በእግር ኳስ የየትኛውም ኮከብ ሕልምና የመጨረሻ ስኬት የዓለም ዋንጫን ከመሳም የበለጠ ሊሆን አይችልም። ይህ ታላቅ ዋንጫ ትልቅ ከበሬታ ከሚሰጣቸው የስፖርት ሽልማቶች መካከል አንዱ ስለመሆኑም በርካቶች ይስማማሉ። ይህን ታላቅ ዋንጫ ለማየት ወይም ለመሳም የሚታደሉት ግን እጅግ ጥቂቶች ናቸው።
በመሆኑም ይህን ዋንጫ የማየትም ይሁን የመንካት እድል የሌላቸው የዓለማችን እግር ኳስ አፍቃሪዎችን ታሳቢ በማድረግ የዓለም ዋንጫ ውድድር በየአራት ዓመቱ በተለያዩ የዓለም ሃገራት ከመካሄዱ አስቀድሞ ዋንጫው በተለያዩ ሃገራት በመዘዋወር የስፖርት ቤተሰቡ ፎቶ አብሮት እንዲነሳ ይደረጋል።
በዚህ ዓመትም የዓለም ዋንጫ በኳታር የሚካሄድ መሆኑን ተከትሎ ዋንጫው በተመረጡ አገራት እየተዟዟረ በስፖርት ቤተሰቦች እየተጎበኘ ይገኛል። ይህን ታላቅ ዋንጫ ለማንሳት ባልታደለችው አፍሪካም በመጪው ግንቦት ወር አጋማሽ ይመጣል። ኢትዮጵያም ዋንጫው መዳረሻውን ከሚያደርግባቸው የአፍሪካ አገራት አንዷ እንደምትሆን ታውቋል።
የዓለም ዋንጫው በአፍሪካ ዘጠኝ ሃገራት ሲዘዋወር መዳረሻውን በኳታሩ ዓለም ዋንጫ ተሳታፊ በሆኑ አምስት ሃገራት ያደርጋል። ሴኔጋል፣ ሞሮኮ፣ ጋና፣ ካሜሮን እና ቱኒዚያ የዓለም ዋንጫው ተሳታፊ እንደመሆናቸው እድሉን ከሚያገኙት መካከል ናቸው። ኢትዮጵያን ጨምሮ አራቱ ሃገራት ደግሞ በውድድሩ ተካፋይ የማይሆኑ የተመረጡ የዋንጫው መዳረሻ ሃገራት ናቸው።
የዓለም ዋንጫው ወደ ኢትዮጵያ ሲመጣ ይህ ለሶስተኛ ጊዜ ሲሆን፤ በመጪው ግንቦት 16 እና 17/2014 ዓ.ም የሁለት ቀናት ቆይታ ይኖረዋል። በዚህ መርሐ ግብር ላይም የእግር ኳስ ቤተሰቡ ከዋንጫው ጋር ፎቶ የመነሳት ዕድል የሚያገኝ ይሆናል፡፡
ከዋንጫው ጋርም ውድድሩን በማሸነፍ ስኬታማ መሆን የቻለ አንድ የእግር ኳስ ተጫዋች ወደ ኢትዮጵያ እንደሚመጣ ባህልና ስፖርት ሚኒስትር ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ጋር ትናንት በሰጡት መግለጫ ጠቁመዋል። እኤአ በ1998 የዓለም ዋንጫ አሸናፊ የሆነው የፈረንሳይ ብሔራዊ ቡድን አባል የነበረው ተጫዋች ዴቪድ ትሬዜጌት ከዋንጫው ጋር በኢትዮጵያ የሁለት ቀናት ቆይታ እንደሚኖረው ታውቋል። ተጫዋቹ ሃገሩ ለዋንጫ በደረሰችበት ጨዋታ ወርቃማ ግብ በማስቆጠር የሚታወቅ ሲሆን፤ በፊፋ 100 በሕይወት ያሉ ምርጥ ተጫዋቾች መካከል አንዱ እንደሆነ ይታወቃል።
የዓለምን እግር ኳስ በበላይነት የሚመራው ፊፋ ውድድሩን ሲያዘጋጅ ለረጅም ዓመታት በስፖንሰርነት አጋር የሆነው ኮካ ኮላ የመጠጥ ፋብሪካ ይህንን መርሐ ግብር አዘጋጅቶታል። በትናንቱ መግለጫ ላይ የኮካ ኮላ ማኔጂንግ ዳይሬክተር ዳረን ዊልሰን፤ ታሪካዊ የሆነው የዓለም ዋንጫ ወደ ኢትዮጵያ መምጣቱን አብስረዋል።
