ኢትዮጵያ ከሰሜን እስከ ደቡብ፤ ከምስራቅ እስከ ምዕራብ በተለያዩ ጊዜያት በርካታ ጀግኖችን ያፈራች አገር ናት። ወራሪ ኃይሎች የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት በመዳፈር በመዳፋቸው ስር ሊያስገቧት አስበው ብዙ ሞክረዋል። መሰል ተደጋጋሚ ሙከራዎችን ካደረጉት ወራሪዎች መካከል አውሮፓዊቷ ኢጣሊያ በግንባር ቀደምትነት ትጠቀሳለች። የፍራንቼስኮ ክሪስፒዋ ኢጣሊያ ዓድዋ ላይ የተከናነበችውን የሽንፈት ካባ በድል ለማካካስ በማሰብ በፋሺስቱ ቤኒቶ ሙሶሎኒ እየተመራች አሰቃቂ ወረራ በመፈፀም ለአምስት ዓመታት ያህል ኢትዮጵያን ቅኝ ተገዢዋ ለማድረግ ጥረት አድርጋም ነበር፡፡
ኢጣሊያ ዓድዋ ላይ የተከናነበችውን ሽንፈት ለመበቀል ለአርባ ዓመታት ያህል ስትዘጋጅ ከኖረች በኋላ በየጊዜው ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚና በባህል መስክ የተፈራረመቻቸውን የሰላምና የትብብር ውሎችና በመንግሥታቱ ማኅበር አባልነቷ የገባቻቸውን ዓለም አቀፍ ግዴታዎች ሁሉ በጠመንጃ አፈሙዝ መቅደድ ጀመረች፡፡
እንዲህ እንዲህ እያለች በ1928 ዓ.ም ኢትዮጵያን ወረረች። ታዲያ መቼውንም ቢሆን በአገሩና በነፃነቱ የማይደራደረው የኢትዮጵያ ሕዝብ የፋሺስትን አገዛዝ ‹‹አሜን›› ብሎ አልተቀበለውም። ይልቁንም ጨርቄን ማቄን ሳይል ‹‹ጥራኝ ዱሩ›› ብሎ ለነፃነቱ መፋለም ጀመረ። የኢጣሊያ ወራሪ ኃይልም አንዲትም ቀን እንኳን እፎይ ብሎ ሳይቀመጥ ከአምስት ዓመታት እልህ አስጨራሽ ትግል በኋላ ሌላ የሽንፈት ማቅ ለብሶ ከኢትዮጵያ ምድር ተባረረ። ታዲያ በዚህ አስገራሚና አኩሪ የመስዋዕትነት ጉዞ ውስጥ ደማቅ የጀግንነት ታሪክ ከፃፉና ለኢትዮጵያ ሉዓላዊነት ከተጋደሉ እልፍ የኢትዮጵያ ጀግኖች መካከል አንዱ ታላቁ አርበኛ ደጃዝማች ኪዳኔ ወልደመድኅን ነበሩ።
ኪዳኔ ወልደመድኅን በዕለተ ዓርብ፣ ሐምሌ 2 ቀን 1907 ዓ.ም ቡልጋ ከሰም ወረዳ፤ የለጥ ቀበሌ፤ ልዩ ስሙ ቡሄ አምባ በሚባለው ሥፍራ ላይ ከእናቱ ከወይዘሮ አስካለ ደጀን እና ከአባቱ ከቀኛዝማች ወልደመድኅን አዩደረስ ተወለደ። አባቱ ቀኛዝማች ወልደመድኅን በዘመኑ የታወቁ ስመጥር ጠበቃ ነበሩ። ኪዳኔ ማርያም እስከ 12 ዓመት እድሜው ድረስ እዚያው ቡሄ አምባ አካባቢ በአያቱ አቶ ደጀን ደብሩ ቤት ሆኖ የቄስ ትምህርት በቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን ተከታትሏል። በመቀጠልም ከወላጆቹ ጋር ሆኖ የአማርኛና የግእዝ ትምህርቱን አጠናቋል።
