በቅድሚያ ለእስልምና ሃይማኖት ተከታይ ወገኖቼ፣ እንኳን ለ1ሺህ 443ኛውን የኢድ በዓል በሰላም አደረሳችሁ። ኢድ ሙባረክ ብያለሁ:: እንዴት ሰነበታችሁልኝ ውድ የአዲስ ዘመን ጋዜጣ አንባቢ ወዳጆቼ:: ሰሞኑን ጎንደር ውስጥ ተፈፀመ የተባለውን ግጭት ካጋጠመው የሰው ሕይወት መጥፋትና የአካል ጉዳት በተጨማሪም በሃይማኖት ተቋማት ላይ ውድመት መድረሱን በማህበራዊ ሚዲያዎችና በሳተላይት ቴሌቪዥኖች ስንከታተል ሰንብተናል። ሃይማኖት በመለኮት ወይም በቅዱስ ሀሳብ ዙሪያ የተቋቋሙ የእምነት፣ የጋራ ምልክት ስርዓት ነው።
ሃይማኖት በህልውና፣ በሞራል እና በመንፈሳዊ ጉዳዮች ላይ በመርሆዎች፣ በእምነት አሠራሮች ስብስብ የተገነቡ ትምህርቶች ናቸው። ሃይማኖቶች፣ በአንድ ህብረተሰብ ውስጥ በመኖራቸው የአብሮነት፣ የመከባበር፣ የወንድማማችነት እና የይቅርታ መልዕክቶችን በቋሚነት ያለማቋረጥ የሚያረጋግጡ ናቸው:: ታዲያ፣ የኛ ነገር ከርሞ ጥጃ፣ አድሮ ቃሪያ፣ ታጥቦ ጭቃ….ሆኖብኛል። ‘’ግጭቱ እንዴት ተነሳ? መቼ? የት? እነማን? ለምን አላማ አዘጋጁት?” የሚለውን ጥያቄ ጉዳዩን ለሚከታተሉት የህግ ባለሙያዎች ትቼ፤ ተቀዳሚ ሙፍቲ ሐጂ ዑመር እድሪስ የሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ትኩረት ማድረጉ ጠቃሚ ይመስለኛል።
በመልዕክታቸው፣ ያልተረጋገጠ ወሬ ህዝብን ከህዝብ የሚያጋጭ ጉዳይ መሆኑንም አስገንዝበው፣ ድርጊቱ የትኛውንም ሃይማኖት የማይወክል እንደሆነ አረጋግጠውልናል። በሕዝቡ ዘንድ ተቀባይነትና እውቅና ያላቸውም አካላት ቢሆኑም ግጭት አባባሽ መልእክቶችን በማሰራጨት እልቂት እንዲፈጠር የሚያደርጉትንም ፅንፈኛ ቅስቀሳቸውን እንዲያቆሙ በአባታዊ ተግሳፅ አሳስበዋል:: ህዝቡም የተነገረውን ሁሉ አምኖ መቀበል ብቻ ሳይሆን መርምሮ ማረጋገጥ እንዳለበት የሰጡትን ቁርጥ ያለማሳሰቢያ ሰላም ወዳድ ኢትዮጵያውያንን ሁሉ በደስታ ተቀብለነዋል። አያይዘውም፣ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ኮሚቴ በማቋቋም እና ቦታው ድረስ በማቅናት ችግሩን ለመፍታት ጥረት እንደሚያደርግም ነግረውናል።
