በአሰልጣኝ እንዳልካቸው ጫካ እየተመሩ ከሁለተኛው ዙር ማጣሪያ በኋላ ፉክክሩን የተቀላቀሉት ታዳጊዎቹ ሉሲዎች በመጀመሪያ የማጣሪያ ጨዋታቸው ዩጋንዳን በሜዳዋ ገጥመው ሁለት ለሁለት በሆነ አቻ ውጤት ማጠናቀቃቸው ይታወሳል። በመልሱ ጨዋታም በአዲስ አበባ አበበ ቢቂላ ስቴድየም አንድ ለአንድ በሆነ አቻ ውጤት አጠናቀዋል። ታዳጊዎቹ የዩጋንዳውን የደርሶ መልስ ማጣሪያ ሦስት ለሦስት በሆነ አቻ ውጤት ቢያጠናቅቁም ከሜዳቸው ውጪ ብዙ ግብ በማስቆጠራቸው ወደ ቀጣዩ ማጣሪያ ሊያልፉ ችለዋል። አራተኛውን የማጣሪያ ውድድር በ2010 እና 2018 የዓለም ዋንጫ ተሳታፊ ከነበረችው ደቡብ አፍሪካ ጋር የተደለደሉት ታዳጊዎቹ ሉሲዎች ከተጋጣሚያቸው አንጻር ልምድ የሌላቸው መሆኑ ብዙ ርቀት ላይጓዙ እንደሚችሉ ስጋት ነበር። ይሁን እንጂ የነበረው ስጋት ከንቱ እንደነበር ደቡብ አፍሪካን በሜዳዋ ጆሃንስበርግ ላይ ገጥመው ባስመዘገቡት አስደናቂ ውጤት ማረጋገጥ ችለዋል። እነዚህ ታዳጊ ሴቶች ከሁለት ሳምንት በፊት ወደ ደቡብ አፍሪካ አቅንተው የተሻለ ልምድ ያላትን ደቡብ አፍሪካን ባልተጠበቀ የሦስት ለዜሮ ውጤት በማሸነፍ ከሜዳቸው ውጪ ጣፍጭ ድል ይዘው ተመልሰዋል። ይህም የትናንቱን የአበበ ቢቂላ ስቴድየም የመልስ ጨዋታ ቀላል አድርጎላቸዋል።
እንደተጠበቀውም ታዳጊዎቹ ሉሲዎች የትናንቱ የመልስ ጨዋታ ላይ ግብ ማስቆጠር ወይም ማሸነፍ ሳይጠበቅባቸው ቀጣዩን ማጣሪያ በቀላሉ ሊቀላቀሉ ችለዋል። በትናንቱ የመልስ ጨዋታ ውጤት ለመቀልበስ አስበው ወደ ሜዳ የገቡት ደቡብ አፍሪካዎች ሰላሳ ሰባተኛ ደቂቃ ላይ ግብ ማስቆጠር ቢችሉም ደግመው የኢትዮጵያን የግብ ክልል መድፈር አልተቻላቸውም። በመጀመሪያው ጨዋታ የቤት ሥራቸውን ጨርሰው የመጡት ታዳጊዎቹ ሉሲዎችም በጨዋታው ተጨማሪ ግብ ተቆጥሮባቸው ጫና ውስጥ እንዳይገቡ ጥንቃቄ ከማድረግ የዘለለ ሥራ ሳይበዛባቸው የሚፈልጉትን ውጤት ይዘው ለመውጣት አልከበዳቸውም። በዚህም በአጠቃላይ ውጤት 3ለ1 በማሸነፍ በቀጣዩና በመጨረሻው ማጣሪያ የናይጄሪያ አቻቸውን እንደሚገጥሙ አረጋግጠዋል።
ወደ መጨረሻው የማጣሪያ ጨዋታ ለማቅናት ሦስተኛውን የማጣሪያ ጨዋታ ትናንትና ከትናንት በስቲያ ካደረጉ የአፍሪካ አገራት መካከል ሞሮኮ ተጋጣሚዋ ኒጄርን በደርሶ መልስ አጠቃላይ ውጤት 18ለ0 በመርታት ለመጨረሻው ማጣሪያ ቀርባለች። በተመሳሳይ ጋና ጊኒን 10ለ1 በሆነ የደርሶመልስ አጠቃላይ ውጤት በማሸነፍ የመጨረሻውን ማጣሪያ ተቀላቅላለች። ሞሮኮና ጋና በመጨረሻው ማጣሪያ እርስበርስ የሚፋለሙም ይሆናል። ካሜሩን ዛምቢያን በድምር ውጤት 5ለ0 አሸንፋ የመጨረሻውን ማጣሪያ የምትፋለም ሌላኛዋ አገር ነች። ካሜሩን የመጨረሻውን ማጣሪያ ከታንዛኒያና ቡሩንዲ አሸናፊ ጋር የምታደርግ ይሆናል። ታንዛኒያ በሦስተኛው ዙር ማጣሪያ የመጀመሪያ ጨዋታዋን ከሜዳዋ ውጪ አድርጋ ተጋጣሚዋ ቡሩንዲን አራት ለዜሮ የረታች አገር እንደመሆኗ የመጨረሻውን ጨዋታ በሜዳዋ አሸንፋ የካሜሩን ተጋጣሚ የምትሆንበት ዕድል ሰፊ ነው።
የዓለም እግር ኳስ መሪ የሆነው ፊፋ የሴቶችን እግር ኳስ ለማሳደግ በተለያዩ የዕድሜ እርከኖች ከሚያከናውናቸው ውድድሮች መካከል ከ17 ዓመት በታች የሴቶች የዓለም ዋንጫ አንዱ ነው። በዚህ የዓለም ዋንጫ እአአ ከ2005 ወዲህ የተወለዱ ሴት እግር ኳስ ተጫዋቾች ተሳታፊ ናቸው። በፈረንጆቹ 2022 ዓመት መጨረሻ በሕንድ አዘጋጅነት ለ7ኛ ጊዜ በሚካሄደው የሴቶች ከ17 አመት በታች የዓለም ዋንጫም ከተለያዩ አህጉራት አዘጋጇ ሕንድን ጨምሮ አስራ ስድስት አገራት ተሳታፊ ይሆናሉ። በዓለም ዋንጫው ተሳታፊ መሆናቸውን የተለያዩ አገራት ከወዲሁ እያረጋገጡም ይገኛሉ። ሦስት አገራት ወደ ዓለም ዋንጫው በሚያልፉበት የኤሽያ አህጉር አዘጋጇ ሕንድ በቀጥታ ተሳታፊ ስትሆን ቻይናና ጃፓንም በ2019 ውጤታቸው መሠረት ተሳታፊ መሆናቸው ቀደም ብሎ የታወቀ ነው። ከመካከለኛውና ሰሜን አሜሪካ እንዲሁም ካሪቢያን አገራትም ሦስት አገራት ተሳታፊ ይሆናሉ። ከደቡብ አሜሪካ አገራት ሦስቱ ተሳታፊዎች ብራዚል፣ ቺሊና ኮሎምቢያ የሕንድ ትኬታቸውን ቀድመው ቆርጠዋል። ከኦሽኒያ ብቸኛዋ ተሳታፊ ኒውዚላንድ ስትሆን ሦስት ሦስት አገራትን የሚያሳትፉት አፍሪካና አውሮፓ በማጣሪያ ሂደት ላይ ይገኛሉ።