ከዓለም ታሪክ እንደተገነዘብነው፤ በአንድ አገር ለውጥ ወይም አዲስ ነገር በመጣ ጊዜ ለውጥ በመጣባት አገር ውስጥ የሚኖሩ ዜጎች በተለያዩ ችግሮች እንደሚፈተኑ ነው። ይሁን እንጂ ከለውጥ ማግስት ለፀብ የጋበዛቸውን ጉዳይ ከስር በመመርመር ለችግሩ ዘላቂ መፍትሄ በመስጠት ወይም በማበጀት አገራቸውን ለትልቅ እድገት ያበቁ በርካቶች መሆናቸውን ታሪክ ያስተምረናል።
በእኛ አገር እንደ አገር ከ1966 ዓ.ም ጀምሮ መሰረታዊ የአገዛዝ ለውጥ የመጣ ቢሆንም ከለውጡ ማግስት የተፈጠሩ ችግሮችን መፍታት አቅቶን ይሄው እስካዛሬ ድረስ በተቸነከርንብት መርዛማ ችንካር እንደተቸነከርን በችግር እየተናጥን እና እርስ በርሳችን እየተበላላን ለአመታት ቀጥለናል። ለዚህም በርካታ አመክንዮች ቢኖሩም ለዛሬው ግን ሁለት አመክንዮችን ለመጥቀስ እሻለሁ።
ከ1966 ዓ.ም ለውጥ ጀምሮ ስለምን ችግራችን መፍታት ተሳነን? ለሚለው አንደኛው ምክንያት የውስጣዊ ሃይሎች የአጀንዳ አመንጭነት ውስንነት መኖር ነው። ማለትም ከለውጥ ማግስት በኢትዮጵያ ለተፈጠሩ ችግሮች ምክንያቶች ወይም አጀንዳዎች ኢትዮጵያን ከሚጠሉ ታሪካዊ ጠላቶች ለኢትዮጵያ ተቀርጸው የተሰጡን እንጂ የህዝባችንን ችግሮች ይፈታሉ ተብለው በመጡ ለውጥ አምጪ ሃይሎች የተቀረጹ ባለመሆናቸው ነው።
ከዚህ ጋር ተያይዞ ለውጡን ያመጡ ሃይሎች በፍላጎታቸውም ይሁን በውጭ ተኩላዎች ተታለው ከታሪካዊ ጠላቶቻችን አጀንዳ በመቀበል ኢንዱአስትሪ በሌለበት አገር ላባደርና ወዛደር በማለት፣ ቢሮ ገብቶ የማያውቅን አርሶ አደር ቢሮክራት በማለት፣ በአንድነቱ ጠንክሮ ቅኝ ገዥዎችን ሳይቀር ያሳፈረን ህዝብ በጎሳው የሚከፋፈል አስተዳደር እና የመንግስት አወቃቀር በመዘርጋት ሲያጋጩን እና ሲያወዛግቡን ኖሩ። ያ ሱሳቸውም አለቃቸው ብሎ ታጥቦ ሊጠሩ የማይችሉ የፖለቲካ ፍልስፋናዎችን በመደረት ዛሬም ድረስ አገር አጥፊ ችግሮችን በገፍ እያመረቱ ይገኛሉ።
ከለውጥ ማግስት ለተከሰቱት ችግሮች መነሻ አጀንዳ የተፈጠረው በውስጥ ሃይሎች ቢሆን ኖሮ ቀኑ ይዘገይ እንደሆነ እንጂ በኢትዮጵያ ሰላም እና እድገት መምጣቱ እንደማይቀር መሆኑን ታሪክ ያስተማረን ሃቅ ነው። ከዚህ ጋር ተያይዞ በአገረ ቻይና የመጣውን ለውጥ እና የፈጀውን ጊዜ ለአብነት ያህል ማየቱ በቂ ነው።