ለአካለ መጠን ሲደርስ በ18 ዓመቱ በ1925 ዓ.ም. አዲስ አበባ የክብር ዘበኛ ሰራዊት አባል ሆነ። ወዲያው በንጉሠ ነገሥቱ ትዕዛዝ ከ69 አዲስ ወታደሮች ጋር ባሌ ተመድቦ እስከ 1927 ዓ.ም ድረስ በተራ ወታደርነት ከዚያም በሃምሳ ዓለቃነትና በባሻነት ማዕረግ ሲያገለግል ከቆየ በኋላ የፋሺስት ኢጣሊያ ጦር ኢትዮጵያን በወረረበት ጊዜ በ1928 ዓ.ም በነደጃዝማች በየነ መርድ መሪነት ከጎባ ወደ ኦጋዴን ዘመተ።
ኪዳኔ ከባላምባራስ አየለ ወልደማርያምና ሌሎች አርበኞች ጋር ሆኖ በዚህ ግንባር በዋቢ ሸበሌና አካባቢው ለዘጠኝ ወራት ያህል ከጠላት ጋር ሲፋለም ከርሞ ወደ ጎባ ተመለሰ። ከሰኔ 1928 ዓ.ም እስከ ሚያዝያ 1929 ዓ.ም ድረስ ከአርሲ፣ ከሲዳማ፣ ከሐረርና ከኦጋዴን ወደ ጎባ የዘለቀውን የጠላት ጦር ሲዋጉ ከርመው፤ መጨረሻ ላይ ተማም ከሚባለው ሥፍራ ላይ በተካሄደው ጦርነት ላይ ማምለጥ በማይቻልበት ሁኔታ ኪዳኔና ሌሎች አርበኞች በጠላት እጅ ወድቀው ተማረኩ። ጠላትም ለአምስት ወራት በጽኑ እሥራት ከያዛቸው በኋላ፤ በጥር ወር 1930 ዓ.ም ከጎባ ወደ ወሊሶ አዛውሮ አሰራቸው።
ባሻ ኪዳኔም እዚሁ እስር ቤት እያሉ አብረዋቸው ከታሰሩት አርበኞች መካከል በምስጢር 100 ሰዎችን አደራጅተው እዚያ ያለውን የጠላት ጦር ፈጅተው ለመሸፈት ከወሰኑ በኋላ በወቅቱ ከስመ ጥር አርበኞች መካከል አንዱ ወደነበሩት ወደ ባላምባራስ (በኋላ ደጃዝማች) ገረሱ ዱኪ ሰው ለመላክ በመዘጋጀት ላይ ሳሉ አሳሪያቸው የፋሺስት ጦር ነገሩን በመስማቱ እጅግ ጥብቅ የሆነ ክትትል ይደረግባቸው ጀመር። ባሻ ኪዳኔም
ይህን ሲገነዘቡ ካደራጇቸው 100 ሰዎች መካከል 55 ወታደር ከነመሳሪያው፤ አራት መትረየስ፤ አስር ሣጥን ጥይት፤ ስድስት ሽጉጥ ከጠላት እጅ ነጥቀው እየተታኮሱ ሲወጡ የጠላት ኃይል ሃያ ወታደርና አንድ መትረየስ ከሁለት ሣጥን ጥይት ጋር ብቻ ገንጥሎ ሲያስቀርባቸው ከተረፈው መሳሪያና ወታደር ጋር ድል አድርገው ሸፈቱ። ወዲያውም ኩሳ ኪዳነምሕረት ከሚባል ሥፍራ ላይ ከደጃዝማች ገረሱ ጋር ተገናኙ።
ባሻ ኪዳኔ ከባላምባራስ ገረሱ ጋር ከተቀላቀሉ በኋላም እስከ ጥቅምት 1931 ዓ.ም ድረስ በደንዲ፤ በሶዶ፤ በበዳቄሮ እና በሌሎች ሥፍራዎች በአርበኝነት ሲዋጉ ቆዩ። በዳቄሮ ከሚባለው ሥፍራ ላይ ሳሉ ሙሴ ሰባስቲያኖ ካስታኛ (ሙሴ ቀስተኛ) የሚባለው ጣሊያናዊ ከፋሺስት አመራሮች ተልኬያለሁ ብሎ ከሦሥት ባላባቶች ጋር መጣ። አርበኞቹም ይህ ሰው ቀደም ሲል በ1930 ዓ.