ የተቀመጠ አንድ ቴፕ አንስቶ ፈታታው። መልሶም ገጣጥሞ አስቀመጠው። ነገር ግን ቤተሰብ አውቆበት ስለነበር ቁጣና ግርፋት ደረሰበት። ይሁን እንጂ ነገሩን አሳምኖ የተሻለ ነገር እንዲመቻችለት አድርጓል። አሁንም ላይ ሊሠራ ያሰበውን ነገር ቀድሞ ያስረዳቸውና የፈለገውን ነገር ያሟሉለታል። በዚህም የቀጣይ ህልሙን ለማሳካት ይጣጣራል።
ሀብታሙ መሆን የሚፈልገው የፊዚክስ ሊቅ ሲሆን፤ ይህንን የመረጠበት ምክንያት ዓለም የሚያስፈልጋት ነገር በብዙ መልኩ እርሱን የያዘ መሆኑን ስለሚያምን ነው። ፊዚክስና ኬሚስትሪ ስለማይነጣጠሉ በትምህርቱም ሁለቱን አጥብቆ ይወዳቸዋል። ከፍተኛ ውጤት የሚያስመዘግብባቸውም እነርሱ እንደሆኑ ነግሮናል። ከአንደኛ ክፍል ጀምሮ በነበረው የትምህርትቤት ቆይታም የደረጃ ተማሪና በዚህ ሁኔታ ትምህርቱን የቀጠለ ልጅ እንደነበር አጫውቶናል።
ከአንደኛ እስከ ስድስተኛ ክፍል ትምህርቱን ሲከታተል የተለያየ ነገር ለትምህርትቤቱ እንዳበረከተ ነግሮናል። በተለይም በአካባቢው ያየውን ችግር ለመፍታት በሚደርጋቸው ሥራዎች ደስተኛ እንደሆነም ነው ያነሳልን። በተለይም እንደአገር ያስፈልጋል ብሎ ያሰበው ተግባር ላይ መሥራት ከምንም በላይ ያረካዋል። እናም ድሮን መሥራት ህልሙ ነው መጠነኛ ድሮን ሠርቶም የተለያየ ተግባር እንደምትከውን አጫውቶናል። ለዚህ ሀሳብ መነሻው የጥምቀት ክብረበዓል ሲሆን፤ ጋዜጠኞች ለቪዲዮ ቀረጻ ሲጠቀሙበት በተደጋጋሚ ያያል። ይህ ነገር ደግሞ ለኬሚካል ርጭት ቢውል የብዙዎችን ችግር ይፈታል ብሎ አሰበ። የተለያዩ መረጃዎችን ከድረገጾች ላይ በማየት ሙከራውንም ጊዜ ሳይሰጥ ጀመረ።
ጅማሮው ብዙም የሚያስደስተው አልነበረም። ነገር ግን ተስፋ መቁረጥ መለያው አይደለምና ደጋግሞ በመሞከር ከፍ ብላ እንድትበር አደረጋት። ካሜራ በማሲያዝ ቪዲዮ የምትቀርጽና ኬሚካል የምትረጭ ድሮንም ሆነችለት። በዚህ ደስተኛ ነው። ግን ብዙ መሻሻሎች ይቀሯታልና አሁንም እንደሚሠራባት ነግሮናል። ለዚህ ደግሞ መምህራን ልዩ እገዛ እያደረጉለት እንደሚገኙም አውግቶናል።
ሀብታሙ ከዚህ በተጨማሪ ሌላም የፈጠራ ሥራ ሠርቷል። ይህም የላብራቶሪ ዕቃዎችን ሊተኩ የሚችሉ ማቴሪያሎችን በመሥራት አገልግሎቱ እንዳይቋረጥ ያስቻለበት ነው። ወደፊት ደግሞ ብዙዎች የሚደነቁበትን ተግባር እንደሚከውንና የፈጠራ ክህሎቱን ከዕለት ዕለት እያሻሻለው ያሰበው ላይ እንደሚደርስ እምነት አለው። ልጆችም በፈጠራ ክህሎታቸው ብዙ መሥራት የሚችሉ በመሆናቸው እኔ ያደረኩትን ቢያደርጉ ደስ ይለኛል ብሎናል።
መጀመሪያ ፍላጎታቸውን መለየት ላይ መትጋት አለባቸው፤ ከአገኙት በኋላ ደግሞ ተስፋ ሳቆርጡ ደጋግሞ መሞከርን ልምዳቸው ሊያደርጉ ይገባል። በመጨረሻ ስኬቴ ይህ ነው ብለው ማቆም የለባቸውም። ሁሌ ለአዲስ ነገር ዝግጁ መሆን እንደሚጠበቅባቸው ይመክራል። ለዚህ ሁሉ ግን ትምህርት ወሳኝ መሆኑን አበክሮ ያስረዳል። ልዩ ትኩረት ሊሰጡት የሚገባው ጉዳይ ትምህርታቸው ነውና በአግባቡ መከታተል አለባቸውም ይላል። እኛም ምክሩ እጅግ የሚጠቅም ነውና ተግብሩት እያልን በቀጣይ በሌላ ዝግጅት እንዲሁም በሌላ ባለታሪክ እስክንገናኝ ቸር ሰንብቱ። መልካም ዕለተ ሰንበተ እንዲሆንላችሁ ተመኘን።
ጽጌረዳ ጫንያለው