በግለሰብ ወይም በሌላ ሕጋዊ አካል እንደ ኮርፖሬሽን ባሉ ንብረቶች ላይ የሚፈጸም ክፍያ ፕሮፐርቲ ታክስ(ግብር) ይባላል፡፡እንዲህ የግል ንብረትን ወይንም ባለቤትነትን የሚመለከተው የክፍያ ሥርዓት በአብዛኛው የግል ቤት አልሚዎች (ሪል እስቴት) ይመለከታል፡፡ የግብር ግምቱም ንብረቱ በሚገኝበት እና የንብረቱ ባለቤት ክፍያ በሚፈጽምበት የአካባቢ አስተዳደር እንደሚሰላ ካሰባሰብነው መረጃ ለመገንዘብ ችለናል፡፡ የፕሮፐርቲ ታክስ በንብረቱ ዋጋ ላይ የተመሠረተ ሲሆን፣ይህም ሪል እስቴት ወይም – በብዙ ፈርጆች – እንዲሁም በተጨባጭ የግል ንብረት ላይ የሚተመን ሊሆን ይችላል። ይህን የፕሮፐርቲ ግብር የንብረት ታክስ ተመኖች እና የታክስ ንብረት ዓይነቶች እንደ ስልጣን ይለያያሉ ይላል ያገኘነው መረጃ።
በግል ንብረት ላይ መሠረት ያደረግነውን የፕሮፐርቲ ታክስ ወይንም የግብር ክፍያ ሥርዓት ለማውሳት የወደድነው ሰሞኑን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባካሄደው የዘጠኝ ወር የእቅድ አፈፃፀም ግምገማ ላይ የተገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ የሥራ መመሪያ በሰጡበት ወቅት ያነሱት ጉዳይ በመሆኑ ነው።ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ እንዳሉት፤ ከአንድ ሚሊዮንና ከሁለት ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ የሚያስገኝ ሕንፃ ገንብቶ የሚጠቀም ሰው የፕሮፐርቲ ታክስ መክፈል አለበት።እንዲህ ያለው የክፍያ ሥርዓት በየትኛውም ዓለም የተለመደ ነው። ቦታው በዘመድ አዝማድና በጉቦ ስለተገኘ ብቻ በነፃ መጠቀም የሚባል ነገር መኖር የለበትም። ቤቱ የግሉ ነው፡፡ግን ግብር መክፈል አለበት፡፡አነስተኛ ገቢ ያለው እንዳይጎዳ ዝቅተኛ የኪራይ ክፍያ ያላቸው ቤቶች በከፍተኛው ውስጥ አይካተቱም። እነርሱን መተው ነው፡፡የሚጣልባቸው ግብርም በጥናት ተለይቶ ግምት መውጣት አለበት፡፡ የቤት ኪራይ ዋጋ የሚወሰነው መሬት የወል ሀብት በመሆኑ ነው፡፡በዚህ መሠረት ዋና ዋና የሚባሉ ሕንፃዎችና ቪላቤቶች ግብር መክፈል አለባቸው፡፡ በአጠቃላይ ቤት ኪራይ ጭማሪ ላይ ቁጥጥር መደረግ እና በተለይም ፕሮፐርቲ ታክስ ክፍያ ላይ ደሀውን ታሳቢ ያደረገ አሠራር መዘርጋት እንዳለበት ጠቅላይ ሚኒስትሩ አሳስበዋል።
መረጃዎች እንደሚጠቁሙት የፕሮፐርቲ ታክስ በአብዛኛዎቹ የኢኮኖሚ ትብብር እና ልማት ድርጅት (OECD) አገሮች የማይንቀሳቀስ ንብረት ታክስ፣ ከገቢ ታክሶች እና ከተጨማሪ እሴት ጋር ሲወዳደር ዝቅተኛ የፌደራል ገቢን ይወክላል። ይሁን እንጂ በዩናይትድ ስቴትስ ያለው የፕሮፐርቲ ታክስ መጠን ከብዙ የአውሮፓ ሃገሮች በእጅጉ የላቀ ነው።