እ.ኤ.አ 1644- 1911 ዓ.ም ቻይና በማንቹ ወይም ቺንግ ሥርዎ- መንግስ ትመራ ነበር። በዚህ አገዛዝ የተማረሩ ኃይሎች በተለይም ደግሞ የቡርዣዋው ክንፍ የሆነው ኬ.ኤም.ቲ እና የኮሚኒስት ክንፍ የነበረው የቻይና ኮሚኒስት ፓርቲ (ሲፒሲ) ቻይናን ለዓመታት ሲገዛት የነበረው ሥርወ መንግስት አሽቀንጥረው ጣሉ። የእነዚህ ሁለት ሃይሎች ትብብር እና ጥምረት የአለምን ህዝብ በአግራሞት እጁን በጉንጩ ላይ ያስጫነ ነበር።
ይሁን እንጂ ቀን ቀንን፤ ዓመትም ዓመትን ሲወልድ ማንቹ ወይም ቺንግ ሥርዎ- መንግስት ለማስወገድ ሳንባችን አጋጥመን በአንድ አንፍንጫ እንተንፍስ ሲሉት የነበሩት ሃይሎች አይን እና ናጫ ሆነው አረፉት። በመካከላቸው የነበረው ቁርቁስ ሰፍቶ እ.ኤ.አ 1926 ዓ.ም የቡርዣዋው ክንፍ የሆነው የኬ.ኤም.ቲ ኃይል የኮሚኒስት ክንፍ የነበረውን የቻይና ኮሚኒስት ፓርቲን (ሲፒሲ) ለማጥፋት ቆርጦ ተነሳ። በአይነቱ የተለየ ከበባም አደረገ። የኮሚኒስት ክንፍ የነበረው የቻይና ኮሚኒስት ፓርቲም (ሲፒሲ) ከተደረገበት ከበባ ለመውጣት እና ራሱን ከጥፋት ለመዳን «ሎንግ ማርች» እየተባለ የሚጠራውን 9000 ኪሎ ሜትር የሸፈነ ጉዞ አደረገ። የኮሚኒስት ክንፍ የነበረው የቻይና ኮሚኒስት ፓርቲም (ሲፒሲ) ከተጋረጠበት ጥፋትም ራሱን አዳነ።
ይህ በእንዲህ እያለ እኤአ 1931 ዓ.ም ጃፓን ቻይናን ወረረች። በዚህም ሁለቱ ለመጠፋፋት የሚፈላለጉ የነበሩ ሃይሎች የውስጥ ጠባቸውን ወደ ጎን ትተው ጃፓንን ለማፋለም በአንድ ላይ ቆሙ። ለአገራቸው ነጻነትም ተዋደቁ። ባደረጉት እልህ አስጨራሽ ትግልም አገራቸውን ከጃፓን ወረራ ነጻ ማድረግ ቻሉ።
ነገር ግን ከነጻነት ማግስት እናት፣ አባት፣ ወንድም.፣ እህት እና ዘመድ የማያውቀው የስልጣን ልክፍት በአገረ ቻይና አገርሽቶ ከአንዴም ሁለቴ አብረው የቆሙትን ኬ.ኤም.ቲ ኃይል እና የኮሚኒስት ክንፍ የነበረው የቻይና ኮሚኒስት ፓርቲን (ሲፒሲ) ጦር አማዘዘ።
ኬኤምቲ የተሰኘው ክንፍ በኮሚኒስት ክንፍ የቻይና ኮሚኒስት ፓርቲ (ሲፒሲ) ላይ ዳግም ጥቃት ከፈተ። ኬኤምቲም የውጭ ድጋፍ ስለነበረው የኮሚኒስት ክንፍ የነበረው ሲፒሲ (የቻይና ኮሚኒስት ፓርቲ) የሚያሸነፍ መስሎት ነበር። ነገር ግን የኮሚኒስት ክንፍ የነበረው ሲፒሲ(የቻይና ኮሚኒስት ፓርቲ) እውነተኛ ለቻይናውያን እድገት እና ብልጽግና የቆመ ስለነበር ከፍተኛ የህዝብ ድጋፍ ነበረው። በዚህም ኬኤምቲን አሸንፎ ቻይናን አሁን ለደረሰችበት እድገት እንድትበቃ አደረገ። ከጦርነት በኋላ ቻይና እንዴት ለዚህ ልትበቃ ቻለች ? ቢባል መልሱ ከለውጥ ማግስት ለሁለቱ ቡድኖች መነሻ የጸብ አጀንዳ የተፈጠረው በውስጣዊ የቻይና ሃይሎች ስለነበር ነው።