ሥልጣኔ ማለት ይህው ነው:: የሠለጠነ ባህል ወይም ኅብረተሰብ የሚገነባው በመነጋገርና በመቻቻል በመተሳሰብ ነው። አንዳንድ ሰዎች ስልጣኔን ሲገልጡት፡- “ስልጣኔ: የፈለጉትን ነገር በፈለጉት ሰዓት ማድረግ መቻል ነው :: ስልጣኔ …. ሁልጊዜ ለውጥ መፈለግ ነው …..ስልጣኔ፡ ንጹህ መሆንና በንጹህ አካባቢ መኖር ነው……. ስልጣኔ፡ ሌላውን ያለመረበሽ እና ራስም ያለመረበሽ ፍላጎት ያለው መቻቻል መተሳሰብ መረዳዳት… የሰውን ሁሉ መብት ለማክበር የመፈለግ እሳቤ ነው:: ……ስልጣኔ: ለችግር ሁሉ መፍትሄ ለማምጣት የሚያስችል መተባበር ነው፤” ብለው ያምናሉ። እኔም በዚህ ሐሳብ እስማማለሁ።
በእርግጥ ሃይማኖት ለአንድ ኅብረተሰብ የሚያምንባቸው ጽኑ መሰረት እምነቶች በመሆናቸው በዓለም ውስጥ በርካታ ልዩ ልዩ ሃይማኖቶች ተፈጥረው ዛሬ በሚሊዮን የሚቆጠር ተከታዮች አፍርተው ዓለም በመቻቻል ነው የሚኖረው። ከነዚህም ሃይማናቶች ዋና ዋናዎቹ በይፋ የመንግሥት ሃይማኖት በመባል ተቀባይነት ካገኙት ውስጥ ክርስትና፣ እስልምና፣ አይሁድና፣ የሕንዱ ሃይማኖት እና ቡዲዝም ዓለም አቀፋዊ እውቅና ተሰጥቷቸዋል:: ከነዚህ ታላላቅ ሃይማኖቶች ውስጥ አንዱ የሆነው እስልምና ነው:: እንደዚህ እንደዛሬው ከዓለም ጫፍ እስከ ዓለም ጫፍ እንዲስፋፋና ብዙ ተከታዮች አግኝቶ እንዲበለፅግ ኢትዮጵያ ቀዳሚውን ድርሻ ትይዛለች።
ምክንያቱም የነብዩ መሐመድ ተከታዮች ስለ እስልምና ሃይማኖታቸው በመካ እንግልት ሲደርስባቸው ተከታዮቻቸውን የላኩት ወደ ኢትዮጵያ ነው። ይህ ባይሆን ኖሮ ምን ሊሆንና ሊፈጠር እንደሚችል አይታወቅም። እናም እነዚያ የነብዩ መሃመድ ተከታዮች ወደ ኢትዮጵያ መጥተው ራሳቸውን በማዳናቸውና በኢትዮጵያ በመጠለላቸው፤ ኢትዮጵያ ለእስልምና ሕልውናም መስፋፋትም ከፍ ያለ ሚና እንዲኖራት ሆኗል። ይሄን የምለውም ያለምክንያት አይደለም። ይልቁንም የሆነውንና የተፈጸመውን በማስረጃነት
በመያዝ ነው። እንዴት ቢሉ በወቅቱ የእስላም አሀዳዊ ጥሪ ፈጽሞ መስማት ያልፈለጉት የመካ ቁረይሾች በሙስሊሞች ላይ የቅጣት በትራቸውን አሳረፉ። አማኞቹ በደረሰባቸው ግፍ እና መከራን በመመረር በገዛ ወገኖቻቸው እየተገደዱ ከእምነታቸው በመመለስ እንደነርሱ የጣኦት አምልኮት ይከተሉ ዘንድ ማእቀብ፣ እየተጣለባቸው ስቃይ እና ሞት ግፍና ብስቁልና ተፈፀመባቸው።