ም ወደ ራስ አበበ አረጋይ ዘንድ ሄዶ የጦሩን ኃይል ከተመለከተ በኋላ ብዙ አርበኛ እንዳስገደለ ሰምተው ስለነበር እነሱንም እንደዚሁ ለማስፈጀት እንደመጣ ስለተገንዘቡት ባሻ ኪዳኔ ወልደመድኅን በመውዜር ጠመንጃ ሲመቱት ‹‹ኢጣልያ ለዘለዓለም ትኑር! ለኢጣሊያ ስል ሞትኩላት›› ብሎ ሲናገር በሽጉጥ ራሱን መትተው ከገደሉት በኋላ የለበሰውን ሙሉ ገበርዲን ልብስና ካፖርት እንዲሁም የንግሥተ ነገሥታት ዘውዲቱ ስዕል ያለበትን የብር ሰዓቱንና በቅሎውን ከነኮርቻው ማረኩት። ከሙሴ ካስታኛ ጋር አብረው የመጡት ባላባቶች የሙሴን መገደል ለፋሺስት ጦር መሪዎች አሳወቁ። ከ25 በላይ የጦር አውሮፕላኖች ያሉበት በርካታ የፋሺስት ጦር ወደ በዳቄሮ ዘመተ። አርበኞቹም ለሦስት ቀናት ሙሉ ሲከላከሉ ከቆዩ በኋላ ከሥፍራው ሸሽተው ሶዶ ላይ ለስምንት ቀናት ያህል ተዋጉ።
ባሻ ኪዳኔ በኅዳር ወር 1931 ዓ.ም. አርበኞቻቸውን አስከትለው ወደ ትውልድ አገራቸው ቡልጋ ገቡ። በዚያም ከፊታውራሪ ኃይለማርያም ማናህሌ እና ከፊታውራሪ ተረፈ ማናህሌ ጋር ተቀላቅለው እስከ መጋቢት 1931 ዓ.ም. ድረስ በውሽንግር፤ ጨፌ ዶንሳ ምሽግ፤ ነጭ ድንጋይ ምሽግ፤ ልዝብ ድንጋይ በተባሉ ቦታዎች ላይ ከጠላት ኃይል ጋር ሲዋጉ ከረሙ። በዚህ ወቀት ታመው በነበረበት ጊዜ የፋሺስት ጦር በሦስት አቅጣጫ ከበባቸው። የጠላት ኃይል እጅ እንዲሰጡ ቢጠይቃቸውም ፍቃደኛ ባለመሆናቸው ከህመማቸው ጋር እየታገሉ ከፋሺስት ጋር ተፋለሙ። በወቅቱ ባሻ ኪዳኔ ከፋሺስት ጦር ጋር ያደረጉት ፍልሚያ እጅግ መራራና እልህ አስጨራሽ እንደነበር ስለአርበኞች ታሪክ የተፃፉ መዛግብት ይመሰክራሉ። ከህመም ጋር እየታገሉ ከፋሺስት ጦር ጋር የተፋለሙት ባሻ ኪዳኔ የጠላት ጦር እርሳቸው መሽገውበት የነበረውን ጫካ በእሳት ነበልባል ግራና ቀኙን ሲያቃጥልው እሳቸው በተዓምር ተረፉ። ከሦስት ቀናት በኋላ የጠላት ኃይል አካባቢውን ለቆ ሲሄድ ባሻ ኪዳኔ ህመሙና ድካሙ በርትቶባቸው ስለወደቁ በብዙ ፍለጋ ነበር የተገኙት።
ከዚህ በኋላ ክረምቱን ቡልጋ ውስጥ በነጭ ድንጋይ፣ ፍልፍል አፈር፣ ጦስኝ ምሽግ እና በመስኖ ከነደጃዝማች ኃብተ ሥላሴ በላይነህ፣ ፊታውራሪ በለጠ ሳሴ፣ ፊታውራሪ አጎናፍርና ሌሎችም ስመጥረ የቡልጋ ልጆች ጋር ሆነው ጠላትን ሲያጠቁና ሲከላከሉ ቆይተው በመስከረም 1932 ዓ.ም በሰገሌ በኩል ተጉዘው ገሊላ ከሚባል ሥፍራ ላይ ከራስ አበበ አረጋይ ጦር ጋር ሲቀላቀሉ ባሻ ኪዳኔ የግራዝማችነት ማዕረግ ተሾሙ። ከዚህ ጊዜ ጀምሮ ወደ ጎጃምና ወደ ጎንደር እስከዘመቱበት 1933 ዓ.ም ድረስ ከራስ አበበ ጋር ጠላትን በየቦታው ሲዋጉ በአርበኝነት ቆዩ። ከብዙ ውጊያዎችና ጀብዱዎች በኋላ በየካቲት 1933 ዓ.ም መሶቢት ከሚባለው ቦታ ላይ በመሪነት የጠላትን ጦር ድል አድርገው ወደ ዋናው ሰራዊት ከተቀላቀሉ በኋላ ራስ አበበ የቀኛዝማችነት ማዕረግ ሾሟቸው።