ከ1966 ዓ.ም ጀምሮ በኢትዮጵያ የመጣው ለውጥ ለምን ከችግር መላቀቅ አቃተው ለሚለው ሌላኛው ምክንያት ደግሞ «የሞራል ሴሰኝነት» ወይም «መርህ አልባ አሽቃባጭነት» ነው። ምሁራን በተማሩት ሙያ፤ የበታች ሹሞች ደግሞ የወከላቸውን ህዝብ ፍላጎቶች አቅም በፈቀደው መጠን እንዲያሟሉ ይጠበቃል። ነገር ግን በእኛ አገር «በሞራል ሴሰኝነት» የተጠቁ ምሁሮቻችን እና የበታች ሹሞች የበላይ ጌቶቻቸውን ለማስደሰት ሲሉ መርህ አልባ በሆነ ደረጃ በማሽቃበጥ ሳይማር ያስተማራቸውን ህዝብ በጥቅም እየሸጡ ከኢትዮጵያ ህዝብ ፍላጎት ጋር በተቃርኖ መቆምን እንደ ጀግንነት ሲቆጥሩት ተመልክተናል ! እየተመለከትንም ነው።
ለዚህ ደግሞ ዋና ምክንያቱ የሚከተለው ነው። የኢትዮጵያ ህዝብ እርሃብን እና ድህነትን ማሸነፍ ዋነኛው ግቡ ሁኖ ሳለ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት እና ተጽኖ ፈጣሪ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ግን የራሳቸውን ጥቅም በማሳደድ እና አገሪቱን በመዝረፍ ይጠመዳሉ። ይህንን ስርቆታቸውን ከህዝብ ለመደበቅ ሲሉ የህዝብን ሰላም ሚያውኩ አጀንዳዎችን ይቀርጻሉ። እነኛ አጀንዳዎች ያድጉና ከቁጥጥር ውጪ ይሆናሉ። በዚህም ሂደት ለውጡ ውሃ ይበላው እና የኢትዮጵያ ህዝብ በችግር እና በስደት ኑሮውን እንዲያሳልፍ ይፈርዱበታል። ህዝብም በዚህ ይቆጣና ከእስክሪፕቶ ነፍጥ ያነሳል። ገዢውንም ያባርራል። ሌላም ቡድን ይተካል። የተተካውም ችግር ይፈታል ሲባል ከበፊቶቹ የተመለከተውን የአስተዳደር አይነት በስም ብቻ ይቀይርና ሁሉም ነገር እንዳለ ያስቀጥለል። መርህ አልባ አሽቃባጮችም በአዲሱ ለውጥ ውስጥ ተጠቃሚነታቸውን ለማስጠበቅ ከዚህ ቀደም ያደርጉት ከነበረው በላይ ማሽቃበጥ ይጀምራሉ። ይህ የማሽቃበጥ አዙሪት ኢትዮጵያን ከችግር እንዳትወጣ ካደረጉ በርካታ ምክንያቶች አንዱ ነው።
በመጨረሻም የለውጥ ሃይሎች ሰላም እና እድገት በማረጋገጥ አገርን ወደፊት የሚያሻግር አጀንዳዎችን በራሳችሁ ቅረጹ፤ ምሁራን እና የበታች ሹሞችም ከሞራል ሴሰኝነት ተላቃችሁ በትክክለኛ መርህ ላይ የተመሰረተ ፖለቲካ አራምዱ መልዕክቴ ነው !!
ሙሉቀን ታደገ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 25 ቀን 2014 ዓ.ም