ባለንብረቶቹ በፕሮፐርቲ ታክስ ውስጥ የሚከፍሉት መጠን የሚወሰነው በሊዝ ስር ባሉ መሬቶች የወቅቱ የገበያ ዋጋ የንብረት ግብር መጠን በማባዛት ነው። አብዛኛዎቹ የግብር ባለስልጣናት የግብር ተመኑን በየዓመቱ ያሰላሉ ። ከሞላ ጎደል ሁሉም የንብረት ታክሶች የሚጣሉት በሪል እስቴት ላይ ነው። ይህ በሕጋዊ መንገድ በመንግሥት መዋቅር የተከፋፈለው የማይንቀሳቀስ ንብረት መሬቱን፤ መዋቅሮችን ወይም ሌሎች ቋሚ ሕንፃዎችን ያጠቃልላል።
በመጨረሻም የንብረት ባለቤቶች በማዘጋጃ ቤት በተደነገገው ዋጋ ተገዢ ናቸው። አንድ ማዘጋጃ ቤት የአካባቢውን ንብረት የሚገመግም የግብር ገምጋሚ ይቀጥራል። በአንዳንድ አካባቢዎች፣ የግብር ገምጋሚው የተመረጠ ባለሥልጣን ሊሆን ይችላል። ገምጋሚው አሁን ባለው ፍትሐዊ የገበያ ዋጋ መሠረት የንብረት ግብር ለባለቤቶች ይመድባል። ይህ ዋጋ ለቤት የተገመገመ ዋጋ ይሆናል። የንብረት ግብር ክፍያ የጊዜ ሰሌዳ እንደየአካባቢው ይለያያል። በሁሉም የአካባቢ ንብረት የግብር ኮዶች ውስጥ፣ ባለቤቱ የግብር ተመኑን ከገምጋሚው ጋር ለመወያየት ወይም ታሪፉን በመደበኛነት የሚወዳደርባቸው ዘዴዎች አሉ። የንብረት ታክስ ሳይከፈል ሲቀር የግብር ባለስልጣኑ በንብረቱ ላይ መያዣ ሊሰጥ ይችላል። ገዢዎች ማንኛውንም ንብረት ከመግዛትዎ በፊት ሁል ጊዜ የቆዩ እዳዎች መኖር አለመኖራቸውንም ይመለከታል።
የሌሎች ሃገሮች ተሞክሮን ከላይ እንደተመለከትነው ሲሆን ይህ ፕሮፐርቲ ታክስ በሃገራችን በምን መልኩ ይፈፀማል? በኛ ሃገር የግብር ሥርዓት ውስጥ ፕሮፐርቲ ታክስ መጀመሩስ ምን ፋይዳ ይኖረዋል ስንል የምጣኔ ሀብት ባለሙያ የሆኑትን ዶክተር ቆስጠንጢኖስ በርኸተስፋን ጠይቀናቸው እንዳስረዱት፤ አንድ ሕንፃ በሚሠራበት ጊዜ ወይም ምንም አይነት ቁሳቁስ መሬት ላይ በሚያርፍበት ጊዜ መንግሥት የተለያዩ ክፍያዎች ያስከፍላል። ክፍያዎቹም የመሬት ታክስ፤ የዓመት ግብር፤ ሕንፃው የሚከራይ ከሆነ ደግሞ የኪራይ ታክስም ይከፈላል። ተሠርተው በጥቅም ላይ ያልዋሉት ሕንፃዎችን ደግሞ ሥራ ላይ ለማዋል ከሚያበረክቱት መካከልም የፕሮፐርቲ ታክስ አንዱ ነው።በኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት መሠረት መሬት በሙሉ የሕዝብ ሀብት ነው።የሚያስተዳድረውም መንግሥት ነው፡፡ስለዚህ ሕንፃ ያረፈበት መሬት ሁሉ የግል ይዞታ ስላልሆነ የፕሮፐርቲ ክፍያ መፈጸም ግድ ነው፡፡