በዚህን ጊዜ ነብዩ ሙሀመድ በ610 እ.ኤ.አ. የነብይነት ማእረግ አግኝተው ስለነበር በመካ ወደ ኢስላም ጥሪ በማድረግ ባልደረቦቻቸው ላይ የሚፈጸመውን ጥቃት ሊከላከሉ እንደማይችሉ ሲገነዘቡ ፣ “ፈጣሪአቸውን በነጻነት ማምለክ የምትችሉት ወደ ሀበሻ ሐገር ስትሰደዱ ነው” በማለት ነብዩ ሙሀመድ ተከታዮቻቸውን በመምከራቸው ወደ ኢትዮጵያ የላኳቸው መሆኑን የተለያዩ ድርሳናት ያመለክታሉ። በወቅቱ ነብዩም በግፍና በመከራ ያሉትን ተከታዮቻቸው እንደዚህም አልዋቸው። “ ወደ ሀበሻ ሐገር ተሰደዱ በርስዋ አንድ ንጉስ አለ ። ከርሱ ፊት ማንም ተበዳይ አይሆንም ፤ “አላህ ካላችሁበት ሁኔታ አውጥቶ ድል እስክትጎናጸፉ ድረስ….” ሒዱ በማለት አሰናበቷቸው።
ታሪክ እንደሚያረጋግጥልን ግንኙነቱ የተጀመረው ኢስላም ከየትኛውም አገር ከመድረሱ አስቀድሞ በፊት ከቅድስቲትዋ መካ ከተማ በመነሳት ወደ ሐበሾች ሐገር ኢትዮጵያ ነው የደረሰው :: በዚህም መሰረት ከነብዩ ሙሀመድ ትእዛዝ ተቀብለው የመጀመሪያውን ስደት (ሂጅራ) ወደ ሀበሻ ወደ ቅድስት ሐገር ኢትዮጵያ የደረሱት አሥራ ሁለት ሁነው ነበር ። ከስደተኞቹ መካከል የነብዩ ሙሀመድ ሴት ልጅ ሩቅያ ቢንት ሙሀመድ እና ባለቤትዋ (በኋላ ላይሶስተኛ ኸሊፋ ወይንም የሳዑዲ ንጉስ የሆኑት)። ኡስማን ቢን አፋን ይገኙበት ነበር ። በማለት አያሌ የታሪክ ድርሳናት ስናገላብጥ የሚሰጠን ምስክርነት ይህንኑ ሐቅ ነው ::
የሃይማኖት ነፃነት እና የሃይማኖት እኩልነት በማረጋገጥ ኢትዮጵያ የረጅም ጊዜ ታሪክ አለት። ይሄን በተመለከተም ከተለያዩ ሰነዶች ማመሳከር፤ ከታሪክም ብዙ ነገሮችን መማር እንችላለን። ታሪክ የማንኛውም ሀገር ንብረት ነው ። ማንኛውም የአገሩ ዜጋ የእምነት ታሪኩን ጠንቅቆ ማወቅ አለበት ። በዚህ ውስጥ ፣ ያለጥርጥር ፣ መምህራንና የሃይማኖት አባቶች፣ የሚዲያ ተቋማት ትክክለኛውን ትምህርት በመስጠት ትውልዱን ማዳን ይኖርባቸዋል ::
በሰው ልጆች የስነልቦናዊ አመለካከት ቢሆንም የፍቅርና የጥላቻ ስሜት ገብቶት በአዕምሮው ብስለት ካልበለፀገ በቀር የህብረተሰብ ተቆርቋሪነትና ሃይማኖታዊ እምነትን ብቃት ባለው ኃላፊነት ለመምራት እጅግ ይከብዳል:: ጊዜው ቆየት ቢልም፣ ተቀዳሚ ሙፍቲ ሐጂ ዑመር እድሪስ፣ በአንድ ወቅት ንግግር ሲያደርጉ ያዳመጥኩት ቁምነገር አለ: : “ በዘረኝነት ተከፋፍለናል:: ደም አፍስሰናል! :: ደሀው የሚልብሰው አቶ የሚጠለልበት ፈርሶ ! በባለ ጠጋው እየተበደለ ፍርድ ሲጓደል እኛም የሃይማኖት አባቶች መገሰፅ ፣ መምከር፣ ማስተማር ፣ መመለስ ሳንችል ፣ ምህረት መጠየቅ ዋጋ የለውም !! ። ፈጣሪ ከዚህ የከፋ ቅጣት ያሰበ ይመስለኛል !! ። እኛ ከመናገር ባለፈ በተግባር ፣ ከክፉ ሥራችን ተመልሰን ፀሎት (ዱአ) ብናደርግ ምህረት የማናገኝበት ምክያት ያለ አይመስለኝም።” በማለት ኀዘንና ቁጭት በተቀላቀለበት ስሜት በጋራ በተዘጋጀው የፆሎት ሥነሥርዓት ላይ ለመንግሥት ባለስልጣኖችና ለክርስትና እምነት አባቶች ያስተላለፏትን መልዕክት ምንጊዜም አረሳትም።