ድርጅቱ እኤአ ከ1976 ጀምሮ ከፊፋ ጋር በአጋርነት እየሠራ ያለ ሲሆን፤ በኢትዮጵያ ደግሞ ከ60 ዓመታት በላይ ቆይታ እንዳለው ተጠቅሷል። ዘንድሮም ዓለም ዋንጫ የሚካሄድበት ዓመት መሆኑን ተከትሎ ‹‹ማመን የተዓምር መሠረት ነው›› በሚል መሪ ሃሳብ ደጋፊዎች ከዋንጫው ጋር ፎቶ የመነሳት ዕድል እንዲያገኙ ትክክለኛው ዋንጫ ወደ ኢትዮጵያ እንዲመጣ መደረጉ ተገልጿል።
በመግለጫው ላይ የተገኙት የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ኢሳያስ ጅራ በበኩላቸው፤ ‹‹ኢትዮጵያ ይህንን ዕድል ካገኙት ሃገራት መካከል አንዷ መሆኗ ትልቅ ትርጉም እንዳለው አንስተዋል። ሕልመኛ መሆንና ለስኬትም ጠንክሮ መሥራት አስፈላጊ ነው። ኳታር ትንሽ ሕዝብ ያላት ትንሽ ሃገር ብትሆንም ሕልሟ ትልቅ በመሆኑ ይህንን ውድድር ለማዘጋጀት ችላለች። ከተመልካችነት ወደ ተሳታፊነት መግባት የሚቻለውም ጠንክሮ በመሥራት ነው፡፡›› በማለት ከዋንጫው ጀርባ በማዘውተሪያ እና በተጫዋቾች ልማት ላይ መሥራት ከተቻለ የማይደረስበት ነገር እንደሌለ ማየት አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ዋንጫው በሕይወት ዘመን አንዴ እና ሁለቴ አልያም ከነጭራሹ የማይገኝ እድል በመሆኑ የሃገራችንን ክብር በሚመጥን ደረጃ ለሁለት ቀናት እንደሚስተናገድ የጠቆሙት ፕሬዚዳንቱ፤ የኮካ ኮላ ድርጅት ዋንጫው ወደ ኢትዮጵያ እንዲመጣ በማድረጉ በራሳቸውና በኢትዮጵያ ህዝብ ስም ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
በኢፌዴሪ ባህልና ስፖርት ሚኒስትር የስፖርት ዘርፍ ዴኤታ አምባሳደር መስፍን ቸርነት በበኩላቸው፤ ሚኒስትሩም ሆነ መንግሥት ከዓለም ዋንጫ መምጣት ጋር በተያያዘ ከኮካ እና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እየሠራ መሆኑን ገልጸዋል። ሃገሪቷ በውድድሩ የመሳተፍ እድል ባታገኝም የዋንጫው መምጣት ግን አሁን ካለችበት ወቅታዊ ሁኔታ አንጻር ሰላማዊነቷን የሚያበስር እንደሚሆን ተናግረዋል። ስፖርት ለሃገራት ገጽታ ግንባታ ካለው ፋይዳ ባለፈ ትውልዱ ዋንጫውን በቅርበት በመመልከት ለነገ እንዲያልምና ተግቶ እንዲሠራ የሚያደርገው መሆኑንም አስረድተዋል።
ከዋንጫው ጋር ፎቶ የመነሳት እድል የሚያገኙ የስፖርት ወዳጆችም አስቀድሞ የኮካ ኮላ ጠርሙሶች ላይ የሚገኘውን ምልክት 10 እስኪሞላ አጠራቅመው ወደ ኩዊንስ ሱፐርማርኬት በመሄድ የመግቢያ ካርድ ማግኘት የሚችሉ መሆኑ ተጠቁሟል።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 27 /2014