በአሁኑ ጊዜ አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ በርካታ ሕንፃዎች በመገንባት ላይ ናቸው። ከተገነቡት ውስጥ አንዳንዶቹ ባዷቸውን ያለጥቅም ቆመዋል፡፡ ሌሎቹ ላይ የሚስተዋለው ደግሞ በከፊል ተከራይተው በከፊል ክፍት የሆኑ ናቸው፡፡ ይህም የሆነበት ምክንያት ሕንፃዎቹ ሲሠሩ ለቢሮና ለንግድ ብቻ ታስበው መሠራታቸው በዋና ዋና መንገዶች አካባቢ የሚገኙ ካልሆኑ በስተቀር የሚከራያቸው እንዲያጡ መሆኑን ተናግረዋል። ከዚህም ባሻገር የመኪና ማቆሚያ የሌላቸው ሕንፃዎችም ተከራይ ከሚያጡት መካከል መሆናቸውንም ያስረዳሉ።
በሃገሪቱ ለሕንፃ ግንባታ የሚውል ግብአት የሚያመርት ፋብሪካ አለመኖሩ ሕንፃዎች ሲሠሩ በውድ ዋጋ እንዲሠሩ አድርጓቸዋል። ብዙ የአፍሪካ ሃገሮች በቅኝ ግዛት ጊዜ የጀመሩት ብሎም ያጠናከሩት የሕንፃ ግብአቶችን የሚያመርቱ ፋብሪካዎች አሏቸው። ሃገራችን ውስጥ ግን በጣም ውስን የሆኑ የሕንፃ መሣሪያ ግብዓቶች አምራች ድርጅቶች መኖራቸውን ጠቅሰዋል። የሕንፃ አከራዮቹም ሊያከራዩት የሚፈለጉት ኪራይ መጠን ሕንፃውን ለመሥራት ያወጧቸውን ወጪዎች ለመሸፈን የሚያስችል በመሆኑ የኪራይ ዋጋው እጅግ ውድ ይሆናል። የቤት ኪራይ ውድ ሲሆን ግን ተከራዮች የሚከራዩትን የክፍል ብዛት ይቀንሳሉ። ባለ ሕንፃዎችም እዳቸውን ካልከፈሉ ባንኮቹ ቤታቸውን የሚወስዱበት ሁኔታም ይኖራል።
ይህ መሆኑም አዲስ አበባ ከተማን ከአፍሪካ በጣም ውድ የተባለች ከተማ እንድትባል አድርጓታል ። ከተማዋን ደግሞ ውድ ካደረጓት ነገሮች መካከል የቤት ኪራይ ከተማዋ ውስጥ ያለው የመኖሪያ ቤት ችግር ሆኖ ሳለ በርካታ ሱቆችንና ቢሮዎችን ሰርቶ ማስቀመጥ አዋጭነት እንደሌለው ተረድተው የከተማ መስተዳደሩ ለሕንፃ ፈቃድ ሲሰጥ ለመኖሪያ ቤት አፓርትመንቶች እንዲሠሩ ማድረግ ይኖርባቸዋል ብለዋል።
ቀደም ባለው ሥርዓት የወሰዳችሁትን መሬት ካልሠራችሁበት ይነጠቃል የሚል አሠራር የነበረ መሆኑን ያስረዱት ዶክተር ቆስጠንጢኖስ ፤መሬታቸውን ከማጣት “ተበድሬ ፎቅ ልሥራ” ያሉ በርካታ የባንክ ዕዳ ያለባቸው ሕንፃዎች መኖራቸውን ይናገራሉ ። ለዚህም በከፍተኛ የውጪ ምንዛሪ የሕንፃ ግብዓት ከውጭ በማስመጣት ሕንፃዎችን ማስገንባት በማስቀረት ሃገሪቱ ያለባትን የውጭ ምንዛሪ እጥረት ፋታ መስጠት ያስፈልጋል ብለዋል።በተጨማሪ ባንኮቹ ራሳቸው ረዣዥም ህንፃዎችን በመሥራት ሃገሪቱ ያለችበትን የውጭ ምንዛሪ እጥረት ጭንቀት ውስጥ እየከተቱ መሆኑን ይናገራሉ። ይህም ሃገሪቱ በአስቸኳይ የምትፈልጋቸውን ነገሮች የኢንዱስትሪ ልማት፤ የግብርና ልማቶች ፤ ከውጭ የሚመጡ ምርቶችን ለመተካት መንቀሳቀስ የሚገባበት ጊዜ ላይ መሆናችንንም አመላክተዋል።