ይሄን ንግግራቸውንና መልዕክታቸውን ባሰብኩ ቁጥር እንዲህ አይነት ሲናፍቀን የኖረ ትክክለኛ ሃይማኖታዊ አባት አሁንም ወደፊትም በእጅጉ እንደሚያስፈልገን አስባለሁ:: በማህበረሰባችን ውስጥ እንዲህ አይነት ሃይማኖታዊ ስነ ምግባር የሚያስተካክል መሪ ከሌለ ወግና ስርዓት አይኖረንም። እረብሻው፣ ግድያው፣ ብጥብጡ፣ ስርዓት አልበኝነቱ ይቀጥላል። ሕግና ስርዓት ከሌለ ደግሞ ነውር ወይም ክብር አይኖርም:: ሥነ-ምግባር ደግሞ በማህበረሰብ ውስጥ ተቀባይነት ያለውንና የሌለውን ድርጊት መለየትና ነውር የሆነውን ድርጊት ነቅሶ በማውጣት ወይንም በማስወገድ እንደ ተቀዳሚ ሙፍቲህ ክቡር ዶክተር ሀጂ ኡመር ኢድሪስን የሚመስሉ ጠንካራ የሃይማኖት አባቶች ከሌሉ ከዚህ የባሱ ብዙ ማህበራዊ ቀውሶች ወደፊት መምጣቸው አይቀሬ ነው ::
በእርግጥ በሰዎች መካከል ብዙ ልዩነቶች አሉ :: ልዩነት ወይም መለያየት ማለት አንድ ሰው በሃይማኖቱ፣ በቋንቋው፣ በብሔሩ፣ በቀለሙ፣ በአመለካከትና በንግግር በሀሳብ ከሌላው ሰው የተለየ ሊሆን ይችላል :: ነገር ግን የሚያስማሙን ጉዳዮች ላይ ተባብረን ሀገራችንን መገንባት ይኖርብናል :: በተለያየንባቸው ጉዳዮች ላይ ደግሞ አንደኛችን ለአንደኛችን ሆደ ሰፊ ሆነን በሰለጠነ መልክ ችግሮቻችንን እንደ ሀገር ተመካክረን መፍታት ተገቢ ነው :: የተለያዩ ሃይማኖቶች በመከተላችን ብቻ ኢትዮጵያዊነታችንን የሚቀይር ምድራዊ ኃይል በፍፁም ሊኖር አይገባውም።
ይህ እውነት እንደተጠበቀ ሆኖ ግን ከልዩነት አቀንቃኝነት ይልቅ አንድነት፣ ሕብረትና ወንድማማችነትን፣ ከመገፋፋትና ፀብ ይልቅ መተባበር፣ መረዳዳትና በፍቅር አብሮ መኖርን፤ ከጥላቻና በቀል ይልቅ መተሳሰብና ይቅር ባይነትን ለትውልዱም፤ ለምዕመኑም ማሳወቅ የተገባ መሆኑ ሊዘነጋ አያስፈልግም። ለዚህ ደግሞ ከሃይማኖታዊና ፍልስፍና ስነ ምግባር ጋር በተያያዘ ጉዳዮች ወላጆች ልጆቻችሁን የሃይማኖት አባቶች ተከታዮቻችሁን መምህራኖች ተማሪዎቻችሁን ፣ በስነ ምግባር የታነፁ እንዲሆኑ ቀዳሚ ኃላፊነት መውሰድ እንዳለባችሁ ተገንዝባችሁ ገና ብዙ ብዙ ሥራ ይጠብቅናል!!