ቀኛዝማች ኪዳኔ ከሌሎች አርበኞች ጋር ሆነው በ1933 ዓ.ም ዳውንት፣ ተንታ እና ደብረታቦር ላይ የሰፈረውን የፋሺስት ጦር እየማረኩ በመስከረም 1934 ዓ.ም ጉማራ ላይ ከፍ ያለ ውጊያ አድርገው ጠላትን ድል አደረጉ። በኅዳር 1934 ዓ.ም ከጎንደር እስከ ቁልቋል በር ላለው ለጠላት ጦር ስንቅና ትጥቅ አቀብሎ ሲመለስ ጥቃት ከፍተውበት ብዙ ባንዳዎችን ገደሉ።
በዚያው በኅዳር ወር 1934 ዓ.ም ጎንደር ከተማ ውስጥ ጄነራል ናሲ የተባለው የፋሺስት ጦር አዛዥ ከብዙ ሺህ ሰራዊት ጋር አካባቢውን በሽቦ አጥሮ በሽቦው ውስጥና ውጭ ፈንጂና ቦንብ ቀብሮበት ነበር። ቀኛዝማች ኪዳኔ ይህንኑ የተቀበረ ቦንብ እየቆረጡ ሌሊቱን ተጉዘው ከምሽጉ ደረሱ። ሲነጋ ተኩስ ተከፈተ። ጠላትም ከከፍተኛ ተራራ ላይ ወደታች ወደነ ቀኛዝማች ኪዳኔ በቦምባርድና ከባድ መትረየስ ሲያጠቃቸው በተራራው ሥር አድርገው ወደ ጎንደር ከተማ የሚወስደውን መንገድ ላይ ሲደርሱ ከጎንደር ከተማ የሚመጡ አስመስለው ከኋላው በጨበጣ የእጅ ቦንብ እየጣሉ ብዙ የጠላት ኃይል ደመሰሱ። እንዲሁም መትረየሶችን ማርከውና ምሽጉን አስለቅቀው ከያዙ በኋላ ጀነራል ናሲ ወዳለበት ወደ ጎንደር መጓዝ ቀጠሉ። ጎንደር ሲገቡም ፋሲል ግንብ ምሽግ ሲደርሱ ምሽጉን ለመድፈር የእጅ ቦንብ ምሽጉ ላይ በብዛት ሲጥሉ ጠላት ተሸንፎ የሰላም ባንዲራ አውለበለበ። ወዲያውኑ 500 የጠላት ወታደሮችን ማረኩ። በከተማው የሚገኙትን የዓረብ ተወላጆች ሱቅና ገንዘብ እንዳይዘረፍ በወታደር አስጠብቀው ወደ ቀጣዩ ዘመቻቸው አቀኑ።
ኅዳር 19 ቀን 1934 ዓ.ም ራስ ብሩ ወልደብርዔል ከእንግሊዛዊው ሜጀር ጀኔራል ፎክስ ጋር ወደ ጎንደር ገቡ። ‹‹ባለህበት እርጋ›› ተባለና ሁሉም ተረጋጋ። ጀኔራል ናዚ ያለድርድር እጁን ሰጠ። የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ በፋሲለደስ ግንብ ላይ ተውለበለበ። በማግሥቱ ኅዳር 20 ቀን ልዑል አልጋወራሽ አስፋወሰን ኃይለሥላሴ ጎንደር ገቡ። የፋሺስት ኢጣሊያ ጦር በኢትዮጵያ የነበረው ቆይታ ተደመደመ! የጎንደሩ ውጊያና ሽንፈት የፋሺስት ኢጣሊያ ጦር በአፍሪካ ምድር ያካሄደው የመጨረሻው ውጊያና የተከናነበው የመጨረሻው ሽንፈት ሆኖ ተመዘገበ። ቀኛዝማች ኪዳኔ ከአልጋወራሹ ጋር ወደ ወሎ ጠቅላይ ግዛት እንዲሄዱ ተደርጎ እዚያው ብዙ ወታደርና መሳሪያ ለመከላከያ ሚኒስቴር አስረከቡ።