ወደመነሻችን ስንመለስ የፕሮፐርቲ ታክስ ክፈሉ በሚባልበት ወቅት ባለ ሕንፃዎችን የውዴታ ግዴታ ውስጥ ለማስገባት ሊደረግ የታሰበ ይመስለኛል ያሉት ዶክተር ቆስጠንጢኖስ በዚህ ሁሉ ችግር ውስጥ የተገነቡ ሕንፃዎች ለሃገር ጠቃሚ እንዲሆኑ ፍላጎትን ባማከለ መልኩ እንዲሠሩ ለማድረግ ብሎም ባዶአቸውን ሲቀመጡ ያለአግባብ ከሚወጣ የጥገና ወጪ ለመዳን ሕንፃዎች አገልግሎት እየሰጡ ለመንግሥትም የሚጠበቅባቸውን መክፈል ይኖርባቸዋል ሲሉ ሀሳባቸውን ሰጥተዋል።
ለዓመታት በአሜሪካን ኒዎርክ እንደቆዩ የሚናገሩት ዶከተር ቆስጠንጢኖስ በውጭ ሃገራት ሕንፃ በዘፈቀደ የማይሠራ እንዲሁም ጥቅም ላይ ውለው ለመንግሥት ተገቢውን ታክስ የሚከፍሉ መሆናቸውንም ተናግረዋል። የፕሮፐርቲ ታክስ ክፍያዎችም በሃገራችን እንደአዲስ የመጣ ጉዳይ ሳይሆን በሌሎች ሃገራት የሚሠራበት መሆኑን በተለያዩ ሃገራት ከነበራቸው ቆይታ በመነሳት አስረድተዋል።
የፕሮፐርቲ ታክስ ክፍያ ይከፈል ሲባል ግን በአዋጅ ወጥቶ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መጽደቅ አለበት ፡፡ ይህ የሚሆነው ከዚህ ቀደም ሕግ ከሌለ ነው፡፡ሕግ ሲወጣም ከሕንፃ ባለቤቶች ፤ ከነጋዴዎች ፤ ከባለንብረቶች እንዲሁም በመንግሥት ደረጃ ያሉ የፖሊስ ጥናት ከሚያደረጉት ጋር በመወያየት ሊሆን ይገባል፡፡ ባለንብረቶች ሕንፃዎችን ለማከራየት በሚችሉበት ሁኔታ በማስተካከል ገቢ እንዲያስገኝ ማድረግ የሚገባቸው መሆኑን አሳስበዋል።
ሕንፃዎች ባዷቸውን እንዳይሆኑ፤ ገቢ አስገኝተው መከራየት እንዲችሉ የሕንፃ ባለቤቶች የኪራይ መጠን መቀነስ ይኖርባቸዋል የሚሉት ዶክተር ቆስጠንጢኖስ ሕንፃ ባዶ ሆኖ በመፈራረስ ላልተገባ ወጪ ከሚዳርግ፤ ባለሀብቱም ሳይጎዳ፤ የማኅበረሰቡን አቅም ባማከለ መልኩ ኪራይ ቅናሽ ሊደረግ ይገባል ይላሉ።
በአጠቃላይ ታክስ መከፈሉ ልማትን ለማስቀጠል መሆኑን በመረዳት አገልግሎት የማይሰጡትን አገልግሎት ላይ በማዋል፤ አገልግሎት ላይ ያሉትንም በእንክብካቤ በመጠበቅ የሃገር ሀብት የፈሰሰባቸውን ሕንፃዎች ለሃገርም ገቢ ማስገኛ ሌላ አማራጭ ሊሆን የሚገባ መሆኑንም ጠቁመዋል። ኢትዮጵያ ከሌሎች ሃገር አንፃር ሲታይ የታክስ ሥርዓቷ ደካማ በመሆኑ በጣም አነስተኛ ገንዘብ ከታክስ የምታገኝ መሆኑን ያነሳሉ። ሁሉም ዜጋ በሃገሪቱ ሀብት እኩል ተጠቃሚ መሆን እንዲችል ባለንብረቱ ተገቢውን የአገልግሎት ክፍያ መክፈል እንዳለበት በነበረን ቆይታ አንስተዋል።
አሥመረት ብሥራት
አዲስ ዘመን ግንቦት 4 ቀን 2014 ዓ.ም