ይሄን ኃላፊነታችንን በየዘርፉ፣ በየ ሙያ ተቋማቱ፣ በየእምነት ተቋማቱ፣ ወዘተ. በሚገባ ያለመወጣታችን ውጤት ነው ዛሬ ላይ ታረቁ በተባለ ማግስት መጣላት፣ ተስማሙ በተባለ ማግስት መለያየት፣ ሰላም ወረደ በተባለ ማግስት ጦር መማዘዙ፣ ስለ እምነታቸው የተሻለን ሽተው በአንድ ቆሙ ባልን ማግስት ድንጋይ መወራወሩና ንብረት ማውደሙ፣… እየተፈራረቀብን፤ የኛ ነገር “ከርሞ ጥጃ፣ አድሮ ቃሪያ፣ ታጥቦ ጭቃ….” ይሉት እየገጠመን ያለው። ይህ ደግሞ መሆን ስለሌለበት ሁሉም በየተሰማራበት ሁሉ ለአብሮነት፣ ለመቻቻልና ወንድማማችነት፣ ለፍቅርና አንድነት፣ ለእኩልነትና ፍትህ ቅድሚያ ሰጥቶ በትምህርቱም፣ በስብከቱም ትውልዱን ሊያስገነዝብና ሊያንጽ ይገባል።
በዚህ ረገድ የታላቁን የረመዳን ወር መጠናቀቅ ተከትሎ ትናንት በአዲስ አበባ በነበረው የኢድ ሶላት ወቅት የሆነውን ማንሳቱ ተገቢ ነው። ምክንያቱም ታላቁን የኢድ ስግደት ገጽታ ለማጠልሸት በጥቂት አካላት ተደረገ የተባለው ከሃይማኖቱ ያፈነገጠ ተግባር ሊደገም ስለማይገባው ብቻ ሳይሆን፤ ትልቁን እውነት በጥቂት አጀንዳ ተሸካሚ ግለሰቦች ተግባር ሊሸፈን ስለማይገባው ነው። ትናንት በኢድ ሰላት ወቅት ሆነ ተብሎ በማህበራዊ ሚዲያ በቀጥታ በተሰራጩ ቪዲዮዎች እንደታዘብነው፤ በዓሉ በደመቀ ሁኔታ እንዳይከበርና የሶላት ስነ-ስርዓቱን ለማወክ በሚመስል መልኩ ምክንያቱ በማይታወቅ ሁኔታ ግለሰቦች ባስነሱት ብጥብጥ እንደ ጎንደሩ እና ሌሎችም ቦታዎች እንደሆኑት ሁሉ በአዲስ አበባ ከተማ ለመድገም መታሰቡ እጅጉን የሚያሳዝን ድርጊት ነው።
ምንም እንኳን በዚህ የጥቂቶች አስነዋሪድርጊት የትልቁ በዓል ታላቅ ድምቀት የማይደበዝዝ ቢሆንም፤ ተግባሩ የኖረውን አብሮነት፣ እስላማዊ የሰላም ባለቤትነትና እሴት ለማጉደፍ፣ ከሰላም ይልቅ ከረብሽ አትራፊ የሆኑ ኃይሎች ሀሳብ እንዲሳካ ታልሞ የተፈጸመ እንደመሆኑ ሊወገዝ ይገባዋል። በተለይ መላው ሙስሊም ባጠቃላይም ሕብረተሰቡ በጋራ ሊያወግዘው የሚገባ ነው። ታላላቅ መልካም ገጾችን ለማጠልሸትና መሰል የጥፋት አጀንዳን አንግበው ለጥፋት የሚሰማሩ ቡድኖችና ግለሰቦችን መንግሥትም ኮስተር በማለት ጠንካራ እርምጃ መውሰድ ግዴታውን ሊወጣ ያስፈልጋል። ምክንያቱም በእነዚህ አይነት እኩያን ምክንያት የሚገለጸው አገር ነው፤ ሃይማኖት ነው፤ ሕዝብ ነው፤ ማንነት ነው፤…። ይህ ሲሆን ደግሞ “ከርሞ ጥጃነት፣ አድሮ ቃሪያነት፤ ታጥቦም ጭቃነት የሚሰጠው ለእኩያኖቹ ግብር ሳይሆን፤ በደምሳሳው ለሰፊው አገርና ሕዝብ መሆኑን ልንገነዘብ ያስፈልጋል። ይህ ደግሞ እንደ ሰለጠነ ሕብረተሰብ ብሔራዊ ውርደት ነው። ይህ እንዳይሆን ልቦና ይስጠን፤ እያልኩ፤ ለዛሬው በዚሁ አበቃሁ፤ በሌላ ጽሑፍ እስክንገናኝ ቸር ይግጠመን!
ከአለባቸው ደሳለኝ አበሻ (ለንደን)
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 25 ቀን 2014 ዓ.ም