በየካቲት 1934 ዓ.ም የፊታውራሪነት ማእረግ አግኝተው መጀመሪያ በወረዳ አስተዳዳሪነት ከዚያም በ1936 ዓ.ም የየጁ፤ የዋድላ ደላንታ፤ የመቄት፤ የሸደሆና የዳውንት ብሔራዊ ጦር አዛዥና የጠቅላይ ግዛቱ ጦር አማካሪ በመሆን አገለገሉ። ከዚያም እስከ 1943 ዓ.ም ድረስ ደግሞ በወሎና በከፋ ውስጥ በአውራጃ አስተዳዳሪነት ተመድበው ሲያገለግሉ ቆዩ። በዚሁ ወቅት ነው የደጃዝማችነት ማዕረግ የተሰጣቸው።
ደጃዝማች ኪዳኔ ከፋ ውስጥ እንደተሾሙ ከጠቅላይ ገዢው ጋር ባለመስማማታቸው ተሽረው ንጉሠ ነገሥቱ ከስልጣን እስከወረዱበት ጊዜ ድረስ በእስራትና በግዞት እንዲቆዩ ተደርገዋል። ንጉሠ ነገሥቱ ከስልጣን ከወረዱ በኋላ ደጃዝማች ኪዳኔ የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማኅበር ሊቀመንበር ሆነው ተመርጠው ሲያገለግሉ ከቆዩ በኋላ ሀገራቸውንና ማኅበሩን ወክለው ሮም ላይ በተካሄደው የዓለም አቀፍ ጸረ ኑክሊየር መሣሪያ ስብሰባ ላይ ለመሳተፍ ሲጓዙ ሞስኮ ላይ፣ ጥቅምት 9 ቀን 1972 ዓ.ም. አረፉ። ስርዓተ ቀብራቸውም ጥቅምት 15 ቀን 1972 ዓ.ም በአዲስ አበባ መንበረ ፀባዖት ቅድስት ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን ተፈፅሟል።
ደጃዝማች ኪዳኔ ወልደመድኅን ከአርበኛነታቸው በተጨማሪ በማኅበራዊ ኑሯቸውም ንቁ ተሳታፊ ነበሩ። በ1949 ዓ.ም በትውልድ ስፍራቸው በቡልጋ የየለጥ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያንን አሰርተዋል። በ1964 ዓ.ም ‹‹ከልደት እስከ ሞት›› የተሰኘች አጭር ሃይማኖታዊና የፍልስፍና መጽሐፍ አሳትመዋል።
ክቡር ደጃዝማች ኪዳኔ ወልደመድኅን ከሀገር ውስጥ በተጨማሪ በርካታ የውጭ ሀገራት ሽልማቶችን አግኝተዋል። ከእነዚህም መካከል የዳግማዊ ምኒልክ ኒሻን ባለአምበል፣ የአርበኝነት ሜዳይ ከአራት ዘንባባ ጋር፣ የድል ኮከብ ሜዳይ፣ የቅዱስ ጊዮርጊስ የከፍተኛ ጀብዱ ሜዳይ ከአንድ ዘንባባ ጋር፣ የኢትዮጵያ የክብር ኮከብ ታላቅ መኮንን ከደረት ኮከብ ጋር፣ የአፍሪቃ ኮከብ ሜዳይ (ከእንግሊዝ መንግሥት)፣ የአፍሪካ የድል ሜዳይ (ከእንግሊዝ መንግሥት) እንዲሁም ሦስት ልዩ ልዩ የሶቭየት ኅብረት ኒሻኖች ይጠቀሳሉ።
አንተነህ ቸሬ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 26 /2014